Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳንጎቴ ሲሚንቶ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ዕርቅ አወረደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ተቀጣጥሎ በነበረው ሕዝባዊ አመፅ ሳቢያ ሁለት ጊዜ ንብረቶቹ የተጎዱበት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የ2010 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው የዋዜማ ድግስ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ዕርቅ አወረደ፡፡

ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ረጂ በተባለ አካባቢ በሚገኘው ግዙፉ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ፍሪዳዎች ተጥለው፣ የተለያዩ መጠጦች ቀርበው የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት፣ የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች የአዲስ ዓመት አቀባበል በዓል ባከበሩበት ሥነ ሥርዓት ላይ የዕርቅ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ዲፕ ካማራ በሥራ ላይ ብዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠራቸውን አስታውሰው፣ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ በየዕለቱ እያደገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እያንዳንዳችሁ የዳንጎቴ ቡድን አባል ናችሁ፡፡ የዳንጎቴ ኢትዮጵያ ቡድን አፍሪካ ውስጥ ካለው ምርጡ ነው፡፡ ለምን እንጣላለን? እስከ መቼ እንጋጫለን? አብረን በጋራ ሠርተን በጋራ መበልፀግ ይኖርብናል፤›› ያሉት ሚስተር ዲፕ፣ በሥራ ላይ ለተፈጠሩ ስህተቶች ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ደግና ይቅር ባይ እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡ ይቅር በሉና እንደ ጉዲፈቻ ልጃችሁ ተቀበሉኝ፤›› ሲሉ የአገር ሽማግሌዎችንና የአካባቢውን ሕዝብ ተማፅነዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከ1,500 በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የድርጅቱ ሠራተኞችና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የአካባቢው ሽማግሌዎች የሚስተር ዲፕን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብለው መርቀው የኦሮሞ ስም አውጥተው የድርጅቱ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪ አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተወካያቸው አቶ ብርሃኑ ፈይሳ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለኩባንያው እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ዲፕ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ከኅብረተሰቡ ጋር አብሮ ተባብሮ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ‹‹አብሮ የመሥራት መንፈስ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ሆን ብለን የፈጸምነው ስህተት የለም፡፡ ነገር ግን ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በሥራ ሒደት የወሰድናቸው አንዳንድ የአስተዳደር ውሳኔዎችን እኔ እንደ ስህተት ባላያቸውም አንዳንድ ግለሰቦችን ቅር አሰኝተው ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢንቨስትመንት ለአንድ አካባቢ በረከት ነው፡፡ ‹‹አንድ ኢንቨስትመንት ወደ አንድ ክልል ሲመጣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ይቀይራል፣ የሕዝቡን አምራችነት ያሻሽላል፡፡ ከዚህ አንፃር የዳንጎቴ ቡድን ወደ ክልላችን መምጣቱ ትልቅ በረከት ነው፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ የቀድሞ ማኔጅመንት በኩል የታዩ አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቀድሞ ማኔጅመንት በአካባቢው ማኅበረሰብና በሠራተኛው ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ በአብዛኛው ሥራውን ለኤጀንሲዎች ሰጥቶ ኤጀንሲዎቹ ደግሞ ለጥቅማቸው ብቻ ትኩረት በመስጠታቸው፣ በሠራተኛውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ጥቂት ግለሰቦች በኩባንያውና በክልሉ መንግሥት ላይ የነበሩ አንዳንድ የአሠራር ክፍተቶችን በመጠቀም ግጭቱን ሲያባብሱ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽመልስ የክልሉ መንግሥት ካካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት ባሳለፈው ውሳኔ ኤጀንሲዎች እንዲወጡ በማድረግ፣ የአካባቢው ወጣቶች በማይክሮ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ሥራውን በቀጥታ ከኩባንያው ውል ፈጽመው እንዲረከቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃው ሁለት ትልልቅ ጥቅሞች አሉት፡፡ አንደኛ ሕዝቡ ግልጽነት ባለው አሠራር ተሳትፎ በሠራው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ዕድል ይሰጣል፡፡ በባለቤትነት ስሜት ፋብሪካው የእኔ ነው ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛ ሠራተኛው በአግባቡ ከተያዘ አምራችነቱ ስለሚጨምር ፋብሪካው የበለጠ ምርታማ ይሆናል፡፡ ይኼ ጥሩ የሆነ የሥራ ድባብ ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ያለፈውን ስህተት በማረምና ከስህተቶች በመማር አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን አብስረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ሰፊ ሥራ ማከናወኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፣ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ዘግቶ ሊወጣ ነው ተብሎ የተዛመተው ዜና ‹‹ተራ አሉባልታ ነው፤›› በማለት አስተባብለዋል፡፡

‹‹የነበሩ ችግሮችን ፈትተን፣ ፋብሪካው በአዲስ ምዕራፍ የበለጠ ምርታማ ሆኖ፣ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ አድርጎና ሌሎች የውጭ ኢንቨስትመንቶችን የሚስብበትን ሁኔታ ነው ያመቻቸነው፤›› ብለዋል፡፡

ዳንጎቴ ሲሚንቶ በናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ የተቋቋመው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ አንድ አካል ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ700 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ በሰኔ 2007 ዓ.ም. ምርት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፣ ለ1,500 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ከረጢት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ሁለተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ አቋርጦታል፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር እንደናገሩት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የተገነባው 700 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ ከናይጄሪያ በመጣ ገንዘብ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ የተወሰደ ምንም ዓይነት ብድር የለም፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ሁከትና ግጭት ሁለት ጊዜ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዙ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ቢቃጠሉበትም ለመንግሥት ምንም ዓይነት የካሳ ጥያቄ እንዳላቀረበ የገለጹት ምንጮች፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሚስተር አሊኮ ዳንጎቴን አስጠርተው ኩባንያቸው በእርሻው ዘርፍ በተለይ በስኳር ልማት ኢንቨስት እንዲያደርግ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡

ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ በኢትዮጵያ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረገ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በብር የሚያገኘውን ትርፍ በዶላር መንዝሮ ወደ አገሩ ለመውሰድ አገሪቱ በገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በመቸገሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ ለማስቀመጥ መገደዱን የገለጹት ምንጮች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገለት ቀና ትብብር በቅርቡ ለመጀመርያ ጊዜ ናይጄሪያ ወደሚገኘው ዜኒት ባንክ ዶላር ማስተላለፍ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች