Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​ፀረ ሙስና ኮሚሽን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃውን ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲያስረክብ ታዘዘ

​ፀረ ሙስና ኮሚሽን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃውን ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲያስረክብ ታዘዘ

ቀን:

በዳዊት እንደሻው

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለ15 ዓመታት በዋና መሥሪያ ቤትነት ሲጠቀምበት የነበረውን ሕንፃ እንዲለቅ ታዘዘ፡፡ በካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትርና በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ በአቶ ዓለማየሁ ተገኑ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ፣ ኮሚሽኑ ሕንፃውን እንዲለቅና በምትኩ በቅርቡ የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲገባበት ተወስኗል፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለገሃር አካባቢ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤት ለቆ አሁን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ወደሚገኝበት ሕንፃ እንዲዛወርም ታዟል፡፡

ይህ ውሳኔ ኮሚሽኑ ቀድሞ ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣኑ፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ከተላለፈ በኋላ የመጣ ነው፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ የነበሩ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ብዛት ቀንሶ ወደ 240 አካባቢ ደርሷል፡፡ በተጨማሪም አሁን ባለው ሥልጣን ኮሚሽኑ ትምህርት፣ ሥልጠናና የጥናት ሥራዎችን ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው፡፡

‹‹አሁን እንድንዛወር የተወሰነልን ሕንፃ በቂ አይደለም፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ተጨማሪ ሠራተኞችን ለመቅጠር ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የገለጹት የኮሚሽኑ ኃላፊዎች፣ አሁን ግን ኮሚሽኑ ለተሰጠው ኃላፊነት አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኮሚሽኑ ለዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን ሕንፃ ለመከራየት አማራጮችን እያየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአቶ ዓለማየሁ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው አዲሱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚባል ስያሜ ሲሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚሁ ዓመት በተደረገው ለውጥ ከዚህ ቀደም በሥሩ የሚገኙ 18 ሺሕ የሚጠጉ ቤቶች ከማስተዳደር ያለፈ ሥልጣን ያልነበረው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ አሁን ግን ግንባታዎችን እንዲያከናውን ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በ33.1 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና በ11 ሚሊዮን ብር በጥሬና በዓይነት በተከፈለ ካፒታል ነው እንደገና የተመሠረተው፡፡ በቅርቡም ከዋና ሥራ አስፈጻሚ በተጨማሪ ሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንደተሾሙለት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ በሥሩ የሚገኙ ይዞታዎች ውስጥ ያሉ ያረጁ ቪላዎችን በማፍረስ አዳዲስ አፓርታማዎችን እንዲገነባ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በደርግ ዘመነ መንግሥት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ተብሎ በ1967 ዓ.ም. ሲቋቋም፣ የተወረሱ ቤቶችን እንዲያስተዳድር እንደነበር ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...