በዳዊት እንደሻው
የኢትዮጵያን የቢራ ገበያ በአሁን ወቅት በዋናነት ከሚመሩት ኩባንያዎች መካከል የሚገኙት፣ የሐይኒከን ቢራ አክሲዮን ማኅበርና በእንግሊዙ ኩባንያ ዲያጆ ሥር የሚገኘው ሜታ ቢራ አክስዮን ማኅበር ተካሰው ፍርድ ቤት ሄዱ፡፡
ሜታ አቦ ክሱን የመሠረተው ሐይኒከን ፀረ ንግድ ውድድር የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ጥቅሜን ነክቶታል በማለት ነው፡፡ ክሱን በፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር በሚገኘው ችሎት የመሠረተው ሜታ፣ ሐይኒከን የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ የሜታን የቢራ ጠርሙሶችና ሳጥኖችን በመያዝ፣ በተወዳደሪነቴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረብኝ ነው ሲል በክሱ አስረድቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሜታ አሻሽሎ ባቀረበው ክስ ሐይኒከን በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ክልል ሐዋሳ፣ ይርጋ ጨፌ፣ ክብረ መንግሥትና ሸኮ ከተሞች በተመሳሳይ የሜታን የቢራ ጠርሙሶችና ሳጥኖችን በመያዝ ማግኘት የነበረበትን ትርፍ እንዳሳጣው በክሱ ገልጿል፡፡
የሜታ ቢራ ጠርሙሶችና ሳጥኖችን የመደበቅና የማከማቸት ሥራ በሐይኒከን በኩል ከጥቅምት 2009 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2009 ዓ.ም. መከናወኑን ክሱ ያብራራል፡፡ በሐይኒከን ድርጊት ሜታ ስምንት ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበትና የንግድ ተወዳዳሪነቱን እንደጎዳው አቤቱታ አቅርቧል፡፡
በዚህም መሠረት ሜታ ችሎቱን የሐይኒከንን ድርጊት እንዲያስቆምለትና ለደረሰበትም ጉዳት ካሳ እንዲወሰንለት ጠይቋል፡፡ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን 20 የሰው ምስክሮችን ሜታ የዘረዘረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ካሁን ቀደም በተመሳሳይ የጠርሙስና የሳጥን መደበቅና ማከማቸት ተግባር ሐይኒከንን በደቡብ ክልል በመክሰስ አሸነፍኩ ያለበትን ውሳኔ ችሎቱ እንዲያስመጣለት ጠይቋል፡፡
በስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ በመንግሥት የተያዙ የቢራ ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ ባወጣው ጥሪ ተጋብዘው የገቡት ሐይኒከንና ዲያጆ፣ እስካሁን በነበራቸው ቆይታ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን ኢንቨስት እንዳደረጉ ይታወቃል፡፡
የቢራ ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ በመንግሥት በወጣው ጨረታ ተሳትፈው፣ አሁን በሥራቸው የሚገኙትን የቢራ ፋብሪካዎች ለመግዛት ችለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሐይኒከን የበደሌና የሐረር ቢራ ፋብሪካዎችን በወቅቱ በ163.4 ሚሊዮን ዶላር ገዝቷል፡፡
እንዲሁም በሌላ ተመሳሳይ ጨረታ ዲያጆ ሰበታ የሚገኘውን የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በወቅቱ ትልቅ በተባለ 225 ሚሊዮን ዶላር ተጫርቶ ገዝቷል፡፡
በወቅቱ በዚሁ ጨረታ ሐይኒከን ተሳትፎ የነበረ ቢሆንም፣ ያቀረበው 188 ሚሊዮን ዶላር አነስተኛ ዋጋ ሆኖ በመገኘቱ ጨረታውን ሳያሸንፍ ቀርቷል፡፡
በአሁን ወቅት ተፎካካሪነቱ እየጠነከረ በመጣው የኢትዮጵያ ቢራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሰባት ኩባንያዎች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት 12 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በዓመት የማምረት አቅም ገንብተዋል፡፡
ሐይኒከን አራት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በዓመት የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ በሥሩም ዋልያ ላገር፣ በደሌ ስፔሻል፣ በደሌ፣ ሐረር፣ በክለር፣ ሶፊ ማልት፣ ሐይኒከን እንዲሁም ዋልያ ራድለር የተባሉ ምርቶችን ያመርታል፡፡
በሌላ በኩል ሜታ በሥሩ ሜታ፣ ማልታ፣ አዝመራ እንዲሁም ጊነስ ቢራን ያመርታል፡፡
የፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር የሚገኘው ችሎት፣ ሐይኒከን መልሱን እንዲያቀርብ ለሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡