Tuesday, February 27, 2024

የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት ከነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ቀናት አዲሱን ዓመት ለመቀበል ቅድመ በማድረግ፣ አሥሩን ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች በመስጠት አክብሯል፡፡ ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ የአዲስ ዓመት አቀባበልን በተመለከተ በነበረው ዝግጅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በ2009 ዓ.ም. የነበሩ ተግዳሮቶችንና በጎ ጎኖችን የጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ችግሮች ግንዛቤ በመውሰድና የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል የ2010 ዓ.ም. የአገሪቱ የከፍታ ዘመን እንዲሆን መንግሥት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የተመዘገበው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በአዲሱ ዓመት እንዲሳካ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ዝግጅት ቀደም ብሎ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ አገሪቱ ባለፈው ዓመት ስላስመዘገበችው ድልና ስለገጠሟት ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. ሊከናወኑ ስለታሰቡ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ ስላለው ወቅታዊ ግጭት፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በተለይም በጠገዴና በፀገዴ መካከል ስለነበረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አፈታትና ሌሎች ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው መግቢያ ላይ እንደተናገሩት፣ ለአሥር ቀናት ተዘጋጅቶ የነበረው ፕሮግራም በ2010 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚሆኑ አጀንዳዎችን ለማስተዋወቅ ያለመ ነው፡፡ በእነዚህ አሥር ቀናት የተከበሩ ፕሮግራሞች በኅብረተሰቡ መካከል መከባበርና መፈቃቀር ተፈጥሮ አገሪቱ የከፍታ ዘመኗን እንድታረጋግጥ የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. አገሪቱ ትልልቅ ድሎችን እንዳስመዘገበች የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ ሲባል ግን ያለምንም ችግር ዓመቱ ታልፏል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ተከስተው የነበሩ ችግሮችን የዘረዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት፣ ድርቅና የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች ጉዳይ ግንባር ቀደም እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ዓመቱ አገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየት መቀጣሏንም አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ማደግ ይገባት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዕድገት ሊመጣ የቻለው ደግሞ በኢንቨስትመንት የተከናወነ ሥራ ጠንካራ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው በተለያዩ ዘርፎች እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህ ቀጣይ እንዲሆን ግን ቀጣይነት ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡  

መንግሥት የጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞ በመቀጠል ከዚህ የተሻለ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዕድገት እንዲመጣ መሠራት እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጎርፍና ሌሎች አደጋዎች በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ነገሪ፣ የአዋሽ ወንዝና የቆቃ ግድብ ሞልተው ከፍተኛ ችግር እያደረሱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም ከፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከክልል የሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከ8.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ ችግር ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ችግሩ ከዚህ የባሰ እንዳይሆን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

ጋዜጠኞች በአገሪቱ ውስጥ በ2009 ዓ.ም. ውስጥ ስለነበሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችና የ2010 ዓ.ም. ዕቅዶችን በተመለከተ ለሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ከሪፖርተር በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ሰሞኑን ስለተፈጠረው ግጭት ወቅታዊ ሁኔታና ዋነኛ መነሻ ምክንያት፣ እንዲሁም ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም፣ ‹‹በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የነበረው ግጭት ከዚህ በፊት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተሳተፉበት በፊት ተደርጎ በነበረው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት የወሰን መካለሉ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ያ ስምምነት አልፈረሰም፡፡ በስምምነቱም መሠረት የሁለቱም ክልል አመራሮች ሥራውን እያከናወኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ሥራ እየተከናወነ ያለው ከሚመለከተው የፌዴራል ተቋም ጋር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን ይህም ሆኖ በቅርቡ ሕይወት የጠፋበት ግጭት እንደተፈጠረ መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼኛው ግጭት ከዚህ የወሰን አከላለል ጋር ምንም የሚገናኝ አይደለም፡፡ በደረሰን መረጃ መሠረት የሁለቱም ክልሎች አመራሮች በነበራቸው ስምምነት ተገዥ ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ ባሉበት ወቅት ማን እንዳሰማራቸው የማይታወቁ ኃይሎች አልፎ አልፎ ትንኮሳዎች እንደፈጸሙ፣ ሕዝቡ ደግሞ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ እስከ ትናንት [ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም.] ድረስም የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በተገኙበት ይህንን ችግር በመፈተሽ እንዲፈታና እንዲቆም ተደርጓል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመሬት ምክንያት፣ ያውም በአንድ አገር ዜጎች መካከል ደም መፋሰስና ሕይወት እስኪያልፍ ድረስ የሚደርስ ግጭት መኖር አልነበረበትም፡፡ ይህ ለማንኛውም አካል ለመንግሥት አመራርም ሆነ ለዜጎቻችን ትልቅ ሐዘን ነው፡፡ ይህ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ባለው የድንበር ግጭት ምክንያት የደም መፍሰስ መከሰቱ ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝብ ውርደት ነው፡፡ ውድ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ ግጭቶች በሁለቱ ክልሎች መካከል አሉ፡፡ በምሥራቅ ኦሮሚያ በሐረር፣ በባሌና በቦረና በኩል የተደረገው ለመናገርም በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ በየቀኑ እንከታተላለን፡፡ መረጃውን በትክክል መግለጽ እንችላለን፡፡ በሚመለከተው አካል ወደፊት እንገልጻለን፡፡ መረጃው እኛ ጽሕፈት ቤትም አለ፡፡ በሁለቱም ወገን እየሞተ ያለው ሕዝብ በጣም ያሳዝናል፡፡ መሆን አልነበረበትም፡፡ ለዚህ መንስዔው ምንድነው የሚለው ጥያቄ እንደ አመራር የእኛም ጥያቄ ስለሆነ ይህን ችግር እያደረሰ ያለው የሶማሌ ልዩ ኃይል ነው ወይ? በማለት ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ምላሻቸው ግን በእነሱ ዕውቅናና ምሪት የተደረገ እንዳልሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ሕዝቡ የሚለው ግን ይህን ችግር የሚያደርሰው የታጠቀ ኃይል እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ግን ይህንን የሚመራው አካል በትክክል ተይዞ ዕርምጃ መወሰድ ስላለበት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤›› በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአተት በሽታ በአማራ፣ በትግራይና በሶማሊያ ክልሎች እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰና የሰው ሕይወት እየቀጠፈ ቢሆንም መንግሥት ብዙም ትኩረት ሲሰጠው አይታይምና በዚህ ላይ የመንግሥት ምላሽ ምንድነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ በምላሻቸው፣ ‹‹ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው የጤና ቢሮዎች በጋራ እየሠሩ በመሆኑ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አነስተኛ ናቸው ሲባል ይሰማልና ይህ ሁኔታ በሚቀጥለው ዓመት እንዳይደገም፣ ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት መንግሥት ቀድሞ ለመተንበይና ለመከላከል ምን አስቧል? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩም ለችግሮች መፍትሔ ሲሰጥ የቆየው በችግሮቹ ግዝፈት መጠን መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው ዓመት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህንን አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር ወይ? ለተባለው የተለያዩ መላምቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመንግሥት በኩል ለአገር ዕድገትና የዜጎችን ጥቅም ለማስከበር ሲባል በየጊዜው ከሕዝቡ ጋር በመወያየት በተቻለ መጠን እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ፣ ልዩነቶችና ጥያቄዎች ሲኖሩም በሰላማዊ መንገድ ማንም ሰው ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡ ይህም ተደርጎ ግን አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ዓላማው ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ደግሞ ዓላማውን አሳክቶ በጊዜው እንደተነሳ እናስታውሳለን፤›› ብለዋል፡፡ ለመጪው ተመሳሳይ ችግር ይከሰታል ተብሎ እንደማይጠበቅ ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት ራሱን ማዘጋጀት እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴም በጥልቀትና ትርጉም ባለው መንገድ፣ እያንዳንዱ የመንግሥት መዋቅር ሕዝቡን የሚያረካ ሥራ እንዲያከናውን አስፈላጊ ዝግጅት በማድረግ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የሚነሱ ጥያቄዎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብና ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያነሳና እንዲስተናገድ፣ አስፈላጊው ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡  

‹‹ስለዚህ 2010 ዓ.ም. የምንቀበለው ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል ብለን ሳይሆን፣ የታቀዱት እያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወንን ዕቅዳችንን የምናሳካበትና የተያዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚያብቡበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ መንግሥትን ብቻ መጠበቅ ሳይሆን አጠቃላይ ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ብቻ አገርን እንደሚመራ ተናግረዋል፡፡ የአገር ባለቤት የሆኑ ዜጎች ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት የሆኑ አመለካከቶችን ለይተው መታገል እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉን በተመለከተም ዕርምጃው አዲስ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ነገር ግን አሁን ባለበት ደረጃ በተለየ ሁኔታ መንግሥት በቁርጠኝነት አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ደግሞ በቀጣይ ሰዎችን በማሰር ብቻ ሳይሆን ይህንን የሙስና ተግባር ለመዋጋት ቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ አስፈላጊው ሙስናን የሚገታ መዋቅር በመዘርጋት በተለይም የሙስና ወንጀል በሚበዛባቸው ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በተገኘው መረጃ መሠረትም እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ ሕዝቡ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደሚፈለገው ከፍታ የሚወስዱ ጉዳዮች ተለይተው መሠራት እንደሚባቸውም አክለው ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ በመከላከል ረገድ ሰፊ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው፣ እነዚህ ችግሮች በየትኛውም ዓለም የሚከሰቱና የተለመዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ባለፈው ዓመት የተከሰቱ ችግሮችን ለምሳሌ ቆሼን በተመለከተ ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ ያውቀው እንደነበረና በዚህ ጊዜ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ግን እንዳልተገመተ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቀድመን በመተንበይ መቆጣጠር ያለብንን በተመለከተ በተለይ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር እንደ ኢትዮጵያ ቀድሞ የሚዘጋጅ አገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ሁሉንም ቀድሞ በመተንበይ ከአደጋ መከላከል ይቻላል ተብሎ እንደማይታሰብም አክለው ገልጸዋል፡፡

ሌላው ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው ጥያቄ በ2009 ዓ.ም. አገሪቱን ብዙ ተግዳሮቶች ቢገጥሟትም 10.5 በመቶ ማደጓን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ደረጃ የመንግሥትዎ ሪፖርት ምንድነው? በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥስ እንዴት ዕድገት ሊመዘገብ ቻለ? የሚል ነው፡፡ በምላሻቸው፣ ‹‹የ2009 ዓ.ም. የኢኮኖሚ ዕድገት በታሰበው ደረጃም ባይሆን ከፍተኛ ውጤት ነው ማለት እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያን የአገር አመራር ሁኔታውን በምናይበት ጊዜ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡ ፖሊሲያችን ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ በሚያስችል ሁኔታ የተቀረፀ ነው፡፡ አንዱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ፖሊሲው ራሱ ነው፡፡ በአንድ ሌሊት ግርግር አቅጣጫውን የሚቀይር ፖሊሲ አይደለም፡፡ መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ የኢንቨስትመንት ሁኔታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሌላው መመስገን ያለበት የሕዝባችን የልማት ፍላጎት ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ዙሪያ የተደረገው ርብርብም ቀላል አይደለም፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገቱም የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ዛሬ ምርታማነት ጨምሯል፡፡ ሌሎች የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካቾችን ስንመለከትም ችግሮች ቢኖሩም ዕድገታችን መሠረታዊ ስለሆነ ያንን ሊያናጋ አልቻለም፡፡ ይህ ቀጣይነትና ትክክለኛ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ መንግሥት በቅርበት እየሠራ ነው የሚገኘው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም በ2010 ዓ.ም. ምንም ዓይነት ተግዳሮት ቢኖርም፣ የታቀዱ ጉዳዮች እንደሚሳኩና ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በቅርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተያዘላቸውን በጀት በትክክል እንዲጠቀሙና አላስፈላጊ ወጪዎችን እንዲቀንሱ መመርያ አውጥቶ ሳለ፣ ትልቅ በጀት ይዞ የአዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማን በሚሊኒየም አዳራሽ ለማክበር ማቀድ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር አይጋጭም ወይ? የሚል ጥያቄም ተጠይቀዋል፡፡ በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹አዲስ ዓመቱን ለመቀበል በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ያለ ወጪ አይከናወንም፤›› ብለዋል፡፡

ክብረ በዓሉን ለማከናወን በዋናነት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚመራና ሌሎች የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት አገራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ይህ ኮሚቴም ወጪ እንደሚያስፈልገው ስለሚታወቅ ወጭውን በተመለከተ ፈንድ አፈላላጊ ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በዚያው መሠረት ፈንድ ለማፈላለግ የተደረገው ጥረት በጣም ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተያዘው ዕቅድ እስከ አራት ሚሊዮን እንደሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ገንዘብ ከመንግሥት ተቋማት ወጥቶ የሚሠራ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደተባለው ወጪው 20 ሚሊዮን ይሆናል የተባለው ሐሰት መሆኑንና ትክክለኛ መረጃ የሚፈልግ አካል ካለም ከጽሕፈት ቤታቸው ማግኘት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡  

የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ውስን እንደሆነና በዚህ ላይ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ ተጠይቀው፣ የእንቦጭ አረም የአንድ ክልል ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ያለኝ መረጃ የሚያሳየው የክልሉና የፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት በመነጋገር እየሠሩ እንደሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ በ2009 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪ እጥረት የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአዲሱ ዓመት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ነው? የሚል ጥያቄም የቀረበላቸው ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ሲመልሱም፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ችግር የለም ያልንበት ጊዜ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የውጭ አቅማችንን ስናሳድግና ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዕቃዎችን የሚተኩ አገር ውስጥ ማምረት እስክንችል ድረስ ግዴታ ከውጭ የሚመጡት ላይ ኢንቨስት ማድረጋችን አይቀርም፡፡ ይህ የሽግግር ጊዜ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እጥረቱ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ በመንግሥት በኩል በተለይ በወጪ ንግድ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል በነበረው የወሰን ችግር በተለይም በጠገዴና በፀገዴ ወረዳዎች መካከል በቅርቡ ስለተደረገው ስምምነት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ‹‹ከዚህ በፊትም ቢሆን የማይፈታ ችግር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጊዜ በመውሰድና በጥልቀት በመመርመር እንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳይቀጥሉ ለማድረግ፣ አሁን በሁለቱም ክልሎች አመራር በኩል የተደረሰው ስምምነት ይህን ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ይሆናል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ በፌዴራል መንግሥት በኩል ክትትል ሲደረግና ድጋፍ ሲደረግ ነበር፡፡ ይህንን ችግር እንዲፈቱ ሲደረግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክልሎች ከፌዴራል የተነጠሉ ናቸው ብለን መገመት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፌዴራሉን መንግሥት የመሠረቱት ክልሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን በቅርበት ስንከታተል ነበረ፡፡ አሁንም የተደረሰው ስምምነት በዘላቂነት ችግሩን እንዲፈታ፣ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፤›› በማለት  ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ያንን አካባቢ የችግር ቀጣና ለማድረግ ይሠሩ የነበሩ አካላት እንዳሉ ጠቁመው፣ ‹‹ከአሁን በኋላ አጀንዳው ተዘግቷል፤›› ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -