Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየሲንኪ ጸሎት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ

የሲንኪ ጸሎት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ

ቀን:

ሰሞኑን ሥራውን በይፋ የጀመረው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከተከራዩት የውጭ አገሮች ኩባንያዎች መካከል የሕንድ ይገኝበታል፡፡ በአልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩት ሕንዶች በተከራዩት መጠለያ (ሼድ) ውስጥ ከሥራቸው በተጓዳኝ ለሚከተሉት ሲንኪ (Sinki) ሃይማኖት አምልኮት የሚፈጽሙበት ሥፍራም አዘጋጅተዋል፡፡ ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርኩ በይፋ ወደ ማምረት መግባቱ በተገለጸበት አጋጣሚ የሲንኪ ተከታዮች ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡ ጸሎታቸው ለሥራቸው ስኬት፣ ለማምረቻ መሣሪያዎቻቸው ደኅንነት ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

(ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው)

ኢትዮጵያዊ ነኝ!
በላሊበላ አስቀድሼ፣ ሸህ ሁሴን ባሌ የተገኘሁ፤
በአባ ገዳ ተመራርቄ፣ መካ ላይ እርዝቅ ያገኘሁ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ሳነቴ ላይ ውርጭና ጉም፣ ዳሽን ጫፍ ግግር በረዶ፤
ደሎ መና የአዋራ ጭስ፣ ዳሎል ላይ የእሳት እርጎ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ጎጥ አይበቃኝ – የሀገር ሥፍር፤
ጎሳ አይገልጠኝ – የሰው ሥዕል፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ኢትዮጵያዊ ነኝ!! 
ይርጋለም ያጋጥኳትን ላም፣ ወለጋ ላይ አሰርሬ፤
ትኩስ እንገርዋን የጠጣሁ፣ አክሱም ላይ ጥገት አስሬ፤
ሰሜን ያለብኩትን ወተት፣ በአርሲ ጮጮ የሞላሁ፤
ጋምቤላ ወተቱን ንጬ፣ የሀረሪ ቆንጆ የቀባሁ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ጃውሌ የደንጊያ ዕጣን፣ ከርቤ ከጊንር ቋጥሬ፤
አቦዳይ ጫት ተዘይሬ፤
ከጅማ አባጁፋር መንደር፣ ከአዎል – በረካ ጀባ፤
ሶዶ ዋዳ ተዘፍኖልኝ – ጎዴ ላይ ቃጢራ አድሬ፤
አፋር ላይ በግመል እንገር፣ ምርቃናዬን የሰበርኩ፤
የሀገሬን ባንዲራ፣ ለአፋር ግመል ማተብ ያሰርኩ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን – ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!

በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

* * *

የይሁዳ አንበሳ ሲያገሳ

ለአምስት ዓመት (1928-1933) ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረው የሙሶሎኒ ፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት በተባበረ ተጋድሎ ድል የተመታው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ በምስሉ ‹‹የይሁዳ አንበሳ›› በመባል የሚታወቁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (1923-1967) ሙሶሎኒን በእርግጫ ሲያጎኑት ይታያል፡፡

(ምንጭ ፒንተረስት (Pinterest)

* * *

ቀሚስ ለብሰው ቅሬታ ያሰሙ ወንድ ተማሪዎች

በእንግሊዝ ዴቨን ግዛት ነው፡፡ በግዛቱ ወንድ ተማሪዎች የሚለብሱት ዩኒፎርም ቁምጣ መሆን የለበትም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ሴቶች ዩኒፎርማቸው አጭር ቀሚስ ወይም ሱሪ መሆን ይችላል፡፡

     ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ የሮቲንግዲን ታዳጊ ተማሪዎች ሙቀቱን መቋቋም ስላልቻሉ ቁምጣ እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም፣ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም፡፡ ውሳኔውን የተቃወሙ 30 ያህል ወንዶች፣ በትምህርት ቤቱ ሴት  ተማሪዎች የሚለብሱትን ዩኒፎርም በመልበስ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

     ነጭ ሸሚዝ በከረባትና ጥቁር በነጭ መስመር ያለውን ከጉልበት በላይ የሚውል ቀሚስ ለብሰው ትምህርት ቤት ከመጡት ታዳጊዎች አንዱ፣ ‹‹ቁምጣ መልበስ አይፈቀድልንም፡፡ በሱሪ ደግሞ ሙሉቀን ልውል አልችልም›› ማለቱን፣ ቀሚስ የለበሱትን ወንድ ተማሪዎች የደገፉም ‹‹ወንዶች ቁምጣ መልበስ ይፈቀድላቸው›› በማለት ሲገልጹ እንደነበር ዘገባው ያሳያል፡፡

* * *

ፊት አልባ ዓሳ ተገኘ

ከሰሞኑ የአውስትራሊያ አጥኚዎች እንግዳ ፍጥረት ማግኘታቸውን ላይቭ ሳይንስ ዘግቧል፡፡ የተገኘው ፍጥረት ፊት አልባ ዓሳ ሲሆን፣ የዓይንም ሆነ የፊት ቅርፅ እንደሌለው ተገልጿል፡፡ በምሥራቅ አውስትራሊያ በሚገኝ ባህር ውስጥ የተገኘው ይህ ዓሳ፣ አዲስ ፍጥረት አለመሆኑን፣ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ1800 ጀምሮ ታይቶ እንደማይታወቅ ተመልክቷል፡፡ ዓሳው ከባህሩ በ4000 ሜትር ጥልቀት እንደሚኖር ታውቋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...