Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን መልሳ ለመመሥረት ማጤን አለባት››

አቶ አብዱል መሐመድ፣ የኢንተርአፍሪካ ግሩፕ መሥራች

አቶ አብዱል መሐመድ የኢንተርአፍሪካ ግሩፕ መሥራች አባል ናቸው፡፡ በኢንተርአፍሪካ ግሩፕ የሰብዓዊ፣ የሰላምና የልማት ጉዳዮች የምክክር ማዕከል የአፍሪካ ቀንድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥም ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያ የ1997 ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ፖለቲካዊ ውይይቶችና ክርክሮች እንዲደረጉ በማገዝ መንቀሳቀሱ ይታወሳል፡፡ አቶ አብዱል የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለዓመታት አገልግለዋል፡፡ በሙያው ዓለምም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ መደቦች ላይ ተመድበው በማገልገልም የካበተ ልምድና ተሞክሮ አላቸው፡፡ ከሚጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ኃላፊነቶቻቸው መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዳርፉር ወታደራዊ ተልዕኮ (ዩናሚድ) የፖለቲካ ክፍል ተጣባባቂ ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የዳርፉር- ዳርፉር የምክክር መድረክ ሊቀመንበር በመሆን መሥራታቸው ይገኙበታል፡፡ በተመድ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ በመሆን ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የዓለም ቤተ ክርስቲያን አግልግሎት ውስጥ በተለያየ ደረጃ ከማገልገላቸውም በላይ፣ ለሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የዕርዳታና የፈጥኖ ደራሽ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የዕርቅ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ያለገሉበትም ከሚጠቀሱ ተሞክሮዎቻቸው መካከል ይመደባል፡፡ ግጭት በማያጣው በመካከለኛው ምሥራቅና በባህረ ሰላጤው አገሮች ጉዳይ፣ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ስላለው ተፅዕኖ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው አቶ አብዱል፣ ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ቀውስ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ በግላቸው ያላቸውን ዕይታና ትንታኔ አሥራት ሥዩም እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተለይም ደግሞ በዓረብ ባህረ ሰላጤ ምክር ቤት (GCC) አገሮች በቅርብ ጊዜ እየተስተዋለ ያለ ከፍተኛ የጦር ኃይል ማጠናከር እንቅስቃሴ አለ፡፡ በተለይ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ አገሮች በመከላከያ ዘርፍ የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው? ለምን እየተዘጋጁ ይመስልዎታል?

አቶ አብዱል፡- በትክክል እንደተረዳኸው በገልፍ አገሮች አካባቢ ከፍተኛ የሚሊተሪ ዝግጅት መስተዋል ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ዋናው ነገር እነዚህ አገሮች ምን ዓይነት የፀጥታ ችግር ቢኖርባቸው ነው፣ በዚህ ደረጃ የጦር ኃይላቸውን ማደራጀት ያስፈለጋቸው የሚለው ጉዳይ  ነው፡፡ በታሪክ ስንመለከት ቀደም ብሎ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የነበረበትና ግጭት የማይጠፋው የመካከለኛው ምሥራቅ ክልል ወደ ሰሜን ያለው ማለትም ኢራቅን፣ ኢራንን፣ ሶሪያን፣ ሊባኖስንና ፍልስጤምን የሚያጠቃልለው ክፍል ነበር፡፡ ይህ አካባቢ በጣም ወታደራዊ እንቅስቃሴ የበዛበትና ግጭቶችም በተደጋጋሚ የሚደርስበት ክልል ነበር፡፡ ነገር ግን በኢራንና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ያለው ዘላቂ ጠላትነት እየከረረ በመሄዱ፣ አሁን የገልፍ አካባቢም እንዲሁ በወታደራዊ ውጥረት ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ዘላቂ ጠላትነት እንደሚታወቀው በየመን ወደ የእጅ አዙር የለየለት ጦርነት ተቀይሯል፡፡ በጂሲሲ ሥር ያሉት አገሮችን ጨምሮ ሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ ቡድን በየመንና በኢራን ይደገፋል ተብሎ ከሚታሰበው የሁቲ የአማፅያን ቡድን ጋር እየተዋጋ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በተለይ ሳዑዲ ዓረቢያ በምዕራቡ ዓለም በአሜሪካና በኢራን መካከል እየተፈጠረ የመጣው መለሳለስ እያሠጋት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዋናነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ከኢራን ጋር የፈረሙት የኑክሌር ስምምነት፣ ለሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት የፈጠረባት ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የወታደራዊ አቅሟን ማጠናከር መርጣለች፡፡ ለነገሩ ከአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በኋላ ሳዑዲ ዓረቢያ አሜሪካ የገባችላትን ድጋፍ ለመስጠት ቃል ለማደስ በሩ ክፍት ቢሆንም፣ በኦባማ ጊዜ ግን ይህ ሥጋት ያየለበት ነበር፡፡ በእኔ አመለካከት ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢራን በኩል ሊሰነዘርብኝ ይችላል የምትለው ጥቃት ሥጋት ያለልክ የተጋነነ ነው፡፡ አሁን ይህ መጋነን ቅጥ ያጣ እየሆነም ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ኢራን ከፀጥታው ምክር ቤትና ከጀርመን ጋር የፈረመችው የኑክሌር ስምምነት ለሳዑዲ ዓረቢያና ለአካባቢው የሳዑዲ ተቀፅላ አገሮች ተጨማሪ የፀጥታ ማረጋገጫ ሲሆን፣ አገሮቹ ግን እንደ ሥጋት እያዩት ነው፡፡ ይህ ስምምነት እነዚህ የምዕራብ አገሮችና የፀጥታው ምክር ቤት የነሳዑዲን የፀጥታ ጉዳይ ለኢራን አሳልፎ የሸጠም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሳዑዲ ዓረቢያዎቹ የሚፈልጉት ማረጋገጫ በጣም የተጋነነና መቶ በመቶ የሆነ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተው የሳዑዲ ዓረቢያ የፀጥታ ሥጋት፣ አገሪቱን ወደ ተጋነነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንድትሄድ አድርጓታል፡፡

      በዚህ አላበቃም፡፡ አሁን ደግሞ እነዚህ የገልፍ አገሮች ከራሳቸው ክልል አልፈው በአጠቃላይ የቀይ ባህር ክልልን እያስታጠቁ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ቀይ ባህር አካባቢ ያሉ ወደቦችን ብናይ ከታች ከኪስማዩ (ሶማሊያ) ጀምሮ ላይ ፖርት ሱዳን ድረስ ያለው ክልል በከፍተኛ የወታደራዊ ድርጅትና ትጥቅ እየተጥለቀለቀለ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ የቀይ ባህር ክልል ባብ ኤል መንደብን ጨምሮ ለዓለማችን የንግድ እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በእስያና በአውሮፓ መካከል ያለው ንግድ 40 በመቶ የሚሆነው በዚህ በባብ ኤል መንደብ እንደሚያልፍ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው የኃይል አቅርቦት ለእስያ አገሮች የሚላከው በዚሁ የባህር መተላለፊያ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ በዚህ ክልል ላይ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው አገሮች አሁን የባህር ኃይላቸውን በቀይ ባህር ወደቦች ላይ እያከማቹ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ብትወስድ አሁን ጂቡቲ ላይ ወታደራዊ ጦር ሠፈር የሌለው አገር ጥቂት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሳዑዲዎቹ የጦር መሣሪያ እየታጠቁ ያሉት ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ነው፡፡ አሁን የመን ውስጥ ያለውን ሁኔታ ብታይ በጣም አሥጊ ነው፡፡ እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታውን ስንቃኝ የመን አሁን የጨነገፈ አገር ሆኗል፡፡ ታዲያ መንግሥት አልባነት ከከባድ ወታደራዊ እንቅስቃሴና የጦር መሣሪያ ጋር ሲደመር ለእነ አልሸባብና አልቃይዳ ልዩ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በመሆኑም የእነዚህ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ መታጠቅ ክልሉን ለማተራመስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ እንደጠቀሱት ለዚህ ክልል ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴና ትጥቅ ምክንያቱ በኢራንና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ያለው ዕድሜ ጠገብ የጠላትነት ስሜት ነው፡፡ የዚህ ስሜት ታሪካዊ ዳራው ምንድነው?

አቶ አብዱል፡- እኔ እንደሚመስለኝ ነገሩ ከመንግሥታቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ የሚወረስ ነው፡፡ ኢራንን የወሰድን እንደሆነ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1979 የእስልምና አብዮት በኋላ በአገሪቱ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል በከፍተኛ ደረጃ በሃይማኖት የተቃኘ መሆኑ ሲታወቅ፣ በአጠቃላይ ለሺዓ እስልምና ተቋማት እንደ ማዕከል ሲያገለግልም ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም የኢራን መንግሥት ለአብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ የሺዓ አናሳ ማኅበረሰቦች እንደ መጠለያ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ኢራን ከሺዓ ማዕከልነት ባለፈ በታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አንድነቱን የጠበቀ ጠንካራ አገር መሆኑም ይታወቃል፡፡ እንዲያውም የኢራን ታሪክ ከአውሮፓም የቀደመ ጥንታዊ መንግሥትነት ልምድ ያለው ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢራን መሠረት ያለው በቅጡ የተደራጀ መንግሥት ያለው አገርም ነው፡፡ ይህ መንግሥት በቅጡ ስትራቴጂካዊ ጥቅሙን ማስከበር የሚችልና ከራሱ አልፎ በአካባቢው ኃይሉን ማሳየት የሚችልም ነው፡፡ በመሆኑም በአካባቢው ካሉት እነ ሳዑዲ ዓረቢያ ባለፈ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምልከታ ኢራንን ብጥብጥ ፈጣሪ አገር አድርጎ ፈርጆታል፡፡ በሳዑዲና በአሜሪካ እንዲሁም በእስራኤል መካከል ፀረ ኢራን ትብብርም ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ለዘመናት እነዚህ ሱኒ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና አሜሪካ ኢራንን የመገደብ ስትራቴጂ ሲያራምዱ ኖረዋል፡፡

      ነገር ግን በዚህ መሀል የአሜሪካን የኢራቅ ወረራ ይህንን የቆየ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ አወሳሰበው፡፡ ወረራው በሚገርም ሁኔታ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሰጠው ለኢራን ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አሜሪካ በወረራው የተጠናከረውንና በሳዳም ሁሴን የሚመራውን የሱኒ ኃይል (የኢራቅ መንግሥትና ባዝ ፓርቲን) ሲያፈራርስ ለኢራን መልካም አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ከወረራው በኋላ በኢራቅ ወደ ሥልጣን የመጣው ኃይል የሺዓ ኃይል በመሆኑ ለኢራን ተፈጥሮአዊ ቅርበት ነበረው፡፡ በጥቅሉ ይህ ወረራ በቀጣናው የነበረውን የኃይል ሚዛን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፋለሰው፡፡ ሌላው በአካባቢው አሻራውን እያሳረፈ ያለው ጉዳይ በሶሪያ የተቀሰቀሰው ግጭት ነው፡፡ የዚህ ግጭት ውጤት ባልተጠበቀ መንገድ የሱኒና የሺዓ ግጭት መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በዚህ መሀል እንደ አልቃይዳ ያሉ ኃይሎች በሳዳም ሁሴን የሱኒ መንግሥት መውደቅ ምክንያት የተፈጠረውን የሱኒ ተሟጋችነት ሚናን ብልኃት በተሞላበት ሁኔታ የተጠቀሙበት ሲሆን፣ ይህም የሽብር እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋፋት በእጅጉ ጠቅሟቸዋል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ቡድኖች በተለይ በኢራቅ ከሳዳም ውድቀት በኋላ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው የእምነት የጎራ ግጭት የቀሰቀሱ ሲሆን፣ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የሺዓ መንግሥትም በዚሁ መንገድ መሄዱ ግጭቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ ወረራ የተሠራው ሌላው ስህተት ደግሞ በዓረቡ ዓለም ሁለተኛው ጠንካራ ሠራዊት የነበረውን የኢራቅ ጦር [አንደኛ ግብፅ ነው] ሜዳ ላይ መበተን ነበር፡፡ ይህ ጦር የሠለጠነ ሲሆን፣ ያለ ምንም ዓላማ ከተበተነ በኋላ የነአልቃይዳ ፍጆታ  ሆኗል፡፡ በተለይ የአልቃይዳ ግንጣይ የሆነው ኢስላሚክ ስቴት ወይም አይኤስ እንዲቀላቀል በር ከፍቶለታል፡፡ ለዚህም ነው አይኤስ አልቃይዳ እንኳን አስቦት የማያውቀውን ያህል ቦታ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር የቻለው፡፡ ከዚህ በላይ በኢራቅ የተፈጠረው ክፍተትና በሶሪያ ግጭት የተገኘውን ቀዳዳ በመጠቀም አይኤስ በጣም ሰፊ ቦታን መቆጣጠር የቻለ በመሆኑ፣ ይህም ስኬት አበረታቶት ካሊፌት እስከ ማወጅ ደርሷል፡፡ በኢራቅ ለምሳሌ ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ (ሞሱል) እስካሁን ይዘው በመዋጋት ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በሌላ በኩል ኢራን ጠንካራ የቀጣናው አገርና የሳዑዲ ዓረቢያ ጠላት ከመሆኗ ባለፈ፣ በአሸባሪነት ዙሪያ ብዙም የታወቀ ሚና ኖሯት አያውቅም፡፡ ነገር ግን አሜሪካም ሆነች እስራኤል የኢራንን መንግሥት ለአሸባሪዎች ድጋፍ በመስጠት ይከሱታል፡፡ እንዲያውም የብዙ የአሸባሪ ግለሰቦች መፍለቂያ ናት የምትባለው ሳዑዲ ዓረቢያ በሽብር ስትወቀስ አይሰማም፡፡ ታዲያ ኢራን በምዕራባዊያን እንድትጠላ ያደረጋት ዋናው ምክንያት ምንድነው?

አቶ አብዱል፡- ዞሮ ዞሮ በኢራን ላይ ያለህ የፖለቲካ አቋም ምንም ይሁን ምን ኢራን አሁንም ቢሆን አንድነቱን የጠበቀ፣ ኃይሉን ከራሱ አልፎ በቀጣናው ላይ ማሳየት የሚችልና ረጅም ታሪክ ያለው አገር ነው፡፡ ይህ አገር ትልልቅ ስትራቴጂካዊ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችል አቅም ያለው አገርም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ኢራን ወዳጆቹን መደገፍና ከጠላቶች መከላከል የሚችል አገር መሆኑም ይታያል፡፡ ኢራን በሌላ በኩል የኑክሌር ቴክኖሎጂ ማበልፀግ አቅም ያለው አገር መሆኑም ታይቷል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ለሱኒ የቀጣናው አገሮች ሲቀጥል ደግሞ ለእስራኤል የማይጋፉት ባላጋራ እየሆነ የመጣ አገር ነው፡፡ በመሆኑም የቀጣናው አገሮች ካለአሜሪካ ዕገዛ የዚህን አገር ግፊት መቋቋም ይከብዳቸዋል፡፡ በቅርቡ የተፈረመውን የኑክሌር ማዕቀፍ ስምምነት ብትመለከት ከስድስት አገሮች ጋር ተደራድሮ የራሱን አገራዊ ጥቅም አስጠብቆ ስምምነት መፈረም፣ በተለይ በዓረቡ ዓለም በቀላሉ የሚገኝ ጥንካሬ አይደለም፡፡ ከዚያ በላይ ኢራን የፈረመችውን ስምምነት በከፍተኛ አፈጻጸም ተግባር ላይ እያዋለች ለመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ ራሷ አሜሪካ መስክረውላታል፡፡ አሁን የትራምፕ መንግሥትና እስራኤል ስምምነቱ በመጀመሪያም የተሳሳተ ነበር ብለው መከራከር ጀምረዋል፡፡ የፀጥታ ምክር ቤት ግን በስምምነቱ ላይ ምንም ችግር የለበትም፣ ሳዑዲ ዓረቢያም ብትሆን የእስራኤልንና የአሜሪካንን አቋም ነው የምታንፀባርቀው፣ ማለትም ስምምነት መኖር አልነበረበትም የሚለውን፡፡

በሌላ በኩል ሳዑዲና እስራኤል በአሜሪካ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲወተውቱ የኖሩት በኦባማ ጊዜ አሜሪካ በቀጣናው ላይ ያላት ግንዛቤ የተለየ ነበር፡፡ እሱም እንደ ኢራን ዓይነት አገሮች ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰድ በቀጣናው ለማቆም የሚከብድ ግጭት መቀስቀስ ሊሆን ይችላል የሚል ነበር፡፡ የኢራን ምላሽ የመስጠት አቅም መናቅ የለበትም የሚለው የኦባማ መንግሥት ዕይታ፣ በተለይ የሆርሙስን መተላለፊያ የመዝጋት አቅም ያላት ኢራን የዓለም አቀፉን የነዳጅ ንግድ ችግር ውስጥ ልትከተው ትችላለች የሚል ሥጋት ነበረው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛውን የመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮችን የሕዝብ አሠፋፈር ካስተዋልን አብዛኛው የሺዓ ማኅበረሰቦች የሚኖሩት የእነዚህ አገሮች የነዳጅ ሀብት ባለበት አካባቢ ነው፡፡ በመሆኑም በሺዓ ማዕከልነቷ ኢራን ለእነዚህ አገሮች በጣም አደጋ መሆን ትችላለች ማለት ነው፡፡ በቀላሉ ኢራን ቀጣናውን ለአገዛዝ አስቸጋሪ ማድረግ ይቻላታል፡፡ አሜሪካኖቹም ይህንን እውነታ ያውቁታል፡፡

በተጨማሪም አሜሪካኖች የአብዛኛው የዓረብ አገሮች አቅም ከኢራን ጋር ሲነፃፀር የት እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ያለ እነሱ ድጋፍ ራሳቸውን መከላከል እንደማይችሉም ይገምታሉ፡፡ በቀላሉ ሳዑዲ ዓረቢያን ማየቱ በቂ ነው፡፡ አሁን በየመን ሳዑዲ ዓረቢያ በሙሉ ኃይሏ ነው የገባችው፡፡ ለጦር መሣሪያና ትጥቅ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በየዓመቱ እያጠፋች ነው፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ትንሽዬ አመፀኛ ጦር ለማሸነፍና ለመቆጣጠር  ነው፡፡ እንደ አንዳንድ መረጃዎች ከሆነ ሁቲዎች ከኢራን ያገኙታል የሚባለው ድጋፍ በጣም የተጋነነ ነው፡፡ ነገር ግን ሳዑዲ ዓረቢያ የገልፍ አገሮችን ከጎኗ አድርጋ በአሜሪካ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ነው ውጊያ ውስጥ የገባችው፡፡ ከዚህ መወሰድ ያለበት ትምህርት ትንሽ ጦር ማሸነፍ ካልቻሉ እንዴት እንደ ኢራን ዓይነት ኃይል ለማሸነፍ ይቻላል? ስለዚህ የቀጣናው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ኢራንን በማግለልና በመጨረሻም ኢራን በቀጣናው የማተራመስ ሚና እንድትጫወት በመግፋት ሳይሆን፣ ከእሷ ጋር በመወያየት ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ አገሮች ኢራንን በአካባቢው እንዳለ አንድ ኃይል መቀበል አለባቸው፡፡ ኢራንም ብትሆን ሌሎችን የቀጣናውን አገሮች መቀበል አለባት፡፡ ከተቻለ እነዚህ አገሮች የሁሉንም ጥቅም የሚያንፀባርቅ የስምምነት ማዕቀፍ ቢኖራቸው ለቀጣናው የወደፊት ሰላም በጣም ወሳኝ ነው፡፡

      የዚህ የገልፍ ቀጣና ጉዳይ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይ በሁለቱ ቀጣናዎች መካከል በጣም ቅርቡ የሚባለው ቦታን ብንወስድ ባብ ኤል መንደብ ነው፡፡ ባብ ኤል መንደብ ግፋ ቢል ከ25 ኪሎ ሜትር አይበልጥም ከዓረቡ ቀጣና የሚርቀው፡፡ በመሆኑም በዚያ ቀጣና የሚፈጠረው ነገር ለአፍሪካ ቀንድም፣ ከዚያ ባሻገርም ለዓለም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በኤደን ባህረ ሰላጤ መረጋጋት መኖሩ የተለየ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ናት፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎችዋ የተመሠረቱት በዚህ የኤደን ገልፍ ላይ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ደግሞ በጣም ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚበዛበት መሆኑን ቀደም ብለን ገልጸናል፡፡ በነገራችን ላይ የገልፍ አገሮች በወታደራዊ ትጥቅ እየተደራጁ ነው ሲባል፣ ለምሳሌ የሳዑዲ ዓረቢያን ዓመታዊ የመከላከያ በጀት ብናይ ከ87 ቢሊዮን ዶላር የማያንስ ነው፡፡ ይቺ አገር ብቻዋን የምታወጣው ወጪ አጠቃላይ የአፍሪካ አገሮች ተጣምረው በመከላከያቸው ላይ ከሚያወጡት የበለጠ ነው፡፡ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለችው፡፡ አንዳንዴ ከሩሲያ በላይ ነው የምታወጣው፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ለ30 ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ የመከላከያ ወጪ ሲታይ ሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ ትኩረት የምታደርግ አገር መሆኗን መረዳት አይከብድም፡፡ ነገር ግን የሳዑዲ ዓረቢያ ጦር በሰው ኃይል ደረጃ ሲታይ ያን ያህል ትልቅ አይደለም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ጥያቄ በዚህ ሁሉ የጦር መሣሪያ ምን ሊሠሩበት አቅደው ነው የሚለው ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ለቀጣናው ሰላም የዚያን ያህል ቢያወጡ የፀጥታ ሥጋታቸውን በተሻለ ሊቀንሱት ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ በየመን ያለው ግጭት ከቀጠለና የጦርነቱ ግፊት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ካዘነበለ ከጊዜ በኋላ ጦርነቱ ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መዛወሩ አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ችግሩ ይህ ሁሉ የጦር መሣሪያ በማይሆኑ ቡድኖች እጅ እንዲወድቅ በር መክፈቱ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለመነሻ ያህል ከታሪካዊው የሳዑዲ ዓረቢያና የኳታር ግንኙነት እንጀምር፡፡ ሳዑዲ በኳታር ላይ የበላይነቱን በመያዝ ለረጅም ጊዜ በተፅዕኖዋ ሥር አቆይታታለች፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኳታር ከሳዑዲ ጋር የነበራትን ቁርኝት በመተው ይልቁንም የራሷን የወደፊት ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቀይሳለች፡፡ ይህ አፋጣኝ የለውጥ ሒደት እንዲፈጠር ሰበብ የሆነው ምንድነው ብለው ያስባሉ?

አቶ አብዱል፡- ሲጀመር ሳዑዲም ሆነች ኳታር የሚከተሉት ዋሃቢ የሚባለውን የእስልምና ክንፍ ነው፡፡ በዚህ አኳኋን ሲታይ ሁለቱም አገሮች በሃይማኖትም ሆነ በዓለም እሳቤዎች ተመሳሳይ አቋም ይጋራሉ፡፡ ሐሳቡን ይበልጥ ለማስጨበጥ ያህል ሳዑዲና ኳታር በንጉሣዊውያን ቤተሰቦች የሚመሩ፣ በሳዑዲ ወገን አል ሳዑድ፣ በኳታር ወገን ደግሞ አል ታኒ የተባሉት ንጉሣውያን ቤተሰቦች አገሮቹን ያስተዳድራሉ፡፡ እርግጥ ኩዌትና ባህሬንን ጨምሮ ሁሉም በሼኮች አማካይነት በንጉሣውያን ቤተሰቦች የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ አንዱ ልዩነት ግን ኳታሮቹ ንጉሣውያን  የተማሩ ወይም በሙስሊም ወንድማማቾች አስተምህሮ የተቀረፁ በመሆናቸው፣ ስለወደፊቱ የአገራቸው መፃኢ ዕድልና ስለዓለም ያላቸው ዘመናዊ ዕይታ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እንደምታውቀው የሙስሊም ወንድማማቾች አስተምህሮ መነሻው ከግብፅ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የነበሩ የግብፅ ምሁራን በኳታር ይሠሩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦችን የማስተማር ዕድል ነበራቸው፡፡ እንደ አልቱራቢ ያሉት የሱዳን ሙስሊም ወንድማማቾችም በዚህ ወቅት ነበር ወደ ኳታር ያቀኑት፡፡ የአሁኑ የኳታር አሚር አባት የሙስሊም ወንድማማቾች ያስተማሯቸው ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ. በ1990 ሽማግሌውን አሚር ከዙፋናቸው አውርደው ነበር፡፡ እኚህ አሚር ኳታርን ወደ ሌላ የተለየ አቅጣጫ እንድታቀና ማድረግ ጀመሩ፡፡ ለአገራቸው የነበራቸው ራዕይ ሳዑዲዎቹ ለራሳቸው ካላቸው ዕይታ የተለየ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት የተንፀባረቀውም የራሳቸውን ገለልተኛ የውጭ ፖሊሲ በቀረፁ ጊዜ ነበር፡፡ 

ለውጡ ሥር እንዲሰድ ምክንያት የሆነው ደግሞ በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ካላቸው አገሮች አንዷ ኳታር መሆኗ ከተረጋገጠበት ወቅት ጋር በመገጣጠሙ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ከገልፍ አገሮች የትብብር ምክር ቤት የተለየ የፖሊሲ ምልከታ እንዲኖራቸውና የተለዩ ተቋማትን እንዲመሠርቱ ረድቷቸዋል፡፡ የዘመናዊነታቸው አንደኛው አካል የሆነው እንደ ቢቢሲ ካሉ ዓለም አቀፍ ሞዴል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር የሚመሳሰለውን አልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ መክፈታቸው ቢሆንም፣ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ግን የራሱን የአቀራረብ ሥልት የሚከተል ሆኖ ብቅ ያለ ነው፡፡ የዓረብ ወጣቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ በማፈላለግ ላይ በነበሩበት ምቹ ወቅት ነበር አልጄዚራን የመሠረቱት፡፡ ስለዚህም ጣቢያው ዘመናዊና ምዕራባዊ ይዘት የሌለው የዜና ምንጭና በአቀራረብ ረገድ ክፍተቱን በፍጥነት ለመሙላት የቻለ ጣቢያ በመሆን ብቅ አለ፡፡ ምርጥ ዶክመንተሪዎችን በማዘጋጀት በኩል ብልጫውን ወስዶ ተገኘ፡፡ የኳታር አሚሮችን መንካት ባይፈቀድለትም፣ ከዚያ ባሻገር ባለው ክልል እንዳሻው የመዘገብ ነፃነትና ገደብ የለሽ ወሰን ተሰጥቶታል፡፡ ተዓማኒነት ማግኘት በጀመረ ማግሥት ግን የአረብ የፀደይ አብዮት ፈነዳ፡፡ ይህም ጣቢያውን ወደ ላይኛው ማማ እንዲወጣ ረድቶታል ማለት ይቻላል፡፡ የዓረብ አብዮትን ሲዘግቡ የነበረው ልክ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማያውቅ በሚመስል አኳኋን ነበር፡፡ በርካታ ሀብት የፈሰሰበት ዝግጅት በማድረጋቸው ኩነቱን በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ ጭምር ችለዋል፡፡ የዓረቡ ዓለም ወጣቶች የየአገራቸው መንግሥታት የሚያስተጋቡትን ፕሮፓጋንዳ በመተው፣ ከቀን ወደ ቀን አልጄዚራን መከታተል በመጀመራቸው የአመራር ክፍሎቹን ማስከፋቱ አልቀረም፡፡ በመሆኑም በጣቢያው ላይ ተባብረው በመነሳት ለህልውናችን አደገኛ ነው እስከ ማለት ደረሱ፡፡ ለረጅም ጊዜ የገዙ መሪዎች ከወደቁ በኋላም ቢሆን በጣቢያው ላይ የተነሳው ተቃውሞ ይበልጥ እየተካረረ ሄዷል፡፡ ሳዑዲዎች አል አራቢያ የተሰኘ ጣቢያ በመክፈት አልጄዚራን ለመቀናቀን ቢሞክሩም፣ ነገሩን ከማባባስ በቀር የፈየዱት ነገር አልነበረም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ለመሳሰለው መብት ሁሉ መከታ ነን የሚሉት አሜሪካውያንም ቢሆኑ፣ አልጄዚራ አሜሪካ በዓረቡ ዓለም ጦርነት እያቀጣጠለች ስለመሆኗ መዘገብ ሲጀምር ትችታቸውን ይሰነዝሩበት ገቡ፡፡ ስለዚህም የዓረብኛ ማሠራጫ ጣቢያው በተለይ የሙስሊም ወንድማማቾች ወይም የእስልምና ፖለቲካ ቡድን እየተባለ የሚጠራው አካል መሣሪያ ተደርጎ ይታይ ጀመር፡፡

ሪፖርተር፡- የእስልምና ወንድማማቾች ወይም የእስልምና ፖለቲካ ቡድን አስተምህሮ ለገልፍ አገሮች የትብብር ምክር ቤት፣ እንዲሁም ለሳዑዲ ሥጋት ሆኖ የሚታየው በምን ምክንያት ነው?

አቶ አብዱል፡- ቀድሞ ነገር ስለሽብርና አሸባሪነት ሳዑዲና የገልፍ አገሮች ምክር ቤት ያስቀመጡትን አስቸጋሪ ትርጓሜ መረዳት ይኖርብሃል፡፡ ከግብፅ በመነሳት በመካከለኛው ምሥራቅ የተስፋፋውን የሙስሊም ወንድማማቾች ወይም የእስልምና ፖለቲካ ቡድን፣ ሳዑዲዎቹ ለየትኛውም ዓላማቸው ሲሉ ከአልቃይዳ ብሎም ከአይኤስ እኩል የሚታይ አሸባሪ ቡድን አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ስለዚህ ሳዑዲና የገልፍ አገሮች ምክር ቤት ኳታርን አሸባሪዎችን በገንዘብ ትደግፋለች ብለው ሲወነጅሉ፣ የሙስሊም ወንድማማቾችን ማለታቸው እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ሳዑዲዎች ይብሱን የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረትን ከእነ አልቃይዳ፣ ከእነ አይኤስ እንዲሁም ከሒዝቦላ እኩል በሽብርተኝነት እንድትፈርጀው አሜሪካን ሲወተውቱ ነበር፡፡ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት ግን ይህ ውትወታቸው ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል፡፡ ከሒዝቦላ ጋር በተገናኘ የሚነሳው ነገር አስገራሚነት አለው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሺዓ እስልምና አካል በሆነችው ኢራን የሚደገፈውና ራሱም የሺዓ ቁርኝት ያለው የሊባኖስ መንግሥት ከሒዝቦላ ጋር ትስስር ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ቡድን ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ አሜሪካ በአሸባሪነት ብትፈርጀውም፣ ኢራን ግን ሕጋዊና ገለልተኛ ንቅናቄ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

በመሆኑም የአሸባሪነት ጉዳይ ከተነሳ ምንም እንኳ ለቃሉ የተሰጠ ጥቅል ትርጓሜ ቢኖርም፣ እያንዳንዱ አገር ማንን አሸባሪ በማለት እንደሚፈርጅና ማንን እንደሚተው የየራሱ ድምዳሜ አለው፡፡ ይህ ክስተት ሁልጊዜም ጥገኛ የሚሆነው አገሮች በቡድኑ አማካይነት በሚፈጠርባቸው ሥጋት ላይ ነው፡፡ የገልፍ ምክር ቤት አባላትን ስታይ አብዛኞቹ ከአይኤስ ጋር ከመዋጋት ይልቅ፣ ብዙውን ጊዜ የሚያጠፉት የሙስሊም ወንድማማቾችን በመዋጋት ላይ  ነው፡፡ ለአብነት ያህል ካየህ ከአይኤስ ጋር ያለውን ፍልሚያ ለአሜሪካኖች የተውላቸው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ዮርዳኖስ፣ ቱኒዚያና ሞሮኮ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ግን የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት የፖለቲካቸው አንድ አካል ሆኖ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በቱኒዚያ ዋናዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ቢሆኑም በግብፅ ግን በአሸባሪነት ተፈርጀዋል፡፡ በፍልስጤም ያለውን የሐማስ ንቅናቄ ካየህ በአብዛኛው በሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ እስራኤል፣ ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ግን አሸባሪ እያሉ ይጠሩታል፡፡ ኳታሮች ደግሞ የተቃውሞ ንቅናቄ ቡድን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- በሳዑዲና በኳታር መካከል ላለው አለመግባባት መነሻው ይህ ከሆነ፣ በቅርቡ ስለተከሰተው ሳዑዲና የገልፍ ምክር ቤት አባላት በኳታር ላይ ስለወሰዱት የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ጫና ቢያራሩልን?

አቶ አብዱል፡- ይህ ክስተት በቀጣናው ውስጥ ውስጡን እየተብላላ የቆየው ውጥረት ውጤት ነው፡፡ ኳታሮች ሳራቸውን እንደ ገለልተኛ አገር፣ እንዲሁም ገለልተኛ የውጭ ፖሊሲ ግቦች እንደሚከተል አገር ነው የሚቆጥሩት፡፡ በበርካታ የዲፕሎማሲ ሽምግልና ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ በሊባኖስ፣ በፍልስጤም፣ በሱዳን፣ በአፍጋኒስታንና በሌሎች በርካታ አገሮች ውስጥ ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡ ታሊባን በኳታር ጽሕፈት ቤት በመክፈቱ በታሊባንና በአሜሪካ መካከል ውጤታማ የፖለቲካ ግንኙነት እንዲፈጠር በማገዝ በተለይ እስረኞችን ለማስለቀቅ ጠቅሟል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ኳታሮች በየመን ጉዳይ ላይ ምክክር እንዲደረግ ለማድረግ ቢጥሩም ሳዑዲ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ በመሆኑም ኳታሮች ማንም ሊያነጋግራቸው ከማይፈልጋቸው ቡድኖች ጋር ፖለቲካዊ ውይይቶችና ድርድሮች እንዲደረጉ የማመቻቸት ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ታሳቢ ያደረጉት ካላቸው የፋይናንስ አቅም፣ እንዲሁም ካላቸው የዲፕሎማሲ ኃይል አኳያ ከተነጠሉ ቡድኖድ ጋር ግንኙነት የመሠረቱ ናቸው ብሎ የሚከሳቸው አካል እንደማይኖር ነበር፡፡ ከኢራንም ጋር ይህንኑ ነበር ያደረጉት፡፡ ምንም እንኳ ኳታሮች ከኢራን ጋር የማይግባቡበት ጉዳይ ቢኖራቸውም፣ የተመጠነ ግንኙነት መፍጠሩ ተገቢ እንደሆነ ግን ተገንዝበው ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢራንና ኳታር የሚጋሯቸው የነዳጅ ማውጫዎች ስላሉ፣ ኳታሮቹ ይህንንም ማበላሸት አልፈለጉም፡፡ ኢራኖቹ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ከኦማን ጋር የሥራ ግንኙነት አላቸው፡፡ እንዲውም በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደርና በኢራን መካከል ለተደረሰው የኑክሌር ማዕቀፍ ስምምነት፣ ኦማኖች በድብቅ ድርድሮቹን በማመቻቸት እንደተሳተፉ ይነገራል፡፡ በኢራን ጉዳይ ኩዌቶችም ከኢራን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ ሆኖም በቀጣናው ኢራንን እንደ ጭራቅ የምትቆጥራትና የዲያቢሎስ አምሳያ በማድረግ የምትፈርጃት ብቸኛዋ አገር ሳዑዲ አረቢያ ነች፡፡ በመሆኑም ሳዑዲዎች ኳታርን ሲወነጅሉና የገልፍ አገሮች ምክር አባላትም ተመሳሳይ አቋም እንዲያራምዱ ሲያነሳሱ መነሻ ያደረጓቸው ሰበቦች ከኢራን ጋር ግንኙነት አላት፣ የሙስሊም ወንድማማቾችን ትደግፋለች፣ እንዲሁም የእስላማዊ ፖለቲካ ቡድንን የሚያበረታታ የዜና ማሠራጫ ጣቢያ በመክፈቷ አሸባሪዎችን ትረዳለች በማለት ወንጅለዋታል፡፡

ሪፖርተር፡- በኳታር ላይ ለተጣለው ዕገዳ ድንገተኛ ምክንያት የሆነው ምንድን ነበር?

አቶ አብዱል፡- እንደሚመስለኝ በአሜሪካኖች የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው ለሳዑዲዎቹ የልብ ልብ የሰጣቸው፡፡ ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ተመሳሳዩን ለማድረግ ቢፈልጉም፣ የአሜሪካ መንግሥት ግን የገልፍ አገሮች ልካቸውን እንዲያውቁ ሲያስጠነቅቃቸው ቆይቷል፡፡ የ80 ሚሊዮን ሕዝብ አገር የሆነችው ኢራን በቀጣናው የወደፊት ህልውና ውስጥ ወሳኝ አካል እንደሆነች መቀበል፣ አሜሪካኖች ለገልፍ ምክር ቤት አባላት ካቀረቧቸው መካከል የሚጠቀሰው ነው፡፡ የኦባማ አስተዳደር በግልባጩ ኢራን በቀጣናው ገንቢ ሚናዋን እንድትጫወት ጫና ለመፍጠር ዝግጁ ነበር፡፡ ይህ አቋም ይበልጥ የተንፀባረቀው ደግሞ በአሜሪካና በኢራን መካከል የኑክሌር ስምምነት ሲፈረም ነበር፡፡ በኦማን አማካይነት በድብቅ የተሸመገለውና በይፋ የተፈረመው ስምምነት ግን እስራኤልና ሳዑዲን በጣም አስቆጥቷቸው ነበር፡፡ በመርህ ደረጃ ሲታይ የማይታሰብ ቢመስልም፣ ስምምነቱ ሁለቱ አገሮች የጋራ ትብብር እንዲፈጥሩና በኢራን ላይ እንዲነሱ ግን ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ እጅግ ተለዋዋጭ አቋም ያላቸው፣ አንዳንዴ ያለምንም አጥጋቢ ምክንያት ፕሬዚዳንት ኦባማ የሠሩትን እያንዳንዱን ነገር ሁሉ ለመናድ የተነሱ የሚመስሉ ፕሬዚዳንት መከሰታቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሳዑዲዎች ዕይታ አኳያ ነገሩን የምታይላቸውና የምትቀበላቸው አሜሪካ ለማግኘት ችለዋል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚከሰት ያሳየው የዚህ ጉዳይ መገለጫ ደግሞ በቅርቡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሳዑዲ ሥርወ መንግሥትን መጎብኘታቸው ነው፡፡ ሳዑዲዎቹ የሱኒ እስልምናን የሚከተሉ የቀጣናውን አገሮች አሠልፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሳዑዲዎች ያቀነባበሩት ድራማ የሚመስል ሲሆን፣ ሱኒ ወይም ሺዓ የሚባል ክፍፍል የሌለ አስመስሎታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ መርዘኛ የሃይማኖት ፍረጃ ወደ አፍሪካ አገሮችም እየተዛመተ ነው፡፡ አዎ ጥቂት የሱኒ እስልምናን የሚከተሉ የአፍሪካ አገሮች አሉ፡፡ አብዛኞቹ የሱፊ እስልምና ተከታዮች ናቸው፡፡ አንዳቸውም ግን ዋሃቢዎች አይደሉም፡፡ ሳዑዲዎች ግን ዋሃቢ ናቸው፡፡ የዋሃቢ አተረጓጎም በአብዛኛው ለሰለፊ ንቅናቄዎች መፈልፈያ በመሆኑ፣ ከዚህ የመነጩ በርካታ ጽንፈኛ ቡድኖች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያው በተለመደው ማንነታቸው ሳዑዲ ያቀረበቻቸውን ነጥቦች በመቀበላቸው፣ እንደ ኳታር ባሉ አገሮች ላይ ለመነሳት ጊዜ አልፈጀባትም፡፡

ሪፖርተር፡- ትራምፕ የሳዑዲ አረቢያ እንቅስቃሴዎችን እንደተቀበሉ ካሳወቁባቸው ነገሮች መካከል በንግግራቸው ኳታርን በይፋ አሸባሪዎችን ትረዳለች ብለው መወንጀላቸው ነው፡፡ ይሁንና አሜሪካ በኳታር የጦር ሠፈር በመመሥረት በኢራቅና በአፍጋኒስታን የምታካሂደውን ጦርነት የምትመራው ከኳታር ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሻሚ ነገር እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

አቶ አብዱል፡- ይህ ሁኔታ የሚሳይህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት የማይሠራ እንደሆነ ነው፡፡ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት የሆነው ፔንታጎንና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኳታር ጉዳይ ላይ የተለየ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ኳታር አሸባሪዎችን ትደግፋለች የሚል አቋም ያራምዳሉ፡፡ እሳቸው ስለወሰኑ ብቻ ነው ይህ የሆነው፡፡ አሜሪካኖች ለሳዑዲዎች በቢሊዮኖች የሚቆጠር የጦር መሣሪያ ሽያጭ እንደሚያከናውኑ ባስታወቁበት ወቅት፣ ፔንታጎን ለኳታር 12 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሣሪዎችን ሲሸጥ ግን ታይቷል፡፡ በቀጣናው ካላቸው ወታደራዊ የአየር ቤዝ ትልቁ የሚገኘው በኳታር  ነው፡፡ ስለዚህ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የምትከተለው ፖሊሲ ችግር ያለበት ነው፡፡ ለሳዑዲዎቹና ለሌሎቹም የተሰጣቸው ዕድል ወደፊት በቀጣናው የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ፍላጎት ላይ ችግር የሚያስከትል አዝማሚያ እንደሚያመጣ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አካሂዳቸውን ካልቀየሩ በቀር አሜሪካኖች በቀጣናው ለተከሰተው ችግር አንድ አካል ሆነዋል፡፡ ሌላው በሳዑዲ በኩል የተፈጠረው በተሳሳተ አስተሳሰብ ኢራንን ዳር ማውጣታቸው ነው፡፡ አየህ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ኢራንን ገሸሽ ማድረግ መላ ቀጣናውን ግጭት ውስጥ ሊያስገባ ወደሚችል አዝማሚያ እንዲገፋፋ ሊያደርግ የሚችል ሥጋት ይፈጥራል፡፡ ራሳቸውን ብቻም ሳይሆን ቀጣናውንም አብረው ሊያጠፉ ወደሚችሉበት አዝማሚያ ማንደርደርም ሊሆን ይችላል፡፡ በገልፍ አገሮች ትብብር ውስጥ የሚኖረው አብዛኛው የሺዓ ሙስሊም ሕዝብ ምንም እንኳ ቁጥሩ አነስተኛም ቢሆን፣ በአብዛኛው በነዳጅ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ስለዚህ ነገሮችን ሳታጤን እንዲሁ በነሲብ በሃይማኖት ከፋፍለህ ለመጓዝ የምታስብ ከሆነ ምንም አታተርፍም፡፡ አሜሪካ ለሳዑዲ የምትሰጠው ከለላም ከሁሉም ግጭቶች አያስጥላትም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አካባቢው ጉዳይ ስንመጣ ከአዲሱ ክስተት ቀድሞ ኳታር በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ ፍላጎት እንዳላትና በአንዳንድ አገሮች ውስጥም እንቅስቃሴ እንደ ጀመረች እንገነዘባለን፡፡ ከየመን ዘመቻ ጋር በተያያዘም ሳዑዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ፍላጎት አላቸው፡፡ በመሆኑም በአፍሪካ ቀንድና ከዚያም ባሻገር ባለው ቀጣና ውስጥ የኳታር ፍላጎት ላይ ወደፊት ምን ሊከሰት ይችላል?

አቶ አብዱል፡- እንደምታውቀው ኳታር ትንሽ አገር ስትሆን ሙሉ በሙሉ በገልፍ አገሮች የተከበበች ነች፡፡ ፈጠነም ዘገየም ሁሉ ቦታ መገኘት እንደማይችሉ መገንዘባቸው አይቀርም፡፡ የቱ ጋ እንደሚቀራቸው ይገነዘባሉ፡፡  እንደ ሊቢያ፣ ሶማሊያና ሌሎች አገሮች ውስጥ የነበራቸውን ተሳትፎ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ ሊያቆያቸው የሚችል በቂ ሀብት ስላላቸው የሚደርስባቸው ነገር አይኖርም፡፡ ፈጠነም ዘገየም አሜሪካኖች ለሳዑዲ ያላቸው ከልክ ያለፈ ፖሊሲም መቀየሩ አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ በሳዑዲዎቹ የማግለል ዕርምጃ ምክንያት በኳታር ያላቸው የጦር ሠፈር እንዲዘጋ በገልፍ ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ ታክሎበት ቱርኮች ደስተኞች አይደሉም፡፡ እርግጥ ቱርኮች ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል፡፡ የገልፍ ምክር ቤት የኳታርና የኢራን ግንኙነትም እንዲቋረጥ ጠይቋል፡፡ እርግጥ ነው ኳታሮች ይህንን ጥያቄ ተግባራዊ አያደርጉትም፡፡ ሌላው ትልቁ ጥያቄ ኳታር ለአሸባሪዎች የምትሰጠውን ድጋፍ ታቁም የሚለው ሲሆን፣ በሳዑዲዎች ትርጓሜ መሠረት የሙስሊም ወንድማማቾችን አለመደገፍ ማለት ነው፡፡ ኳታሮች ከአሜሪካ በሚመጣባቸው ተጨማሪ ግፊት የተነሳ ለሙስሊም ወንድማማቾች የሚሰጡትን ድጋፍ ለመቀነስ የሚገደዱ ይመስለኛል፡፡ አልጄዚራን እንድትዘጋ ለቀረበው ጥያቄ ኳታር የምዕራቡን ዓለም ድጋፍ የምታገኝ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከሚዲያ አኳያ የሕዝቡን ሐሳብ መጋፋት ስለማይቻሉ ነው፡፡ ይሁንና ውጥረቱ ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካ ቀንድ ስላላቸው ፍላጎትስ ምን ሊባል ይችላል?

አቶ አብዱል፡- ሳዑዲዎቹ በአፍሪካ ቀንድ እያደረጉ ያሉት ነገር ቢኖር ለአቋማቸው ድጋፍ ማሰባሰብ ነው፡፡ ይህ ማለት ፖሊሲያቸውን የሚደግፍላቸው ሲያገኙ በምላሹ ድጋፍ መስጠት ማለት ነው፡፡ እንደ ኤርትራ ያሉ አገሮች እስካሁን ከሳዑዲ ጎን ለመሠለፍ ተነስተዋል፡፡ ጂቡቲዎች እያቅማሙ ነው፡፡ ለየትኛው ጎራ አቋማቸውን እንደሚያሳዩ እስካሁንም ግልጽ አልሆነም፡፡ ከዚህ ባሻገር ሶማሊያ በሚደንቅ ግፊት ውስጥ ሆናም ቢሆን አሁንም እየተከላከለች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያንም አነጋግረዋታል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ አለመግባባቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደምትፈልግና የኩዌትን የአደራዳሪነት ሚና እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡ የኢትዮጵያ አቋም ትክክለኛ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ሳዑዲዎቹ በድጋሚ ለኢትዮጵያ ጥያቄ ማቅረባቸው እንደማይቀር ይሰማኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በየመን የሚካሂደው ጦርነት በቀጠለበት ወቅት የቀጣናው የሚሊታሪ እንቅስቃሴም እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደፊት ምን ዓይነት ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡ ምናልባትም በቀጣናው የምንገኘውን ሁላችንንም ሊያካትተን ይችላል፡፡ እንደምታውቀው አካባቢው የዓለምን 40 በመቶ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያስተናግደው ስትራቴጂካዊው የባብ ኤል መንደብ መተላለፊያ የሚገኝበት ሥፍራ ነው፡፡ በመሆኑም አካባቢው የምዕራብ ኃይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት፣ የቻይናና የሌሎችም አገሮች ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይሎች የሚገኙበት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሥፍራ ዓለም አቀፍ የማሪታይም መስመር ከመሆኑም ባሻገር፣ እንደ ቻይና ያሉ የእስያ አገሮችም ዋነኛ የኃይል ፍጆታቸው የሚተላለፍበት መስመር በመሆኑ ዓለምአቀፍ አካባቢው ይዘት ተላብሷል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያለ 100 ሚሊዮን ሕዝቦች የሚኖሩበት፣ የባህር በር ለማግኘት በሌሎች አገሮች በኩል ለማለፍ የሚገደድ፣ የተለየ ፈተና የሚገጥመው አገርም በዚሁ ቀጣና ውስጥ አለ፡፡ ይህ አገር በኢኮኖሚ እያደገ ነው፡፡ ይህ ዕድገት ሳይገታ ለመጓዝ እንዲቻል ንግድ ያስፈልጋል፡፡ ንግዱን ለማቀላጠፍ የሚረዳ መሠረተ ልማት ለመገንባት ትልቅ ኢንቨስትመንት ተካሂዷል፡፡ በዚያም ላይ በአፍሪካ ከትልልቆቹ አንዱ የሆነ የመርከብ ድርጅት ያለው አገር  ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በየዓመቱ መጠነ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እያስተናገደ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ኢንቨስትመንት በጂቡቲ በኩል በሚገኘው የባህር በር ላይ ጥገኛ በመሆን የሚካሂድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ጂቡቲ በተግባርም ሊታይ በሚችል ምክንያታዊነት፣ በአንድ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኙ አገሮች ሆነዋል፡፡ በፖለቲካ ሊተሳሰሩ ባይችሉም በኢኮኖሚ ረገድ ግን ከፍተኛ ትስስር ፈጥረዋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሒደት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ተሞክሮን በጥሩ ምሳሌነት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት የጥቅም ፍላጎት አኳያም ከሌሎች አገሮች የበለጠ የቀጣናውን ሰላም መሆን አጥብቃ ትሻለች፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያን ይህንን መረጋጋት እንዴት ልታረጋግጥ ትችላለች? ከተባለ እንደሚመስለኝ የኢትዮጵያ ስትራቴጂ አውጪዎች ሁሉንም ነገር በመመልከት አማራጫቸውን ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ የሆኑ የትብብር ስምምነቶችን መሠረት ያደረገና በባህር በር የመጠቀም መብቷን የሚያረጋግጥ አካሄድ ማለት ነው፡፡ ይህ ስምምነት በምንም ሁኔታ የማይነካ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከተቻለን እንዲህ ያለውን ተመሳሳይ ስምምነት ከሌሎች ጎረቤት አገሮችም ጋር ማድረግ ይገባናል፡፡ እስካሁን የታየው የሥጋት ስብስብ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ዝግጁ ሆና መጠበቅ አለባት፡፡ ኢትዮጵያ የማትቋቋመው ቀጣና ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም፣ ስትራቴጂካዊ ሥልት ሊኖራት ይገባል፡፡ ሌላው ሊታይ የሚችለው ጉዳይ አስፈላጊ ከሆነ ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን መልሳ መመሥረት እንዳለባት ማጤን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ባህር ኃይል የፈራረሰ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም እንዲህ ላለ እንቅስቃሴ እንዲቀመጥ የተደረገ ይመስለኛል፡፡ ይህ የፀጥታ ሥጋት እንደ ቻይና ያሉ ሌሎች አገሮችም የሚጋሩት በመሆኑ፣ ዕቃዎችንና አገልግለቶችን ያለ ፀጥታ ሥጋት በቀይ ባህር በኩል የማስተላለፍ ዋስትና የማግኘት ጥረቷ የዓለም አቀፍ ማዕቀፍ አካል እንዲሆን ግፊት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡  

ሪፖርተር፡- በሳዑዲና በኳታር መካከል የተከሰተው አለመግባባት የገልፍ አገሮች ምክር ቤትንም የሚያዳክም እንደ መሆኑ ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ?

አቶ አብዱል፡- አይደለም፡፡ በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ትክክለኛ ሊሆን የሚችለው አካሄድ በገልፍ አገሮች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ማበረታታት፣ እንዲሁም ሰላማዊ የማሪታይም ንግድ መተላለፊያ እንዲኖር መጣር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን መፍትሔ የማፈላለግ፣ ሁሉንም ያሳተፈና ግልጽነት የተላበሰ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲመጣ መደገፍ አለባት፡፡ ሰላም የሰፈነበት ቀይ ባህር እንዲኖር ማድረግና ያሉት ግጭቶችም ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው መተላለፊያ እንዳያሳጧት ማድረግ ይኖርባታል፡፡ እንደማስበው ኢትዮጵያ ይህንን ሐሳብ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በዓረብ ሊግ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል በማስተጋባት ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርባታል፡፡ የመሪነት ሚናዋን መጫወት ይኖርባታል፡፡ ይህንን የምለው በቀጣናው ከሚገኙ አገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን የግጭት አፈታት ሥልትን የመከተል ባህል ስላዳበረች ነው፡፡ ይህ አካሄድ የዲፕሎማሲ ባህላችን አካል ነው፡፡ በጋራ ደኅንነት እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ከመሠረቱ ሁለቱ የአፍሪካ አገሮች አንዷ ነች፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም መሥራች ነች፡፡ በኢጋድ ውስጥ ኢትዮጵያ ንቁ አባልና የመሪነት ሚና የምትጫወት በመሆኗ፣ ይህ ብቃቷ ከሌላውም ጊዜ የበለጠ እንዲዳብር ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...