Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትታሪክ እንደምን አድርጎ ወጥውጦ እንደሠራን

ታሪክ እንደምን አድርጎ ወጥውጦ እንደሠራን

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የዛሬውም ጉዳዬ ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ ሲባል የማወራው ስለነገሥታቱ ቆጠራ ሳይሆን ስለሕዝቦች ተራክቧዊ ጉዞ ነው፡፡ በታሪክ ላይ ሲበዛ ማተኮሬ ምናልባትም መንሰፍሰፌ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ታሪክ ተጣርቶና ተጠንቶ ወደ ኅብረተሰባዊ ንቃትነት ከተሸጋገረ ብዙ ጉርብጥብጥን ያገርማል፡፡ ኦሮሞው፣ ጎጃሜው፣ ጎንደሬው፣ ትግሬው፣ መንዜው፣ ቤተ ጉራጌው፣ ሐዲያው፣ . . . ወዘተ ወደኋላ ዘወር ብሎ ምን ከምን አድርጎ ታሪክ እንደ ወጠወጣቸው ማየት ሲጀምር አመለካከቱ የብሔርተኝነትም ሆነ የማናህሎኝነትን ጥበት እየገፈተረ ይሰፋል፡፡ በዕውቀት ጉድለቱ፣ በንቀቱ፣ በመራራ ስሜቱ፣ በጎሰኛ አድሎአዊነቱ ማፈር ይጀምራል፡፡ ተዘማምዶና አብሮ መጓዝን ከታሪክ ይማራል፡፡

ብዙ ሰው ስለኢትዮጵያ ታሪክ ሲያወራ ከአክሱም ተነስቶ በአንድ አቅጣጫ ቁልቁል ከማየት አይወጣም፡፡ ከገዢዎች ዘመቻ ውጪ ያሉትን ሌሎች የታሪክ አክርማዎች መለየት አይችልም፡፡ በዝርዝር እንደምናየው የኢትዮጵያን ስም ይዞ ከሰሜን ወደ ደቡብ እየሰፋ ከመጣው አስገባሪነት የበለጠ ኢትዮጵያን ‹‹የሠራው›› የኢትዮጵያን ማኀበራዊ ጥንቅር በዋናነት የደረሰው የኦሮሞ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በ‹‹ኢትዮጵያ››ነት የሚታወቅ ቀዳሚ ጅምሯ ከአክሱማውያን የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ሥልጣኔ ብዙ ማኅበረሰቦችን ያሳተፈ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች አክሱም ሲዳከም በሰሜን እስከ የመንና መረዌ ድረስ የተንጠራራው መስፋፋት አቅጣጫ ተቀየረ፡፡ ማዕከላዊ መቀመጫውም ወደታች ተንሸራትቶ የገዢዎች ለውጥ ተደረገ እንጂ፣ የሮሃ ላሊበላ ሥልጣኔና መንግሥት የአክሱም ቅጣይ ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ በሰሜን በኩል ሰፍታ የነበረቸው ኢትዮጵያ ተመልሳ ጠባ እንደገና ደንበር ገተር እያለች ወደ ደቡብ መስፋፋፋት ትቀጥላለች፡፡ በዚህ ሒደታዊ ታሪክ ውስጥ የሦስት ዓይነት ተዋንያንን ተራክቦ እናገኛለን፡፡

አንደኛው ወደ ደቡብ የሚያመራው ሰሜናዊ ክርስቲያናዊ ኃይል ነው፡፡

ሁለተኛው በመሀል ደቡብ፣ በደቡብ ምሥራቅና በምዕራብ የነበሩና በየበኩላቸው የመስፋት፣ የመዋዋጥ፣ ንዑስ ትግል ያደርጉ የነበሩ መንግሥታትና ከእነዚህ ሁሉ ልቆና የኢትዮጵያን ስም ይዞ የነበረውን ገዢ አሸንፎ በእስልምና የበላይነት ሰፊ አገር ለተወሰኑ ዓመታት ለመግዛት የሞከረው ከአዳል ሐረር የተነሳው ጠቅላይነት ነው፡፡

ሦስተኛው ሁለቱም በውጊያ ደቀው የክርስቲያናዊው ገዢ አንዱ ቁራሽ ወደ ጎንደር ሲያፈገፍግ፣ ሌላው ሸዋ ላይ ሥር ለመያዝ ሲጥር፣ የሐረሩ ደግሞ እንዳይሆን ሆኖ የተሰባሰበ ኃይሉ ተበታትኖ በሐረር ዙሪያ ግንብ ሲያጥር፣ በአራቱም ማዕዘን እየተሠራጨ እስከ ሰሜን አናት ድረስ መያያዣ የሆነው ኦሮሞ ነው፡፡

በእነዚህ ሦስት ኃይሎች መስተጋብር ውስጥ የክርስቲያናዊ ገዢዎች ሚና እንደገና ያየለበት ሒደት መጣ፡፡ የምኒልክ መራራ ጠቅላይነት የዚህ ሒደት መደምደሚያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ይህንን የመሰለ ቢጋር አለው፡፡

የ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ንቅናቄ ያስከተለው ውጤት ቅርባችን ነው፡፡ ኦሮሞ በእንቅስቃሴው ያላናጋው ያላንጎዳጎደው የአካባቢ ነባር መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰብ አልነበረም፡፡ ዛሬ እየተጻፈ ያለ የአካባቢ መንግሥታትና የብሔረሰብ ታሪክና ባህል ሁሉ የ16ኛው ክፍለ ዘመኑ የኦሮሞ እንቅስቃሴ ያስከተለበትን ለውጥና ተፅዕኖ (መቦጨቅ፣ መበተን፣ መዋጥ ወይም መወራረስ) ከመተረክ ያላመለጠውም ለዚህ ነው፡፡ በየትኛውም የኋላ ማኅበረሰባዊ ዝምድምዶሽ ውስጥ በአራቱም ማዕዘን ኦሮሞ ተጎዝጉዟል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘውን ስም ይዞ ወደታች አገር እያሰፋ ሲመጣ የኖረው መንግሥት ታሪክም ቢሆን ከኦሮሟዊ መስተጋብር አልተላቀቀም፡፡

የአፄ ልብነ ድንግል ዘር ሸዋ ቢበቅልና ቢያንሰራራ ከኦሮሞ ጋር ተዛምዶ ነው (ጌታቸው ኃይሌ 1997፤ የአባ ባህርይ ድርሰቶች 104)፡፡ ወደ ጎንደር ሸሽቶም መንግሥት ቢያደራጅ ከኦሮሞ አላመለጠም፡፡ የኦሮሞ ሚና ከነገሥታቱ ጋር በመዋጋት ብቻ የጠበበ አልነበረም፡፡ አልገዛም ባይ ወይ ተቀናቃኝ መሳፍንት ያካሂዱ በነበረው ትንቅንቅ ውስጥ ሁሉ ኦሮሞ የአንዱ ወይ የሌላው መጠጊያ/አጋር ሆኖ ተሳትፏል፡፡ ሱስንዮስን ያሳደገ፣ ያዘጋጀና ለንግሥ ያበቃ ኦሮሞ ነው፡፡ በአፄ እያሱ (አድያም ሰገድ) ዘመን በሹመት ቅሬታ የነበረው ደጃች ወሌ በንጉሡ ላይ አልገዛ ብሎ ሊነሳ የቻለውና የአፄ ሱስኒዮስ የልጅ ልጅ ነኝ ባዩን ይስሃቅን ለማንገሥ የቻለው፣ አንጋሽና ነጋሽ ከአፄ እያሱ ኃይል ጋር ለተወሰነ ጊዜ መዋጋት የቻሉት በኦሮሞዎች ድጋፍ ነበር፡፡ ደጃች ወሌ ከንጉሡ ጋር ከታረቀ በኋላ እየተዘዋወረ በአማሮችና በኦሮሞዎች ጉልበት ሲዋጋ የቆየውንም ይስሃቅን ይዞና አስሮ ለአፄው ኃይል ያስረከቡት ኦሮሞዎች ነበሩ (ተክለ ፃድቅ 1961፤ 173-5)፡፡ ለአፄ በካፋ መጠጊያ የሆነው ኦሮሞ ነው፡፡ አፄ ባካፋ ሞቶ፣ ከቋረኛዋ (አገው) ምንትዋብ ያፈራው ያልጠና ልጁ ዳግማዊ እያሱ ተብሎ በነገሠነና መንግሥታዊ ሞግዚት የሆነችው እናቱ ቋረኛ ዘመዶቿን በዙሪያዋ አድርጋ ሥልጣን በተቆጣጠረች ጊዜም ጳጳስና ዕጨጌው ጭምር በተሳተፉበት የቋረኛ ነጋሢነት ባልተዋጠላቸው መኳንንቶች አመፅ ጎንደር በተከበበች ሰዓት፣ እናትና ልጁን ከከበባ አውጥቶ ለማሸነፍ ያበቃቸው የአሮሞዎች አጋዥነት ነበር (የተጠቀሰው፤ 256-9)፡፡ እቴጌ ምንትዋብና እያሱ ዳግማዊ ለጎንደር ቤተ መንግሥት እንግዳ ለነበረው የቋራ ንጉሠ ነገሥትነት የአማራና የትግሬ መኳንንት በቀላሉ አለማጎንበሳቸው በተለያየ መልክ ቅዋሜ (ኦሮሞን ጭምር) እያስነሱ መተናነቃቸው፣ ከጦርነት ባሻገር የኃይል ሚዛን ለመጠበቅ የሚረዳ አጋዥ ወደ መፈለግም ወሰዳቸው፡፡ ዳግማዊ እያሱ ከወሎ ኦሮሞ መኳንንት የምትወለደውን ውቢትን አገባ፡፡ በኋላም እቴጌ ምንትዋብ ምልምል እያሱ ከሚባል ወዳጇ ከወለደቻቸው ልጆች አንዷን (ዳግሚት ወለተ እስራኤል የምትባለዋን) ለኃይለኛው የጎጃም ኦሮሞ ደጃዝማች ዮሴዴቅ ዳረለት፡፡ (ከዮሴዴቅና ከእቴጌ ምንትዋብ ልጅ የጎጃሙ መስፍን ራስ ኃይሉ ዮሴዲቅ ይወለዳል) ከዳግማዊ እያሱና ከወሎዋ ውቢት እዮአስ ይወለዳል፡፡ (ስርግው ገላው 2002 ገጽ 77፤ አንድርዜይ . . . 2003፤ 208፡፡)

ከዚህ ማስተዋል እንደሚቻለው ኦሮሞ ጎንደር፣ ጎጃምና ወሎ ውስጥ ተርመስምሶ የጎንደር ሥልጣንን ተናንቆ በነገሥታቱ የደፋ ቀናና የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ተወዛውዞም አላበቃም፡፡ በዚያው ሒደት ውስጥ በየአካባቢው በነበረው መኳንንትነትና መሳፍንትነት ውስጥ ዘልቋል፡፡ በኦሮሞ ስምነት ተለይተው የሚታወቁ መጠሪያዎች ያሏቸው እየመረጡ እከሌ፣ እከሌ ማለት እውነቱን አያሳይም፡፡ አሮሞነትን የማይጠቁሙ ስሞች ለኦሮሞች እንደዋሉ ሁሉ የኦሮሞ ስሞችም ለሌላ ብሔረሰብ ሰዎች መጠሪያ ሆነዋል፡፡ በተክለ ፃድቅ መኩሪያ (1961)፣ ገጽ 136-8 እና 166-7 ላይ የተዘረዘሩትን ሹሞችና መኳንንት በስም ለመለየት መሞከር ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ ኦሮሞ የራሱን ኦሮሟዊ የመሳፍንትነት ዘርና ገዥነት ከወሎ – የጁ ወረሂመኑ ፈልቅቋል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያም ቀስ በቀስ የተከተሉ መደባዊ ሽግግሮሾች የገዳ አስተዳደራዊ ሥርዓትን እየሸረሸሩ በስተኋላ የሞቲ (ንጉሣዊ) አስተዳደሮችን የሚያበቅሉበት ሒደት ቀጥሏል፡፡

በጎንደር ነገሥታት የመጣጣል ትግል ውስጥ ኦሮሞች በደጅ ከመሳተፍ አልፈው ቤተ መንግሥት ገብተው የግቢ ፖለቲካና ሴራ አውጠንጣኝ የመሆን ምዕራፍ ውስጥ የሚገቡት በኢዮአስ ቀዳማዊ (1748-1762) ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ወደ ዘመነ መሳፍንት የሚወስደው የቁልቁለት ጉዞ የጀመረውም ገልብጦ የመንገሥ/የማንገሥ ደባዎች ከበዙበት፣ ነገሥታቱ ሴራዎችን እረጭ የሚያደርግ አቅም ያጡ ሆነው ከዛሬ ነገ እገለበጣለሁ ብሎ በመሥጋትና ቀዳዳ በመድፈን የሚትረከረኩበት የ‹‹ትንንሽ›› (አጫጭር ዘመን) ነጋሢነት ከመጣበት ጊዜ ከ18ኛው መቶ መጀመርያ አንስቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አባቱን አፄ እያሱ ቀዳማዊን አስገድሎ ከነገሠውና ‹‹እርጉም ተክለ ሃይማኖት›› በመባል ይታወቅ ከነበረው ንጉሥ አንስቶ በ25 ዓመታት ገደማ ጊዜ ውስጥ አምስት ነገሥታት ተፈራርቀዋል፡፡ (ተክለ ፃድቅ 1961፡ 211-2፤ ስርግው  2002፤  71፡፡)

ከአምስተኛው ከአፄ በካፋ በኋላ የመጣው የእያሱ ዳግማዊ ዘመነ መንግሥት በአጠቃላዩ የቁልቁለት ጎዳና ውስጥ ያጋጠመ ጉብታ ነበር፡፡ እሱ በውስጥ ቂም ሲሞት፣ (የአባቱ የበከፋ ዘመድና ለእናቱ የሚስጥር ወዳጅ የነበረውንና የገዛ እህቶቹ አባት የሆነውን ‹‹ምልምል›› እያሱን በማስገደሉ ያቄመች እህቱ በመርዝ ገድላዋለች ይባላል፡፡) ቀድሞ ኃይል ለማጠናከር ተብሎ በተፈጠረና ጠቅሞም በነበረ የጋብቻና የሹመት ትስስር ጎንደር ቤተ መንግሥት የተገናኙት የቋራና የወሎ የጁ መኳንንቶች የሥልጣን ሹኩቻቸው አገጠጠ፡፡ ለክፉም ለደጉም የእዮአስ እናት ውቢት አጎቷና ወንድሞቿ የኦሮሞ ጦር ይዘው እንዲመጡላት እስከማድረግ ደረሰች፡፡ ጎንደር ከተማ ጠመንጃ በዛባት፡፡ ኦሮሚኛ በጎንደር ቤተ መንግሥት ንጉሡ ጭምር የሚነጋገርበት ቋንቋ ሆኖ ደመቀ፡፡ ይሁን እንጂ ቋረኞቹና ኦሮሞች ለይቶሏቸው ጦር አልተማዘዙም፡፡ ሁለቱንም ወገኖች ማሽቀንጠር ለሚፈልጉት ወገኖችም ኃይል በተሰባሰበበት ሁኔታ ግልበጣ መሞከር ጭራሽ የሚተናነቁትን ማስማማት ይሆንባቸው ነበርና የተሻኳቾቹ ቅራኔ እስኪፈነዳ ይጠብቁ ነበር፡፡ ቋረኞቹ የእዮአስ የአባት እናት ወገኖችና የኦሮሞዋ እናቱ ወገኖች በጎንደር እንደራሴነት ቦታ ላይና በተዘወዋሪ መንገድ የገጠሙት ትንንቅ አስገራሚ ነበር፡፡ በሞት አጋጣሚ እንደራሴነትን ከቋረኞቹ መፈልቀቅ ኦሮሞዎች ባልቻሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ የተነሳ አካባቢያዊ አመፅን ለመቅጨት የተደረገ የዘመቻ ተልዕኮን ሳይቀር በሥውር መጠቃቂያነት ተጠቅመውበታል (ተክለ ፃድቅ፣ 1961፣ 273)፡፡

በቋረኛ አያትና በኦሮሞ እናት ወገኖች የሥልጣን ትግል የተወጠረው ንጉሥ እዮአስ የሚገላገል መስሎት ከትግሬ ራስ ሚካኤል ስሁልን ጠርቶ የጎንደር እንደራሴነትን ይሰጠዋል፡፡ ይህም ሁለት ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ 26 ሺሕ ጦር ይዞ የራስ ሚካኤል ጎንደር መግባትና አስተዳደሩን አሳምሮ ስም መገንባት መጀመር የቋረኞች መሳጫ ብቻ ሳይሆን፣ የንጉሡም ሥልጣን መንሸራተቻ ሒደት ነበር፡፡ ቋረኞች በፊናቸው ራስ ሚካኤልን ከንጉሡ አጋጭቶ ከማስፈንቀል ጥረት አልፈው እንደራሴነት የተነጠቀውን ራስ ማርያም ባሪያውንና ላስታን አሳብረው አሳመፁ፡፡ ራስ ሚካኤል የላስታውን አማፂ አባብሎና ከራስ ማርያም ነጥሎ ቢያስገባ ንጉሥ እዮአስ በበኩሉ ራስ ሚካኤልን የማስነከስ ትርፍ አገኛሁ ብሎ ይመስላል በሥውር አስገደለው፡፡ ራስ ማርያም ባሪያው ተሸንፎና በኦሮሞ ተይዞ ቢመጣ ከራስ ሚካኤል ፍላጎት ውጪ አሁንም ንጉሡ አስገደለው፡፡ ንጉሡ በዚህም አላበቃ እንደሚባለው የዳሞቱን ፋሲል አሳምፆ በጌምድርን እንዲወር፣ ራስ ሚካኤል አመፁን ለብቻው እንዲጋተር ከማድረግም በላይ በጎን ፋሲልን እንዲያግዙ የራሱን አሽከሮች ይልካል፡፡ በጦርነቱ ከመድከም ይልቅ ባለድል ሆኖ ራስ ሚካኤል ሲመጣ የንጉሥ አሽከሮች ጭምር ተማርከው ነበርና ጉዱ በጎንደር መኳንንት ፊት ይጋለጣል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ተከሳሽ እንደራሴው ራስ ሚካኤል ከሳሽና አስፈራጅ ይሆናል (275-7)፡፡ ራስ ሚካኤል ንጉሥ እዮአስን አስገድሎም የዘመነ መሳፍንት ሿሚ ሻሪነት አሟሺና ጀማሪ ይሆናል፡፡ ብልህነቱም እዚሁ ላይ ያልቃል፡፡

ከጉልበት ይልቅ እርቅ በማቅረብ ከየአካባቢ መሳፍንት ጋር ተግባብቶና አግባብቶ እነሱ የመከሩበትን ከማንገሥ ጋር ቀይ ባህርን የተቆጣጠሩትን ቱርኮች አባብሎ መሣሪያ የሚያስገባበትን ቀዳዳ እየፈለገ ኃይሉን ከማጠንከር ይልቅ፣ ለሥልጣን ፍላጎት የሌለውን ሽማግሌውን የበካፋን ወንድም ከወህኒ አምባ አምጥቶ አነገሠና እህቱን ዳረለት፡፡ ይሁን እንጂ ሃይማኖተኛው አዛውንት ለይስሙላ ንጉሥነት እንኳ ሊጠቅመው አልቻለም፡፡ ወደ ወህኒ አምባ መልሱኝ እያለ ሲያስችግር በመርዝ አስገደለና የሟቹን ልጅ የ15 ዓመት ወጣት ደግሞ ዳግማዊ ተክለ ሃይማኖት አሰኝቶ አነገሠ፡፡ ከዚህ ሒደት ጋር ቅዋሜና መሸፈት እየበረከተ ራስ ሚካኤልም መቆጣጠር እየተሳነውና የጭካኔ ቅጣቱ እየበረታ፣ ጭካኔው መልሶ አመፅን እያስፋፋ ይሄዳል፡፡ የጨነቀው ራስ ኃይል ለማሰባሰብ “ንጉሡን” ይዞ ወደ ትግሬ ሲሄድ አመፀኞቹ ደግሞ ጎንደርን ይዘው ሱሱንዮስ የሚባል ሰው አነገሡ፡፡ ራስ ሚካኤል 40 ሺሕ ሠራዊትና ‹‹ንጉሡን›› ይዞ ወደ ጎንደር ሲያቀና አንጋሾቹ የከዱት አቅመ ቢሱ ሱስኒዮስ ከጎንደር ሸሸ፡፡ ራስ ሚካኤል በበኩሉ ጎንደር ሲገባ ሱስኒዮስን ደግፈው የነበሩ ሁሉ በታማኝነት ቢሰግዱለትም ከድተው የነበሩትን ከመኳንንት እስከ ቀሳውስት በስቅላት ቀጣ፡፡ ጭካኔ እንደገና አመፅና ውጊያን አራብቶ ራስ ሚካኤልን ወደ መጨረሻ ውድቀቱ ይወስደዋል፡፡

ራስ ሚካኤል ከተወገደ ወዲያ በእነ ደጃች ወንድ በወሰን የሚደገፈው ራስ ጎሹ ሥልጣን አልባውን ዳግማዊ ተክለ ሃይማኖትን ዙፋኑ ላይ ይተውና የጎንደር ገዢነት ሥልጣኑን ይጠቀልላል፡፡ በአፄ እዮአስ ላይ ሞት የፈረዱትንም እያስለቀመ ያስገድላል፡፡ የዞረበት ንጉሥ (ተክለ ሃይማኖት) ሥልጣን በእጁ የሚያስገባ መስሎት የጎሹ አጋሮች ዘወር ያሉበትን አጋጣሚ ጠብቆ ራሱ ጎሹን በማሰር ሲዳፈር ኃይል ከእነማን ዘንድ እንደነበረች ይታያል፡፡ በእነ ደጃች ወንድ በወሰን ኃይል ከእስር የወጣው ታሳሪ አሳሪውን ንጉሥ አውርዶ ግዞት ይሰድና ሰለሞን የሚባል እጅግም በዙፋን ያልቆየ ሰው አነገሠ፡፡ የአንጋሹም ጉልበት ከሌላው ሁሉ ገኖ አለመውጣቱ፣ የዘውድ ፈላጊው ሩጫ፣ (ሌላው ቀርቶ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥ የደረሰውን ሥነ መለኮታዊ መከፋፈል ሁሉ ለዘውድ ፍለጋ መጠቀሚያ ያደረገ ቅስቀሳና ትንቢቱ)፣ ሽፍትነቱና ውጊያው ሲበዛ፣ ሰፋ ባለ የመሳፍንቶች ድጋፍ የአፄ ተክለ ሃይማኖት ዳግማዊ ወንድም ተክለ ጊዮርጊስ ነገሠ፡፡

በአጀማመሩ ተክለ ጊዮርጊስ ሥልጣን ያለው ንጉሥ መሳይ ነበር፡፡ የየጁውን አሊን ራስነት ማዕረግ ሰጥቶ በእንደራሴነት መሾሙ፣ ተቃውሞ ያስነሳበትን የማርና የገንዘብ ግብር ማወጁና ተቃውሞ እየገጠመው ማስገደዱ ‹‹ሥልጣኑ››ን የሚገልጽ ነበር፡፡ (አንድርዜይና . . . 2003፤ 223 – 8፡፡ ተክለ ፃድቅ፣ 1961፤ 280-9) ምናልባትም ትልቁ ራስ አሊን እንደራሴ ማድረጉ በየጁዎች ኃይል ሌላውን የመመከት ብልኃትን መሞከሩም ይሆን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ሥልጣን እንዳለውና እንደሌለው ለራሱም ለሌላውም ከማሳየት ያልተሻለ ጅል አድራጎቱ፣ ቀደም ብሎ በ1760ዎች መጀመርያ የተከፈተውን የዘመነ መሳፍንት ሒደት ለመቀየር የተደረገ የመጨረሻ ቅዠት – የመፈራገጥ ቅፅበት – ከመሆን የዘለለ እርባና አልነበረውም፡፡ የተክለ ፃዲቅ መኩሪያን የአጠራር ማረሚያ እንጠቀምና “ፍፃሜ ንግሥ” የጀመረው ከተክለ ጊዮርጊስ ሳይሆን ከዮሐንስ ዳግማዊ ነው፡፡ የበጌምድር ሰው ራስ አሊን መውደዱና ከግንብ ጠባቂ (ከወግ) ያለፈ ንጉሥ አለመፈለጉ ዘመነ መሳፍንት ይፋ ሆኖ የታወጀበት፣ ገዢነትና አንጋሺት ከአንዱ ወደ አንዱ መስፍን ይዋዥቅና ይወላገድ የነበረበት የመጀመርያው ምዕራፍ አልቆ አንድ ዘር ላይ ከሞላ ጎደል የረጋ ምዕራፍ የጀመረበት ክፍል ነው፡፡ ለዚህ ለሁለተኛ ምዕራፍ ታቦር የሰጠው “የየጁዎች ዘመን” የሚል ስም ተገቢ መጠሪያ ነው፡፡

በተረፈ ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› የሚለው አጠራር ቀደም ሲል እያሽቆለቆለ የመጣውን የንጉሠ ነገሥታዊ ኃይልና አሰባሳቢነት ውድቀት የሚገልጽ እንጂ እሸቱ እንደሚለው ‹‹ከፀረ ኦሮሞነት አስተሳሰብ›› የተፈጠረ (እሸቱ 2001፤ 126) አልነበረም፡፡ የሴሩ ጓንጉል ዘሮችን ሥልጣን በመቀናቀንና በመፈንቀል እንቅስቃሴዎች ውስጥ በኦሮሞነትም ሆነ በአዲስ ክርስቲያንነት ማናናቅ ቀደም ሲል ተያይዞ ሥር እየሰደደ ለመጣ ከዓይን ያልራቀ የሥልጣን ሩጫ መገለጫ/ማሳበቢያ (መልክ) እንጂ ይዘት አልነበረም፡፡ በሌላ አባባል የአመፅና የሴራው መነሻና መድረሻ ፀረ ኦሮሞነት አልነበረም፡፡ በነበረው ሁኔታ የጎንደር ገዥነቱን ሥልጣን የያዙት የትግሬ/የጎጃም ወይም የጎንደርና የሰሜን መሳፍንት አንደኛቸው ቢሆኑ ኖሮም በጊዜው የነበረው ሴራና አመፅ አይቀርላቸውም ነበር፡፡

‹‹ከኦሮሞ ወገን ኃይል ተነስቶ ሲነግሥ ‹ዘመነ መሳፍንት›› እንደተባለ አድርጎ ማቅረብና ‹‹ራስ አሊ . . . በጊዜያቸው የነበሩትን የአካባቢ ገዥዎች በበላይነት ሲያስገብሩ የነበሩ ቢሆንም፣ በታሪክ ጸሐፊዎች የንጉሥነት መጠሪያ ይገባቸው እንደሆነ ያሰቡበት ጊዜ አይታወቅም” ብሎ ማለት፣ ከዚህም ጋር ራስ አሊ ከእንግሊዝ ጋር በተደረገ የወዳጅነት ስምምነት ላይ ‹‹አሊ የሐበሻ ንጉሥ›› ብሎ መፈረሙን ማያያዝ፣ (እሸቱ፣126) ሀቅንና ምኞትን ማሳከር ይሆናል፡፡ የታወጀም ሆነ የተፈጸመ ንግሥና ከነበረ ለዚያ ማስረጃ ማቅረብ ነው፡፡ የታሪክ ጸሐፊ ኃላፊነት የነበረውን ይዞ መተንተን እንጂ፣ ማዕረግ መሸለም አይደለም፡፡ ከግንብ ጠባቂ ንጉሠ ነገሥት ይበልጥ በመንግሥት መሪነት ይታወቅ የነበረው፣ መንግሥቱንም ይመራ የነበረው ራስ እንደራሴው ነበር፡፡ ራስ አሊም እንደዚያ ነበር፡፡ ይህ በጊዜው የነበረ ሥልጣንም ንጉሠ ነገሥት አከል ሥልጣን ነበር፡፡ ራስ አሊም ንጉሠ ነገሥት አከል ነበር፡፡ “አሊ የሐበሻ ንጉሥ” ብሎ መፈረምም የዘመኑን ግንጥል ጌጥ ሥልጣን ይፋ ሹመት የጎደለውን “ንጉሥነት” የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ከውጭ ጋር በተደረገ ግንኙነት ላይ ራስ አሊ (ትንሹ) ይህንን ማዕረግ በፊርማ ማስቀመጡ ያዘለው ትርጉምም ከግለሰብ ዝና የላቀ (ክብደት ባለው መልክ አገርን የመወከል ግንዛቤ ያለበት) ይመስላል፡፡

ወጣም ወረደ የጁዎች ለኢትዮጵያ ገዢነት አዲስ ገብ መሆናቸው፣ የአፄ እዮአስ ዘመን ከቋረኞች ጋር የተስማማ ገዢነት ያልነበረበት መሆኑና ከራስ ሚካኤል ጋር የተፈጠረው ጉድኝት መበለሻሸት የአመፀኛ ፈተናቸውን ማባባሱ እንዳለ ሆኖ፣ በዚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከክፍፍል ወጥታ ገዢዎችን ማስማማት ባልቻለችበት፣ አባብዬም ሆነ ወግቼ አንዱን ልክ አገባሁ ሲባል ሌላው ያፈነግጥ በነበረበት በዚያ የመመሳጠርና የሽፍትና ዘመን ማዕከላዊ ገዥነቱን ይዘው የነበሩት የጁዎች ከአንዱ አማፂ ወደ ሌለው እየዘመቱ በተለመደው የእርቅ፣ የሹመትና የጋብቻ ዘዴም እየተጠበቡ አንሳ የተረከቧት ኢትዮጵያ ጠቅላላ ፍርስርሷ እንዳይወጣ በመታገልና በመጠበቅ ባለውለታ ሆነው አልፈዋል፡፡

ከእነሱም በኋላ ቢሆን የዘመኑ አስገባሪ ሥርዓት ይፈልገው የነበረው በኃይል ልቆ ለጥ ሰጥ የማድረግ አቅም በቶሎ አልተገኘም፡፡ የቋራውን ካሳና የትግሬውን ካሳ አማቋል፣ አንጨርጭሯል፡፡ እነሱም የእሳትና የጎራዴ ቅጣታቸውን አዝንበዋል፡፡ ምኒልክ ሰሜን ሕዝብ ላይ ሠልጥኖ የኖረውን አቀጣጥ (ከነምሕረት መሥፈሪያው) ወደ ደቡብ አስፋፍቶ የማስገበሩን ሥራ በሰፊ ይዞታ አጠናቋል፡፡ ጎራዴና ጠመንጃ በጨካኝ ግፍና በእየዬ ካነፀው አንድነት ይልቅ ኦሮሞ ማኅበራዊ መርፌ ሆኖ ሕዝቦችን እየወሰወሰ ያነፀው አንድነት ሥር የሰደደ ነበር፡፡ ችግር የነበረው የመልከኛ ፈላጭ ቆራጭነት ያመረተው ጭካኔ፣ ቂምና ጥላቻ እውነተኛውን የመዘናነቅ አንድነት ጋርዶ ሲመዘምዝ መቆየቱ ነበር፡፡

የመወራረሱ ጥልቀትና ስፋት በራሱ ‹‹የጠራሁ ዘር››፣ ‹‹የይሁዳ ዘር›› ባይነት ላይ ክፉኛ የሚሳለቅ ነው፡፡ ባልታወቀው ጸሐፊ በተጸፈው የቴዎድሮስ ታሪክ መሠረት  (አጤ ቴዎድሮስ በሦስት ቀደምት ጸሐፍት 2004፣ ገጽ 134) ኦሮሞዋን ተዋበችን ያገባው የቋራው ካሳ መኳንንትን ወደሱ ለማባበል “ጥንት ኢትዮጵያ የእስራኤል መንግሥት ናት፣ የዳዊት የሰለሞን ትውልድ ነው የሚገዛት፣ እንዴት . . . ” የሚል ቅስቀሳ ተጠቅሟል፡፡ አፄ ዮሐንስ 4ኛ በእናቱ በኩል የኦሮሞ/የአፋር ‹‹ደም›› ሳይኖረው አይቀርም ከመባሉ ሌላ፣ ልጁ ራስ አርዓያ ከአፋር እናት የተገኘ ነበር (ክብሮም አሰፋ የራያ ሕዝብ ባህል ቋንቋና ታሪክ፣ 2005፤ 97-8)፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ቤት ውስጥ በምኒልክም፣ በእቴጌ ጣይቱ በኩል (ከልጅ ጋብቻ የተገኘም) የኦሮሞ “ትውልድ” አለ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ዘንድ በአባትም በእናትም፣ በባለቤቱ በእቴጌ መነን በኩል ትውልድ ሲቆጠር ሩቅ ሳይኬድ ኦሮሞ ዘንድ ይደረሳል (ታቦር ዋሚ፣ 2006፣ 276-7)፡፡ ወደ 15ኛ/16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ራቅ ብንል ከሐዲያና ከዳዋሮ ጋራድ ጋር መጋባትና መዋለድ ተደጋግሞ ሲከሰት እናገኛለን፡፡ (ተክለ ፃድቅ 1961፤ 21-2 አንደርዜይና . . . 96)፡፡ ለሰለሞን ዘር እንደገና መመለስ መጀመርያ የሆነው አፄ ይኩኖ አምላክ ራሱ በእናቱ በኩል የዘር “ጥራት” ያንሰዋል የሚል ነገር አለ፡፡ የይኩኖ አምላክ እናት ታደሰ ታምራት የአንድ ባላባት ባሪያ ነበረች ሲል፣ ኮንቲ ሮሲኒ ደግሞ የአዛዥ ጫላ ባሪያ እንደነበረች መጻፉን ታቦር ይናገራል (2006፤ 65)፡፡ በይኩኖ አምላክ ዘር ውስጥ ሳይኖር አይቀርም የተባለው “አጥንተ ሰባራነት” አልበቃ ብሎ፣ እነ ልብነ ድንግል ውስጥ ‹‹የገባው›› ሐዲያነት ይታከልበታል፡፡ ከዚያ ደግሞ . . .  

በጥቅስ ምልክት እያስገባን ስለ ኦሮሟዊ/ሐዲያዊ ትውልድ ማውራታችን በደም የሚተላለፍና የማይተላለፈውን በቃላት ማስቀመጥ ስለቸገረንና የተለመደውን የተምታታ አጠቃቀም ለማስታወስ ብለን ነው፡፡

ኦሮሞነት፣ ትግሬነት፣ ሐዲያነት፣ ወዘተ፣ ወዘተ በአብሮ መኖር ትስስር የሚገኙና ሰዎች ላይ የሚቀረፁ ማኅበራዊ ማኅተሞች ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ማኅተሞችና ዘር ደግሞ ለየቅል ናቸው፡፡ ሆኖም መዋለድ እንደሚያቀራርብ ሁሉ በማኅተም አንድ የሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር ውስጣዊ የእርስ በርስ መወላለድን ያመጣል፡፡ በተረፈ በደም መወራረስን በጋራ ባህል የመቀረፅ አጥር አይገድበውም፡፡ ብሔረሰባዊና አካባቢያዊ ማንነት (ጎጃሜነት፣ ወለጌነት፣ . . . ወዘተ) እንደዚሁ በደም አይወሰንም፣ በደም አይተላለፍም፡፡ ከየትኛውም ማኅበረሰብ ይበልጥ ክፍት የሆነው ኦሮሞ በጉዲፈቻና በሞጋሳ ኦሮሞነትን ሊያቀዳጅ የቻለው ለዚህ ነው፡፡ አንድ ኦሮሞ የፈረንሣይ ባህልና ቋንቋ ውስጥ ቢያድግ ከጥቁረቱ በስተቀር ሳፊ ፈረንሣዊ ነው የሚሆነው፡፡ ነጩን ፈረንሣዊም ኦሮሞዎች ቢያሳድጉት ነጭ ኦሮሞ ሆኖ ነው የሚወጣው፡፡ እዚያ ከተዋለዱት ኦሮሞች እኩል ኦሮሞ የሚያሰኘው ባህልና ሥነ ልቦና ይጎናፀፋል፡፡ ይህ ነጭ ኦሮሞ ባሳደገው የኦሮሞ ማኅበራዊ ማህፀን ውስጥ ሦስት ጉልቻ መሥርቶ መኖር ቢቀጥል፣ በዙሪያው የሚያገኘው የቅርብ ዕድል ከነባሮቹ ጋር መጋባትና መዋለድ ነው፡፡ በአንድ ሰው ያየነው ምሳሌ ብዙ ውጥንቅጥ ግለሰቦች አንድ አምሳያ ማኅበረሰብ ውስጥ ቢቀላቀሉም ያው ነው፡፡ የማኅበረሰቡ የጋራ ባህልና ልቦና ለውሶና አቡክቶ አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ ጉዳዩ አንድ ማኅበረሰባዊ ግቢ ውስጥ እንግዳ ሆኖ ከመግባት የተለየ፣ የተለያዩ የማኅበረሰቦች ቁራጮች መጎዳኘት/መሰባጠር ከሆነም አብሮ መኖር አዘማምዶ የጋራ ባህርይ ይሰጣቸዋል፡፡ ኦሮሞ – አማራ – ትግሬንና የዶባ ሕዝብ ርዝራዦችን በስተኋላ የለወሰው ራያነት፣ የሰላሌ ኦሮሞ – አማራ፣ የሶዶ ጎራጌ – ኦሮሞ የቅልቅል ገጽታዎች፣ ወዘተ የዚህ አብነት ናቸው፡፡

የሰው ልጆች ምድር ላይ ከታዩበት ጊዜ አንስቶ ሁለት የልውጠት ጉዞዎች (በዝግመት የሚጠራቀሙና ቅርፅ የሚያበጁ) ሥጋዊና ማኅበራዊ ልውጠቶች አልተለዩዋቸውም፡፡ የዘሮች መዘርዘርም ሆነ መወራረስ ሥጋዊ ነው፡፡ የቋንቋና ባህል መገኘትም ሆነ ማዘርዘርና መልሶ መወራረስ ማኅበራዊ ነው፡፡ እነዚህ የሁለት ፈርጅ ልውጠቶች በምሥራቅ አፍሪካም ውስጥ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ሲካሄዱ ኖረዋል፡፡ ስደት፣ ፍልሰት፣ መዘማመት፣ ምርኮ መውደቅና በባርነት መጋዝ ሁሉ ተራ ሰውን ከመሳፍንት ሳይለዩ እየበተኑ፣ እያሰባጠሩና እያጎዳኙ ሥራቸውን ሲሠሩ ኖረዋል፡፡ “ሐበሻ” የሚለው ቃል ድብልቅ በሚለው አጠቃቀሙ ይገልጸናል፡፡ የሥጋ ዘራችን ዥንጉርጉነትና ክልስልስነት ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ጠረፋማ አካባቢ ተገልለው የኖሩ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ ወዘተ ሕዝቦች ሳይቀር ጎንደርና ትግራይ ድረስ ተበትነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መካከል ምን ያህል የደም መወራረስ እንዳለ ለመረዳት የ‹ዲኤንኤ› ምርመራ ቢሞከር ሁሉን የሚያስገርምና ብዙ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ትቢያ የሚከት ውጤት እንደሚገኝ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አይጠራጠርም፡፡

በማኅበራዊ ገጽታችን ውስጥ በቋንቋና በባህል በኩሻ – ኩሽና በኩሻ – ሴም ውስጥ ያለው መወራረስ፣ የእንሰት ባህል፣ የስሞችና የአለባበስ መወራረስ፣ የትከሻና አንገት ነክ ውዝዋዜው ሁሉ ሰፊ አካባቢ ያደረሰ ሆኖ መገኘቱ የቅልቅል ገጽታ መታያ ነው፡፡  ቅልቅልን በመሸመን ረገድም ቢሆን የኢትዮጵያን ስም ይዞ ከሰሜን ወደ ደቡብ እየሰፋ ከመጣው አስገባሪነት የበለጠ ዋናው ጥበብ ሠሪ ኦሮሞ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የማኅበራዊ ጥንቅር ታሪክ በዋናነት ደርሷል፡፡ በሁላችንም ላይ ኦሮሞነትን ጽፎብናል፡፡ ውቃቢ፣ አቴቴ፣ አድባር፣ ቦረንትቻ ያልደረሱበት የኢትዮጵያ ክፍል የቱ ነው? የኦሮሞ የፈረስ ስም አወጣጥ የመሳፍንት መዋቢያ ያልሆነበት አካባቢ የቱ ጋ ነው? ኦሮሞ የሰውና የሥፍራ ስሞቹን ያላተመባቸው አካባቢዎችስ ይገኛሉ?

በሃይማኖት ውስጥ ብንገባ እንኳ በክርስትና መስፋፋት ውስጥ የሙስሊሞችን ታሪክ፣ በእስልምና መስፋፋት ውስጥ የክርስቲያኖችን ታሪክ፣ በሁለቱም ውስጥ የቤተ እስራኤሎችን፣ የአረማውያንና የዋቄፈታዎችን ታሪክ እናገኛለን፡፡  ክርስቲያናዊ የበላይ ገዢነትን የማዝለቅና በእስላማዊ የበላይ ገዢነት የመቀየር ፍላጎት እነ አህመድ ኢብራሂምንና እነ ልብነ ድንግልን ቢያዋጋቸውም፣ ሰፊ አገር ጠቅልሎ የመግዛት ፍላጎት ሁለቱንም አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ (አህመድ ኢብራሂም ደንቢያን በመቀመጫነት መርጦ ለመደላደል ከማሰብ አልፎ፣ በጋብቻ ተሳስረን ሰላም እናውርድ ሲል ልብነ ድንግልን አስጠይቆ ልኮበት ነበር ይባላል (አንደርዜይና . . . 2003፤  139)፡፡) በየጁዎች የጎንደር ገዥነት ውስጥ በአንድ ጊዜ የእስልምናንም የክርስትናንም ገጾች እናገኛለን፡፡ የኦሮሞ ገዢነት የኢትዮጵያ የገዥነት ታሪክ አካል ሆኖ፣ አስገባሪነትና በአማፂ ገዢ ዳፋ ተገዢው ሕዝብ የሚዘረፍበትና የሚፈጅበት አቀጣጥ በኦሮሞ ገዢነትም በኩል ሲላወስ እናገኘዋለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...