Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊልብ አንጠልጣዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የገጠመው የፋይናንስ ድርቅ

ልብ አንጠልጣዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የገጠመው የፋይናንስ ድርቅ

ቀን:

የቀድሞ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ በ2005 ዓ.ም. ክረምት መንግሥት አራት ዓይነት የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም እንደሚጀመር ይፋ ሲያደርጉ፣ በመኖሪያ ቤት ዕጦት ሲሰቃይ ለቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ታላቅ የምሥራች ነበር፡፡

አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደ አቅማቸው በመቆጠብ በ10/90፣ በ20/80፣ በ40/60 እና በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጭምር ምዝገባ አካሂደዋል፡፡ ቤቶቹን ለማግኘት የግድ ቁጠባ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ክፍያ የፈጸመ ቅድሚያ ያገኛል በመባሉ ጭምር፣ በርካታ ነዋሪዎች ጥሪታቸውን ለማፍሰስ ወደ ኋላ አላሉም፡፡

በ40/60 ፕሮግራም ከተመዘገቡ 164,779 ነዋሪዎች ውስጥ አንዱ አቶ ነገደ ወልደ ሰማያት ናቸው፡፡ አቶ ነገደ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለዓመታት በኪራይ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ መንግሥት ከጀመራቸው የመኖሪያ ቤቶች በተለይ በ40/60 ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በመመዝገብ የቀደማቸው ብዙ ነዋሪ አይደለም ይላሉ፡፡

አቶ ነገደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የቤት ፕሮግራሞቹን ባስተዋወቁበት ወቅት ቅድሚያ የከፈለ ቅድሚያ የሚያገኝበት አሠራር መኖሩን በመግለጻቸው፣ እሳቸው ካለባቸው የመኖሪያ ቤት ችግርና ለረዥም ዓመታት በማያቋርጥ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ሲሰቃዩ የቆዩ በመሆናቸው ምዝገባ በተጀመረ በመጀመርያው ቀን ጣጣቸውን መጨረሳቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም በተጀመረበት ነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ለባለ ሁለት መኝታ ሙሉ ክፍያ የሚጠየቀውን 250 ሺሕ ብር ከፍያለሁ፤›› በማለት አቶ ነገደ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ በ18 ወራት ይጠናቀቃል ቢባልም አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በቀላል ሒሳብ እኔ ከዚያ ወዲህ ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ከ114 ሺሕ ብር በላይ አውጥቻለሁ፤›› በማለት የችግራቸውን ጥልቀት አብራርተዋል፡፡

‹‹ምን ዓይነት አሠራር ነው?›› ሲሉ አቶ ነገደ የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም የመዘግየቱን ሚስጥር ይጠይቃሉ፡፡

አቶ ነገደን ጨምሮ በተለይ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ተመዝግበው እየተጠባበቁ የሚገኙ ነዋሪዎችን ያስደነገጠው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ  አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የ2009 በጀት ዓመት የአሥር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ያካተቱት ሐሳብ ነው፡፡

‹‹በቤት ልማት ፕሮግራም በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 750 ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ቢሆንም፣ በበጀት ያልተደገፈ በመሆኑ ዕቅዱን ለማስፈጸም ትልቅ ችግር ሆኖ ሳይፈታ ቀጥሏል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፈቀደው የቤት ልማት ፋይናንስ ዘግይቶ በመለቀቁ የሥራ ተቋራጮችና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሥራ በማቆም ተበትነው የነበረ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በብድር ፋይናንስ ድጋፍ እንዲሰባሰብ በማድረግ ግንባታውን ለማስቀጠል ተችሏል፤›› በማለት ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በ2009 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ እንደገለጸው፣ ‹‹ለሚገነቡ ቤቶች የግንባታ ግብዓቶች መግዣ የሚውል የቦንድ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከግንባታ ፕሮጀክቶቹ መረጃ በመሰብሰብ የፍላጎት ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት 31.03 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገንዘብ ፍላጎት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀርቦ 15 ቢሊዮን ብር የቦንድ ብድር ተፈቅዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 8.5 ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት (20/80)፣ 6.5 ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ (40/60) ተደልድሏል፡፡ በዚህም ሥራውን ማስቀጠል ተችሏል፤›› በማለት የሚገልጸው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፣ ‹‹ነገር ግን ሀብትን በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ማዋል በሚለው መርህ መሠረት፣ ክፍያዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅርብ ክትትል ቁጥጥር ተግባራዊ እንዲደረጉ መወሰኑን ተከትሎ የክፍያ አፈጻጸሙ የተጠበቀውን ያህል ቀልጣፋ ሊሆን ባመቻሉ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ያለው የቦንድ ብድር አጠቃቀም በአጠቃላይ 2.45 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ሊል አልቻለም፡፡ ይኼውም ለ40/60 ቤቶች 1.05 ቢሊዮን ብር፣ ለ20/80 ደግሞ 1.4 ቢሊዮን ብር ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል፤›› ሲል ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ይህ አፈጻጸም ለ40/60ም ሆነ ለ20/80 ተመዝጋቢዎች መልካም ዜና አይደለም፡፡ አቶ ነገደ እንደሚሉት በተለይ የ40/60 ቤቶች ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቅርቡ ይተላለፋሉ እየተባለ እስካሁን ቆይተው በድጋሚ የፋይናንስ ጫና አለ በሚል ምክንያት ወደ ሌላ አማራጮች ለመሄድ ማሰቡ አሳሳቢ ነው፡፡

‹‹ሁኔታው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ ያደርጋል፤›› ሲሉ አቶ ነገደ ያብራራሉ፡፡ ሚኒስትሩ መንግሥት በቤቶች ልማት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ አማራጭ አድርገው ካቀረቧቸው መካከል የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበርን ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሰኔ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳብራሩት በመንግሥት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ የሚገነቡ ቤቶች ቀደም ሲል በርካታ ቤቶች በመጀመራቸው ሥራው ግዙፍ በመሆኑ ለቤቶቹ ልማት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡  

‹‹በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለመቅረፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቤት ግንባታ አማራጭን በሰፊው ለማስቀጠል በልዩ ትኩረት እንዲፈጸም እናደርጋለን፤›› ሲሉ አዲሱን አካሄድ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት በ2005 ዓ.ም. ክረምት ይፋ ካደረጋቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም 101 ማኅበራት የተቋቋሙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ማኅበሮች በየካ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ አካባቢ ቦታ ተሰጥቷቸው ግንባታ ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ፕሮግራም ብዙ ቢባልበትም፣ ማኅበራቱ አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል፡፡

አቶ ስንታየሁ ምትኩ የአንድ መኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ናቸው፡፡ አቶ ስንታየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መጀመርያ የነበረው አሠራር በመቀያየሩ ብዙ ችግሮች አጋጥመው ነበር፡፡  

‹‹መጀመርያ በተዋወቀው ፕሮግራም አፓርትመንቶችና በመሀል ከተማ የሚገኙ ቪላ ቤቶች ነበር እንዲገነቡ የታሰበው፡፡ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎ ሁሉም ግንባታዎች አፓርታማ እንዲሆኑ ተደርገዋል፤›› ሲሉ አቶ ስንታየሁ ገልጸው፣ ‹‹ማኅበራት 50 በመቶ የሚሆነውን የግንባታ ወጪ በባንክ ካስገቡ በኋላ በሁለት ወር ውስጥ መሬት እንደሚቀርብ የተገለጸ ቢሆንም፣ ገንዘቡ በዝግ ሒሳብ ተቀምጦ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፤›› ሲሉም ፕሮግራሙ ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበሩበት ገልጸዋል፡፡

አቶ ስንታየሁ እንደሚሉት፣ ይህንን አማራጭ መንግሥት ይዞ መቅረቡና ከዚህ በኋላም በሰፊው ይዞ መቀጠል ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ባንኮች ፋይናንስ ካላደረጉት ፍጥነቱና ተፈጻሚነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡ ባንኮች በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ ሠራተኞቻቸው የፋይናንስ ድጋፍ ያቀረቡ በመሆናቸው፣ የማኅበራቱ የግንባታ አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን አቶ ስንታየሁ ጠቁመው፣ ፋይናንስ ማግኘት ያልቻሉ ማኅበራት ግን አሁንም በችግር ውስጥ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

አሁን ለብዙዎች ጥያቄ የሆነባቸው ጉዳይ ባንኮች ለማኅበራት ፋይናንስ ማቅረብ አለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም የተመዘገቡ ነዋሪዎች ገንዘብ እየቆጠቡ የሚገኙ ቢሆንም ለግንባታው የሚሆን ፋይናንስ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገባው መጠን እያቀረበ አለመሆኑ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 17 ሺሕ የሚጠጉ የ40/60 ተመዝጋቢዎች ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ በየዓመቱም ከስድስት ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ የስድስት ወራት ሪፖርት እንደተቀመጠው 31.01 ቢሊዮን ብር የቦንድ ብድር እንዲለቀቅ ቢጠየቅም፣ የተፈቀደው ግማሽ ያህሉ ማለትም 15 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ገንዘብም ቢሆን ፍሰቱን ጠብቆ እየተለቀቀ ባለመሆኑ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎችና ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ከግንባታ ሳይቶች እየተበተኑ ነው፡፡ ተቋማቱን በድጋሚ ለማሰባሰብም ትልቅ ችግር እየሆነ ይገኛል፡፡

መንግሥት ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ተግባራዊ በሚሆነው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 750 ሺሕ ቤቶች እንደሚገነባ ዕቅድ አውጥቷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት በየዓመቱ 150 ሺሕ ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የትራንስፎርሜሸን ዕቅዱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ሁለት ዓመታት ቢቆጠሩም ግንባታው በዕቅዱ መሠረት አልሄደም፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ መኖሪያ ቤት ለመገንባት 200 ሺሕ ብር ያስፈልጋል ቢባል፣ በአጠቃላይ 150 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት 30 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህ ገንዘብ እየቀረበ ባለመሆኑ የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በየካቲት 2009 ዓ.ም. በታተመው ‹ቁጠባ› መጽሔት ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንደገለጹት፣ ባለፉት 12 ዓመታት ከ311 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ 175 ሺሕ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 136 ሺሕ ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ባለፉት 12 ዓመታት የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች 311 ሺሕ ብቻ ቢሆኑም ሁለት ዓመታት በተቀነሱለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ 750 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱ፣ የዕቅዱን መነሻ ሐሳብ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡ ነዋሪዎች አንድ ሚሊዮን ይጠጋሉ፡፡ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በመጪው ነሐሴ ወር አራተኛ ዓመት የሚያስቆጥር በመሆኑ፣ በየዓመቱ ቤት የሚፈልጉ ዜጎች እየጨመረ በመሄድ ላይ እንደሚገኝ እየታየ ነው፡፡ ተመዝጋቢዎች ቤታቸውን የሚያገኙበት ወቅትና አዳዲስ ቤት ፈላጊዎችም መስተናገድ የሚጀምሩበት ጊዜ አጓጊ ሆኗል፡፡

መንግሥት ለቤት ልማት የሚያስፈልገው ወጪና ግንባታውን የሚያካሂዱ ተቋማት ከአገር ውስጥ ብቻ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት የመኖሪያ ቤት ጉዳይ የተቀናጀ መልክ እንዲኖረው የተደረገ ቢሆንም፣ እጥረቱ ግን ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ በመሆኑ በፍጥነት ግንባታው እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ተወስኖ ነበር፡፡

ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ 28 የሚጠጉ የውጭና የአገር ውስጥ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ተወዳድረው ነበር፡፡ ነገር ግን ምክንያቱ ባልተገለጸ ምክንያት ዕቅዱ ተፈጻሚ መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡

በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዘርፍ የውጭ ኮንትራክተሮች ለማስገንባት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ መኩሪያና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በይፋ መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. ባካሄደው የጂአይኤስ ዳሰሳ በከተማው 387 ሺሕ ቤቶች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ ከእነዚህ ቤቶች መካከል 269,814 የሚሆኑት የውኃ መስመርና በቂ የመኖሪያ ስፋት የሌላቸው፣ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ያልሆኑባቸው፣ ያረጁና የተጎሳቆሉ ሠፈሮች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆኑት በግልም ሆነ በጋራ መጠቀም የሚያስችል መፀዳጃ ቤት የሌላቸው ናቸው፡፡

ከ1995 እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት  አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ይህንን ገጽታ ለመቀየር በርካታ ዕርምጃዎች ወስደው ነበር፡፡ እነዚህ ጎስቋላ መንደሮች በሚገኙባቸው መሀል ከተማ በዚያን ጊዜ በየዓመቱ በ1.5 ቢሊዮን ብር 50 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት ታቅዶ ነበር፡፡

በዚህ ዕቅድ ተጠቃሚ ለመሆን ከ400 ሺሕ በላይ የአዲስ አበባ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው ነበር፡፡ በዶ/ር አርከበ የሚመራው የከተማው ካቢኔ ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መንገዶችን የተጓዘ ቢሆንም፣ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) አሸንፎ በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ከተማውን መረከብ ባለመቻሉ፣ የዶ/ር አርከበ ካቢኔ በባለአደራ አስተዳደር ተተክቷል፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ እንደ እንዳጀማመሩ መቀጠል ያልቻለ ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል በስኬት መጠናቀቅ የቻለው የ10/90 ፕሮግራም ብቻ ነው፡፡

እስካሁን አንድም ቤት ሊተላለፍለት ያልቻው የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ለባለአንድ መኝታ 16,547፣ ለባሁለት መኝታ 75,547 እና ለባለሦስት መኝታ 72,439 ነዋሪዎች፣ በድምሩ 164,775 ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የኮሙዩኒኬሸን የሥራ ሒደት መሪ አቶ ዮሐንስ ዓባይነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የ40/60 ፕሮግራም በሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተካሄደ ነው፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ 1,292፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 20,932 እና በሦስተኛው ምዕራፍ 17,005 ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡

በድምሩ 39,229 ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን፣ በመጀመርያው ምዕራፍ የተጀመሩት 1,292 ግንባታቸው ተጠናቆ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ርክክብ መካሄዱ ተሰምቷል፡፡ ‹‹በ13 ሳይቶች እየተነቡ ካሉት መካከል በሠንጋ ተራና በክራውን ሳይቶች ከተገነቡ 19 ሕንፃዎች ውስጥ 17 ሕንፃዎች (876 ቤቶች) ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረክበናል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በሁለተኛው ምዕራፍ እየተገነቡ ያሉት 20,932 ቤቶች የግንባታ አፈጻጸማቸው 65.2 በመቶ፣ በሦስተኛው ምዕራፍ እየተገነቡ የሚገኙት 17,005 ቤቶች 36 በመቶ ደርሰዋል፤›› በማለት አቶ ዮሐንስ አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በጀት ዓመት ለ40/60 ቤቶች 6.5 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተገነባ ሲሆን፣ የማጠናቀቂያ ዕቃዎች የግዥ ሒደት አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን ግን ኮንትራክተሮቹ ራሳቸው እየገዙ እንዲያከናውኑ በመደረጉ ችግሩ ተቃሏል ይላሉ አቶ ዮሐንስ፡፡

በ20/80 ቤቶች በኩል በ2006 ዓ.ም. የተጀመሩና በሁለት ፓኬጆች የተከፋፈሉ 52,651 ቤቶች አሉ፡፡ በመጀመርያው ፓኬጅ 26,480 ቤቶች ሲሆኑ፣ አፈጻጸማቸው 65.52 በመቶ ደርሷል፡፡ በሁለተኛው ፓኬጅ የተካተቱት 26,171 ቤቶች አፈጻጸማቸው 48.3 በመቶ መድረስ ተመልክቷል፡፡ ለእነዚህ ግንባታዎች በበጀት ዓመቱ 8.5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡

በአጠቃላይ የ40/60ም ሆነ የ20/80 ቤቶች ግንባታ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ መሆኑ፣ አቶ ነገደን ጨምሮ ቤት ተመዝግበው ለሚጣበቁ ነዋሪዎች መልካም ዜና አይደለም፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ በግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 ቤቶች

ተ.ቁ

የሳይቱ ስም

ብሎክ ብዛት

የቤቶች ብዛት

አሁን ያለበት ደረጃ (%)

1

አስኮ

13

1,836

64.86

2

እህል ንግድ

6

792

90.37

3

ሕንፃ አቅራቢ

8

1,136

81.77

4

መሪ ሎቄ

17

1,988

64.82

5

ቦሌ ቡልቡላ አንድ

28

3,108

86.39

6

ቦሌ አያት ሎት አንድ፣ ሁለትና ሦስት

93

5,691

64.71

7

ቦሌ አያት አንድ ሎት አራት

40

4,038

56.08

8

ቱሪስት

11

2,343

64.82

              68.20 በመቶ

 

 

በሦስተኛው ምዕራፍ በግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 ቤቶች

ተ.ቁ

የሳይቱ ስም

ብሎክ ብዛት

የቤቶች ብዛት

አሁን ያለበት ደረጃ (%)

1

ቦሌ በሻሌ

58

5,596

29.16

2

ሰሚት

10

400

46.38

3

ቦሌ አያት ሁለት

48

7,101

38.59

4

ቦሌ ቡልቡላ ሁለት

24

2,908

49.08

                አማካይ 36.91 በመቶ

 

ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...