Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በሕንዳውያን የተሠራው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት

ትኩስ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕንዳውያን ከ62 ዓመት በፊት በ1948 ዓ.ም. ያሠሩትና ሲኒማ አምፒር አጠገብ ይገኝ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (1923-1967) ሐውልት! በመስከረም 1967 ዓ.ም. በዘመነ ደርግ ፈርሶ ከተጣለ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አፀድ ውስጥ ያለ አንበሶቹ እንደነገሩ የቆመ፡፡ በወቅቱ ለማየት በታደልነው ሐውልቱ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የምንኖር የሕንድ ተወላጆች በሥራችንና በኑሮአችን ደስ ስላለን ለግርማዊ ንጉሥ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 25ኛው ዓመት የዘውድ በዓል ኢዮቤልዩ ይህን ሐውልት መታሰቢያ አቅርበናል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 1948 ዓ.ም.፡፡››

  • ሔኖክ መደብር

***

ተጠየቅ መስከረም!

ተጠየቅ መስከረም፤
ዛሬስ ዋዛ የለም
አንተን ለመቀበል እንቁጣጣሽ እያልን፤
ከርስ እንሞላለን፤ እንሳከራለን፤ እንጨፍራለን፡፡
አልገባኝም እኔን አንተ መወደድህ፤
ስትገባ ስትወጣ ድግስ መቀበልህ፤
ዶሮው፤ በጉ፤ ሰንጋው ይታረድልሃል፤
ርጥብ ቄጠማና ደም መውደድህ ታውቋል፡፡

እንስማው ተናገር፤
የያዝከውን ነገር፡፡
ስጦታህ ምንድን ነው? ለኛ ያመጣኸው
ክፈተው ሣጥንህን፤ እስቲ እንመልከተው፡፡
ለምለሙን ሳር እንደሁ ይጋጡት ከብቶቹ፤
ለኛ ምን ይዘሃል? ለኛ ለሰዎቹ
ሞት ሊጠፋ ነው ወይ ባዲስ ፍልስፍና?
መድኃኒት አመጣህ ለሕመም ደሀነት ለኛ ድንቁርና

ተጠየቅ መስከረም፤ ያመት መጀመሪያ፤
መነሻ፤ መድረሻ የሰው ልጅ የታሪክ መቁጠሪያ፡፡
ተጠየቅ መስከረም ማን አዲስ ይለብሳል ቡቱቶውን ጥሎ፤
ፎቅ ቤት ማን ይሠራል ጎጆውን አቃጥሎ፡፡
ተጠየቅ መስከረም፤ ያለፈው መስከረም ምን ታሪክ ነገረህ
ምን ሰማሁ፤ ምን አየሁ፤ ምን ተሰማኝ አለህ

መዝገቡ ምን ይላል አንብበው፤እንስማው፤
የቱ ያመዝናል? ሥራ ነው? ምኞት ነው?

መስከረም ተጠየቅ
ተናገር አትሳቅ
ጎተራው ተሟጦ በዕዳ ለታሰረው፤
ለዚያ ለገበሬ ሳያርፍ ለሚሠራው፤
ሚስቱና ልጆቹ እየተላቀሱ ለሚፈጽም ተግባር፤
በጦር ግንባር ላለው ለዚያ ለወታደር፤
ካልጋ ተቆራኝቶ ታሞ ለሚያጥረው፤
ወይ አይሞት፣ ወይ አይድን ስቃይ ለታደለው፤
ለወላድዋ ድሀ ባልዋ ለሞተባት፤
የልጆችዋ ረሀብ ሰቀቀን ለበላት፤
ምን ይዘህ መጥተሃል?
ተናገር፤ እስቲ በል?

በፍርሃት፤ በስጋት፤ ስቃይ ለሚበሉት፤
ፍትሕ ይዘህ መጣህ ወይ? ሕግና እኩልነት?
ሰላም አመጣህ ወይ? ነጻነትና ሀብት
ሰውን ልታድስ ነው? ወይስ ልታሻግት
የዘንድሮው አክሊል ትጋት ነው ስንፍና
ችግር ደባል ነው ወይ ዘንድሮም እንዳምና
ተናገር ላዳምጥህ
ትዝብት አይሰለችህ
ለኔ ያመጣኸው በሳቅህ ገብቶኛል፤
አንዲት ጥያቄ ናት ምን ሠራህ የምትል፡፡
ይጭነቅህ ይጥበብህ ግራ ይግባህ አንተም

መስፍን ወልደማርያም ‹‹እንጉርጉሮ›› (1967)

******

‹‹ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል››

‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡

አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡

‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡

ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡

‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡

ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …

‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡

ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡

‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡

ልጃቸው እንኳን አንድ ቀን አፏ ተስቶት ብትተቻቸው ‘አንቺም አልጋሽ የቢሮ ወንበር ነው’ ብለው ጆሮዋን ሲገርፏት እንደ ቀንድ አውጣ ተሰብስባ የሽሙጥና የኩርፊያ ልጋጓን ከመጐተት በስተቀር ቆማ አልመለሰችላቸውም፡፡ ማንንም ሰው ዝም የማሰኘት ችሎታ አላቸው፡፡

‹‹በል አንተ›› ብለው ሳይጠቁሙት ወሬ የሚጀምረውን ምሳሌ ጠቅሰው ‘መናገርን’ እስኪረግም ይወቁታል፡፡ መልካም ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ የወደቀ ምራቅ ይመልሳሉ፣ ግመል ያሰክራሉ የአንድን የሰው ፀባይ የማያልቅ የሚቃረን የሚፋቀር ጐን ይሰጡታል፡፡ ‘ድንቅነት’ በእሳቸው ምላስ ሺሕ ፊት አላት … ‘ርግማን’ እልፍ ፊት አላት፡፡

እና ስልክ ለመደወል ቢጠፉ ለአካባቢው ሆነ ለማንም አይገርምም፡፡ የሚበቃ ምክንያት አላቸው፡፡ ባይኖርም ይሰጣሉ፡፡ ከሰጡ ደግሞ መቀበል ድንቅ ነው፡፡

አበባ ሥጋውን አመቻችታ ለመቁረጥ መስመር ስትፈልግ ልስላሴውና ቅዝቃዜው ማረካት፡፡ ቁርስዋንም ስላልበላች ቁርጥ ለመሞከር የድልህ ዕቃ አውጥታ ትንሽ ድልህ መክተፊያው ጣውላ ላይ ጠብ አድርጋ እየከተፈች አልፎ አልፎ ጥሬ ሥጋ እየዋጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡ ራስ ምታቱ ግን ኦ! ኦ! ያው ነው፡፡ ሻሽዋን አጠንክራ አናቷ ዙሪያ መጠምጠሙ ነው በትንሹም ቢሆን ያዋጣት፡፡

ስልክ መደወያ ቦታው በደብሪቱ የፈጠራ ችሎታ የሚወሰን ስለሆነ፣ ጭን የመሰለ ሰውነታቸውን ተሸክመው ማድ ቤት ሲገቡ መጀመሪያ ያዩት ግራ ጐኑ ላይ ቡግንጅ ያበቀለ የመሰለውን የአበባን ፊት ነው፡፡ ይሔ ቡግንጅ ደግሞ እንደ አናሳ ፍጡር ይነቃነቃል፡፡ ደማቸው ፈላ፡፡

‹‹ለራስሽ ደገስሽው?››

ቢላውን ቀምተው ቃጡባት ‹‹አንገቷን ማለት ነው›› አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተደራሲያቸው ባይታይም፡፡ በነጠላ አይናገሩም ሲበሽቁ … የጐዳቸው አንድ ሰው ተከታይ አለው፤ እና ‹‹እናንተን ምን ማድረግ ይሻላል?›› ይላሉ … እሳቸውም ተከታይ አላቸው ግን አማራጭ ብዜቱን ገለልተኛ በግምት የሚመጠን ያደርጉታል፡፡

‹‹ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል … ሴት ደረቅ እንጀራ አነሳት? … ቢበሉት ከቂጥ በላይ አይሆን … ‘ቂጣም ያሰኛል’›› አሉ፡፡

  • አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች