Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ረዥም ጊዜ የፈጀው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ምሥረታ ትልቅ ስኬት ነው››

ማንደፍሮ እሸቴ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ከሙዚቃ፣ ከሥነ ጽሑፍ፣ ከፊልም፣ ከቴአትርና ድራማ እንዲሁም ከሥነ ጥበብና ከፎቶግራፍ ባለሙያዎች በተውጣጡ 12 የአመራር አካላት፣ እሑድ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ተመሥርቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣውን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ተከትሎ የተቋቋመው ማኅበር በቀዳሚነት የሮያሊቲ ክፍያን በመሰብሰብና ለባለሙያዎች በማድረስ ሙያተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በምሥረታው ዕለት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር-ኢ/ር) እና በርካታ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ለሙያተኞች እሮሮ እልባት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ በአንፃሩ ስለማኅበሩ መቋቋም፣ ስለነተሱት ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ እሸቴን (ዶ/ር)፣ ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር የምሥረታ ሒደት ምን ይመስል ነበር?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ሒደቱ የተጀመረው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ በ2004 ዓ.ም. ወጥቶ በ2007 ዓ.ም. መሻሻሉን ተከትሎ፣ ማኅበራት ተወካዮቻቸውን በመላክ አደራጅ ኮሚቴ ተመሠረተ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህ አደራጅ ኮሚቴዎች ተገናኝተው የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብና መመሥረቻ ጽሑፍ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ሒደት አልፈውም ወደ ምሥረታ ምዕራፍ መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሮያለቲ ከመሰብሰብና ከማከፋፈል ጋር በተያያዘ ማኅበሩ በዘርፉ የሚኖረው ሚና ምንድነው?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- በመጀመርያ ባለመብቶች መብቶቻቸውን ለማስከበርና ተፈጻሚ ለማደረግ ነው፡፡ በግላቸው ተጠቃሚዎች ዘንድ መድረስ አይችሉም፡፡ የጋራ አስተዳደሩ ሚና ከዚህ ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ ቀጥሎ የሚመጡትን ጥቅሞች ተጠቃሚው ዘንድ በራሱ እየሮጠ መሰብሰብ አይችልም፡፡ ወደ ሙዚቃ ስንመጣ እንደዚሁ ነው፡፡ አንድ ሰው ሙዚቃ ካወጣ በኋላ በሬዲዮ፣ በሬስቶንራት፣ በታክሲ፣ በቴሌቪዥንና በመሳሰሉት ሲቀርብ ለእነዚህ ተጠቃሚዎች በግል መድረስ አይቻልም፡፡ የተሻሻለው አግባብ ባለመብቶች የጋራ የሆነ አስተዳደር ማኅበር ይመሠርታሉ፡፡ ማኅበሩ በመሠረታዊነት ሦስት ተግባራትን ያከናውናል፡፡ አባላትን ይሰበስባል፡፡ የእነሱን መብት ያስተዳድራል፡፡ ሲያስተዳድር መጀመርያ የሚያደርገው ከተጠቃሚዎች ሮያሊቲ መሰብሰብ ነው፡፡ ለተጠቃሚዎች ፈቃድ ከሰጠ በኋላ የሰበሰበውን ገንዘብ ወደ አባላቱ ያሠራጫል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ሥራውን ከሚጀምረው ከዚህ ማኅበር ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ከሳይንስ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባገኘው ፈቃድ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ሊመሠርት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የሁለቱን ማኅበራት አካሄድ ጽሕፈት ቤቱ እንዴት እያስተናገደ ነው?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- የኢትዮጵያ የሙዚቀኞች ማኅበር ከሒደቱ ራሱን አግልሏል፡፡ ባለመብቶች በፈለጉት ማኅበር ውስጥ ገብተው መሥራት ይችላሉ፡፡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአገልግሎት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ያስቀመጠው ሕግና መመርያዎችን ጠብቀው የሚወጡ ማመልከቻዎችን ጽሕፈት ቤቱ ይመለከታል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አግባብ የሚመጡትን ማመልከቻዎች እንመለከታለን፡፡ ዛሬ የተመሠረተው ማኅበርም ገና ለጽሕፈት ቤቱ ማመልከቻ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የመተዳደሪያ ደንቡና የመመሥረቻ ጽሑፉ ፀድቋል፡፡ ዋና ዋና አመራር አባላቱ ተመርጠዋል፡፡ ከዚያ ማመልከቻውን ከቀሪ ጉዳዮች ጋር አያይዘው ለጽሕፈት ቤታችን ያቀርባሉ፡፡ አሟልተው ሲያቀርቡ በጽሕፈት ቤታችን ይታያል፡፡ ስለዚህ ሌላ ማኅበርም የሚመጣ ከሆነ በዚሁ አግባብ እንመለከተዋለን፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በአዋጅ የተቀመጠለት የሥራ ድርሻ ይህ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብና የመመሥረቻ ጽሑፍ በሕጉ መሠረት መቀረፁን ያረጋግጣል፡፡ ሲያረጋግጥ ያፀድቀዋል፡፡ የጋራ አስተዳደር አደራጅ ኮሚቴ ከተመሠረተ ጀምሮ ጽሕፈት ቤቱ በአዋጅ ድጋፍ መስጠት ግዴታው ስለሆነ ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የመተዳደሪያ ደንቡና የመመሥረቻ ጽሑፉ ለጽሕፈት ቤታችን ቀርቦ፣ እኛና ሌሎች አካላት የሰጠነው አስተያየት መካተቱን ተመልክተን የማረጋገጥ ሥራ አከናውነናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ከጉዳዩ ራሱን ያገለለበትን ምክንያት እንዴት ትመለከቱታላችሁ? አለመካተቱ ክፍተት አይፈጥርም ወይ?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ይህንና መሰል ጉዳዮችን በሌላ መድረክ ስለምናይ፣ በዋነኛነት ምሥረታው ላይ ባለንበት ማኅበር ዙሪያ ብንነጋገር የተሻለ ነው፡፡ ያኛውን በሌላ መድረክ ሰፊ ሽፋን ሰጥተነው እንወያያለን፡፡  

ሪፖርተር፡- አዲሱ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች በጋራ የሚያስተናግድ ስለሆነ፣ ሙያዎቹን እንደየባህሪያቸው በተናጠል ከሚያስተናግድ ማኅበር ጋር ሲነፃፀር ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ መሄድ ይችላል?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- የማሻሻያ አዋጁ ቢያንስ ሦስት ዘርፎች በሥሩ አካቶ እንዲመሠርት ያስቀምጣል፡፡ አሁን ያለው ከሦስት ዘርፎች ባለፈ ሌሎች ዘርፎችም ተጨምረው ማለትም አምስት ዘርፎች በአንድ ላይ የመሠረቱት ነው፡፡ ይኼ ፍላጎት ነው፡፡ ባለሙያው ወይም ባለመብቱ ይሻለኛል ያለውን አግባብ ይዞ መጥቷል፡፡ እንደ ጽሕፈት ቤት እኛ የምንመለከተው በትንሹ ማሟላት ያለበትን ማሟላቱን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህንንም ስላሟላ ያስኬደናል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎ አስተያየት ባለው ነባራዊ ሁኔታ የተሻለው አካሄድ ይኼ ነው?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ይህንን በተመለከተ በሚሰጠው አስተያየት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚመሠረቱ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት ቢቻል በከፊል የመንግሥት እንዲሆኑ ይመክራል፡፡ በእኛ አሠራር ከፊል የመንግሥት መሆኑን ዘለን ሙሉ በሙሉ ባለመብቶቹ ማኅበራቸውን ያስተዳድሩ ወደሚለው ተሂዷል፡፡ ስለዚህ የእኛ ሕግ የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ከሚሰጠው  አስተያየት ወጣ ብሎ ለማኅበራቱ የተተወ ጉዳይ ነው፡፡ በተሻሻለው መንገድ ሄደናል፡፡ መንግሥት በከፊል እንዲኖር የሚፈለግበት ምክንያት ሮያሊቲ በመሰብሰብና ሮያሊቲ በማከፋፈል ሒደት ውስጥ የግል ማኅበራት ጉልበት ኖሯቸው ሊሄዱ የሚችሉበት አግባብ ላይ ተግዳሮት ሊገጥማቸው ስለሚችል ነው፡፡ በከፊል የመንግሥት ሲሆን ሰብሮ የማለፍ ጉልበት ይኖረዋል ተብሎ ይመከራል፡፡ ነገር ግን ከዚህ አልፈን ሄደናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ በእያንዳንዱ የሙያ ዘርፍ ውስጥ ካሉ ባለድርሻ አካላት ምን ያህሉን ይወክላል? የማኅበሩ ውክልና ላይ ጥያቄ ያላቸው ባለሙያዎች ስላሉ ነው፡፡

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ በየዘርፉ ያሉ ተዋናዮች መካተታቸውን በየሒደቱ ተረጋግጧል፡፡ መጨረሻ ላይ አባል የሚሆኑት ግለሰቦቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦች ማኅበሩ ተመሥርቶ ወደ ሥራ ሲገባ መጥተው ሥራዎቻቸውን ያስመዘግባሉ፡፡ ይህንን ማኅበር ዕውን ወደ መሆን ያመጡት ማኅበራት ናቸው፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ አባላት ሆነው የሚቀጥሉት ግለሰቦች ናቸው፡፡ ግለሰቦች ደግሞ የማኅበሩ አባል የሚሆኑት ሥራዎቻቸውን ለማኅበሩ ሲያስመዘግቡ ነው፡፡ በዚህ ሒደት አልተካተትኩም የሚል የለም፡፡ ምክንያቱም ግለሰቡ ራሱ ማመልከቻውን አቅርቦ መዝግቡልኝ ይላል፡፡ በዚህ አግባብ መብት ወደ ማስከበር ስለሚመጣ የውክልና ጥያቄው ላይ ምንም ችግር አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- የሮያሊቲ ክፍያ ሲፀድቅ ባለሙያዎች ለዓመታት ያሰሙት ከነበረው ከሥራቸው ተገቢውን ጥቅም ያለማግኝት እሮሮ እንደሚላቀቁ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ መመሥረቱ ሙያተኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ምን ይዞ ይመጣል?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ሮያሊቲ እየሰበሰበ የሚያከፋፍል ተቋም አልነበረም፡፡ የጋራ አስተዳደር ማኅበር የሚያገናኘው ሁለት ተዋንያን ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ባለመብቶቹ የሥራው ባለቤቶች፣ ከዚያ ተጠቃሚው የሚገናኙበት መድረክ ነው፡፡ ይኼ መድረክ በመፈጠሩ ምክንያት በፊት ሲጠበቅ የነበረው ነገር የመወለጃው ወይም ጥቅም የማግኘት ጊዜው ቀርቧል ማለት ነው፡፡ የሚሰበሰበውን የሚያስከፍል ተቋም መጥቷልና፡፡ ከዚያ በፊት ግን የማኅበሩ ትልቁ ሥራ የመሰብሰቢያውን ቀመር በመመርያ ደረጃ ማዘጋጀት ነው፡፡ አዘጋጅቶም እንዲፀድቅለት ለጽሕፈት ቤታችን ማቅረብ አለበት፡፡ ስለዚህ የማከፋፈያ ቀመሩን አዘጋጅቶ ለጽሕፈት ቤታችን ማቅረብ አለበት፡፡ ሁለቱ ወሳኝ ነገሮች ትልቅ ሥራ ይጠይቃሉ፡፡ የአገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል? በእኛ አገርስ የትኛውን ብንከተል የተሻለ ነው? የሚለውን ይዞ ሁለቱን ትልልቅ ሥራዎች ማከናወን አለበት፡፡ ጽሕፈት ቤታችን በዚህ ረገድ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የበርን ስምምነት እንዳለመፈረሟ ከኢትዮጵያ ውጭ የተሠሩ ጥበባዊ ሥራዎች በአገሪቱ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅት የሚኖረው የሮያሊቲ ክፍያ ጉዳይ እንዴት ይደረጋል?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ከበርን ኮንቬንሽን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር ጽሕፈት ቤታችን ኢትዮጵያ ብትፈርማቸው ጠቃሚነት አላቸው በማለት አራት ስምምነቶችን ዓይተን ወደሚቀጥለው ደረጃ አሸጋግረናል፡፡ በደረጃው ታይቶ ጥቅማችንን የሚያስጠብቁ ስምምነቶች በመሆናቸው ከተረጋገጠ፣ በሕግ አግባብ የሚመለከታቸው አካል ያፀድቃቸዋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ እንደ ጽሕፈት ቤት ሥራችንን አከናውነናል፡፡ ጉዳዩም በሒደት ላይ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚሠሩ ሥራዎችና ኢትዮጵያ ውስጥ ተሠርተው ውጭ አገር ጥቅም ላይ የሚውሉ ሥራዎች፣ በሰጥቶ መበቀል መርህ መሠረት ባለሙያውና ባለመብቱ የሮያሊቲ ድርሻውን ሊያገኝ የሚችልበትን ዕድል በቀጣይ ወራት እናረጋግጣለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ስምምነቱ ይፈረማል ብለን እናስባለን፡፡ የመጨረሻውን የሚያፀድቀው ኃላፊነት የተሰጠው አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ከሚተችባቸው ጉዳዮች አንዱ ከንግድ ምልክቶች ጋር ይያያዛል፡፡ የተለያዩ ተቋማት ተመሳሳይ የንግድ ምክልት ተሰጥቷቸው ለውዝግብ ከተዳረጉባቸው አጋጣሚዎች የዋልያ ንግድ ምልክት ይጠቀሳል፡፡ በንግድ ምልክቶች አሰጣጥ ክፍተቶች ለምን ይፈጠራሉ?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ምዝገባ የሚካሄደው አመልካች መጥቶ ይህንን መዝግቡልኝ ሲል ነው፡፡ ተመሳሳይ የሚለው እንደ ዕይታ ይለያያል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ተመሳሳይ አይደለም የሚለውን ነገር ሌሎች ወገኖች ተመሳሳይ ናቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሒደቱ አልፎ አቤቱታ ሲቀርብበት እዚያው ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች እንደገና የሚጣሩበት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ  አለ፡፡ የዋልያም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በዚህ ሒደት ያለፉ ናቸው፡፡ ክርክር መነሳቱ የተለመደ ነው፡፡ ክርክሩን በአግባቡ ለመቋጨት ተከራካሪ ወገኖች የሚያቀርቧቸው ክርክሮች ሕጋዊና ሞራላዊ ናቸው የሚለው ለጽሕፈት ቤቱ ጉድለት ሳይሆን፣ ተከራካሪዎች በአንድም በሌላም የሚያነሷቸው ጉዳዮች ናቸው ብለን እንይዛቸዋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ስህተቶቹ የሚፈጠሩት ከባለሙያዎች የብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ ነው?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ጽሕፈት ቤቱ የሚያናውናቸው ሥራዎች በአጠቃላይ ወደ ላይ ቀርበው መታየታቸው አይቀርም፡፡ በየደረጃው አንድ ባለሙያ የሚመስለውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አንድ ባለሙያ የሰጠው ውሳኔ እዚያው ጽሕፈት ቤቱ ውስጥ መታየት ይችላል፡፡ የአቅም ክፍተት ወይም ሕጉን በአግባቡ አለማንበብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስህተቱ ከተፈጠረ በኋላ የማረሚያው ሥርዓት እስኪደርስ፣ ሥርዓቱም ተንቀሳቅሶ ውጤት እስኪወጣ ድረስ ስህተት መፈጠሩን የከፋ ነገር አድርገን ባናየው፡፡ ጽሕፈት ቤታችን ይህንን ሕግ ለማስተዳደር ገና ታዳጊ ነው፡፡ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የንግድ ምልክት መመዝገብ ከጀመረ አሥር ዓመቱ ነው፡፡ ስንቶቹ እንደዚህ ዓይነት ተግዳሮች ገጥሟቸዋል? ብለን ብናይ ጥቂት ናቸው፡፡ የማይጮህላቸው ነገር ግን ትክክል የሆኑ በርካታ ውሳኔዎች አሉ፡፡ እነሱ ጎልተው አይሰሙም፡፡ ጎልቶ የሚወጣው አንዱ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ጎልተው አልተደመጡም የሚሏቸውን ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና የሚባሉ ጉዳዮች ቢገልጹልን?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ከተከናወኑ ሥራዎች አንደኛው ለጽሕፈት ቤቱ የሚቀርቡ በርካታ አቤቱታዎችን ለመቀነስ፣ ክርክሮች በግልጽ ችሎት ባለጉዳዮች ባሉበት እንዲዳኙ አድርጓል፡፡ ጽሕፈት ቤታችን የመልካም አስተዳደር ሥርዓትን ከማስፈን አኳያ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ረዥም ጊዜ የፈጀው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ምሥረታ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ትልቁ ብለን የምንጠቅሰው ይኼንን ነው፡፡ በፈጠራ ሥራ ረገድ ደግሞ ትልቁ ነገር በአገራችን በፈጠራ ሥራ ሊሰማሩ የሚችሉ ተማሪዎች፣ በምርምር ሥራ ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች የወቅቱ ሳይንስ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ ሰነዶች ሰብስቦ በማቅረብ ጽሕፈት ቤታችን በርካታ ሥራዎች አከናውኗል፡፡ የፓተንት ሰነዶችን በመሰብሰብና በማደራጀት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት ማድረስ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገራችን ከመካከለኛ ገቢ ወደ ከፍተኛ  ገቢ እንድትሸጋገር፣ ቴክኖሎጂ ከመኮረጅ ቴክኖሎጂ ወደ መፍጠር ደረጃ መሸጋገር ግድ ይላል፡፡ ቴክኖሎጂ ማዘጋጀት ብቃት ያለው ኃይል ለመፍጠር የሚቻለው ደግሞ መጀመሪያ የቴክኖሎጂ መረጃ በማግኘት ስለሆነ፣ ይህንን መረጃ የማቅረብ ሥራ አከናውነናል፡፡ ከብዙዎቹ በጥቂቶቹ እነዚህን ይመስላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አዕምሯዊ ንብረታቸውን በጽሕፈት ቤቱ በማስመዘገብ ሒደት ላይ ያሉ መረጃቸው ከጽሕፈት ቤቱ በአንድም በሌላም መንገድ ሾልኮ ወጥቶባቸው የንብረቱ ባለቤት ባለመሆናቸው፣ ያላግባብ መጠቀሚያ እንደሆኑ ቅሬታ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ተዓማኒነት ረገድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽዎ ምንድነው?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሚሰጥበት ምክንያት አንድን ጉዳይ ታሳቢ አድርጎ ነው፡፡ የፈጠራ ሥራ ባለቤት ነኝ የሚል ሰው መረጃውን ለሰፊው ሕዝብ ክፍት መሆን ይችላል በማለት እያደረገ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የፈጠራ ሥራውን ለሕዝብ ክፍት አድርጎ፣ ለፈጠራ ሥራ ባለሙያ ወይም ባለቤቱ የሞኖፖሊ መብት ይሰጣል፡፡ እንደ መንግሥት የሞኖፖሊ መብት በመስጠት፣ እንደ ፈጠራ ሥራ ባለቤት መረጃውን ክፍት ማድረግ ነው፡፡ ፈጠርኩ የሚለው ሰው እንዲታወቅ ካልፈለገ ያለው አማራጭ እኛ ዘንድ አለመምጣት ነው፡፡ እኛ ጋ ከመጣ ማንም ሰው ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ መረጃውን የማግኘት መብት አለው፡፡ ይኼ ዓለም አቀፍ አካሄድ ነው፡፡ ይህ ክስ አግባብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጽሕፈት ቤታችን የመጣ መረጃ ሾልኮ ወጥቷል ብለን ብንገምት እንኳ፣ መረጃው መጀመርያ የመጣበት ቀን ነው ገዥ የሚሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ የፈጠራ ሥራ ተብሎ የሚመጣው በሙሉ ያኛውን መከልከል አይችልም፡፡ አያስቆመውም፡፡ የሞኖፖሊ መብት የሚሰጠው መጀመርያ መጥቶ ያስመዘገበው ሰው ነው፡፡

ለምሳሌ በቅርቡ በሚስጥር እንዲጠበቅልን እንፈልጋለን ብለው ባለሙያዎች ወደ ጽሕፈት ቤታችን መጥተው ነበር፡፡ በሚስጥር እንዲጠበቅላቸው ከፈለጋችሁ እኛ ጋ መምጣት አትችሉም ብለን ሕጉን አሳየናቸው፡፡ ጥበቃ እንዲያገኙ ሲፈልጉ መረጃው ሕጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ለጠየቀው ሰው መስጠት ይቻላል፡፡ ጥበቃ ይሰጠኝ ብሎ የቀረበው ሰው የሕዝብ ሰነድ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ የሚፈለገው በዚያ ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ቀጣይ የማሻሻያ ሥራዎች እንዲከናወኑ ነው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደገው በዚህ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ባለሙያው ያገኘውን ነገር ካሳወቀ በኋላ ለ20 ዓመታት በሞኖፖሊ ብቻውን ለመጠቀም መብት ያገኛል፡፡ ነገር ግን ሌሎች ምርምር እያካሄዱበት በእሱ ላይ ተመሥርተው ቀጣይ የፈጠራ ሥራ ማከናወናቸው ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ነው እንጂ፣ የባለቤትነት መብት አይሰጣቸውም፡፡   

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር የአመራር አባላት በቀጣይ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ምን ይዘው መምጣት ይጠበቅባቸዋል?

ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ከዚህ ቀጥሎ ማኅበሩ ማመልከቻ ይዞ ይቀርባል፡፡ ዛሬ [ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም.] የፀደቁትን ሰነዶችና የአባላት ሥራ ዝርዝር ያቀርባል፡፡ አባላቱ አሉን የሚሏቸውን የሥራ ዝርዝሮች ያቀርባሉ፡፡ ጥቂት የዶክመንተሪ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ካለቁ በኋላ ፈቃድ ወደ መስጠት እንገባለን፡፡ እስከ ዛሬ ስንደግፋቸው ነው የቆየነው፡፡ ከዚህ በኋላ የምንሠራው የመቆጣጠር ሥራ ነው እንጂ፣ በውስጡ ሌላ ድርሻ የለንም፡፡ በሁለት እግራቸው ለማቆም ነው እስከ ዛሬ ስንሠራ የነበረው፡፡ በሁለት እግራቸው ከቆሙ በኋላ ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ የአባላትን መብት የሚያስተዳድሩ ሰዎች ስለሆኑ በአግባቡ እያስተዳደሩ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን የሚያጣጣው ሦስተኛው ወገን ጽሕፈት ቤቱ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በኋላ ወደ ቁጥጥር ሥራው እያዘነበለ ይመጣል፡፡ የቁጥጥር ሥራውን ሙሉ በሙሉ ከመጀመሩ በፊት፣ ሮያሊቲ መሰብሰበና የማከፋፈያውን ቀመር በድጋፍ አብሮ የመሥራት ግዴታ ይኖርበታል፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች