Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኤች አይቪ ጥላ ስር

በኤች አይቪ ጥላ ስር

ቀን:

እርግዝናቸው የመጀመሪያቸውና የሕይወታቸው ሌላኛው ምዕራፍ መባቻ በመሆኑ በጣም ተደስተውና የልጃቸውን መወለድ በጉጉት እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ደስታቸው ግን ከጥቂት ሳምንታት በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡ ወይዘሮ ዝናሽ (ስማቸው ተቀይሯል) የእርግዝና ክትትል  የጀመሩ ሰሞን ፀባያቸው ተቀየረ፡፡ ጭንቅ ጥብብ ይላቸው ጀመር፡፡

ሁኔታቸው የሆርሞን ለውጥ የፈጠረው የተለመደ የነፍሰ ጡር ባህሪ ሳይሆን የደም ምርመራ ውጤታቸው በደማቸው የኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚገኝ በማሳየቱ የተፈጠረ ጭንቀት ነበር፡፡ የፀረ ኤድስ መድኃኒት ተጀመረላቸው፡፡  እየዋለ እያደርም ተገቢውን ክትትል እስካደረጉ ድረስ ከቫይረሱ ጋር መኖር እንደሚቻል አመኑ፡፡ ልጃቸውም ከቫይረሱ ነፃ ሆና ተወለደች፡፡ ይህ ከሆነ አሥር ዓመታት ተቆጥሯል፡፡

ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት ወ/ሮ ዝናሽ፣ በዙም ሳይቆዩ ሌላ ችግር ተጋረጠባቸው፡፡

አዲስ ከጀመሩት ሥራ ጋር መድሀኒቱን የሚወስዱበት ሰዓት ሊመቻችላቸው አልቻለም፡፡ ‹‹በአንድ ድርጅት የፅዳት ሥራ ነበር የምሠራው፡፡ ሥራ የምገባው ንጋት 12 ሰዓት ነው፡፡ አንዴ ማፅዳት ከጀመርን ከአራት ሰዓት በፊት አንጨርስም፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ከሥራ ጋር አልተመቻቸልኝም በሚል ሰዓቱን ጠብቀው መድኃኒቱን መከታተል እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

በስራ ምክንያት ጠዋት ሁለት ሰዓት መውሰድ የሚገባቸውን መድኃኒት ረፋዱ ላይ አራት ሰዓት መውሰድ ልምዳቸው እንዳደረጉ፣ ይህ የጎንዮሽ ችግር ሊኖረው እንደሚችል አለማወቃቸውን፣ ከዓመት በኃላ ግን በሆነው ባልሆነው መታመም መጀመራቸውን፣ ‹‹በሽታ ላይ ጣለኝ፣ ሰውነቴ መቆሳሰል ጀመረ፣ አልማዝ ባለጭራም ወጣብኝ›› በማለት ይገልፃሉ፡፡

በተደረገላቸው ህክምና ከዚህ ቀደም ይወስዱት የነበረው መድኃኒት መላመዱ ተነግሯቸው ሌላ መድኃኒት እንደተቀየረላቸው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እየወሰዱት ያውን መድኃኒት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ ነው፡፡ መድኃኒቱን የሚወስዱትም ከአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መድኃኒት አጣን ብለው የሚያማርሩ ሰዎች ሲያጋጥሟቸውም እሳቸው ወደሚወስዱበት ድርጅት እንዲሄዱ እንደሚመክሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሰዓቱን ጠብቃ መድኃኒት የማትወስድ አንድ በቅርብ የማውቃት  ነበረች፡፡ በእኔ ላይ ደርሶ ስላየሁኝ በስንት ጉትጎታ ሰዓቱን ሳታዛባ መድኃኒቱን እንድትወስድ አድርጌአለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት አኚህ ወይዘሮ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው የሰባት አመት ልጃቸው ከቫይረሱ ጋር እንዲኖር ሆኗል፡፡ እሳቸውም ዳግመኛ ላለመውለድ ወስነዋል፡፡

እስከ ዛሬ አወዛጋቢና ቁርጥ ያለ ምላሽ ካላገኙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መካከል ኤች አይቪኤድስ መቼና እንዴት ተከሰተ የሚወለው ጉዳይ ነው፡፡ በአንዴ የብዙዎችን ሕይወት በመቅጠፉና መድኃኒት ሊገኝለት አለመቻሉ ዓለምን አሸብሮ ነበር፡፡ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችና በሚዲያዎች ኤች አይ ቪ በአስፈሪ መንፈስ ይገለጽም ነበር፡፡ በየቴሌቪዥን መስኮቱ አፅም፣ ጣረሞትና ሌሎችም አስፈሪ ነገሮች የኤችአይቪ ምሳሌ በመሆን ይቀርቡ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ስለበሽታው የነበረው ግንዛቤ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ብዙዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1996 የበሽታው ሥርጭት ጣሪያ የነካበት ወቅት ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የነበረው የሥርጭት መጠን 15.6 በመቶ፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ 12.7 በመቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 በኢትዮጵያ ከኤች አይ ቪ ጋር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቁጥር በከተማ 660,000፣ በገጠር ደግሞ 490,000 ደርሶ እንደነበር (HIV AIDS in Ethiopia where is the epidemic heading) በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ2006 የተሰራው ጥናት ያሳያል፡፡ ይህ ቁጥር ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ 720,000 እና 750,000 ሊያሻቅብ ችሏል፡፡ የሥርጭት መጠኑ ከፍተኛ በነበረበት እ.ኤ.አ. 2000  186,000 አዲስ የኤች አይ ቪ ኤድስ ኬዝ ተመዝግቧል፡፡ ይኼው ቁጥር ከሦስት ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2003 በከተማ 95,000፣ በገጠር ደግሞ ወደ 137,000 ከፍ ብሎ ነበር፡፡

ወቅቱ መተማመን የጠፋበት፣ መገለልና መድልዎ ያየለበትና ቫይረሱ ጥቁር አሻራውን ያሠፈረበት ነበር፡፡ ኤችአይቪን የሕይወታቸው ፍፃሜ አድርገው የሚወስዱ ብዙ ነበሩ፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ባወቁበት ቅፅበት ራሳቸውን ያጠፉም አሉ፡፡ ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በአለም 70 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ 35 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ሞትም ምክንያት ሆኗል፡፡

እንዲህ ዓለምን ግራ አጋብቶ የነበረው ኤድስ እስካሁን ፈውስ ባይገኝለትም የቫይረሱን ሥርጭት መግታት የቻለው የፀረ ኤድስ መድኃኒት መገኘቱ በመጠኑም ቢሆን ዕፎይታን ፈጥሯል፡፡ በሰው ልጆች ላይ የታወጀ ጦርነት ያህል ግዝፈት የነበረውን ወረርሽኝ ለመከላከል የተለያዩ መንግሥታትና አለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊነት ወስደው በዘመቻ መልክ ሰርተዋል፡፡

በአገር ውስጥም ከመንግስት ጎን ለጎን ተስፋ ጎህ፣ መቅደም ኢትዮጵያና ሌሎችም የፀረ ኤድስ ክበባት የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጠር ረገድ የድርሻቸውን መወጣት ችለዋል፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ኤች አይ ቪን ለመቆጣጠር  ንቅናቄ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የተለያዩ ሚዲያ አካላትም ጉዳዩን አጀንዳቸው አድርገው ብዙ ሠርተዋል፡፡ በየመንገድ ዳሩና በየተቋማቱ ይዘጋጁ የነበሩ የቡና ጠጡ ፕሮግራሞችም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በየጊዜው በተከናወኑ የዘመቻ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ያለው የኤች አይ ቪ ሥርጭት መጠን ወደ 1.2 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ መልካም ለውጥ ሊባል ቢችልም አንድ አገር ከወረርሽኝ ነፃ ነች የሚባለው የሥርጭት መጠኑ ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን ነው፡፡

በቅርብ ዓመታት የሥርጭት መጠኑን ከአንድ በመቶ በታች ለማውረድ እ.ኤ.አ. በ2030 ደግሞ አንድም ሰው ኤች አይ ቪ እንዳይጠቃ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የሥርጭት መጠኑን ለጊዜው ማለዘብ መቻሉ ግን በኤች አይ ቪ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ፊታቸውን ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንዲያዞሩ ማኅበረሰቡም እንዲዘናጋ እድል ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር የኤች አይ ቪው ግርሻ በሚል ከዚህ ቀደም ባወጣው ጽሑፍ መዘናጋቱ የፈጠረውን ክፍተት ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በከተማና በገጠር እንዲሁም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥርጭት መጠኑ የተለያየ ነው፡፡ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሥርጭት መጠኑ ቀድሞ ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ያለው የቫይረሱ ስርጭትም እስከ 23 በመቶ መድረሱን በጽሑፉ ለመቃኘት መሞከራችን የሚታወስ ነው፡፡

ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች መጠን ከዚህ ቀደም ካለው ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ አይባልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ስለበሽታው ግንዛቤ ያላቸው ሴቶች 18 በመቶ፣ ወንዶች ደግሞ 31 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ 32 በመቶ የሚሆኑ አዲስ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚያዙት ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሳምንታት በፊት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2021  የነበረውንና የሚኖረውን የኤች አይ ቪ ኤድስ የሥርጭት መጠን፣ እንደሁም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ብዛት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2015 ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 715,400 ሲሆን፣ 283,877 ወንዶች፣ 431,526 ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. 2016 ከቫይረሱ ጋር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 718,500 ከፍ ብሏል፡፡ 284,737 ወንዶች 433,763 ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 754,256 እንደሚያሻቅብ ተተንብዮዋል፡፡ በየዓመቱ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር  እ.ኤ.አ.በ2015 ከነበረው 27,104 በ2021 ወደ 20,735 ዝቅ እንደሚል ሪፖርቱ ያብራራል፡፡ በኤድስ ምክንያት በየዓመቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እንዲሁ ከ27,104 ወደ 20,735 ዝቅ እንደሚል በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በአፋር ክልልና እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የቫይረሱ ሥርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በሦስት ክልሎች ማለትም በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ የሥርጭት መጠኑ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንደሚሄድ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

 በሶማሌ ክልል እ.ኤ.አ. በ2015 የነበረው የቫይረሱ ሥርጭት 0.76 እንደነበር፣ እ.ኤ.አ. በ2021 ግን ወደ 0.8 ከፍ እንደሚል፣ በሐረር ክልል በተመሳሳይ ዓመት የሥርጭት መጠኑ 2.86 እንደነበር፣ በ2021 3.13 እንደሚደርስ፣ በጋምቤላም 4.01 እንደነበርና ወደ 4.49 እንደሚያሻቅብ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ደግሞ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን እ፣ኤ.አ. በ2015 4.9 በመቶ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 5.2 ከፍ እንደሚል ሪፖርቱ ያትታል፡፡    

ለዚህም የተለያዩ ችግሮች መምክንያትነት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ በአገሪቱ የነበረውን አስከፊ የኤች አይቪ ወረርሽኝ ችግር በተሰሩ ስራዎች መቀነስ ተችሏል፡፡ ይህ መቀጠል ካልቻለ ወደኋላ የሚመልሱ ነገሮች መኖራቸውን በኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍየኢትዮጵያ የሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ተረፈ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የመከላከያ ግብአቶች ላይ የአቅርቦት ችግሮች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ የኮንዶም ተደራሽነት እንደሚታሰበው አይደለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አንድ ፍሬ ኮንዶም እስከ 40 ብር የሚሸጥበት ሁኔታም ታይቷል፡፡

‹‹በአንድ ወቅት ከጤና ቢሮዎች ጋር ምክክር እያደረግን ለኤችአይቪ መከላከያ የሚሆን ኮንዶም ለጤና ድርጅቶች ትሰጣላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ አቀረብንላቸው፡፡ መልሳቸው ግን ‘ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል ሳይሆን ለቤተሰብ ምጣኔ ብቻ ነው’ የሚል ነበር፡፡ እርግዝናን በሌላ መንገድ መከላከል ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች እርግዝናን ለመከላከል ኮንዶም እየተጠቀሙ ይገኛሉ፣›› በማለት ኮንደምን እንደ እርግዝና መከላከያ የመጠቀም ልምድ መኖሩንና ይህም በአቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኤችአይቪ መመርመሪያ መሣሪያዎች እጥረትም ሌላው ችግር ነው፡፡ ኤችአይቪ ለመመርመር ሦስት ኪት ያስፈልጋል፡፡  በመጀመርያው ምርመራ ውጤቱ ፖዘቲቭ የሆነው በሌላ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል በትክክል ኤችአይቪ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ በሁለተኛው ኪት ምርመራ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ይህኛውም ፖዘቲቭ ከሆነ ደግሞ ሌላ ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልግ ፖዘቲቨ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁለተኛው ምርመራ ኔጌቲቭ እንደሆነ የሚያሳይ ከሆነ ሁለቱን ውጤቶች የሚያስታርቅ ሦስተኛ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋለል፡፡  ለዚህም ነው አንድን ሰው ለመመርመር ሦስቱ ኪቶች የሚያስፈልጉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስቱም መመርመርያ ኪቶች በአንድ ላይ ላይገኙ እንደሚችሉ ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ 722000 የሚሆኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ 62 በመቶ፣ ከእነዚህ ውስጥ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት እየወሰዱ የሚገኙት 53 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ እ.አ.አ. በ2020፣ 90 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ተጠቂዎች ራሳቸውን አውቀው መድኃኒቱን መውሰድ እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም በፌዴራል የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻሎ ዳባ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና መድኃኒት ከመውሰድ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች መድኃኒቱን የሚያቋርጡ መኖራቸው ሌላ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ መድኃኒቱን ጀምረው የሚያቋርጡበት ሁኔታ መድኃኒቱ ከቫይረሱ ጋር እንዲላመድ እያደረገው ይገኛል፡፡ ለዚህም ሁለተኛ ደረጃ ፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት እንዲወስዱ እንደሚገደዱና የመድኃኒቱ ዋጋ ውድና ለአገሪቱም የማይመከር መሆኑን አቶ ሻሎ ገልፀዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ግለሰብም ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በቅርበት ክትትል የሚያደርጉላቸው 11 የቫይረሱ ተጠቆዎችም  አሉ፡፡ እነዚህ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ችግረኛና ራሳቸውን እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው በቂ ዕውቀት እንደሌላቸው፣ ከአሥራ አንዱ ሰዎች መካከከል መድኃኒቱን እንዳሻቸው የሚወስዱ መኖራቸውን፣ ብሞት ይሻለኛል ብለው መድኃኒቱን የማይወስዱ እንዳጋጠሟቸውም ይናገራሉ፡፡

‹‹ከምንከባከባቸው አንዱ ችግረኛና የሚበላ አጥተው የሚቸገሩ ናቸው፡፡ መድኃኒቱ ደግሞ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህም አንዳንዴ አልውጥም ብለው መድሀኒቱን ያልፋሉ፡፡ እኔ እንዲወስዱ ከማግባባት ባለፈ ምንም ማድረግ አልችልም›› ይላሉ፡፡

የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቱ የኤድስን ሥርጭት በመቆጣጠር ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወትና 96 በመቶ የሚሆነውን ኤች አይ ቪ መከላከል የሚያስችል ነው፡፡ በአግባቡ ተወሰደም መኖር እንደሚቻል ይነገራል፡፡ በአግባቡ ከተወሰደ በደም ውስጥ ያለውን የቫይረሱን ሥርጭት ከመቀነስ ባለፈ ከአንዱ ወደ ሌላ የመስተላለፍ አቅሙ እንደሚቀንስ፣ በአግባቡ አለመውሰዱ ግን የመድኃኒቱን ጥቅም ከማሳጣቱ ባሻገር ሌላ አደጋ እንዳለው ዶ/ር ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ ጀምሮ ማቋረጥና ሰዓቱን ጠብቆ አለመውሰድ ቫይረሱ መድኃኒቱን እንዲላመድ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ታማሚው ቫይረሱን የማስተላለፍ ዕድሉ ወደነበረበት እንዲመለስ ይሆናል፡፡ የከፋው ነገር ግን ታማሚው የሚያስተላልፈው ቫይረስ መድኃኒት የተላመደው መሆኑ ነው፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ እንደሚሉት፣ መድኃኒት የመላመድ ችግር በሁለት መንገዶች ይከሰታል፡፡ የመጀመርያው አንድ ሰው በተፈጥሮው ለመድኃኒቱ የተላመደ ይሆናል፡፡ ይህ ከስንት አንድ የሚያጋጥም ነው፡፡ ሌላው መድኃኒቱን በአግባቡ ካለመውሰድ አኳያ የሚፈጠር የመላመድ ሁኔታ ነው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው መድኃኒት የመላመድ ችግርም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ነው፡፡ ‹‹አሳሳቢና መከላከል ያለብን ነገር ነው፤›› በማለት ጉዳዩ ትኩረት ተደርጎበት ሊሠራ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመጣባት አዲስ አበባ ለመጨመሩ ምክንያት ምን መሆኑንና በተነሱት ነጥቦች ላይም በአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ የዕቅድ፣ በጀት ክትትልና ግምገማ ሥራ ሒደት መሪውን አቶ ታሪኩ ሞላን ሪፖርተር አነጋግሮዋቸዋል፡፡

‹‹መድኃኒት የተላመደ ቫይረስ ጉዳይ እንደተባለው ሥጋት ሆኗል፤›› የሚሉት አቶ ታሪኩ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች መድኃኒት እንደሚያቋርጡ ይህም ዋጋ እንደሚያስከፍል ይናገራሉ፡፡ ወደ አምልኮ ቦታዎች ሲሄዱ መድኃኒቱን ለቀናት የማቋረጥ ነገር አለ፡፡ መድኃኒቱን ለዓመታት የወሰዱና በጊዜ ብዛት የዳኑ መስሏቸው የሚያቋርጡ ሰዎች መኖርም ሌላው ችግር ነው፡፡ ከአንድ አገር ወይም ወደ ሌላ  ቦታ ሲዘዋወሩ መድኃኒቱን የማቋረጥ ሁኔታ መኖሩና፣ መድኃኒት የተላመደ ቫይረስ እንዲስፋፋ እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

የፀረ ኤድስ መድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ታሪኩ፣ የተጓዳኝ በሽታዎች መድኃኒትን በተመለከተ ግን ‹‹የተጓዳኝ በሽታዎች መድኃኒት ለኤች አይ ቪ ሕመምተኞች ተብሎ ተለይቶ አይመጣም፡፡ በግዢ ላይ ችግር ሲያጋጥም እንደማንኛውም ሰው ሊቸገሩ ይችላሉ›› ብለዋል፡፡

የመመርመሪያ አልጎሪዝሙ ከአንድም ሁለት ጊዜ በመቀየሩ የመመርመሪያ ኪቶች አቅርቦትን በተመለከተ ክፍተት መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች መካከል ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁት 60 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ በ2020 የእነዚህን ሰዎች ቁጥር ወደ 90 በመቶ ከፍ የማድረግ ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መሥራት የሚል እስትራቴጂ እየተከተሉ ነው፡፡ ‹‹ሁሉንም ሰው ዝም ብሎ መመርመር ብክነት ነው፡፡ ይልቁኑ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መመርመሩ ዕቅዱን በቀላሉ ለማሳካት ይረዳናል፤›› በማለት የመመርመሪያ ኪቶቹ አቅርቦት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንዲያመዝን መደረጉም የአቅርቦት ችግር ያለ እንዳስመሰለው ተናግረዋል፡፡

በየክፍለ ከተማው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር መዋዠቅም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ በየክፍለ ከተማው የሚገኙት የጤና ጣቢያዎች በጀት የሚያዝላቸው በሚያገለግሏቸው ሰዎች መጠን ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች በመልሶ ማልማትና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአንዱ ክፍለ ከተማ ወደ ሌላው ይሄዳሉ፡፡ መመርመሪያ ኪቶችና ሌሎችም ግብዓቶች በየክፍለ ከተማው የሚታደሉት በፊት በነበሩት ነዋሪዎች ቁጥር ልክ ነው፡፡ ይህም በአንዱ ክፍለ ከተማ ብዛት ያለው ክምችት እንዲኖር፣ በሌላው ደግሞ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ብዙ ክምችት ያለው ክፍለ ከተማ ዝቅተኛ ክምችት ላለው እንደሚሰጥ፣ የተፈጠረው ክፍተት በመረጃ እጥረት እንጂ ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡   

የቫይረሱ ስርጭት መጠን ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣበትን ምክንያት ሲያብራሩም ‹‹በከተማው ያለው ሰፊ እንቅስቃሴ፣ የመጤ ባህሎችና ወጎች መስፋፋት፣ ወሲብን እንደ አንድ መዝናኛነት የሚጠቀሙ ሰዎች መብዛት፣ የጭፈራ ቤቶች ማየልና ሌሎችም በከተማው የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት መጠን እንዲጨምር ምክንያቶች ናቸው፡፡›› ብለዋል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የሥርጭት መጠን ጠቅለል ተደርጎ እንደ ክልል መጠቀሱና የአዲስ አበባ ደግሞ ራሱን ችሎ ለብቻው መገለጹ ውጤቱ ተጋንኖ እንዲታይ ማድረጉን አቶ ታሪኩ ተናግረዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከየጤና ጣቢያዎች ተሰብስበው ከታዩ የምርመራ ሪፖርቶች አንፃር በከተማዋ ውስጥ ያለው የቫይረሱ ሥርጭት ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ የተለያየ ነው፡፡ በቂርቆስ፣ በአዲስ ከተማና በአቃቂ ቃሊቲ ያለው የቫይረሱ ሥርጭት ከ4.5 በመቶ በላይ፣ በጉለሌና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች ከ3.5 በመቶ በታች፣ ሲሆን በቀሪዎቹ ክፍለ ከተሞች ደግሞ የሥርጭት መጠኑ ከ3.5 በመቶ እስከ 4.5 በመቶ መሆኑን አቶ ታሪኩ ይናገራሉ፡፡

              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...