በጦርነትና ረሃብ ወደተለያዩ ጎረቤት አገሮች ተሰደው ከሚገኙ ደቡብ ሱዳናውያን፣ ከ345 ሺሕ በላይ የተጠለሉት በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ነው፡፡
‹‹ጉኝየል›› ከደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ካምፕ አንዱ ሲሆን፣ ካምፑ ከጋምቤላ በስተምሥራቅ ከዋና ከተማዋ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በክልሉ ከተመሠረቱ ካምፖች ስድስተኛው ‹‹ጉኝየል››፣ በውስጡ ከ50 ሺሕ በላይ ስደተኞችን አስጠልሏል፡፡
በጉኝየል አካባቢ የመኖሪያ መንደር፣ ከሕፃናት መዋያ እስከ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ግቢና ከነጫጭ ድንኳኖች ወደ ጎጆ ቤቶች የተቀየሩ ቤቶች ይገኛሉ፡፡
‹‹ጉኝየል›› በርካታ ሥራ ፈት ወጣቶች የሚታዩበት ቢሆንም፣ ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚሠሩም አሉ፡፡ የካምፑን ፀጥታ የሚያስጠብቁ ካኪ የለበሱ ስደተኞችም በብዛት ያሉ ሲሆን የንግድ መደብሮች ያሉ ሲሆን አንድ የደቡብ ሱዳን ዶላር በማስከፈል ሞባይል ቻርጅ የሚያደርጉም አሉ፡፡ በምግብ አቅርቦትም በርከት ያሉ ስደተኞች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በሻይ ቤት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራችው ንቦኝ ኩን አንዷ ነች፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰ የእርስ በርስ ጦርነት አራት ልጆቿን ይዛ ሸሽታ ኢትዮጵያ የገባችው ንቦኝ፣ ባሏ ይሙት ይኑር አታውቅም፡፡ ‹‹ባለቤቴ ወደ ጦርነቱ እንዲቀላቀል በግድ ከቤቱ እንደወሰዱት አደጋ ላይ ወደቅን፡፡ ጦርነቱ እየከፋ መጥቶ መንደራችን ሙሉ በሙሉ ወደመ፡፡ አራት ልጆቼንም ይዤ ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመሆን የአምስት ቀን ጉዞ በማድረግ ኢትዮጵያ ገባን›› ስትል ትናገራለች፡፡ ጉዞዋቸው ምን እንደሚመስል ላቀረብንላት ጥያቄ ስትመልስ፣ ‹‹ብዙ ሆነን ነበር የወጣነው፡፡ በሕመም የሞቱ አሉ፡፡ ምጣቸው ተፋፍሞ መንገድ የወለዱም ነበሩ፡፡ በጣም ከባዱ ፈተና የሚፈልጉን ሰዎች እንዳይደርሱብን በ24 ሰዓት ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ብቻ መተኛታችን ነበር›› ትላለች፡፡
የንቦኝ ሻይ ቤት በውስጡ ከ10-15 ሰው ይይዛል፡፡ ንቦኝ አንድ ተቆራጭ አንባሻ በአንድ ጭልፋ ወጥ በአሥር ብር ትሸጣለች፡፡ ንቦኝን ያገኘኋት ከሻይ ቤቱ በስተቀኝ በሠራችው በረንዳ መሳይ ማዕድ ቤት ሁለት ድስት ጥዳ ልጇን አቅፋ እያማሰለች ነበር፡፡ ወደፊት ምን እንደምታስብ ጠይቄያት ‹‹ለጊዜው በአገሬ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ ይህን ሥራዬን በማጠናከር ልጆቼን የተሻለ ትምህርት ቤት ማስተማር እፈልጋለሁ›› በማለት መልሳለች፡፡
ሌላኛው የስደተኞች መንደር ደግሞ ከ‹‹ጉኝየል›› የተሻለ ይመስላል፡፡ በሳርና በጭቃ የተሠሩ ጎጆ ቤቶችም ረድፋቸውን ጠብቀው ይታያሉ፡፡ እዚህ በአንድ ቤት የሚኖሩት ከአራት እስከ ስድስት የቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፣ እነ ንቦኝ ግን የሚኖሩበት በአንድ ክፍል ከአሥር እስከ 15 ሆነው ነው፡፡ ይህ መንደር ስደተኞቹ በቀጣይም ብዙ ጊዜ እንደሚቆዩበት የሚያሳይ ይመስላል፡፡
ከመንገዱ በስተግራ ማት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በስተቀኝ ደግሞ መዋዕለ ሕፃናት ይገኛል፡፡ የሁለቱም ግቢዎች ዙሪያ በሽቦ ታጥሯል፡፡ በስፍራው ያሉ ሕፃናት በሙሉ በማያውቁት ጉዳይ ለስቃይ የተዳረጉ ናቸው፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሕፃናት የሚማሩበት ሲሆን፣ ወላጆቻቸውን የማያውቁ ሕፃናትም እዚህ ይውላሉ፡፡ ሥፍራው ስንደርስ፣ ዝናብ ጥሎ ግቢው በጭቃ ተጨማልቆ ነበር፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በስስ ቁምጣና ቲሸርት በባዶ እግር ጭቃው ውጧቸው ቆመዋል፡፡ ጉዳታቸው ከፀጉራቸው እስከ እግራቸው ይታያል፡፡ ምንም የትምህርት መርጃ መሣሪያ ይዘው አይታዩም፡፡ ከስደተኞች የተውጣጡ አስተማሪዎቻቸው ወደ ክፍል እንዲያስገቧቸው ዓይን ዓይናቸውን ያያሉ፡፡ ችግር በላያቸው ላይ እየወረደ እንደ ሕፃን ማልቀስና ማስቸገር አይታይባቸውም፡፡
በአንድ ክፍል ከ100 በላይ ሕፃናት ሆነው በሁለት ፈረቃ የሚማሩ ሲሆን፣ ከተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሕፃናቱን እያስተማሩ ቢሆንም፣ የመማሪያ ክፍል እጥረት፣ የመማሪያ መጻሕፍት ችግሮች እንዳሉባቸው የመዋዕለ ሕፃናቱ ዳይሬክተር ሚስተር ቻን ፒክላቶ ገልጸውልናል፡፡
ከመዋዕለ ሕፃናቱ ካሉ ልጆች በተጨማሪ፣ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ታዳጊ ሕፃናት የሚማሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አለ፡፡ በዚህ ያሉት ተማሪዎች ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ባዶ እጃቸውን አንዳንዶቹ ደብተር፣ ቦርሳ፣ አንድ ሉክ ይዘው ይታያሉ፡፡ ንጽሕናቸውም ሻል ያለ ነው፡፡ ከወላጅ ጋር የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ከእህት ከወንድም ጋር ብቻ የሚኖሩ መኖራቸውን ሰምተናል፡፡ የሁለተኛ ጂ ክፍል ተማሪ የሆነው ሰልጀስ ካርየስን ከሠልፉ መሀል ነበር ያገኘነው፡፡
ትምህርቱን ሲጨርስና ሲያድግ ሐኪም መሆን ይመኝ እንደነበር ገልጾ፣ ዛሬ ግን ይህ ፍላጎቱ መክሰሙንና ከአንድ ወንድሙ ጋር ብቻ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ይናገራል፡፡
ትምህርት ቤቱ ሁሉንም ልጆች ማስተናገድ አልቻለም፡፡ በአንድ ዴክስም እስከ ስድስት የሚደርሱ ተማሪዎች ይቀመጣሉ፡፡ የአራተኛ ክፍል ሒሳብ አስተማሪ የሆነችው ኒየን ፓስቲክ፣ በአገሯ በተፈጠረው ጦርነት እንደምታዝንና በካምፑ የሚገኙ በርካታ ሴቶች መማር ሲገባቸው፣ ቁጭ ብለው እንደሚውሉና ለተለያየ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡
በስፖርት ማዘውተሪያው ግቢ ቢሮዎች፣ ክሊኒኮች ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ሜዳዎች ሥርዓቱን በተጠበቀ መልኩ ተሠርተው ይታያሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ሰሞኑን የተከበረውም ከዚሁ ሥፍራ ነው፡፡ በዕለቱ ከአሥር ሺሕ በላይ ስደተኞች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ሕፃናት፣ ሴትና አካል ጉዳተኞች ይበዛሉ፡፡ በተለይ በሰው የሚመሩ አቅመ ደካማ አባትና እናቶች፣ ታዝለው የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞችና በአዕምሮ ዝግመት የተጠቁትን አልፎ አልፎ ማየቱ የስደትን ክፋት ያሳያል፡፡
ጉኝየል ካምፕ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. መመሥረቱን ለሪፖርተር የገለጹት የስደትና ከስደት ተመላሽ ጉዳይ አስተዳደር የጉኝየል ካምፕ አስተባባሪ አቶ ጁነዲን ረሺድ ናቸው፡፡ ‹‹ካምፑ የተቋቋመው በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ድርቅና ረሃብ በፈጠሩት ቀውስ ተሰደው የመጡትን፣ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመሆን እንደ ትምህርት፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ ንፁህ መጠጥ ውኃ ለማቅረብ እንዲሁም ሴቶችንና ሕፃናትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ነው፡፡
ከ350 ሺሕ በላይ ስደተኞች በጋምቤላ ክልል መገኘታቸው ክልሉን ከኢትዮጵያ ካሉት የስደተኛ መጠለያዎች በቀዳሚ ሥፍራ ያስቀምጠዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች ዘንድ ደግሞ ይህ ቁጥር መብዛት የተለያየ ስሜትን ፈጥሯል፡፡
የክልሉ ተወላጅ የሆነው ተርገር ተር እነሱ በመምጣታቸው ምንም ችግር እንዳልገጠመው ይናገራል፡፡ ወደ ከተማም የሚመጡት ውስንና አልፎ አልፎ በመሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ለውጥ እንደሌለ ገልጿል፡፡ ሌላው የክልሉ ነዋሪ ቿን (ስሙ ተቀይሯል) የባጃጅ ሾፌር ሲሆን፣ በተርገር አስተያየት አይስማማም፡፡ በተለይ እሱ በፀጥታ ጉዳይ የእነዚህ ስደተኞች አንድ ቦታ መሰብሰብ ለአገርም ቢሆን ሥጋት እንደሚመስለው ይገልጻል፡፡ ‹‹ስደተኞቹና እኛ የሚቀራረብ ባህል፣ አመጋገብ ቢኖረንም እንደከተማ ነዋሪ ደግሞ በቅርቡ በተከሰተው ግጭት የካምፑ ነዋሪዎች ከካምፓቻቸው በመውጣት በከተማው ነዋሪ ላይ ያደረሱት ጥቃት ድጋሚ ሊፈጠር የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ሁሌም ሥጋት አለኝ›› በማለት ተናግሯል፡፡
‹‹የስደተኞች መምጣት ሥጋት ሳይሆን ለከተማ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ፣ ከፀጥታ ችግር ይልቅ ቤተሰባዊ ግንኙነትን በማጠናከር ድንበር የሚጠበቅበትን አጋጣሚ የሚፈጥር ነው›› የሚሉት የጋምቤላ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የከተማዋ ዋና ከንቲባ ክቡር አቶ አካኔ ኡጋዳ ኡፓዲ ናቸው፡፡ ስደተኛው ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ተፅዕኖ አላደረሰም ወይ ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ይህ የማይካድ ሐቅ ቢሆንም፣ በቅርቡ ‘ደኑን እንዳንነካ መብራት ይግባልን’ ብለው በመጠየቃቸው ሶላር የሚጠቀሙበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጨማሪ የስደተኞች መጠለያ ስለተከፈተ ወደጋምቤላ የማይመጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በኢትዮጽያ መከበሩ ለበርካታ ዓመታት ስደተኞችን በማስተናገድ ለምትታወቀው ኢትዮጵያ ዕውቅና እንደመስጠት ነው ሲሉ አቶ ዘይኑ ጀማል የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡