Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናባህር ዳርና ደብረ ታቦርን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች አመፅ አደራጅተዋል የተባሉ...

  ባህር ዳርና ደብረ ታቦርን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች አመፅ አደራጅተዋል የተባሉ ተከሰሱ

  ቀን:

  መንግሥትን በኃይል የመለወጥ የፖለቲካ ዓላማ በመያዝ ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሚገኙ የባህር ዳርና የደብረ ታቦር ከተሞችን ጨምሮ፣ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች አመፆችና ረብሻዎች እንዲፈጠሩ የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ተግባር ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 17 ሰዎች በሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

  የወንጀል ሕግ አንቀጽ 35፣ 38፣ 32(1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001  አንቀጽ (4) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ የተባለው አርበኞች ግንቦት ሰባት ክንፍ (ሴል) የሆነውን ‹‹የአማራ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ›› (አሕነን) በሟቋቋም፣ አባላትን ሲመለምሉና ሲያደራጁ ቆይተው ዓላማቸውን ለመፈጸምና ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

  በአማራ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ያመጡት የመንግሥት ባለሥልጣናት መሆናቸውን በመነጋገር፣ ሥልጣን ያለውን መንግሥት በማስወገድ ሌላ መንግሥት ማቋቋም እንዳለባቸው ወስነው ቡድኑን ማቋቋማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

  ‹‹መንግሥትን በኃይል በማስወገድ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ መታገል ነው፤›› በማለት ውይይት አድርገው በርካታ አባሎችን በመመልመል፣ በማሠልጠንና በማስታጠቅ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት ተከሳሾች ታደሰ መሸሻ፣ አዱኛው ካሳዬ፣ ዮናስ ጋሻው፣ ይስማው ወንድሙ፣ ጌታ አስረዳ፣ ክንዱዓለም አስፋው፣ አቻምየለህ ደሴ፣ ደባሱ ቦጋለ፣ ዓለማየሁ ደሴ፣ አበባው መኮንን፣ ቀለምወርቅ ዘለለ፣ ሙላት ጥላሁን፣ ታፈረ መኮንን፣ መልካለም ጌጡ፣ ደረጀ አብርሃም፣ ቄስ ደመቀ ዓለሜና ነብዩ ሉሌ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

  ተከሳሾቹ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብረ ታቦር ከተማ የሽብር ድርጅት ክንፍ አመራር የሆኑት ጌታ አስረዴ፣ ይስማው ወንድሙና አዱኛው ካሳ ተሰባስበው ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ጦርነት ለመጀመር መስማማታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

  በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶችን መዝጋት፣ ጥይት ለቡድኑ ታጣቂዎች ማሠራጨትና ማከፋፈል ተቀዳሚ ሥራቸው ቢሆንም በዋነኛነት የክልሉን መንግሥት ፖሊስ ልዩ ኃይል አዛዥ ላይ ዕርምጃ መውሰድ፣ በፖሊስ ጣቢያ፣ በመከላከያ ካምፕና በማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት ማድረስ ተቀዳሚ ዕቅዳቸው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያብራራል፡፡

  ተከሳሾቹ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ያስተላለፉባቸው መንገዶች ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር፣ ጣራ ገዳም፣ ጎንደር፣ ጋይንትና ጭስ ዓባይ መሆናቸውንና ሌሎች ቦታዎችንም እንደሚያካትት ክሱ ይዘረዝራል፡፡

  በስማ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያና ማረሚያ ቤቶች ላይ ታጣቂዎችን በማሰማራት ጥቃት እንዲፈጽሙ የግንቦት ሰባት ሴል የሆነው የአሕነን ቡድን እስከ 3,000 ጥይቶችንና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን አስታጥቆ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ በደቡብ ጎንደር ውስጥ ያሉ የሴሉ አባላትን በማደራጀትና በደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ በትጥቅ የታገዘ አመፅ በማቀድና በማነሳሳት፣ 40 ሰዎችን ማዘጋጀታቸውንና በደቡብ ጎንደር ዞን ከተሞች ውስጥ አመፅ ለሚያደርጉ 1,000 ጥይቶች መላካቸውን ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡

  በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሴሉ መሪና አደራጅ በመሆንና ተልዕኮ በመስጠት፣ ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. አመፁ እንዲካሄድ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ አመፁ በጎንደርና በወረታ በመጀመሩ በምድር ድንጋይ፣ በመካነ ኢየሱስና በንፋስ መውጫ ከተሞች ወጣቶች የአመፁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በባህር ዳር፣ በፍኖተ ሰላምና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ረብሻውና አመፁ በመነሳቱ የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዲከሰት ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንዳላቸው የተጠየቁት ተከሳሾቹ እንዳላቸው በመግልጻቸው፣ በጠበቃ ተወክለውና መቃወሚያቸውን ይዘው ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...