Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማስተር ፕላን ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቀች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የከተማ የውኃ ፍሳሽ አወጋገድና ሳኒቴሽን ተዘንግቷል ተብሏል

በደቡብ ኮሪያና በኢትዮጵያ መካከል በበርካታ መስኮች ጠንካራ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የባህል ግንኙነቶች በመሠረትም፣ በአካባቢ ጉዳይ ላይ ያን ያህል የጠበቀ ግንኙነት ባለመኖሩ በዚህ መስክ በተለይም በፍሳሽ ውኃ ማጣሪያ ፕሮጀቶች ላይ የማስተር ፕላን ዝግጅት ላይ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቷን አስታወቀች፡፡

የደቡብ ኮሪያ የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ያዘጋጀውና የኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም የኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተወካዮች የታደሙበት የኮሪያ ኢትዮጵያ የአካባቢ ፎረም በዚህ ሳምንት አጋማሽ ሲካሔድ እንደተገለጸው፣ ለውኃ ፍሳሽ ማጣሪያ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ዝቃጭ አወጋገድ ሥርዓት ማስተናገጃ የሚውል ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ይደረጋል፡፡

ዶ/ር ሊ ቻንግ ሒም፣ በደቡብ ኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ቢሮ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ቻንግ ሒም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የውኃ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስተር ፕላን ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚደረግ የአካባቢ ጥበቃ የሁለትዮሽ ግንኙነት መመስረቻ ይሆናል፡፡

 

በመጪው ዓመት ሥራው ይጀመራል ያሉት የማስተር ፕላን ዝግጅት ሥራው ሦስት የተመረጡ ከተሞችን ሊያካልል እንደሚችል ዶ/ር ቻንግ ሒም አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ምን ያህል ገንዘብ ሊጠይቅ እንደሚችል ለማወቅ በአገሪቱ በፍሳሽ አወጋገድ መስክ ያሉ መረጃዎችን ማጠናቀር እንደሚጠይቅና በርካታ ዝርዝር ሥራዎችም እንደሚካሔዱ ገልጸዋል፡፡ ሥራው ገና ጅምር ላይ በመሆኑ ኮሪያውያኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ የመረጃ ልውውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሥራው እንደሚጠናቀቅ የተጠቀሰው ይህ ፕሮጀክት፣ ኮሪያ በየዓመቱ ለአገሮች የምታደርገው የአካባቢ ጥበቃ ድጋፍ አካል ሲሆን፣ በአፍሪካ ከሞዛምቢክ በመከተል ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንደምትሆን ዶ/ር ቻንግ ሒም ጠቅሰዋል፡፡

ከኮሪያ መንግሥት ባሻገር የኮሪያ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማጣሪያ ሥራዎች ውስጥ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በፎረሙ አስታውቀዋል፡፡ ከመንግሥትና ከግል የተውጣጡ 20 ተሳታፊዎች በተሳተፉበት መድረክ፣ ልምዳቸውን ያካፈሉ ኩባንያዎች በደረቅና በፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ መስክ ስለሚሠሯቸው ሥራዎች አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የግል ኩባንያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡ በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥር የውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገርአቀፍ ፕሮጀክቶች አስባባሪ አቶ ታምሩ ገደፋ እንዳብራሩት፣ በዚህ ዓመት ይፋ የተደረገውና ከዓለም ባንክ በተገኘው የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር (የመንግሥትን የ60 ሚሊዮን ዶላር መዋጮ ይጨምራል)፣ በአዲስ አበባና በ22 ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች የሚተገበረው የውኃና የሳኒቴሽን ፕሮግራም ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን በውኃ አቅርቦትና በሳኒቴሽን ሥራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ለመጪዎቹ ስድስት ዓመታት እንደሚተገበር ገልጸዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረው ሌላኛው የአምስት ዓመት ፕሮጀክትም በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በመንግሥትና በሌሎችም አበዳሪዎችና ለጋሾች የሚደገፈው አገር አቀፉ የውኃ፣ የሳኒቴሽንና የሃይጂን ፕሮግራም (ዋን ዋሽ ናሽናል ፕሮግራም) የ485 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 382 ወረዳዎች፣ 124 አነስተኛና 20 መካከለኛ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ እንሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ይህም ሆኖ መንግሥት በአምስቱ ዓመት ዕቅዱ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የያዘላቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም፣ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግሮች እንዳጋጠሙት አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በከተማና በገጠር አካባቢዎች የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቶችን ለመገንባት እየጣረ ቢሆንም፣ በተለይ የከተማ ፍሳሽ ውኃ አወጋገድ በእጅጉ የተረሳ መስክ እንደሆነ አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎችም የፍሳሽ አጋገድ ሥርዓት የጎደላቸውና ተገቢውን ሥርዓት ያልተከተሉ በመሆናቸው፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር አኳያ ትልቅ ሥጋት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች