Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሳይበጁ አረጁ!

በተቀመጠላቸው ዕቅድ መሠረት ይተገበራሉ ተብለው ወደ ሥራ የተገባባቸው መንግሥታዊ ፕሮጀክቶችን መለስ ብለን ስንመለከት፣ አብዛኞቹ በዕቅዳቸውና በክንዋኔያቸው መካከል በጣም ሰፊ ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ እንዴት ቢታቀድ ነው በተግባርና በጽሑፍ በሰፈረው መካከል የዚህን ያህል ልዩነት የታየው የሚያስብሉም ጥቂት አይደሉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በታቀደላቸው ልክ ተፈጽመዋል የሚባሉ ፕሮጀክት ለማግኘት ብዙ ድካም ይጠይቃል፡፡

በጣት ልንቆጥራቸው ከምንችላቸው ጥቂቶች በቀር፣ በየትኛውም ዘርፍ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራው ተጠናቆ ለሥራ የበቃ ፕሮጀክት ማየት ብርቅ እየሆነ መጥቷል፡፡

ከሰሞኑም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሥራ አፈጻጸማቸውን ካደመጥንላቸው ተቋማት ውስጥ አብዛኛዎቹ በዕቅድና በክንክዋኔያቸው መካከል ያለውን ልዩነት ስንሰማ፣ ነገሩን በብርቱ እንድናስብበት ሳያደርገን አይቀርም፡፡

በተለይ ወሳኝ የሚባሉ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሥራ አፈጻጸም በዕቅድ ልክ መሥራት እጅጉን ከብዷቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ምሳሌ ልናነሳ የምንችለው የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ሳይጠናቀቅ ሥራቸው አልቆ ለፍሬ ይበቃሉ ተብለው ሲጠበቁ ከነበሩት ውስጥ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ አንዱ ነው፡፡

እንዲገነቡ መሠረት የተጣለላቸው እነዚህ ፋብሪካዎች፣ የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት በመሸፈን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ አገራዊው የማምረት አቅም ላይ ብሎም አኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚያኖሩት አሻራ ታሳቢ ተደርጎ እንዲገነቡ በጀት የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡

 ፕሮጀክቶቹ እንደታሰበው ዳር ሳይደርሱ ከዓመት ዓመት በመንከባለል ከዓመታት ቆይታም በኋላ ‹‹ወፌ ቆመች. . .›› እያሰኙን ይገኛሉ፡፡ በመጀመርያው የዕቅድ ዘመን መጠናቀቅ የነበረባቸው የስኳር ፋብሪካዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው ከምርታቸው መቋደስ ያልተቻለበት ምክንያት ግን ከዓመት ዓመት ይለያያል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኳር ፕሮጀክቶቻችን የተማርንባቸው ናቸው ያሉበት ጊዜም ይታወሰናል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በእርግጥም መዘግየታቸውን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አምነዋል፡፡ መፍትሔ ይበጅላቸዋል ብለው ከተናገሩም ሰነባብቷል፡፡ ነገር ግን ብዙም የተለወጠ ነገር ሳይታይ ዘንድሮም ምክንያት ሲደረደር እየሰማን ነው፡፡

በአንድ ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች ሥራቸው ሳይጋመስ ወጪያቸው አራት ቢሊዮን ብር ከደረሰ፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ያልቃሉ ተብለው ስድስትና ሰባት ዓመት ከፈጁ እንዴት ቢታቀዱ ነው እንዲህ የሚጓተቱት አያስብልም? ችግሩ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ የፕሮጀክቶቹ ወቅታዊ የግንባታ ደረጃን የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎችም የተምታቱ ሆነው መገኘታቸው የበለጠ አነጋጋሪ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው፡፡

ከሰሞኑ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ የምክር ቤት አባላት ሲሞግቱ እንደሰማነው በኮርፖሬሽኑ ስለስኳር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የቀረቡት አኃዞች የተምታቱ መሆናቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ የበለስ ስኳር ፋብሪካ አፈጻጸም አኃዛዊ መረጃዎች በስኳር ኮርፖሬሽኑ ከቀረበው አኃዛዊ መረጃ አኳያ የተምታታ ሆኗል፡፡ የተምታታ አኃዝ የቀረበው በአንድ ፕሮጀክት ላይ ብቻ ሳይሆን አራት ፕሮጀክቶች ላይ ነው፡፡ ደግነቱ የተወካዮች ምክር ቤት ይህንን በመገንዘብ ሞግተዋል፡፡

አንድ ፕሮጀክት ይጠናቀቃል የተባለበት ጊዜ ማለፉ ብቻ ሳይሆን፣ በመቶኛ ምን ያህል ነው? በሚለው ላይም ኮርፖሬሽኑ ሌላ አስገንቢው አካል ሌላ አኃዝ ይዘው መቅረባቸው ከምን የመነጨ ነው? ምን ያህል ተጨማሪ ገንዘብ ፈሰሰበት? የሚለው ሥሌት ውስጥ ቢገባ የምንሰማው ነገር የባሰ ይሆን እንደነበር ለመገመት ይቻላል፡፡ በኮንስትራክሽን ሒደት ተንቀራፎ ይቅርና እጅግ ተፋጥኖ ቢሠራ እንኳ የግንባታ ዋጋ ማሻቀቡ አይቀርም፡፡ ለዚህ ዋቢ የሚደረግ በርካታ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የዋጋ ግሽበት፣ የግብዓት እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ መጥፋት ወዘተ. ይጠቀሳሉ፡፡

ቀርፋፋ ፕሮጀክቶች ለሌላ ልማት ማዋል የምንችለውን ገንዘብ አለአግባብ እየወሰዱብን በመሆኑ፣ የት ላይ እንደሚቆሙ ማወቅ አለብን፡፡  ትግበራን ካነሳን ዘንዳ የስኳር ፕሮጀክቶችም ሆኑ ሌሎችም ከአንድ ዓመት በላይ ዘግይተው ቢጠናቀቁ የሚያደርሱት ኪሳራ ምን ነው? ሁለት ዓመት ሲዘገዩስ? ከዚያ በላይ እስከ አሥር ዓመታት ሳያልቁ እንዲሁ እየተጓተቱ ሲያዘግሙስ?

እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚመደብላቸው ገንዘብ አልበቃ ብሏቸው የእጥፍ እጥፍ እያስጨመሩ በመሆናቸው የመፍትሔ ያለህ አልን እንጂ፣ በሌሎች ዘርፎችም ውስጥ በዕቅድና በክንውን መካከል ያለው የአፈጻጸም መጓደል ተጠረቃቅሞ አንድ ቦታ ላይ ሊያንገጫግጨን ስለሚችል ይተሰብበት፡፡

የስኳር ፋብሪካዎች ጉዳይ ከሌላው የባሰ ነው የምንልባቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም አንዱንና ዋናውን እንጥቀስ፡፡ ‹‹በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ስምንት አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታን አጠናቆ ሥራ በማስጀመር አሁን 3.6 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋውን ዓመታዊ የስኳር ምርት በአሥር እጥፍ በማሳደግ 42 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ከሚመረተው ስኳር ውስጥ 12.2 ሚሊዮን ኩንታል የተጣራና 17.7 ሚሊዮን ጥሬ ኩንታል ወደ ውጭ በመላክ 1.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል፤›› የሚለው ኮርፖሬሽኑ ራዕይ ተጠቃሽ ነው፡፡  

የቤቶች ግንባታም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ግንባታዎቹ በመዘግየታቸውና በመቆማቸው ጭምር ገንዘቡን ለመንግሥት ሰጥቶ ቤት ለመረከብ በተስፋ የሚጠብቀውን ሰው ልብ መስበሩ ሳያንስ፣ የግንባታው መዘግየት ያስከተለውን የዋጋ ጭማሪ እንዲሸከም የሚፈረድበት መሆኑ ሲታይ አሳዛኝ ነው፡፡ ዕቅዱ ይፋ ሲደረግ በመጀመርያ የተዋዋለበት የክፍያ መጠን ያውም በመንግሥት እንደ ዘበት ተጥሎ፣ ይህንን ያህል ካልጨመርክ ቤት አታገኝም የሚባልበት ከሆነ ሌላውማ ከዚህ የከፋ ነገር ባያደርግ፣ ገንዘቡን ይዞበት ባይጠፋ ምን ይገርማል፡፡

ስለዚህ በዕቅዳችንና በክንውናችን መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት እያጠበቡ መሄድ ካልተቻለ ለዕቅዳችን ክንውን አለመሳካት ዘወትር ሰበብ ከመደርደር መፍትሔ ማሰብ ያሻል፡፡ በተለይ በተለይ አንድ ፕሮጀክት መዘግየት ገደብ ሊቀመጥለት ካልተቻለ በእልህ መግፋቱ አንዳንዴ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ሲያስከፍል፤ ጉዳቱም ሊብስ ይችላል፡፡ ሲታቀድም መፈጸም የምንችለውን ቢሆን ከብክነት ያድናል፡፡

እንደ ምሳሌ ያነሳው የስኳር ፕሮጀክቶቻችንን ነውና የፕሮጀክቶቹ መንቀራፈፍ ከትልቁ አገራዊ ጠቀሜታው እንዲታገል ከማድረግ ባሻገር እንደ ሸማች ስኳር ፍለጋ መኳተናችን ሰበቡ ይኼው የተነጋገርንበት ጉዳይ ነው፡፡

አገሪቱ ስኳር ለውጭ ገበያ አቅርባ የወጪ ንግድ ምርቶች ሰንጠረዥ ውስጥ ስኳር ተካትቶ ሲጠበቅ በተቃራኒ በአገር ውስጥ የሚመረተው ምርት አልበቃ ብሎ ስኳር ከገቢ ንግድ ሰንጠረዥ ውስጥ ያለመሰረዙ ምክንያት ይኸው የስኳር ፕሮጀክቶች እንቅርፍፍ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ምርት ተከተዋል የተባሉትም ቢሆኑ ያመርታሉ በተባለው የምርት መጠን እያመረቱ አለመሆኑ ነው፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት