Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከተሳሰብን ያንሰናል ያልነው ይትረፈረፋል!

ሰላም! ሰላም! “ካላጣሽው አካል በልቤ ላይ ተሰንቅረሽ፣ ታሰኚኝ ጀመረ ደግሞ ደግሞ እንደምን አለሽ?” እያልኩ ሳፏጭ ማንጠግቦሽ አልጣማትም። “እኔ ያለሁት እዚህ አጠገብህ ማን ናት እሷ ተሰንቃሪዋ?” ብላ ፍጥጥ። ጉድ እኮ ነው። ብለን ብለን በ‹ኢማጅኔሽንም› ልንጣላ ነው? ምኑን ቀረው። በስም ስንጣላ፣ በአቀማመጥ ስንጣላ፣ በአረማመድ ስንጣላ ከረምንና ደግሞ አሁን በተውላጠ ስም ጭቅጭቅ። ምንድነው ግን ጉዱ? እ? ‘ፈራሁ የምፀናበት ልብ አጣሁ ነው’ ያለው ያ ባለቅኔ። አይ ሞት። ሁሉን አፈር አልባሹ። “ሞት ባይኖር ኖሮ እኮ እንዲህ አንናናቅም ነበር፤” ሲለኝ ነበር የባሻዬ ልጅ። “ማን ከማን ሲናናቅ አየህ?” ስለው፣ “ተማሪና አስተማሪ፣ መሪና ተመሪ፣ ፈጣሪና ፍጡር ናቸዋ። አታይም እንዴ ዙሪያህን?” አለኝ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ነካ የሚያደርገኝ ነገር አለ። ዙሪያህን ሲለኝ ቀጥታ ወስጄው ዘወር ስል ማንጠግቦሽ ቆማለች። “ዛሬ ያቺን ስንቅር ሳታወጣ ወደ ቤት እንዳትመጣ፤” ብላ ረግጣን ሄደች። “ምንድነው?” አለኝ የባሻዬ ልጅ ደንግጦ።

ነገሩን በጥሞና አስረዳሁት። “የወፍ ቋንቋ፣ የአሞራ ክንፍ ባደለኝ የሚባልበት ዘመን ላይ ደረስን በለኛ። ምነው ማንጠግቦሽ ያውም በሕዝብ ዘፈን እንዲህ የምትሆነው?” ብሎ ሲታዘባት ምንም ወዳጄ ቢሆን ቅር አለኝ። እንግዲህ ይኼው ነው።  ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት አገራችን ‘ሁለት ሞት ሙቱ’ ብሎ ሲያዝብን እንኳን በዋልንበት ባልጠረጠርነው ነገር ለመኳረፍ ቅፅበት አይፈጅብንም። እናም እኔ የምላችሁ ዝም ብላችሁ ከላይ ከላይ ስታስቡት፣ ይኼ ‹ጥልቅ ተሃድሶና ዘላቂ ልማት› በኩነኔና በፍረጃ የደመቀ የእያንዳንዳችንን ጓዳ ሳያፀዳ እንዲያው ብቻውን ይዘልቅ ይመስላችኋል? አፌ እንዳመጣለት ባፏጨው ፉጨት ትዳሬ እንደ ቀልድ ብርድ ከገባው፣ የራሴ የሆነ አቋምና ቀኖና አርቅቄ ያፀደቅኩ ቀን ምን ሊፈጠር ነው? ብላችሁ ማሰብ እኮ ነው። አሁን ይኼ ከአገር ጉዳይ ጋር ምኑ ይገናኛል ባዮች ካላችሁ ‘በእኔ ሕይወት ቀዳዳ ብትገባ አገርህን ታያለህ’ ያለውን ደራሲ ፈልጋችሁ ጠይቁት! 

ይልቅ አሁን ተሃድሶና ምናምን ስል አንድ ነገር  ትዝ አለኝ። መቼም እኛ ብዙ ነገር የምናከሽፈው ጠርጥረን ከዚያ በጥርጣሬ ላይ በተመሠረተ መረጃ ነገራ ነገሩን ሁላ በማራከስ ነው።  ምስኪኗ አገራችን መቼም ትከሻዋ ስፋቱ ይኼው አለን። እናም መጠርጠር እያለ እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችው ውስጥ ሆነ ተብሎ የተዘለለ ነገር ይመስለኛል። ምነው እኔ ብቻ ሆንኩ? እናንተስ አይመስላችሁም እንዴ? በቃ ፌስቡክ ካልሆነ ‹ኮሜንትና ላይክ› ነውር ሆኖ ቀረ? ይሁና። ይኼም በልዩነት ይመዝገብልና። ልዩነት ደግሞ ውበት ነው ብሏል። ማ? ሕገ መንግሥቱ። በልዩነት ማመን ከእኔና ከእናንተ ካልጀመረ ከላይ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ዘንድሮ አላዋጣም። ለነገሩ በዚህም እርግጠኛ አይደለንም።

አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ኑሯችን ስንጫወት፣ “እኔ አንዳንዴ ሳስበው እንኳን ስለዕርምጃችን፣ በልተን ስለማደራችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን ቀርቶ ስለድህነታችንም እርግጠኞች ነን ብዬ አላስብም። ዓይናችን ስለማየቱ፣ ጆሯችን ስለመስማቱ፣ በማሰባችን ከእንስሳት የምንለይ የዓላማ ፍጡራን መሆናችንን ማመን ብሎ ነገርማ እርሳው፤” አለኝ። ከሁሉ ደሃ ስለመሆናችንም እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ ትንሽ ቆይቶ (የምሁር ነገር ምን ይታወቃል) ‘ድህነታችን በጥናት ይረጋገጥ’ እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት ሠፈር የሚገኝ ፎቶ ቤትን አንዱ ቢጠይቀኝ፣  “ወደ ቀኝ ታጥፈህ መሰለኝ . . . ” ብዬ መመለስ። በዚህ ዓይነት ‘የረገጥከው አፈር የማን ነው?’ ቢለኝ ‘የእኛ መሰለኝ’ ልለው ይሆን? በቁም አፈሩ ይቅለላቸውና እየተባልን ታዲያ ሌላ ምን ይመጣልኛል!

እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመግዛትና መድኃኒት በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን . . . አቤት ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ለነገሩ አድርገነው ቢሆን ዛሬ የያዝነውን ይዘን እንዳለነው ቢሆን የምንለው ዕድሜ ይመርበት ይክፋበት እርግጠኛ መሆን አንችልም። ነገርኳችሁ እኮ? መራገጥ እንጂ ማረጋገጥ የእኛ አይደለም ስላችሁ? እኔን ካላመናችሁ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። “ላለፈው ዕድሜ ከመቆጨት ለሚመጣው አስብ፤” ይላሉ። ይመስለኛል እኛ ግን የምናስበው ገና ላለፈው ቂም በቀል ማስታወሻነት ስላላቆምናቸው ሐውሎቶች ነው። ካልመሰላችሁ ይችም በልዩነት ትያዝልኝ። ይህቺ የባሻዬ አባባል ከዚህ በፊት  የሰማናት ስለመሰለን የራሳቸው ትሁን አትሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም’ ካላችሁ ደግሞ እንደፈቀደችሁ። የመጠርጠር መብታችሁ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በጎዳናው ተምኔት የተፈቀደ ነው። (መረጋገጡን እንኳ እንጃ) ግን አደራ ባሻዬን በኩረጃ ስማቸውን ስታጠፉ እንዳይሰማና ኢንተርኔቱን በሴራ እንዳታዘጉት።

ለነገሩም በግንቦትም ተዘግቷል። የወር አቆጣጠሬ ቅኔው ካልገባችሁ በቃ ይኼን ፋይል ቶሎ ዝጉት። ደግሞ በኋላ . . . ሆ  የምሬን ነው! እና ባሻ ፍራሽ ማደስ በእሳቸው አልተጀመረም። ስንቱ ብርሁነቱን ንቆ፣ ትኩስ ኃይሉን በመምሰልና በማስመስል አምክኖ በሰው ወርቅ እየደመቀ እያየን፣ አንድ የአገር አንጡራ ሀብት አረጋዊ ያለችውን ቢያሽሞነሙንና ቢጥፍ ነውር አይመስለኝም። አያችሁ ሰው መጠየቅ ያለበት ባለው አቅምና እውቀት ልክ መሆን አለበት። አልተሳሳትኩም መቼም። “ጥሬ እፈጭ ብለሽ ዱቄት አታፍሺ . . . ” ሲባል የሰማሁበት ጊዜ ለምን እንደሆነ እንጃ ሩቅ ይመስለኛል። እናንተ ሰዓቱ ነው ትውስታችን ነው እየፈጠነ ያስቸገረን? በ40 ሳንጨማደድ እንደ ባለ80 ምርኩዝ ማለት አበዛንና እኮ! መቼም ምርኩዝ ለያዘ 40/60 ቅድሚያ ይታደላል ብለን አይመስለኝም። ነገሩን ማለቴ ነው!

ሥራና ነገር እየተምታታብኝ ክረምቱን እንዴት እንደምዘልቀው ጨንቆኛል። እስኪ ወደ አሻሻጥኩት ከባድ መኪና ገጠመኝ ልውሰዳችሁ ደግሞ። ገጠመኝ ላውሳችሁ ይባላል እንጂ ወደ ገጠመኝ ልውሰዳችሁ አይባልም ስትሉ ሰማሁ መሰለኝ። ይኼ ጭቅጭቅ መሆን ያለበት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መሰለኝ። እሱ ውኃ ወቀጣ ነው ካላችሁ ምንም ችግር የለም፣ ከእኔ ጋር መቀንጠስ ነው። መቼም በድለላ ሥራ ጥርስ ስትነቅሉ ትልቁ ወሮታችሁ በከባድ ሚዝን ከሚጫወቱ የኑሮ ተፋላሚዎች ጋር መዋል ነው። ቀላል ሚዛኑማ ጥርስ ሳታበቅሉም ትውላላችሁ። ታዲያ አንድ ቅጥቅጥ የሚገዛ ደንበኛዬ መኪናውን ቶሎ አስፈትሾ ቀልቡን ሰብስቦ ሊዋዋልልኝ አልቻለም። በቅርብ ሠርቶ ስላጠናቀቀው ቤት በየአቅጣጫው እየተደወለለት ያወራል። በቅርቡ ፎርብስ መጽሔት ላይ ልማቱ ያፈራው ቢሊየነር የመባል ዕቅዱን ይነዛል።

በመርከብ አስጭኖ ከአውሮፓና ከቻይና ስለሚያስመጣቸው የቤት ዕቃዎች ይቀዳል። በዕቃ ግዢ ለሚያግዙትና ከዚያው ሆነው ለሚያማክሩት ሰዎች በስልክ ሲመልስ አንድም ርካሽ ዕቃ እንደማይፈልግ “የሰው መሳቂያ አታድርጉኝ” በሚል መኩራራት ይጋበዛል። “ያዝኩ ሲሉ መያዝ፣ አለሁ ሲሉ መቅረትን በሰው እንኳ አይቶ አልተማረም እንዴ ይኼ ሰው?” ብሎ የቅጥቅጡ ባለቤት ቢታዘበው ጓደኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “ምን ይደረግ ገንዘብ እውቀትን የትና የት መርቶት እያየህ ለምን በእሱ ትፈርዳለህ?” ይለዋል። መልሶ ደግሞ በከፊል ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ “እንደ እኛ ያለውን ደካማ ደግሞ መኖሪያ ቤት ፀሐዩ መንግሥታችን በዕጣ ሊያንበሸብሽ ነው። ከሁሉ የገረመኝ ግን የዘንድሮ ጉንጭ አልፋ ዲስኩር በቤት ዕደላና በሌሎች የልማት ሥራዎች አታሞ ስልት መታጠፉ ነው፤” አለኝ። ይኼኔ ጓደኛው ተቀብሎ፣ “ታዲያ በአንዲት መርፌ ላይ ስንት ሺሕ መላዕክት መቆም ይችላሉ?’ ከሚል ውኃ የማይቋጥር ክርክር ለእኛስ ቢሆን ይኼ አይሻለንም?” አለውና ፈገግ አለ። እየበሉ ማልቀስን እንዴት እንደተካንንበት ታያላችሁ? ምን ምርጫ አለ እንዳንል አምስተኛው ዓመት ይታዘበናል ብለን ዝም።

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ዝጌን ዘግቼ ሳበቃ ውኃ ጥም ሊገድለኝ ደረሰ። የባሻዬን ልጅ ደወልኩለትና የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ስንገናኝ ግሮሰሪዋን ከወትሮዋ በተለየ የዋጋ ጭማሪ አድርጋ ታዳሚዎቿን ታስተናግዳለች። የግሮሰሪያችን ባለቤት፣ መቼም ይኼ ሕዝብ በሃይማኖቱና በሚስቱ ነው የሚገኘው ብሎ (እምዬ ምኒልክ ሊያተርፉበት ሳይሆን ሊያተርፉት በማርያምና በሚስቱ እንደመጡበት አልገባውም) ከመጽሐፈ መክበብ ያገኘው መሆኑን በትልቁ ጠቅሶ፣ “ራሱን የማይወድ ሌላውን አይወድም” የሚል ጥቅስ ለጥፏል። ለዚህም የተጋነነ ጭማሪ ስላደረገ በዝምታ የሚታለፍ መስሎታል። ገና አንድ መለኪያ ሳይቀምስ የዋጋ ጭማሪው ያሰከረው የዘወትር ደንበኛው ጥጉን ይዞ፣ “የት ሄደን እንብላ?’ ስንል ዝም የተባልነው አንሶ ‘የት ሄደን እንጠጣ’ በሚልም ከመንግሥት ጋር ልታቀያይመን ነው? ተው የቄሳርን ለቄሳር የእኛን ለእኛ!” ይለዋል።

 “አወይ ዘመን! አወይ መጨካከን! እላያችን ላይ የትርፍ ክብድት እያነሱብን ገላጋይ አጥተን እኮ ክብደት የለሾችን ሆንን ጎበዝ! ሲያዩን አንከብድ ሲቆጥሩን አንሞላ፤” ይላል ሌላው። ገና ከአሁኑ በዚህ ሁኔታ እንደለመደው ተመላልሶ እየጠጣ ፀንቶ ኑሮውን የመርሳቱ ዓላማው አደጋ ላይ እንደወደቀ የተረዳው ደግሞ፣ “እሱ ምን ያድርግ? እስከ ዛሬ የተጎዳው አይበቃም? ስንት ጓደኞቹ ሕንፃ እየሠሩ በክለብ ተቧድነው ክለብ ሲከፍቱ፣ እሱ እስከ ዕለተ ሞቱ ግሮሰሪ ላይ መቅረት አለበት?” ይላል። ከዚህ ሁሉ በላይ በቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ ይገኛሉ ተብለን፣ ዝም ይላሉ ተብለን ልንቄል መታሰባችን ያንገበገበው፣ “ራሱን ቢወድ ነዋ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሲጓዝ አንገቱን የደፋው? የምድር ሕግ አደረግከው የፈጣሪን ቃል እንዳሻህ ለራስህ መጠቀሚያ እያደረግክ የምትለጥፈው? አንሳ ወዲያ!” ሲል አምባጓሮ ያስነሳል። እኔና የባሻዬ ልጅ፣ መለኪያችንን እያጋባን በተመስጦ ውስጥ እንዳለን አንዱ፣ ‹‹ወገኖቼ ሆይ በምድር ላይ ስንኖር ለሥጋችንም ሆነ ለነፍሳችን እኩል ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ መሠረት አንዳችን ለሌላችን ፍቅር መስጠት አለብን፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ሰዎች ነንና እንደ ፈጣሪ ልጆች እንተሳሰብ፡፡ አንዳችን ስንጎዳ ሌላውን ይመመው፡፡ ሌላው ሲደሰት ሌላኛው አይክፋው፡፡ ልባችንን ከፍተን እንተሳሰብ፡፡ ከተሳሰብን ትንሹ ነገር ይትረፈረፋል፤›› ሲለን ‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን› ብለን በሙሉ ልብ ተቀበልነው፡፡ አዎ! እኛ ከተሳሰብን በቂ አይደል? መልካም ሰንበት!  

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት