በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች በ2009 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸማቸውን የሚያሳዩ ግርድፍ መረጃዎች፣ አሁንም በአትራፊነት መዝለቃቸውን ያመለክታሉ፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች በጥልቅ ከ7.8 ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ጋር በንጽጽር ሲታይ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ማስመዝገባቸውን ያመላክታል፡፡ በቀደመው ዓመት ባንኮቹ አትርፈው የነበረው 6.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ እንደ ግርድፍ መረጃው ከ16ቱ ባንኮች ውስጥ ሦስቱ ከ2008 የሒሳብ ዓመት ያነሰ ትርፍ ያገኙ ቢሆኑም፣ የቀሪዎቹ 13ቱ የግል ባንኮች ያስመዘገቡት የትርፍ ዕድገት ጭማሪ አጠቃላይ የአገሪቱ የግል ባንኮችን ዓመታዊ የትርፍ መጠን ዕድገቱን ይዞ እንዲጓዝ ማድረጉን ያሳያል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ አሁንም ከፍተኛውን ትርፍ በማትረፍ ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዳሸን ባንክ ደግሞ ዘንድሮ ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሳደግ ሁለተኛው የግል ባንክ ሊሆን ችሏል፡፡ በግል ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ መጠን መረጃ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የግል ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር ማድረስ የተቻለው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ ይህንንም ትርፍ ያስመዘገበው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ ዳሸን ባንክ 1.06 ቢሊዮን ብር በማትረፍ የትርፍ መጠኑን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ሁለተኛው ባንክ ሆኗል፡፡ ባንኩ ባለፈው የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበውን የ987 ሚሊዮን ብር ጥቅል ትርፍ በ7.4 በመቶ በማሳደግ 1.06 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡
እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም ከአገሪቱ የግል ባንኮች ከፍተኛውን ትርፍ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ባንክ የዘንድሮ የትርፍ መጠኑን ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ ዓምና 1.004 ቢሊዮን ብር ማትረፍ የቻለው ባንኩ ዘንድሮም የትርፍ መጠኑን በ43.7 በመቶ ወይም ከ439 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አሁንም ከግል ባንኮች ቀዳሚ መሆን መቻሉን ይኸው ግርድፍ መረጃ ያሳያል፡፡
ቀሪዎቹ ባንኮች በ2009 የሒሳብ ዓመት ያገኙት የትርፍ መጠን ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ከ2.8 በመቶ እስከ 61 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ያለበት ትርፍ ማግኘታቸውን ይኸው የባንኮቹን የሥራ አፈጻጸም የሚያሳየው ግርድፍ መረጃ ያመለክታል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከቀዳሚ የሒሳብ ዓመት ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት ቀዳሚ የሆነው ወጋገን ባንክ ሲሆን፣ ከዓምናው 61 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት የ2009 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኘው ትርፍ 760 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ በቀዳሚው ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት አግኝቶ የነበረው ትርፍ 472 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ከወጋገን ባንክ ቀጥሎ የትርፍ መጠኑን በማሳደግ ሁለተኛው ባንክ ሆኖ የተቀመጠው አቢሲኒያ ባንክ ሲሆን፣ በ2008 የሒሳብ ዓመት አግኝቶ ከነበረው የትርፍ መጠን የ278 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘት ችሏል፡፡ ባንኩ በ2008 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ መጠን 472 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ካለፈው ሒሳብ ዓመት ከ54.1 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ ማስመዝገቡ የተገለጸው ሌላው ባንክ ደግሞ እናት ባንክ ነው፡፡ እናት ባንክ በ2008 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 110 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ በ2009 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 169 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ይህም የዘንድሮ ትርፍ በ56 ሚሊዮን ብር መጨመሩን ያሳያል፡፡ እንደ ግርድፍ መረጃው ከሆነ ከ16ቱ ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸውን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻሉ ሰባት ባንኮች ሆነዋል፡፡ እነሱም አዋሽና ዳሸን ባንኮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ በቀዳሚነት ሲቀመጡ፤ ወጋገን፣ አቢሲኒያና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻላቸውን መረጃው ያሳያል፡፡ ኅብረትና ብርሃን ባንኮች ደግሞ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ በማግኘት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ በተለይ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈው ዓመትም የትርፍ መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በ2009 የሒሳብ ዓመትም ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ከቀዳሚዎቹ ሰባት ባንኮች አንዱ ሊሆን ችሏል፡፡
ብርሃን ባንክ በ2008 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት አትርፎ የነበረው 364 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2009 የሒሳብ ዓመት ደግሞ ትርፉን በ142 ሚሊዮን ብር በማሳደግ 506 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡
ከእነዚህ ሰባት ባንኮች ሌላ ዘጠኙ ባንኮች ከታክስ በፊት ያስመዘገቡት ዓመታዊ ትርፍ መጠን ከ75 ሚሊዮን እስከ 380 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ከቀደመው ዓመት ያነሰ ትርፍ በማስመዝገብ የተጠቀሱት ሦስት ባንኮች ደግሞ ዘመን፣ ደቡብ ግሎባል ባንክና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ናቸው፡፡