Friday, February 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የዜጎቿ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን ጭምር ናት!

የአፍሪካ ኅብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ እየተካሄደ ሳለ፣ ኢትዮጵያ ከዜጎቿ በተጨማሪ የአፍሪካውያን አገር ለምን እንደሆነች ታሪክ እያጣቀሱ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ አኅጉራዊው ድርጅት የአፍሪካ ኅብረት 55 አባል አገሮች የሚሳተፉበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደማጭነቱ እየጨመረ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አፍሪካውያንን አሰባስቦ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ባደረገው ጉዞ ኢትዮጵያ ሁሌም ግንባር ቀደም ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1963 የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረትም ሆነ እ.ኤ.አ. በ2002 ወደ የአፍሪካ ኅብረት ሽግግር ሲደረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ባለፉት 54 ዓመታት ኢትዮጵያ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን የአፍሪካ ማዕከል በማድረግ ለአፍሪካውያን ቤታቸው ሆና አገልግላለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት በተለያዩ ጊዜያት አስቸጋሪ ጉዳዮች ሲገጥማቸው ግንባር ቀደም ሆና ለመፍትሔ የተጋች አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህም ሳቢያ የአፍሪካውያን አለኝታ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ዜጎቿ አገር መሆኗ ግልጽ ቢሆንም፣ አንድ ቢሊዮን ለሚጠጉ አፍሪካውያንም ሁለተኛ ቤታቸው ናት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን እርስ በርሳችን ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ሳይቀር ይህን ያህል የጠበቀ ዝምድና አለን፡፡ ቅን ልቦና ካለን ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡፡

ለአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ መሠረት የተጣለው ደግሞ ጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት ወደር የሌለው መስዕዋትነት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይሎች አፍሪካንና ሌሎች አኅጉራትን እንደ ቅርጫ በተከፋፈሉበት ወቅት ኢትዮጵያም የእነዚህ ኃይሎች የትኩረት መስህብ ነበረች፡፡ በተለይ ጣሊያን በታሪካዊው የውጫሌ ውል ላይ በፈጸመው ሸፍጥ ምክንያት ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ታላቅ ትንግርታዊና ዘመን የማይሽረው የዓውደ ግንባር ውጊያ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያና ተምሳሌት የሆነ አንፀባራቂ ድል የተገኘው በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ነበር፡፡ አንድ የአውሮፓ ታላቅ ቅኝ ገዥ ኃይል በግማሽ ቀን ጦርነት በዓደዋ ተራሮች ላይ ፍርክስክሱ ሲወጣ አውሮፓውያኑ አንገታቸውን ሲደፉ፣ በመላው ዓለም በቅኝ ገዥዎች ቀንበር ሥር የነበሩ ጥቁሮች ደግሞ አንገታቸውን ቀና አደረጉ፡፡ የጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ወደር የሌለው ድል በዓለም ሲናኝ ኢትዮጵያ እንደ አንፀባራቂ ኮከብ የብዙዎችን ቀልብ ሳበች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ለፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ተምሳሌት ሆነች፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ልብ ውስጥ ተጻፈች፡፡ ሌላው ቀርቶ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ ለመውጣት የኢትዮጵያን ፈለግ ተከተሉ፡፡ በታሪኮቻቸው ውስጥም የኢትዮጵያ መነሳሳት መፍጠር ተከትቧል፡፡

በታላቁ የዓደዋ ድል ማግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፓን አፍሪካኒዝም የሚባል የምሁራን ንቅናቄ ተጀመረ፡፡ የእዚህ ንቅናቄ ዓላማ ደግሞ አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸውን በተለያዩ አገሮች የተበተኑ ወገኖች ግንኙነት በማጠናከር የትግል አንድነት መፍጠር ነበር፡፡ በወቅቱ ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ በስተቀር ሁሉም አፍሪካውያን በቅኝ ግዛትነት ይማቅቁ ነበር፡፡ ከአፍሪካ ምድር በባርነት ተግዘው የአሜሪካ የጥጥ እርሻዎች ውስጥ ጉልበታቸው በነፃ ይበዘበዙ ነበር፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሥራቾች በአሜሪካና በካሪቢያን የሚገኙ የአፍሪካ ዳያስፖራዎችን ለጋራ ዓላማ በማነሳሳት አፍሪካውያን በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ለአንድነት እንዲነሳሱ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የአፍሪካውያን ዕጣ ፈንታም የተያያዘ መሆኑን ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ይህ ሁሉ መነሳሳት የተፈጠረውና የታሰበው ዓላማ ዕውን የሆነው ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይል ላይ በተጎናፀፉት ወደር የሌለው ድል ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ድል ደግሞ የመላ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው በዚህ ታላቅ ክብር ነው፡፡ ይህ ክብር ዘለቄታ ኖሮት እንዲቀጥል ግን እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እየተከባበርንና እየተዋደድን፣ አፍሪካውያን ወገኖቻችንን በሙሉ ልብ መቀበልና ማስተናገድ አለብን፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝና ከአፓርታይድ እንዲላቀቁ ኢትዮጵያ ያበረከተቻቸው አኩሪ አስተዋጽኦዎች መቼም አይዘነጉም፡፡ ያስከብሯታልም፡፡ ታሪካችንን እያከበርን አፍሪካውያንን በፍቅር ስንቀበል እንከበራለን፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን እጅግ በጣም የተከበረ ሕዝብ ያላት ታሪካዊት አገር ናት፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ልማድ፣ የፖለቲካ አመለካከትና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ በመኖርም ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ልዩነቶቻቸውን አክብረው በአንድነትና በፍቅር ከመኖራቸውም በላይ፣ ዓለምን ያስደመመ ፀረ ኮሎኒያሊስት ጦርነት ማሸነፍ የቻሉት ሥነ ልቦናቸው በጣም ተቀራራቢ ወይም አንድ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ እጅግ አኩሪ የሆነ የጋራ መገለጫ እሴት 55 አገሮች ለተሰባሰቡበት የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለመሆን ከመቻሉም በላይ፣ የአፍሪካ ኅብረት በዕቅዱ ለያዘው የአፍሪካውያን ውህደት ትልቅ ግብዓትም ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ሕዝብ ሊከበር ይገባል፡፡ ለዘመናት ያከናወናቸው አንፀባራቂ ሥራዎቹም መከበር አለባቸው፡፡ ይህ ታላቅ ሕዝብ አሁንም በዓለም ስሙን የሚያስጠሩት ግዙፍ ተግባራትን የማከናወን ዕምቅ አቅም አለው፡፡ ከአፍሪካውያን ወገኖቹ ጋር ለጋራ ጥቅም በሙሉ አቅሙ መሳተፍ ከቻለ ደግሞ ሌሎች አንፀባራቂ ድሎች ማስመዝገብ ይችላል፡፡ በታላቅ ሥነ ምግባርና ትህትና እንግዳ የመቀበል አኩሪ ዝና ያለው ይህ ታሪካዊ ሕዝብ በእናት አገሩ ፍቅር የተቃጠለ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መስዕዋትነት ከመክፈል ወደ ኋላ አይልም፡፡ አሁንም አገሩን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃትና ጥፋት ለመከላከል ዝግጁ ነው፡፡ ደሙ ውስጥ የሚዘዋወረው የአገር ፍቅር ብቻ ሳይሆን፣ የእርስ በርሱ መዋደድና መከባበር ጭምር ነው፡፡ ዕድሉን ካገኘ ደግሞ ይህ ፍቅር ለአፍሪካውያን ወንድሞቹም ይተርፋል፡፡

አሁን ግን እያስቸገረ ያለው ከሕዝብ ፍላጎት ያፈነገጠ ጽንፈኝነትና ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ከዚህ ታሪካዊና ጀግና ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ጽንፍ የረገጡና ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ዓይነት የከረሩ አቋሞቻቸው በተለያዩ ፈርጆች ይደመጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ሰፊ መሬት፣ የውኃ ሀብት፣ የተለያዩ ማዕድናት፣ በጣም ማራኪ የአየር ንብረት፣ የእንስሳት ሀብትና የመሳሰሉትን የታደለች አገር ናት፡፡ በተፈጥሯዊም ሆነ በታሪካዊ የቱሪዝም መስህቦች አቻ የሌላት ናት፡፡ ከሁሉም በላይ በወጣቶች ብዛት ትልቅ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ ሁሉም ክፍሎች በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራት ከተቻለ ይህችን አገር የአፍሪካ ገነት ማድረግ ይቻላል፡፡ በተለይ የሕዝባችንን አኩሪ የጋራ እሴት በመጠቀም ከጠባብነትና ከትምክህተኝነት ጽንፍ ውስጥ መውጣት ከተቻለ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአጭር ጊዜ መገንባት አያቅትም፡፡ እየታየ ያለው ግን አገርን አፍርሶ ሕዝብን ለፈተና የሚዳርግ ከንቱ ድርቅና ነው፡፡ ከመነጋገር ይልቅ መራራቅ፣ ለመደራደር ከመሞከር ይልቅ በጥላቻ ተፈራርጆ ተያይዞ ለመጥፋት መዘጋጀት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመቀራረብ ይልቅ ኋላቀር አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቆ በቃላት ጦርነት መነዳደፍ የበላይነቱን ይዟል፡፡ ከሥልጣን በላይ የሆነው ይህ ታላቅ ሕዝብ ተረስቶ የግልና የቡድን ጥቅም በርትቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጎዳና አገር ከማጥፋት በስተቀር ለማንም አይጠቅምም፡፡ በአጭሩ መቆም አለበት፡፡

ትናንት በኢትዮጵያውያን ታላቁ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል የዘመሩ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እስኪታዘቡን ድረስ፣ እርስ በርሳችን እየተናከስን ለታሪካዊ ጠላቶች ሚስጥር ስንሸጥ እንውላለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተምሳሌታዊነት በተከበረበት የዓለም አደባባይ ላይ እርስ በርስ እንወጋገዛለን፡፡ ከዚያም አልፈን ተርፈን አፍሪካውያን ወገኖቻችንን እያንጓጠጥን እኛ አፍሪካዊ ያልሆንን ይመስል እንመፃደቃለን፡፡ በዚህ ዘመን ያለውን ትውልድ ድርጊት እነዚያ ኩሩዎቹና ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ለአፍታ ዕድል አግኝተው ቢሰሙ በእጅጉ ይፀፀታሉ፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ድሮም ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ልዩነቶችን አቻችሎ አንድነት ላይ ማተኮር ትልቁ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ታላቅ እሴት እየተናደ ካሬ ሜትርና ሔክታር እያልን እንጨቃጨቃለን፡፡ የገዛ ወገኖቻችንን እያሰቃየን አስከፊ ድርጊቶችን እንፈጽማለን፡፡ አገራችን በጣም ሰፊ ሆና ከእኛ ተርፋ ለሌሎች እንደምትበቃ እያወቅን እርስ በርስ እንወጋገዛለን፡፡ በዘር፣ በሃይማኖትና በሌሎች ልዩነቶች ላይ እየዘመትን ወገኖቻችንን እናስከፋለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ግን መገለጫዋ ይኼ አይደለም፡፡ የኩሩዎቹ ኢትዮጵያውያን መገለጫ መተሳሰብ፣ መፋቀር፣ አብሮ መሥራትና ለውጤት መብቃት ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል መሆናቸውን መቀበል ነው፡፡ ማንም ከማንም እንደማይበልጥ ከልብ መቀበል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፍትሐዊ እኩልነት አብሮ በሰላም መኖር ነው፡፡ በዚህ ቀና አስተሳሰብ ስንመራ ኢትዮጵያዊነት የበለጠ ይጠነክራል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን ኢትዮጵያ የዜጎቿ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን ጭምር መሆኗን እናረጋግጣለን! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...

ቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

በንጉሥ ወዳጅነው  በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ትናንትም ቢሆን የተመረጡም ሆኑ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...