Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሐሩር የወለዳቸው የጤና ጠንቆች

ሐሩር የወለዳቸው የጤና ጠንቆች

ቀን:

ክረምት በገባ ቁጥር የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በዝናብ መጥለቅለቃቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ በየመንገዱ የበረዶ ግግር መታየትም እንግዳ ነገር መሆኑ ቀርቷል፡፡ ከቀናት በፊት በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ ግን ከወትሮው ጠንከር ያለ ነበር፡፡ ቦሌ አካባቢ ይታይ የነበረው ግግር በረዶ የአገሪቱ የአየር ንብረት መቀየሩን በግልጽ ያሳየ ነበር፡፡ ከበረዷማ አገሮች ጋር የሚወዳደር ባይሆንም በከተማዋ ግን ብዙም ያልተለመደ ዓይነት ነበር፡፡

ዝናቡ ካባራ ጥቂት የማይባሉ ደቂቃዎች የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በረዶው ግን በቀላሉ ሊቀልጥ አልቻለም፡፡ መንገዱን ያጥለቀለቀው ጎርፍም እግረኞች እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸው ነበር፡፡ እንጀራቸው መንገድ ዳር ቆሞ የታክሲዎችን ፍሰት ማሳለጥ የሆነ ተራ አስከባሪዎች ጎርፉ መሀል ቆመው ሥራቸውን ለመሥራት ተገደዋል፡፡ አንዳንዶች ሱሪያቸውን ወደላይ ጠቅልለው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጫማቸውን አውልቀው እጃቸው በመያዝ በጎርፍ የተጥለቀለቁትን የከተማዋን መንገዶች በድፍረት አቋርጠው ለመሄድ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በአንደኛው አካባቢ ደግሞ ከቀርከሀ የተሠራ አግዳሚ ወንበር መሀል አስፋልት ላይ ደርድረው ጎርፉን ለማምለጥ እንደ ድልድይ ሲጠቀሙበት ተስተውሏል፡፡ ከዚያም አልፎ ጊዜያዊ የገቢ ምንጭ እየሆናቸው ነው፡፡ ከአንደኛው ጫፍ ለሚቆሙ የቀርከሀው ባለቤቶች መጠነኛ ገንዘብ መክፈል ግድ ነው፡፡

የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የሌላት አዲስ አበባ እንዲህ ያለ ዝናብ ሲጥል በጎርፍ ለመጥለቅለቅ ቅርብ ነች፡፡ የጣለው ዝናብ ከፊሉ በየጉድጓዱ ሲገባ፣ የቀረው ደግሞ ሚሊዮኖች ወጪ በተሠራው አስፋልት ላይ በመተኛት የትራፊክ ፍሰቱን ያስተጓጉላል፣ መንገደኞችን ደግሞ ከመንቀሳቀስ ያግዳል፡፡ እንዲህ ባሉት አጋጣሚዎች መንገደኞችን ከአንደኛው የመንገድ ጥግ ወደ ሌላኛው አዝለው እንደ ጀልባ የሚያሻግሩ ሰዎችን የሙጥኝ ማለት የክረምት ድባብ እየሆነ መቷል፡፡ አዝለው ላሻገሩበት የላባቸውን የተወሰነ ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሁለት የመንገዶች ጥግ የሚቆሙ መንገደኞች ተራቸው እስኪደርስ እርስ በርስ እየተሳሳቁ ይጠብቃሉ፡፡ እንደተዛዘሉ ሚዛናቸውን ስተው ላለመውደቅ የሚንገዳገዱ ሰዎች ሲያጋጥሙ ሳቃቸው ይበረታል፡፡ ሁኔታቸው መንገድ ዳር ቆመው ኮሜዲ ቴአትር የሚመለከቱ እንጂ በፈጠሩት የችግር ጊዜ ዕርምጃ የሚዝናኑ አይመስሉም፡፡ ጥርሳቸው የሚከደነው ተራቸው ደርሶ ያለዚያ ቀን ዓይተውት ከማያውቁት ሰው ጀርባ ላይ ሲፈናጠጡና ከአሁን አሁን ወደቅኩኝ የሚል የጭንቀት ስሜት ሲያድርባቸው ብቻ ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በዚህ መልኩ ሲያልፍ ዕድል ጀርባዋን የሰጠቻቸው አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ከሰሞኑ ከአዲስ አበባ 345 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጅማ ከተማ የደረሰው የጎርፍ አደጋ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በመሙላታቸው በዙሪያቸው ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሥጋት እስከመሆን መድረሳቸውን፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የጎርፍ ግብረ ኃይል ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ጤና ምርምርና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዋና የሥራ ሒደት ኃላፊው ዶክተር አብረሃም ተስፋዬ እንደሚሉት፣ በዚህ ክረምት በአዲስ አበባ ሦስት ጊዜ ያህል የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች የጎርፍ አደጋ አስተናግደዋል፡፡ በሰው ሕይወት የደረሰ አደጋ ባይኖርም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አሉ፡፡

በዝናባማው የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ የሚጠበቅ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድግግሞሹን ከሌላው ጊዜ በተለየ እየጨመረ ስለመምጣቱ ጥርጥር የለውም፡፡ ከየት መጣ ሳይባል ድንገት ዶፍ የመጣሉ ነገር እየተለመደ መጥቷል፡፡ ንጋት ላይ ያለው የጠዋት ድባብ ምሽት መስሎ የሚያልፍባቸው ቀናትም በዝተዋል፡፡ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በግልጽ እየታየ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ መንገዶች ይከሰታል፡፡ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ የባህር ሞገድ፣ መሬት በራስዋ ዛቢያ ላይ የምታደርገው ጉዞ፣ የፀሐይ ኃይል መጠነኛ ልዩነት ሲያሳይ የሚፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሯዊ ለውጥ ይመደባል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች በሚወጣ በካይ ጋዝ፣ በደን መጨፍጨፍ፣ በነዳጅና በመሳሰሉት የሚፈጠረው ደግሞ ሰው ሠራሽ ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎች ናቸው፡፡ ለሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ሰው ሠራሹ ነው፡፡

ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ የዓለም የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች የሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱን የተገነዘቡት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ነበር፡፡ ይሁንና ትልቁ የሙቀት መጠን ለውጥ መታየት የጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነበር፡፡ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ እስካሁን አንድ ዲግሪ ሴልሽየስ የሙቀት ጭማሪ ታይቷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአየር ንብረት ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ መንግሥቱ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው የሙቀት መጠን ጭማሪ በዓለም ላይ ከተመዘገበው ከአማካይ ከፍ ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ እስካሁን ባለው ጊዜ ብቻ 1 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሙቀት ጭማሪ ታይቷል፡፡ “Review of Climate Change And Health In Ethiopia; Status And Analysis” በሚል በ2016 የተሠራ አንድ ጥናት ደግሞ የአገሪቱ የሙቀት መጠን ከ1960ዎቹ ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ በ1.3 ዲግሪ ሴሊሽየስ ከፍ ማለቱን ያሳያል፡፡ ይህም በየአሥር ዓመቱ በአማካይ የ0.28 ዲግሪ ሴሊሺየስ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡

አንድ ዲግሪ ሴሊሺስ ወደ ፋራናይት ሲቀየር 33.8 ይደርሳል፡፡ የግማሽ ዲግሪ ሴሊሽየስ ልዩነት እንኳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በብዙ ሰብሎችና ነፍሳት መጥፋትና መልማት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የፓሪሱ ስምምነት እስከ ክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ የሙቀት ጭማሪው ከ1.5 ዲግሪ ሴሊሽየስና 2 ድግሪ ሴሊሺየስ መካከል እንዲሆን የማድረግ አላማ አለው፡፡

ይሁንና ይህ ከምኞት ባለፈ ምን ያህል ዕውን ይሆናል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ለዚህም 66 በመቶ የሚሆነው የአለም የሙቀት መጠን የጨመረው ከ1980ዎቹ ወዲህ መሆኑን ማጤን በቂ ነው፡፡ 3/4 የሚሆነው የካርበንዳይ ኦክሳይድ ልቀት፣ 1/5 የሚቴንና ከፍተኛውን የናይትረስ ኦክሳይድ ልቀት ምንጭ የኃይል ዘርፉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ በከፍተኛ ሙቀትና ከሌሎች የአየር ፀባዮች ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የሞት አደጋዎች ከቀጥተኛ አደጋ የሚመደቡ ሲሆን፣ የተለያዩ በሽታዎች ስርጭት መጨመር፣ የምግብ እጥረት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ እንደ ማጅራት ገትር፣ ወባ፣ ተቅማጥ ያሉ በሽታዎች መብዛት እንዲሁም የውሀ እጥረት የድርቅና የጎርፍ አደጋዎች መከሰት ቀጥተኛ ካልሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ቀውሶች መካከል ናቸው፡፡

 እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥ በሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች 600 ሺሕ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ 95 በመቶ የሚሆነው ኬዝም በታዳጊ አገሮች የተከሰተ እንደነበር የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል እ.ኤ.አ በ2015 በአገሪቱ በ50 አመታት ውስጥ ታይቶ የማያውቀውና ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ለረሀብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶችን ደግሞ ለእልቂት የዳረገው ኤልኒኖ በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል? የእሱ ተቃራኒ ሆኖ የመጣው የላኒና ተፅዕኖም በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሚኖሩባቸው ቀዬዎች በጎርፍ ምክንያት እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ እነዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች በጤና ላይ ሊያሳድሩ የሚችሏቸው ችግሮች እንዳሉም ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

በ “Review of Climate Change And Health In Ethiopia; Status And Analysis” ጥናት ላይ እንደተመለከተውም፣ በአገሪቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ በጎርፍና በሙቀት ሳቢያ የሚባዙ በሽታ አምጪ ህዋሳት፣ ውኃ ወለድ፣ ማጅራት ገትርና ከአየር ብክለት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮች በአገሪቱ እየተበራከቱ እንደሚገኙ ጥናቱ ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የውኃ፣ የግብርናና የጤና ዘርፎች በአየር ንብረት ተፅዕኖ ሥር ወድቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች ለዕልቂት ሲዳርግ፣ በርካቶችን ደግሞ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዳርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች እየተከሰተ የሚገኘው የጎርፍ አደጋም ለጤናው ዘርፍ ትልቅ ሥጋት የሆነው የአተት ወረርሽ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ሊያዛምት እንደሚችል ሥጋት ሆኗል፡፡ ‹‹በአምስት የአገሪቱ ክልሎች አተት ተከስቷል፡፡ ከተማው ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ርብርብ እያደረግን ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ አስጊ ሁኔታዎች አሉ፤›› የሚሉት ዶክተር አብርሃም በሽታው በጎርፍ አማካይነት ሊስፋፋ እንደሚችል ሥጋት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ እ.ኤ.አ. ከ2030 እስከ 2050 በየዓመቱ ተጨማሪ ሩብ ሚሊዮን የሞት አደጋዎች እንዲከሰቱ እንደሚያደርግ የዓለም ጤና ድርጅት ካለው ሁኔታ በመነሳት ትንበያውን ያስቀምጣል፡፡ የምግብ እጥረት፣ የወባ በሽታ፣ ተቅማጥና ከፍተኛ ሙቀት ይከሰታሉ ለተባለው የሞት አደጋ ምክንያት ናቸው፡፡ ተቅማጥ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ሞት ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ በየዓመቱ 525,000 ሕፃናት በተቅማጥ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ 1.7 ቢሊዮን ኬዞችም ይመዘገባሉ፡፡

ችግሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች አስከፊ ገጽታ ያለው ሲሆን፣ የንፁሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን በማሻሻል፣ የግልና የአካባቢ ንፅሕናን በመጠበቅ አደጋውን መቀነስ እንደሚቻል የተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ውኃ ቅንጦት ለሆነባት ኢትዮጵያ ለዘመናት ህልም የሆነባትን ውኃ ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ እስከ 2030 ችግሩን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ለውጥ ታመጣለች ማለት ከምኞት ባለፈ ምን ያህል ዕውን ሊሆን እንደሚችል አጠያያቂ ነው፡፡

‹‹ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ወርልድስ ወተር 2017›› በሚል በቅርቡ ‹‹በወተር ኤድ››  ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ 51 በመቶ የሚሆኑ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንፁሕ ውኃ አያገኙም፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ፣ በቁጥር ሲሰላ 40.9 ሚሊዮን የንፁሕ ውኃ ችግር ያለባቸው የገጠር ነዋሪዎች መገኛ በመሆን ከህንድ፣ ከቻይናና ከናይጄሪያ ቀጥላ ከቀዳሚዎቹ ችግር ካለባቸው አገሮች በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ በሪፖርቱ ከተካተቱት አገሮች በ15ኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች፡፡ በንፁሕ ውኃ ተደራሽነት ረገድ ከመጨረሻዎቹ አሥር አገሮች ተርታ የተሠለፈችው ኢትዮጵያ ትልቅ መሻሻልን እያሳየች መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በውኃ አቅርቦት ዙሪያ የሚሠራው ዓለም አቀፉ ወተር.ኦርግ የተባለው ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግር እንዳለባቸው፣ በኢትዮጵያ የወተር ኦርግ ዳይሬክተሩ አቶ ሰልፊሶ ኪታቡ ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ ከውኃና ከፅዳት ጋር ተያያዥ በሆኑ የጤና ችግሮች በየ90 ደቂቃው አንድ ሕፃን እንደሚሞት የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገውን ሪፖርት ዋቢ አድርገው ይገልጻሉ፡፡

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ባለው ችግር ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሲታከልበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ ግልጽ ነው፡፡ የምግብ እጥረት ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች አንዱ ሲሆን፣ ለቀነጨረ ዕድገት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ትልቁ የጤና ሥጋትም ከአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎች መሆናቸውን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥርዓተ ምግብ አስተባባሪው አቶ ቢራራ መለሰ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የእናት ጡት የማጥባት ጉዳይን አስመልክቶ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ገልፀዋል፡፡ በቂ ምግብ ባለማግኘትና በረሃብ  ምክንያት ከ1.4 እስከ 2.1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚሆን የዓለም ዓመታዊ የምርት ፍጆታ እንደሚጠፋ፣ በአገሪቱ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2009 አገሪቱ በረሃብ ምክንያት 55.5 ቢሊዮን ብር ወይም 16.5 ከመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የምርት ፍጆታ ማጣቷን ተናግረዋል፡፡

ባለው ያልተመጣጠነ ምግብ ችግር እ.ኤ.አ. በ2016፣ 67 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ዕድገት እንዲቀጭጭ ሆኗል፡፡ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑ ሕፃናት የመቀንጨር ችግር በስፋት የሚታየውም በአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የመቀንጨር ችግር 46.3 በመቶ ሲሆን፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 42.7 በመቶ፣ በአፋር ክልል 41.1 በመቶ ችግሩ ተንሠራፍቶ ይገኛል፡፡ አገሪቱን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚጎበኛት የድርቅ አደጋ ለችግሩ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ግልጽ ነው፡፡

 90 በመቶ የሚሆነው የወባ በሽታ ሥርጭት በአፍሪካ እንደሚገኝ፣ 92 በመቶ የሚሆነው የሞት አደጋም በአፍሪካ እንደሚከሰት፣ ከፍተኛው የዓለም ሙቀት በተመዘገበበት እ.ኤ.አ. በ2015፣ 212 ሚሊዮን የወባ ኬዞች እንደነበሩ፣ 429 ሺሕ የሞት አደጋ መከሰቱን እ.ኤ.አ. በ2016 የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡ የበሽታው ሥርጭትም ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ከፍተኛ ሆኖ ይታያል፡፡  

በኢትዮጵያም በርካቶችን እንደቅጠል አርግፏል፡፡ የሕመም ስሜት ሲሰማቸው ወባ ይሆን ብለው የሚበረግጉ ስንት አሉ፡፡ እንደ ቀልድ የጀመራቸው ሕመም ወባ መሆኑን ሳያውቁ ከአሁን አሁን እድናለሁ በሚል ስንቶች አልቀዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ሞቃታማ የአገሪቱ ክፍሎች ሄዶ በወባ ሳይያዙ መመለስ ከባድ ነበር፡፡ በተሠሩ ሥራዎች ሥርጭቱን መቀነስ ቢቻልም አሁንም ድረስ የጤናው ዘርፍ ፈተና ነው፡፡ በአገሪቱ ከባህር ወለል በታች በ2,000 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይከሰታል፡፡ በኢትዮጵያ 75 በመቶ ያህሉ አካባቢዎች ለወባ ትንኝ መራቢያነት ምቹ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ወባማ አካባቢዎች ከ52 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይኖራሉ፡፡

‹‹አየር ንብረት ለውጥ ሲከሰት የተለያዩ በሽታ አምጪ ህዋሳት የመራባት ዕድል ይጨምራል፡፡ ስለዚህም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ብዙ በሽታዎች ይኖራሉ፡፡ አተትም ከእነዚህ ውስጥ ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት በአዲስ አበባ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶ/ር አማረ መንግሥቱ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት በአገሪቱ ትልቅ ፈተና ያላቸውን የተለያዩ 20 በሽታዎች በመምረጥ የበሽታ ቅኝት ያደርጋል፣ የሚቀርቡ  ሪፖርቶች መሠረትም ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ እንዲሁም ከጎርፍ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሚያደርጉት ርብርብ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም ያለውን የበሽታውን ሥርጭት በከፍተኛ መጠን መቀነስ ተችሏል፡፡ ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ ጥረቱን ሊቀለብሰው እንደሚችል ሥጋት ነው፡፡

የዓለም ትልቅ አጀንዳ ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ካደጉት አገሮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የተቃጠለ አየር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በለውጡ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች የሁሉም አገሮች የጋራ ሥጋት ናቸው፡፡ ተፅዕኖው ደግሞ አንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች የመረረ ክንዱን ያሳርፍባቸዋል፡፡

87 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የካርበን ልቀት ከመሬት አጠቃቀምና ከእርሻ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በዋናነት በደን መጨፍጨፍ የሚከሰት ነው፡፡ በየዓመቱም 19,000 ሔክታር ደን እንደሚጨፈጨፍ በዚህ ከቀጠለም እ.ኤ.አ. በ2030፣ ዘጠኝ ሚሊዮን ሔክታር የሚሸፍን ደን እንደሚመነጠር አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ በደን ምንጣሮ ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው ዓመታዊ የካርበን ልቀት 18 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ 4.7 ሚሊዮን ቶን ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ ተከላከላለች፡፡ ይህም የአገሪቱ የልቀት መጠን ካደጉት አገሮች አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ነፃ እንድትሆን ዋስትና የሚሰጣት አይደለም፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ ተጋላጭነት ካላቸው አገሮች ተርታ የምትመደብ አገር ነች፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ጠንካራ ክንዱን ከሚያሳርፍባቸው አገሮች መካከል በድርቅ የምትመታው ኢትዮጵያ የመጀመርያዋ ነች፡፡ ይህም የሆነው አገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ተፅዕኖዎችን መከላከል የምትችልበት አይበገሬ አቅም ባለመገንባቷ የተከሰተ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በዝናብ ላይ የተመሠረተ ግብርና መሆኑም ለተጋላጭነቷ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡  

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመከተል ላይ ትገኛለች፡፡ ስትራቴጂው ሁለት ነገሮችን ያጣመረ ነው፡፡ የመጀመርያው ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን በመጠቀም የባዮ ማስ ጭፍጨፋን ማስቀረት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የተጨፈጨፉ ደኖችን ቀጣይነት ባለው መልኩ መልሶ ማልማትና ማስተዳደርን ይመለከታል፡፡ በተጨማሪም የትራንስፖርት ዘርፉ ከነዳጅ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ኤሌክትሪክ እንዲገባ ማድረግ ትኩረት ተሰቶታል፡፡ በዚህ ረገድ በኤሌክትሪክ የሚሠራውን የቀላል ባቡር ፕሮጀክት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ ከከተሞች የሚወጡና ለካርበን ልቀት ምንጭ የሚሆኑ ቆሻሻዎችን በአግባቡ መያዝና ወደ ኃይል መቀየር የስትራቴጂው አካል ናቸው፡፡

የተያዘው ስትራቴጂ አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ እንዳትበገር እንደሚያደርጋት የሚታመን ቢሆንም አፈፃፀሙ ላይ ግን ክፍተት መኖሩ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በየጊዜው እየተከሰተ አገሪቱ በረሃብ እንድትታወቅ ከሚያደርገው ድርቅ፣ መንደሮችን ከሚያንሳፍፈው ጎርፍ ለመዳን ጠንካራ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...