Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅውበት በየፈርጁ!

ውበት በየፈርጁ!

ቀን:

  1. በደቡብ ኦሞ ሸለቆ ኪቢሺ ከተማ አቅራቢ  የሚገኙት የሱሪ ብሔረሰብ ታዳጊ ወጣቶች  ውሎ
  2. የሱሪ ልጃገረድ  በባህላዊ አጋጊያጥ ተውባ 

ወይራነት

በራስ ህይወት ፈለግ – በጠገግህ ስትሄድ
እወቅ!
ጥምዝ ጠመዝማዛ – ዳገታም ነው መንገድ፤
ሀቅ!
እንኳን በራስ መንገድ
ሰው በሰውም ቢሄድ
አይቀር መንገዳገድ፤

የመሄድህ ሁነት – የመጓዝህ ዳና
እንኳን በሰውና – በአምላክ ባይቃና
ገስግስ!
ፍሰሰው እንደ ወንዝ – አቅጣጫ እየቀርክ
ቅያስ እያሳበርክ
አለዚያ ምኑን ኖርክ!
ኑር!
እንኳንስ ሰውና – ተፈጥሮም ያድማል
ጠልፎ አንተን ለመጣል – ከነፋስ ይቀድማል፤

- Advertisement -

እንደ ግራትካ’ሱ
እንደ ሊማሊሞ
እንደ ዓባይ በርሃ
ልክ እንደ ሀረጎ
ወይ እንደ ደንገጎ
ጥምዝምዝ
ጉርብጥብጥ
ዳገት
ወይ ቁልቁለት
ሀሩር ሲሆንብህ
ጠንክር እንደ ወይራ
ካለፍክ በኋላ – ከልካይህ ሁሉ ነው – ስላንተ እሚያወራ!!

  • ደመቀ ከበደ

*******

አዲስ አበባ እንዴት ነች?

አዲስ  አበባ  የተሰየመችው  እቴጌ ጣይቱ  ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም. ፍልውኃ  ፊል-ፊል  ወደሚልበት  መስክ  ወርደው  ሳሉ ከዚህ  በፊት  አይተዋት  የማያውቋት  አንዲት  ልዩ  አበባ  አይተው ስለማረከቻቸው  ቦታውን ‹‹አዲስ  አበባ!›› አሉ። ከተማዋ  እቴጌ  ጣይቱ  በመረጡት  ቦታ  ማለትም  በፍል ውኃ  አካባቢ  ላይ  በባላቸው  በዳግማዊ  ምኒልክ ተቆረቆረች።

የአዲስ አበባ ከተማ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ነው። እነዚህንም በተለያዩ ዘርፎች ከፍሎ በቅደም ተከተል ማየት ይቻላል።

በርካታዎቹ የከተማዋ ቀደምት ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ መሬት በጉልት መልክ በተሠጣቸው መሣፍንትና መኳንንት ስም ነው። በዚህ መልክ ስያሜያቸውን ካገኙት ሠፈሮች መካከል ራስ መኰንን ሠፈር፣ ራስ ተሰማ ሠፈር፣ ራስ ብሩ ሠፈር፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ራስ ሥዩም ሠፈር፣ ራስ ሙሉጌታ ሠፈር፣ ደጃዝማች ውቤ ሠፈር፣ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ደጃዝማች ዘውዱ አባኮራን ሠፈር እና ሸጎሌ (የአሶሳ ገዢ በነበሩት በሼክ ሆጀሌ አል ሐሰን የተሰየመው) ሠፈር ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመላው የአገሪቱ ማዕዘናት መጥተው አዲስ አበባ በሠፈሩ ብሔረሰቦች የተመሠረቱ ሠፈሮች ይጠቀሳሉ። በዚህ መልክ ከተመሠረቱት ሠፈሮች መካከል ለአብነት አደሬ ሠፈር፣ ጎፋ ሠፈር፣ ወሎ ሠፈር፣ ወርጂ ሠፈር፣ መንዜ ሠፈርና ሱማሌ ተራ ይገኙበታል። የወርጂ ሠፈርን የመሠረቱት የወርጂ ብሔረሰብ አባላት በቆዳና በበርኖስ ንግድ የተሠማሩ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። በተመሣሣይ መልኩ የሱማሌ ተራ ነዋሪዎች ዋነኛ መተዳደሪያ የሻይ ቤት ሥራ እንደነበር ይታመናል።

በሦስተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች ተሠማርተው በተለይም በቤተ መንግሥቱ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎች በነበራቸው ባለሙያዎች የተቆረቆሩ ሠፈሮችን እናገኛለን። እነዚህም ከብዙ በጥቂቱ ሠራተኛ ሠፈር፣ ዘበኛ ሠፈር፣ ሥጋ ቤት ሠፈር፣ ኩባንያ ሠፈር፣ ጠመንጃ ያዥ ሠፈር፣ ካህን ሠፈር (በኋላ ገዳም ሠፈር) ፣ ገባር ሠፈር ፣ ሠረገላ ሳቢ ሠፈርና ውሃ ስንቁ ሠፈርን ያካትታሉ። ሠራተኛ ሠፈር በአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በዕደ ጥበባት ሙያ በተሠማሩ ነዋሪዎች የተመሠረተ ሠፈር ነው። የሠፈሩ መሥራቾች ዋነኛ ሙያ የብረታ ብረት ሥራ እንደነበረ ይነገራል። ይሄም የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለምሳሌ ማረሻ፣ የፈረስ እርካብን፣ የቤት እቃዎችን፣ የጋሻና ጦር እና የጠመንጃ ዕድሳትን ይጨምራል። በቤተ መንግሥቱ በአናጢነት የተሠማሩ ባለሙያዎችም የሚኖሩት በሠራተኛ ሠፈር እንደነበር ይነገራል።

በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ክስተቶችና ታሪካዊ ክንዋኔዎች ነው። ሰባራ ባቡር፣ እሪ በከንቱ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ አፍንጮ በር፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ጣሊያን ሠፈር፣ ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣ ሽሮ ሜዳና ነፋስ ስልክ ተብለው የሚጠሩትን ሠፈሮች በዚሁ ዘርፍ መፈረጅ ይቻላል።

ሰባራ ባቡር ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ሙሴ ሰርኪስ ተርዚያን በሚባሉ አርመናዊ ነጋዴ አማካይነት ከውጭ አገር መጥቶ አሁን ስያሜውን ባገኘበት ቦታ ተበላሽቶ በቀረው የመንገድ መሥሪያ ተሽከርካሪ (ሮለር) ምክንያት ሠፈሩ ሰባራ ባቡር እንደተባለ ይነገራል። አገሬው “የሠርኪስ ባቡር” እያለ የሚጠራው መሣሪያ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞለት ነበር።

«ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ፣

ምኒልክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠረ።»

ሌላው በከተማው ከሚገኙ ዋና ዋና ሠፈሮች መካከል በከተማዋ ቀደምት ነዋሪዎች በሆኑት የኦሮሞ ተወላጆችና የቦታ ስሞች የተሰየሙ ሠፈሮችን እናገኛለን። ከነዚህም መካከል ጉለሌ፣ ጎርዶሜ፣ ቀበና፣ ኮተቤ፣ የካ፣ እንዲሁም ገርጂ እና ላፍቶ የተባሉት ሠፈሮች ለአብነት ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም በከተማዋ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን እና አጥቢያዎች የተሰየሙ ሠፈሮች ሌላው ዋነኛ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ከሚገኙ ሠፈሮች መካከል ተቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው አራዳ ጊዮርጊስ ሠፈር ነው። አራዳ በተለይም ከጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል ከመሆኑ አኳያና በርካታ ማሕበራዊ ክንዋኔዎችን ያስተናግድ የነበረ ሠፈር እንደመሆኑ በስነቃል ብዙ ተብሎለታል። ለአብነት

«ሱሪ ያለቀበት አይገዛም አዲስ፣
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ጊዮርጊስ።
እስኪ አራዳ ልውጣ ብርቱካን ባገኝ፣
ትናንት ኮሶ ጠጣሁ ዛሬ መረረኝ።
ምነው በአደረገኝ ከአራዳ ልጅ መሣ፣
እንኳን ለገንዘቡ ለነፍሱ የማይሣሣ።
የአራዳ ዘበኛ ክብሬ ነው ሞገሴ፣

በቸገረኝ ጊዜ የሚደርስ ለነፍሴ» የሚሉት ይገኙባቸዋል።

በዚህ ዘርፍ የሚመደቡ ሌሎች ሠፈሮች ደግሞ አማኑኤል ፣ ዮሴፍ ፣ ኪዳነ ምሕረት፣ ቀራኒዮ መድኃኔ ዓለም፣ እና ቀጨኔ መድኃኔ ዓለምን ያካትታሉ። ከ1888 ዓ.ም. የዐድዋ ጦርነት ድል እና ከአዲስ አበባው ስምምነት በኋላ ጣሊያን፣ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታትና አሜሪካ የአገራችንን ሉዓላዊነት በመቀበል ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል። በዚህ ሂደት በርካታ አገሮች የነዚህን አገሮች ፈለግ በመከተል ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተዋል።

ከአዲስ አበባ በርካታ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ ስያሜያቸውን ያገኙት ከእነዚህ ኤምባሲዎችና ቀደም ሲል ደግሞ ከሌጋሲዮኖች ነው። ፈረንሣይ ሌጋሲዮንና ሩዋንዳ ሠፈሮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። በመጨረሻም ከአዲስ አበባ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ በታዋቂ የውጭ አገር ዜጎች ስም የተሠየሙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ቤኒን ሠፈርና ተረት ሠፈር ይገኙበታል። ቤኒን ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ከጣሊያን ወረራ በፊት ታዋቂ ነጋዴ በነበሩት የአይሁድ ተወላጅ ቤኑን ሲሆን፣ ተረት ሠፈር ደግሞ ስያሜውን ያገኘው በአዲስ አበባ ከተከፈቱት ከመጀመሪያዎቹ ሆቴሎች አንዱ በነበረው በሆቴል ዳፍራንስ ባለቤት ፈረንሣዊው ሙሴ ቴረስ ስም ነው።

  • አዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽሕፈት ቤት ‹‹አዲስ አበባ ባለፈውና ባዲሱ ሚሌኒየም›› (2000)

********

የኮስታሪካው ፕሬዚዳንት ያኘኳት ተርብ

የኮስታሪካው ፕሬዚዳንት ሉዊስ ጉ ሊርሞ ሪቬራ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ እያደረጉ ነው፡፡ በፎቶ ጋዜጠኞችም በተጨናነቀው ሥፍራ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ በመስጠት ላይ የነበሩት ሪቬራ፣ አፋቸውን ለንግግር በከፈቱበት ቅፅበት አንዲት ተርብ ዘላ ትገባለች፡፡ ፕሬዚዳንቱ ተርቧን ከመትፋት ይልቅ ዋጥ ያደርጓታል፡፡ ወዲያውም ሳቃቸውን በመልቀቅ ውኃ ከመጎንጨታቸው አስቀድመው ‹‹ተርቧን በላኋት፣ ተርቧን በላኋት›› እያሉ መናገር ጀመሩ፡፡ ሃፍንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ ተርቧን ድንገት የዋጧት ሪቬራ ጉዳዩን እንደምንም አለመቁጠራቸው በአካባቢው የነበሩ ጋዜጠኞችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...