Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ሊቀላቀል ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ትራንስፖርት ክፍል የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲስክ አገልግሎት በሚል ስያሜ፣ ከአየር ትራንስፖርት ተጨማሪ የተቀናጀ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠት ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አባዲ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአየር ትራንስፖርቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አየር መንገዱ የተቀናጀ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን አቅም ገንብቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር የተቀናጀ የአየር፣ የየብስ፣ ባህር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም በመሥራት ላይ መሆናቸውን አቶ ፍጹም ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ በመሆናቸው በፓርኮቹ የሚመረቱ ምርቶችን በፍጥነት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎትና ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በአንድ የጭነት ሰነድ የሚሠሩበትን አሠራር ለመዘርጋት ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር አርከበ እቁባይ (ዶ/ር) የአገሪቱን የሎጂስቲክስ ዘርፍ ለማዘመን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው፣ የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በጥምረት ለመስጠት ያቀዱትን የአየር፣ የየብስና የባህር ትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ አገልግሎቶች ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎ ስምንት የጭነት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ዘመናዊና ግዙፍ የሆኑ ቦይንግ 777 አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ አየር መንገዱ በቀን 8,672 ቶን ጭነት የማጓጓዝ አቅም ያለው በመሆኑ፣ በዓመት 343,000 ቶን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል፡፡

አየር መንገዱ በነባር የካርጎ ተርሚናሉ 380,000 ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የነበረው ሲሆን፣ ሐሙስ ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ያስመረቀው ዘመናዊና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል 600,000 ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎ በራዕይ 2025 የ19 የጭነት አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በዓመት 820,000 ቶን ጭነት ለማጓጓዝ አቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት አሥር ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያስገባ ሲሆን፣ በ2025 15 ቢሊዮን ብር፣ በ2030 ደግሞ 50 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎ ዘመናዊና ግዙፍ አውሮፕላኖችን መግዛቱንና የካርጎ ተርሚናሎች መገንባቱን ያወሱት አቶ ፍጹም፣ አሠራሩን በማዘመን በወረቀት የሚከናወኑ ሥራዎችን በማስወገድ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክስ አሠራሮች በመቀየር በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገው ብቃት ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

አየር መንገዱ የገዛቸው ዘመናዊ አውሮፕላኖችና የገነባቸውን መሠረተ ልማቶች በመጠቀም እንደ ጄኔራል ኤሌክትሪክ፣ ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስና ቴክኖ ያሉ ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ አምራቾች የማከፋፈያ ጣቢያቸውን አዲስ አበባ በማድረግ በትብብር ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባውን ዘመናዊና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬና የዓለም ሲቪል አቪዬሽን ድርጀት ፕሬዚዳንት በርናድ አልዩ (ዶ/ር) መርቀው ከፍተውታል፡፡

በ150,000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው የካርጎ ተርሚናል በዓመት 600,000 ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ የካርጎ ተርሚናሉ የደረቅ ጭነት፣ የአትክልት፣ የፍራፍሬ፣ የአበባና የሥጋ ምርቶችን አቀዝቅዘው የሚያቆዩ መጋዘኖችና አውቶማቲክ መጫኛ ማሽኖች የተገጠሙለት ነው፡፡

በአንድ ጊዜ 18 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተለያዩ ምርቶች ማራገፍና በአንድ ጊዜ ስምንት አውሮፕላኖችን የመጫን አቅም አለው፡፡ ከካርጎ ተርሚናሉ አጠገብ ባለ ሁለት ፎቅ የቢሮ ሕንፃ ተገንብቷል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የካርጎ ተርሚናሉ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ምርጥ ከሚባሉት የአምስተርዳም ስኪፎል ኤርፖርት፣ የሲንጋፖር ቻንጋይና የሆንግ ኮንግ ኤርፖርቶች የሚስተካከል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አኃዝ በማደግ ላይ መሆኑንና አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ እያደረገች ያለችውን ሽግግር ለማገዝ የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ዘርፍ መለወጥ እንዳለበት አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እያደገ የመጣውን የኤክስፖርትና የኢምፖርት ንግድ ፍላጎት ለማሟላት የሎጂስቲክስ ዘርፍ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መልቲሞዳል ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለመግባት ከዲኤችል ኩባንያ ጋር አብሮ መሥራት እንደጀመረ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘረጋው ሰፊ የበረራ መስመር ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአበባ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ኤክስፖርት ዘርፍ በማሳደግና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት አየር መንገዱ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለሥራ በተዘዋወሩባቸው የአፍሪካ አገሮች ባካሄዷቸው የሁለትዮሽ ትብብር ውይይቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ የተገነባው የካርጎ ተርሚናል ለአበባ፣ ለአትክልትና ለፍራፍሬ አምራቾች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘለዓለም መሰለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አዲሱ የካርጎ ተርሚናል በመጠኑና በቴክኖሎጂ ቀዳሚ ነው፡፡ ለአትክልት፣ ለፍራፍሬ፣ ለአበባ፣ ለዕፅዋትና ለሥጋ የተለያዩ ክፍሎች መኖራቸው ምርቶቹን እንደ ዓይነታቸው ለየብቻ ከፋፍሎ ማስቀመጥና መላክ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ነባሩ ተርሚናልም በጣም ጥሩ የሚባል ቢሆንም የተለያዩ ክፍሎች ስላልነበሩት አልፎ አልፎ የምርቶች መደባለቅ ችግር ነበር፡፡ ቅሬታም ከላኪዎች አካባቢ ይነሳ ነበር፡፡ አሁን የተገነባው ካርጎ ተርሚናል የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል፤›› ያሉት አቶ ዘለዓለም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አበባ ብቻ ሳይሆን እንደ እንጆሪ ያሉ ፍራፍሬዎችና ዕፅዋቶች አምርታ በመላክ ላይ መሆኗን፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው በምርት ጥራት ብቻ ሳይሆን፣ የተሟላ ማቀዝቀዣ ያለው ትራንስፖርትና የመጋዘኖች አገልግሎት ሲኖር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአበባ ምርት ከኬንያ ጋር የምንወዳደረው በእርሻችን ብቻ ሳይሆን ምርቶቻችንን የምናጓጉዝባቸው ተሽከርካሪዎች፣ መጋዘኖችና አውሮፕላኖች ጭምር ነው፤›› ያሉት አቶ ዘለዓለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍና ዘመናዊ የካርጎ ተርሚናል መገንባቱና ዘመናዊ የጭነት አውሮፕላኖች መግዛቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ‹‹ይህ ምን ማለት ነው ምርታችን ሳይበላሽ የጥራት ደረጃውን እንደጠበቀ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ያስችለናል፡፡ ለምርታችን የተሻለ ዋጋ እናኛለን፣ ለአገራችን የበለጠ የውጭ ምንዛሪ እናስገኛለን ማለት ነው፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት ትልቅ ሥራ ነው የሠራው፤›› ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ መብራህቱ መለስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አዲሱ የካርጎ ተርሚናል በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በመገንባት ላይ ላሉት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው፡፡ የግብርና ውጤቶችን ሳይበላሹ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከፍተኛ ጥንቃቅ የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህን ለማድረግ ማቀዝቀዣ ያልተለየው የየብስና የአየር ትራንስፖርትና መጋዘን አገልግሎት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኋላቀር በሆነ የምርት አሰባሰብ ምክንያት እስከ 60 በመቶ የሚደርስ የምርት መባከን እንደሚከሰት የተናገሩት ሚኒስትር ዴታው፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን ትልቅ ሥራ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመገንባት ላይ ባሉት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ውስጥ ማቀዝቀዣ ያላቸው መጋዘኖች እንደሚገነቡ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባው ዘመናዊና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል በአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ወሳኝ መሠረተ ልማት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካርጎ በአሁኑ ወቅት 37 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በ2030 ወደ 57 ለማሳደግ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች