Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላይ የብቃት ጥያቄ አነሳ

ፓርላማው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላይ የብቃት ጥያቄ አነሳ

ቀን:

  • የፓርላማ አባላት ማንኛውም ባለሥልጣን የሕግ ተጠያቂነት አለበት ብለዋል
  • የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ‹‹የሚፀፅተኝ ነገር የለም›› አሉ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸምና ከሌሎች ተቋማት ጋር ባለው ጤናማ ያልሆነ ተቋማዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ የብቃት ጥያቄ አነሳ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኮርፖሬሽኑን የ2009 ዓ.ም. አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ረቡዕ ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ካደመጠ በኋላ ነው፣ በአመራሮቹ ላይ ጥያቄ ያነሳው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባነሳው ጥያቄ ኮርፖሬሽኑ የያዛቸው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆናቸውንና ከማጠናቀቂያ ጊዜያቸው በላይ ለዓመታት መጓተት፣ የኮንትራት አስተዳደር ችግሮች፣ የዕቅድ መጣረስ፣ የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓት ተግባራዊ አለመሆንና ሌሎች በርካታ ችግሮች መኖራቸው በአብዛኛው የአመራር ብቃት ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው ብሏል፡፡ ችግሮቹ እንዲቀረፉ ቋሚ ኮሚቴው በተደጋጋሚ ቢያነሳም፣ በተቋሙ በኩል ተጨባጭ መልስ እየተሰጠ አይደለም ብሏል፡፡ መንግሥት አጠቃላይ የአሠራር ሥርዓቱን ለማዘመን በመንግሥት ተቋማት የሚገብራቸውን ሳይንሳዊ የለውጥ መሣሪያዎች፣ ኮርፖሬሽኑ ሊተገብር ይቅርና ከአመለካከት ጀምሮ እንደማይቀበለው የጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ አሠራሮቹን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሮ እንደሆነ ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮርፖሬሽኑ የያዛቸው ፕሮጀክቶች ከመጓተታቸው ባለፈ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ከሆኑ የመንግሥት ተቋማት ጋር ተግባብቶ በቅንጅት እንደማይሠራ፣ በተደጋጋሚ እንዲያስተካክል ቢመከርም ለውጥ አለመምጣቱን ጠቁሟል፡፡

ለዚህ ማሳያም በኮርፖሬሽኑና የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች በሆኑ የመንግሥት ተቋማት የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም አስመልክቶ የሚወጡ ሪፖርቶች፣ የሚጣረሱ መሆናቸውን በማስረጃ አስረድቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከያዛቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ፋብሪካዎችና አንድ የማዳበሪያ ፋብሪካ ይገኝበታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት አፈጻጸም 91 በመቶ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት ግን 77 በመቶ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የጣና በለስ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት አፈጻጸም በኮርፖሬሽኑ ሪፖርት መሠረት 57.2 በመቶ መሆኑ ቢገለጽም፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት ሪፖርት ግን 25 በመቶ ብቻ መሆኑን እንደሚጠቁም ቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል፡፡ ኦሞ ኩራዝ አንድ ስኳር ፋብሪካን ኮርፖሬሽኑ እንዳጠናቀቀ ሲገልጽ፣ ባለቤቱ ግን 93.5 በመቶ ነው ይላል፡፡

በተመሳሳይ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት አፈጻጸም 46.5 በመቶ መድረሱን ኮርፖሬሽኑ ቢልም፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት ግን 42.3 በመቶ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው እንደገለጸ በመጥቀስ የችግሩ መንስዔ እንዲብራራለት ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

በያዩ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ከመጓተቱ በዘለለ፣ በፋብሪካው ግንባታ ላይ ችግሮች መከሰታቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአካል ተገኝተው መታዘባቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

በማስረጃነትም ሪቴይኒንግ ዎል (የድጋፍ ግንብ) ስድስት መቶ ሜትር ያህል መሰንጠቁን፣ የኩሊንግ ታወሩ እየሰመጠ መሆኑን፣ ግንባታው የተመረጠበት አካባቢ ረዥም የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን በማውሳት መንስዔውንና ዘላቂ መፍትሔውን ጠይቋል፡፡ በማከልም ‹‹ለማዳበሪያ ፋብሪካው ኮርፖሬሽኑ 60 በመቶ ክፍያ ተከፍሎት የፈጸመው 42.3 በመቶ ሆኖ ሳለ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቁ ተገቢ ነው ወይ?›› ሲል ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የስኳርና የማዳበሪያ ፋብሪካዎቹ በተገባው ውልም ሆነ ተሻሽለው በቀረቡ መረሐ ግብሮች መፈጸም አለመቻላቸውና ይህም በፕሮጀክቶቹ ባለቤት ተቋማት ላይ፣ እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ለደረሰው መባከን ተጠያቂው ማን እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው የኮርፖሬሽኑን አመራሮች ጠይቋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮርፖሬሽኑ ላይ ለሚመጣ ተጠያቂነት እርሳቸው ብቻ ተጠያቂ መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹በግሌ የማምነው ለዚህ አገር ልማት እየወደቅንና እየተሰዋን እንደምንሠራ ነው፡፡ መጠየቅ ካለብኝ እኔ ልጠየቅ፡፡ ከእኔ ውጪ ማንም እንዲጠየቅ አልፈልግም፡፡ እኔ የሚፀፅተኝ ነገር የለም፡፡ መታወቅ የተፈለገው ይህ ከሆነ ለዚህ ዝግጁ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ደካማ የሥራ አፈጻጸም እንደነበር ያመኑት ዋና ዳይሬክተሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የራሱ የውስጥ ችግር፣ እንዲሁም በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ችግሩ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በ2009 ዓ.ም. በአመዛኙ በፀጥታ ሥራ ላይ ሲሳተፍ በመቆየቱ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የፕሮጀክት አፈጻጸሞችን አስመልክቶ የቀረቡ ሪፖርቶች መጣረስ ስለተባለው መሬት ላይ የሚታይ በመሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡ ኦሞ ኩራዝ አንድ ስኳር ፋብሪካ የሙከራ አገዳ መፍጨት ጀምሯል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የመንግሥትን የአሠራር ሥርዓት የመቀበል ችግር አለበት ተብሎ የቀረበው ጥያቄ በራሱ ስህተት ያለበት ነው በማለት መልስ አልሰጡበትም፡፡ በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ተሰንጥቋል የተባለውም ስህተት እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተፈረጠው ችግር የአፈር መንሸራተት ነው ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ይበሉ እንጂ በሥፍራው ጉብኝት ያደረጉ የፓርላማ አባላት ፕሮጀክቱ ለመሰንጠቁ የፎቶ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በሪቴይኒንግ ዎል ላይ መሰንጠቅ የሚታይ ቢሆንም፣ ከዋናው ፋብሪካ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ አክለውም ምንም ዓይነት ተጨማሪ ክፍያ አለመጠየቁን፣ የተጠየቀ ቢኖርም የዋጋ ልዩነት ክፍያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አስተያየት አሁንም ቢሆን ፕሮጀክቶች መጓተታቸውንና ከዚህ በላይ የሚታየውን ችግር ኮርፖሬሽኑ እንዲፈታ አዟል፡፡ ኮርፖሬሽኑም ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ እንደሚያጠናቅቅ ገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...