Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቡና ግብይት ሒደት ውስጥ አዳዲስ አሠራሮች ከመጪው ወር ጀምሮ ይተገበራሉ ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ውስብስብ ችግሮች ጠፍንገው እንደያዙት ሲገለጽ የቆየውን የአገሪቱን የቡና ግብይት ሥርዓት በማስያዝ በተሻለ መንገድ እንዲጓዝ ያስችላሉ የተባሉ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ከማሳ እስከ ግብይት ከዚያም አልፎ የወጪ ንግዱ ላይ የሚታየው የእሴት ሰንለሰት ላይ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚያሰረዱ አዳዲስ አሠራሮችን ለመቅረጽም እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሰፊው ሲመከርበት የቆየው የቡና ጉዳይ ችግሮቹ ተለይተው መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ውሳኔዎች ተወስነው ወደ አፈጻጸም እንዲገባም ተደርጓል፡፡ እንደ መፍትሔ የተቀመጡ በርካታ የአሠራር ለውጦችን ያካተተ፣ የአገሪቱን የቡና ግብይት ሥርዓት በበላይነት የሚመራና የሚገዛ አዲስ አዋጅ መቅረፅ አንዱ ዕርምጃ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ለቡና ሪፎርም ሥራዎች አንጓ ይሆናል የተባለው የቡና ግብይትና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ይህንን ረቂቅ ሕግ ሲገመግም የቆየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቁን በያዝነው ሳምንት አጋማሽ በማፅድቁ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ሕግ ሆኖ የሚወጣበት ቀን እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

እስካሁን የነበረውን የቡና ግብይት መሠረታዊ ነው በተባለ መንገድ ይለወጣል የተባለውን ይህንኑ ረቂቅ አዋጅ ያፀደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እንደላከው ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

አዲሱ ረቀቅ አዋጅ አጠቃላይ ከምርት ጀምሮ ወደ ውጭ እስኪላክ ድረስ መከወን ይገባዋል የተባሉ አዳዲሶቹን የታመነባቸውን አሠራሮችና እነዚህ አሠራሮች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን ድንጋጌ የያዘ ነው፡፡

የቡና ባለድርሻ አካላት በጋራ ስምምነት የደረሱባቸውን ነጥቦች አካቶ የተረቀቀው ይህ አዋጅ ከዚህ በኋላ በአገሪቱ የቡና ግብይት ውስጥ ከፍተኛ ሚና በሚኖረው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነው፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደረሰው ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ፀድቆ በአዲሱ በጀት ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ እንደሚጠቅሰው፣ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ሕግ ሆኖ የሚወጣበት ሒደት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአዋጁ የማይቃረኑና የአዋጁን ድንጋጌዎች የማያፋልሱ አዳዲስ አሠራሮች ግን ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

በሪፎርሙ መሠረት ከቡና ግብይት ጋር ተያይዘው ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አሠራሮች ውስጥ ቡናን በመኪና ላይ ሳለ መገበያየት መቻል አንዱ ነው፡፡

በአዲሱ አዋጅ ውስጥ የሚካተቱ ሆነው የአዋጁን መፅደቅ ሳይጠብቁ ይተገበራሉ ከተባሉት ሌሎች አዳዲስ አሠራሮች ውስጥ ቡና አቅራቢዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበት አሠራር ይገኝበታል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያም ቢሆን በአዲሱ አሠራር መሠረት ራሱን ያደራጀ በመሆኑ፣ አዳዲሶቹን አሠራሮች ይተገብራል ተብሏል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት በአዲስ አሠራሮችና የግብይት ሒደቱም በጠቅላላው በአዲሱ አዋጅ የሚመራበት የቡና እሴት ሰንሰለት እንደሚፈጠር የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከግብይት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋማትም ለአዲሱ አሠራር በሚመች መንገድ ዝግጅት እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ትልቅ ለውጥ የሚጠበቀው ሌላው ጉዳይ፣ በምርት ገበያው ወንበር ገዝተው በአገናኝነት በሚሠሩ አባላት በኩል ግብይት የሚፈጸምበት አሠራር የግድ መሆኑ ቀርቶ ተገበያዮች ከፈለጉ ብቻ የሚገበያዩባቸው እንዲሆኑ ይደረጋል የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ቀድሞው አካሄድ የቡና ግብይት በምርት ገበያው ባለወንበሮች አገናኝነት ይፈጸም የሚለው አስገዳጅ አሠራር ይቀራል፡፡ የቡና ግብይት ተዋናዮች ምርቶቻቸውን ከፈለጉ ብቻ በምርት ገበያ ውስጥ ባሉ አገናኞች መሸጥ የሚችሉ ሲሆን፣ ካላስፈለጋቸው ግን ቡና አቅራቢዎቹ በቀጥታ በምርት ገበያ ውስጥ የራሳቸውን ምርት ለመሸጥ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን ቡና አቅራቢም ሆነ ላኪ በቡና ግብይት ውስጥ ተገበያይቶ ቡናውን መሸጥና መግዛት የሚችለው በምርት ገበያው ወንበር ባላቸው አገናኞች አማካይነት ብቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

በዚሁ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጥታ ይገበያዩ የነበሩ የቡና ዓይነቶች ውስጥ የልዩ ጣዕም ወይም የስፔሻሊቲ ቡናዎች ተብለው የሚታወቁትን ቡናዎች የሚገበያዩም በሚያመቻቸው መንገድ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን አሠራር አዋጁ ይደነግጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቡናው ዱካ ወይም በአካባቢው ስም የመሸጥ መብትም የዚህ ድንጋጌ አካል እንደሚሆን ታውቋል፡፡

ቀድሞ ብልሹ አሠራር ይታይባቸዋል የተባሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አሠራር ላይ ለውጥ ያመጣል የተባለው አዲሱ ቡና ከምርት ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ ያለውን ረዥም ሰንሰለት ለማስቀረት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል፡፡

የቡና ዘርፍን የተመለከተው ሪፎርም ከአዋጁ ቀደም ብለው የተወሰዱ ዕርምጃዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ዕርምጃዎች ውስጥ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ባለሥልጣን ተጠሪነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደ ንግድ ሚኒስቴር መዛወሩ አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት እንዲዋሃዱ መወሰኑም የዚህ የሪፎርም አካል ነው፡፡ የአገሪቱን የቡና ዘርፍ በበላይነት የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲቋቋም መወሰኑም ይታወሳል፡፡

ይህ ለውጥ በተለይ የአገሪቱን የቡና የወጪ ንግድ ከማሳደግ አንፃር ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን፣ የቡና ምርትን ለማሳደግ፣ እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ጭምር ዕድል ይሰጣል፡፡ አዲሱ ድንጋጌ እሴት የተጨመረባቸው የቡና ምርቶችን የሚልኩ ኩባንያዎች እንደማንኛውም ተገበያይ ቡናን ከምርት ገበያው ተጫርተው የሚገዙበት አሠራር ይፈቅድላቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች