Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግብርና ንግድ ሥራ የተሠማሩ ወጣቶች ለመሠረቷቸው የግብርና ማዕከላት ድጋፍ አገኙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በአነስተኛ ገበሬዎች ላይ ያተኮሩ የግብርና ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩት ወጣቶች ጽጌሬዳ ሰሎሞንና አብርሃም እንድሪያስ ይባላሉ፡፡ ሁለቱም በግብርና መስክ ለአነስተኛ ገበሬዎች አገልግሎት ከዚህ ቀደም ሲሰጧቸው የነበሩ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የግብርና ማዕከላት የሚመሠርቱባቸውን ድጋፎች ከጀርመን መንግሥት አግኝተዋል፡፡

ጽጌረዳ ሰሎሞን በሙያዋ ላቦራቶሪ ቴክኒሻን ብትሆንም፣ በግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ንግድ መስክ በ1999 ዓ.ም. የሚንቀሳቀስና ጽጌሬዳ የግብርና ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት የተባለውን መደብር በኦሮሚያ፣ ሉዴ ሒጦሳ ወረዳ ውስጥ ከባለቤቷ አቶ ታደሰ ፀጋዬ ጋር በመሆን ስትሠራ ቆይታለች፡፡

የጀርመን መንግሥት በጂአይዜድ አማካይነት ከሚሰጣቸው ድጋፎች መካከል የግብርና አግልግሎት ማዕከላት ፕሮጀክት የተሰኘው አንዱ ሲሆን፣ ይህንን በሚያስፈጽመው፣ ‹‹ከልቲቬቲንግ ኒው ፍሮንታየርስ ኢን አግሪካልቸር- ሲኤንኤፍኤ›› በተባለ ተቋም አማካይነት ፕሮጀክቶችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በዚህ ተቋም አማካይነት ድጋፍ ካገኙ መካከል የሆነችው ጽጌሬዳ፣ በኬሚካል፣ በዘር አቅርቦት መስክ ስታከናውን በቆየችው ሥራ በኩል የ30 ሺሕ ዩሮ ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ለዚህ ድጋፍ መጠይቅ ከሆኑት ዋናው ተመጣጣኝ የገንዘብ መጠን ያለው መዋጮ ማድረግና ቀጣይነቱ የሚያስተማምን የግብርና ንግድ ሥራ ውስጥ መገኘት እንደሆነ ያብራራችው፣ የተቋሙ የፕሮግራም ኃላፊ ወይዘሪት ርብቃ አምሃ ነች፡፡ እንደ ወይዘሪት ርብቃ ማብራሪያ ከሆነ እኩል መጠን ያለውና በዓይነት የሚደረገው መዋጮ ለወደፊቱም ዘላቂነት ያለው የግብርና ንግድ ሥራ እንዲኖር፣ አነስተኛ ገበሬዎችም ከዚህ አገልግሎት በዘላቂነት መጠቀም እንዲችሉ ታስቦ የዘተረጋ ፕሮግራም እንደሆነ ገልጻለች፡፡

በመሆኑም ጽጌሬዳና ባለቤቷ በሚሠሩበት ከተማ የፕሮጀክቱ ዕድል በመጣበት ወቅት ተወዳድረውና እንዲያሟሉ የተጠየቋቸውን መስፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው የ30 ሺሕ ግምት ያለው ሙሉ የግብርና ግብቶች፣ መለዋወጫዎችና ሌሎችም እንደሚሟሉላቸው ጽጌሬዳ አብራርታለች፡፡ የዕቃዎቹ ርክክብም በመጪው ዓመት ህዳር ወር እንደሚደረግ ከተደረገው ስምምነት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ወጣት አብርሃም እንድርያስ በበኩሉ ግሪን አግሮ ሶሉሽን የተባለ ኩባንያ መሥራች ሲሆን በዲጋሉ ጢጆ ወረዳ ውስጥ የሳጉሬ ግብርና አገልግሎት ማዕከልን በመመሥረት ለገበሬዎች የሜካናይዜሽን አገልግሎት፣ ለዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ለቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች በሜካናይዜሽን እርሻ መስክ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ልዩ የእርሻ መሣሪዎችን በማከራየትም ይቀሳቀሳል፡፡

አብርሃም የያንግ አፍሪካ ሊደርስ ኢኒሺዬቲቭ የአምና ተሳታፊ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከታዋቂው የአሜሪካው ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለግብርና ግብዓቶችና ምርት ማጓጓዣ፣ ብሎም ለሜካናይዜሽን እርሻ የሚረዳ ተሽከርካሪ በአገር ውስጥ ለማምረት ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ እሱም የ30 ሺሕ ዩሮ ግምት ያላቸው ለሥልጠና የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላቱ የዕድሉ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ዋና መዳረሻውን በአርሲ ዞን በማድረግ የሮቤ፣ የኢተያ፣ የአሰላ፣ የሳጉሬ እንዲሁም የሁሩታ ግብርና አገልግሎት ማዕከላት የተባሉትን አምስት አነስተኛ የግል ድርጅቶች ለመመሥረት ለእያንዳንዳቸው 30 ሺሕ ዩሮ መጠን ያላቸው ልዩ ልዩ የቁሳቁስ ድጋፎችን አቅርቧል፡፡

ፕሮግራሙ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል ከወይዘሪት ርብቃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእስካሁኑ የሙከራ ሒደት ድጋፍ ባገኙት አምስት የግብርና አገልግሎት ማዕከላት አማካይነት የ375 ሺሕ ዩሮ ግምት ያላቸው ሸያጮችን ማከናወን እንደተቻለ፣ ለ25 ሺሕ ደንበኞችም ምርቶችና አገልግሎቶችን ማዳረስ እንደተቻለ፣ ከ1,600 በላይ ገበሬዎችንም ለማሠልጠን እንደተቻለ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በጀርመን መንግሥት በአነስተኛ ግብርና መስክ ድጋፍ ከሚደረግበት የማዕከላት ማቋቋሚያ ድጋፍ ባሻገር፣ በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፉ 26 ፕሮጀክቶችም በአገር አቀፍ የተቋቋሙ ሲሆን፣ እነዚህን ማዕከላት የሚመሠርቱ ሰዎችም ከ40 እስከ 50 ሺሕ ዶላር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች