Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልል ደረጃ በድጋሚ ሊዋቀር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተከፍሎ የወጣው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የክልል መዋቅሮችን ተከትሎ በድጋሚ ሊዋቀር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአራት ዓመት በፊት ሲቋቋም ማኔጅመንቱ ለህንድ ኩባንያ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ውጤታማ ተቋም መገንባት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋምን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን በድጋሚ ለመፍጠር ታቅዶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ፣ ሁለቱ ተቋማት እንደተለያዩ መቆየትና ይልቁንም መጠናከር እንደሚገባቸው በመስማማት የትግበራ ሥራ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ እንደሚሉት፣ ኃይል የማከፋፈል ሥራው በአገር አቀፍ ደረጃ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ራሱን እየቻለ እንዲቋቋም ይደረጋል፡፡

‹‹አሁን በተቋሙ ሥር 15 ዲስትሪክቶች ቢኖሩም ሰባት የሚሆኑት በአንድ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የትኛው ምን እንደሠራ ማወቅም ስለማይቻል ለቁጥጥርም አመቺ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የጎንዮሽ አወቃቀር በመጠቀም በሁሉም ክልሎች ለመበተን መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጥናቱ እየተሠራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ጎሳዬ፣ ተቋማቱ ለጊዜው ለማዕከል ተጠሪ እንደሚደረጉና ወደፊት ግን ተጠሪነታቸውን ለክልሎች እንደሚሆን አክለዋል፡፡

የተቋሙ ሠራተኞች ራሳቸውን እያደራጁ በየክልሉ ከሚቋቋሙ የኃይል አቅርቦትና ጥገና ተቋማት ጋር መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በደል እየደረሰብኝ ነው በማለት ቅሬታውን ማሰማቱ ይታወሳል፡፡

ክልሉ ባቀረበው ቅሬታ በአማራ ክልል ያሉ የኃይል ማስተላለፊያዎችና ትራንስፎርመሮች በደርግ ዘመን የተገነቡና ያረጁ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት በየጊዜው ለብልሽት ይጋለጣሉ ብሏል፡፡ 197 ኩባንያዎች ቢቋቋሙም የኃይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ሥራ አለመግባታቸውንም ክልሉ መግለጹ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች