- የአዲሱ ሕንፃ ዲዛይን ቦርዱን አሟግቷል
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ለማስገንባት በማሰብ ከዚህ ቀደም ያወጣውን ዲዛይን በሌላ እንዲቀየር ተወሰነ፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ለመገንባት የወጠነውን የሕንፃ ዲዛይን እንዲሠሩለት የሥነ ሕንጻ ኩባንያዎችን በማወዳደር ከአሸናፊው ድርጅት ጋር የተዋዋለበትን የዲዛይን ሥራ በመረከብ ለግንባታ ሲዘጋጅ ቆይቶ ነበር፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ የዲዛይን ለውጥ ለማድረግ የሚያስገድደውን ውሳኔ የወሰነው፣ ቀደም ብሎ ያሠራው ዲዛይን ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ለግንባታ የሚውል ቦታ እንደሚሰጠው በገመተው ቦታ ላይ ለሚገነባ ባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ የሚስማማ ዲዛይን በማሠራቱ ነበር፡፡
ሆኖም ቀደም ብሎ ለግንባታ እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበበትን ቦታ የከተማው አስተዳደር ሳይቀበለው በመቅረቱና በምትኩ በሌላ አካባቢ ቦታ ስለተሰጠው በዚሁ አግባብ ዲዛይኑን ለመቀየር እንደተገደደ ታውቋል፡፡ በመሆኑም አዲስ ዲዛይን በድጋሚ ለማሠራት ወስኗል፡፡
ዲዛይኑን በመለወጥ አዲስ ለማሠራት የሚያስቸለውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አባላት እርስ በርስ ሙግት ውስጥ ገብተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ መልክ ይሠራል የተባለውን ዲዛይን ማን ይሥራው የሚለው ጉዳይ የቦርድ አባላቱን ለሁለት ከፍሎ እንዳከራከረ የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ አንደኛው ወገን አዲስ በተሰጠው ቦታ ላይ ለሚገነባው ሕንፃ ሌላ ዲዛይን ለማሠራት ሥራውን ለሚሠሩ አማካሪዎች ጨረታ እናውጣ የሚል አቋም አራምዷል፡፡ ሌላኛው የምክር ቤቱ አመራር አካል በበኩሉ አዲሱን ዲዛይን ከዚህ ቀደም ለንግድ ምክር ቤቱ የባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ ዲዛይን ለሠራው ኩባንያ በድጋሚ ይሰጠው በማለቱ፣ በሁለት ሐሳቦች መካከል በተነሳው የሐሳብ ልዩነት ለውሳኔ ተቸግረው እንደነበር ታውቋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት ንግድ ምክር ቤቱ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ እንዲሰጠው አመልክቶ የነበረውን ቦታ ታሳቢ በማድረግ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ለማስገንባት አሸናፊ የሆነውን ዲዛይን የሠራው አማካሪ ድርጅት ለዲዛይኑና ለማማከሩ ሥራ የሁለት ሚሊዮን ብር ኮንትራት ተፈራርሞ ነበር፡፡ እንደ አዲስ ዲዛይኑ ይሠራ የሚሉት የቦርድ አባላት፣ ሥራው አዲስ በመሆኑ ጨረታ መውጣት አለበት ብለው ቢሟገቱም በድምጽ ተበልጠው የቀድሞውን ዲዛይን ለሠራው ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡
በመሆኑም ለአዲሱ ባለ 12 ወለል ሕንፃ ዲዛይን ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ የዲዛይን ሥራውን ከሦስት ዓመት በፊት እንደሚገነባ ለታሰበው ባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ ዲዛይን በመሥራት አሸናፊ ለሆነው ኩባንያ ይሰጥ የሚለው ቡድን በአብላጫው በማሸነፉ በዚሁ መሠረት ስምምነት ላይ እንደተደረሰ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ ውሳኔ ያልተስማሙት ወገኖች፣ ሥራው አዲስ በመሆኑ ጨረታ ሊወጣ ይገባል፣ ያለ ጨረታ ቀድሞ ለሠራው ኩባንያ ዳግም ይሰጥ መባሉ ትክክል አይደለም በማለት ሞግተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንጋፋ ከሚባሉት የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን የራሱ የሚለው ሕንፃ ባለመኖሩ አዲሱን ሕንፃ በቶሎ ለማስጀመር ፍላጎት ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ እስከ 500 ሚሊዮን ብር ይፈጃል የተባለውን ይህን ሕንፃ በመስከረም 2010 ለመጀመር ያቀደ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አዲሱ ዲዛይን ለውጥ ግን ሥራ ሊያዘገየው ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡