Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉየባሕረ ሰላጤው አገሮች ትርምስና የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት አሠላለፍ በኢትዮ ኤርትራ ፖለቲካ ላይ...

  የባሕረ ሰላጤው አገሮች ትርምስና የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት አሠላለፍ በኢትዮ ኤርትራ ፖለቲካ ላይ የሚኖረው ሚና

  ቀን:

  በያየሰው ሽመልስ

  የዓረቦቹ ፍቅር ንፋስ ገብቶት እያወዛገበ ነው፡፡ የተለያዩ አገሮችም በሁለት ጎራ  በተከፈለው ኳታር በአንድ ወገን፣ ሳዑዲ የምትመራው ቡድን በሌላ በኩል የዓረቡ ዓለም ላይ እየተሠለፉና እንዲሠለፉ እየተጠየቁ ናቸው፡፡ በዚህ ሠልፍ ውስጥ እንዲገቡ ከሚፈለጉት አገሮች መካከል የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የዓረቦቹ ፍላጎት ይህ ከሆነ ታዲያ የቀጣናው አገሮች ፍላጎት የትኛው ነው? ኳታር ወይስ እነ ሳዑዲ? ለዚህ የሚዳርጋቸው ገፊ ምክንያትስ ምንድነው? እነዚህ የአሠላለፉን ቅርጽ የሚወስኑ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

  ነባሩ የዓረቦቹና የምሥራቅ አፍሪካ ዳራ

  በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የመካከለኛው ምሥራቅን ፖለቲካ ከቀየሩ አጋጣሚዎች መካከል ከእስራኤል መመሥረት በተጨማሪ የዓረቡ ዓለም ነዳጅ ማግኘት አንዱ ነው፡፡ የዘይት ዶላርም ነገሥታቱን አፈርጥሟቸው ፖለቲካዊ ልዕልና የሚስገኝላቸውን እንቅስቃሴ ለማድረግ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሯሯጡ፡፡ ጋዜጠኛው ፋሪድ ዘካሪያ ‹‹The Future of Freedom Illiberal Democracy at Home and Abroad›› በሚለው መጽሐፉ፣ የሺዓና የሱኒ እስልምናን ፖለቲካ አድርጎ ለመንቀሳቀስ ነዳጅ የወለደው ገንዘብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ይተነትናል፡፡

  ይህ መሯሯጣቸው ካዳረሳቸው አካባቢዎች አንዱ ምሥራቅ አፍሪካ ነው፡፡ በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ21ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በቀጣናው የተከሰቱ አያሌ ሁነቶች የዓረቦቹ እጅ እንዲበረታ አድርጎታል፡፡

  የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት፣ የሶማሊያ የእርስ በርስ ግጭት (በኋላም የአልሸባብ መምጣት)፣ የኤርትራና የየመን ጦርነት፣ የኤርትራና የጂቡቲ ግጭት፣ የኤርትራና በየመን ውጊያ፣ የሃኒሽ ደሴቶች ፖለቲካ፣ የወሃቢዝም መስፋፋትና የሃይማኖት አክራሪነት ማቆጥቆጥ፣ የግብፅና የሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ የሀላየብ ደሴት ጉዳይ፣ የየመን የእርስ በርስ ጦርነት ሳዑዲ መራሹ ቡድን ኳታርንና ኤርትራን ሳይቀር አስልፎ ኤደን መሥፈሩ… ዓረቦቹ በተለይም ኳታርና ሳዑዲ ረብጣ ዶላራቸውን እንዲያፈሱና ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽሙ አካላትን እንዲያስተባብሩ አስገድዷቸዋል፡፡ የዲፕሎማሲ ገበያውንም በገንዘብ ሊሸምቱት ሲጣደፉ ኖረዋል፡፡ ወፍራም ገንዘብ ያፈሰሱበት ፖለቲካም፣ ዛሬ በዚህ ለሁለት በተከፈለው የጭንቅ ወቅት ወሮታውን እንዲከፍላቸው ይሻሉ፡፡ ለዚህም የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማግኘት በየበኩላቸው ገንዘብን መሣሪያ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ እናስ በዚህ ኳታርን ለማግለል በተከፈተው ዘመቻ ላይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ማንን ደገፉ/ከማን ጎን ቆሙ? ከነሳዑዲ ወገን ወይስ ከተገለለችው ኳታር?

  ሶማሊያ

  በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አጋዥነትና በራሳቸው በአገሬው ሰዎች ፊታውራሪነት የፈራረሰችው ሶማሊያ ታገግም ዘንድ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጦር አዝምተዋል፡፡ የቀጣናው አገሮች ደም ገብረው ሰላም ለማምጣት በሚጣደፉበት በዚህ ወቅት፣ የኳታርና የሳዑዲ መንግሥታት ያዘመቱት ታጣቂ ዶላር ነው፡፡ ዶላሩ ሁለት ሥራ ይሠራል፡፡ በአንድ በኩል በደቀቀችው አገር መሠረተ ልማት ሲገነባ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የራሳቸውን ፍላጎት የሳዑዲንና የኳታርን የሚያሟሉ የጎሳ ቡድኖችን ያስታጥቃል፡፡

      አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ ፋርማጆ ወደ ሥልጣን በመጡበት ‘ምርጫም’ የኳታርና የሳዑዲ ዶላር ሲከሰከስ መክረሙ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በእርግጥ የዓረቦቹ ጥረት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት (መሐመድ ሐሰን) ማስመረጥ እንደነበር ውስጥ ውስጡን ሲነገር ከርሟል፡፡ ይኼኛው ባይሳካም ግን ተመረጡ የተባሉትን ፕሬዚዳንት ቀልብ መሳባቸው አልቀረም፡፡ ለዚያም ይመስላል መሐመድ ፋርማጆ ‹ምርጫውን› ባሸነፉ ማግሥት የመጀመሪያ የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በሳዑዲ ማድረጋቸው፡፡ ኳታር በሶማሊያ የሚገኙ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት በሚል ከምትሰጠው ገንዘብ በተጨማሪ፣ የእርሷን ጥቅም ለሚያስከብሩ የጎሳ ቡድኖችም ጠቀም ያለ ዶላር እየደጎመች አገሪቱን በማተራመስ ረገድ የራሷን ሚና ተወጥታለች፡፡

  በሁለቱም ቢላ በሳዑዲም በኳታርም ስትበላ የነበረችው ሶማሊያ አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡ ከእነ ሳዑዲ ወገን የ80 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ቀርቦላት ኳታርን እንድታባርር ብትጠየቅም ሳታደርገው ቀርታለች፡፡ ይባስ ብሎም የባሕረ ሰላጤውን አገሮች የአየር ክልል እንዳይጠቀም የተከለከለው የኳታር አየር መንገድ፣ በሶማሊያ ሰማይ ላይ እንዲበር ከመሐመድ ፋርማጆ መንግሥት ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ደግሞ ለእነ ሳዑዲ ዓረቢያ ምቾት የሚነሳ ነው፡፡

  እስካሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ በመነጋገር ይፈታ ዘንድ የሶማሊያ ፍላጎት መሆኑን፣ ይህ እንዲሆንም እስከ ማሸማገል የሚደርስ ሚና እንደምትወጣ ተናግራለች፡፡ ሆኖም ከድርጊቷና ከአጠቃላይ እንቅስቃሴዋ ግን ለኳታር ያደላች ትመስላለች፡፡ አየር ክልሏን መፍቀዷ፣ ከእነ ሳዑዲ የቀረበላትን ጉርሻ አልቀበልም ማለቷ ወዘተ ወገንተኝነቷን የሚያመለክት ይመስላል፡፡

  ሶማሊያ ይህንን ያደረገችበት ምክንያት ይፋ አላደረገችም፡፡ የሚጠረጠር ሀቅ ግን አለ፡፡ የሳዑዲ ወዳጅ የሆነችውና በኳታር ላይ አድማ ከመቱት አገሮች አንዷ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ነች፡፡ ይቺ አገር የሶማሌላንድን በርበራ ወደብ ከሞቃዲሾው አስተዳደር ዕውቅና ውጭ የማስፋፊያ ግንባታ አድርጋለት ለ30 ዓመታት በሊዝ ተከራይታዋለች፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ከፑንትላንድም ሆነ ከሶማሌላንድ ጋር የሚደረግ የውጭ ግንኙነት በእኔ በኩል ማለፍ አለበት ይላል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ግን ያንን አላደረገችም፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥቷን አበሳጭቷል፣ እስከ ፍርድ ቤት ሄጄም እሟገታለሁ ብሏል፡፡ እናም ከኳታር ጎን ለመቆም የሚያስገድደው ምክንያት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከእነ ሳዑዲ ወገን መሆኗ ሊሆን ይችላል፡፡

  ሱዳን

  የአልበሽር አገር የመካከለኛው ምሥራቅ ሙስሊሞችን ባሰባሰበው የዓረብ ሊግ ውስጥ አባል ነች፡፡ በዛ ያሉቱ የሊጉ አባላት ወደ የመን ጦር አዝምተው ከሁቲዎች ጋር ሲፋለሙም ወታደሮች ልካ ከእነ ሳዑዲ ጎን ቆማለች፡፡ በእርግጥ በዚህ ዘመቻ ላይ ኳታርም ጦር ልካለች፡፡ ከዚያም በዘለለ ጠቀም ያለ የዲፕሎማሲ ጉርሻ ስታገኝ የቆየችው ከዚሁ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ነው፡፡

  አልበሽር በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላ ወደ 38 አገሮች ሄደው በሰላም ሲመለሱ አብዛኛውን ጊዜ የተጓዙት በዚሁ በዓረቡ ዓለም ነው፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል የአልበሽር ክስ እንዲቋረጥ፣ አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለችው ማዕቀብ እንዲነሳ… ኳታርና ሳዑዲ በየፊናቸው እየጣሩ ስለመሆኑ ሲዘገብ ከርሟል፡፡ ወታደራዊ ሽርክናቸውም ከላይ እንደተገለጸው በየመን ጦር እስከማዝመት የደረሰ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ (Military Cooperation) በተለይ ከሳዑዲ ጋር የጀመሩት ወዳጅነት ይበልጣል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በሰሜናዊ ሱዳን የሁለቱ አየር ኃይሎች የጦር ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ሱዳን ወደ የመንም ጦር ያዘመተችው በሳዑዲ ጥሪ እንደነበር እሙን ነው፡፡

  ይህ ሁሉ እያለ ግን የሱዳን ስም ከኳታር ጋር ተዳምሮ እየተነሳ ነው፡፡ አንዳንድ የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደሚሉት በዚህ ምርጫን ማስተካከል ግድ በሆነበት አጋጣሚ፣ ዶሃና ካርቱም ሊዋደዱ የሚገደዱበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህም በእነ ሳዑዲ ወገን የግብፅ መኖር ነው፡፡ ግብፅና ሱዳን በተደጋጋሚ የሚወዛገቡ አገሮች ናቸው፡፡ ለወትሮው የሃላየብ ደሴት ታጋጫቸው ነበር፡፡ በዚህ ፖለቲካ ምክንያት ግብፅ የዳርፉር አማፅያንን ታስጣቅብኛለች ስትል ሱዳን አቤቱታ እያሰማች ኖራለች፡፡ ይህ ሳይዘጋ መገንባት የጀመረውን የህዳሴ ግድብ ሱዳን በመርህ ደረጃ ደግፋ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ፣ የሁለቱን አገሮች የዲፕሎማሲ ሽኩቻ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሱዳን አምርተው ‹የሱዳን ፒራሚዶችን› መጎብኘታቸውና ከዚያ በኋላም የሰጡት አስተያየት የግብፅ ልሂቃንን አበሳጭቶ ነበር፡፡

  ይህ ሁሉ ችግር ሳይፈታ ነው እንግዲህ የባሕረ ሰላጤው አገሮች ወደ ክፍፍል የገቡት፡፡ በክፍፍሉ ውስጥ ግብፅ ከሳዑዲ ወገን ሆና ብቅ አለች፡፡ ይህ ሱዳንን ከኳታር ወገን የሚያሠልፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ከጥቂት በላይ የሆኑ ጸሐፊያንም ያንን ይላሉ፡፡ ሱዳኖች በይፋ የሰጡት መግለጫ ግን መሀል ሰፋሪ መሆናቸውን የሚያሳይና ዲፕሎማሲያዊ ቃላት የበዙበት ነው፡፡

  ጂቡቲና ኤርትራ

  እነዚህ አገሮች የዓረብ ሊግ አባላት መደበኛና ታዛቢ አባል ናቸው፡፡ ዓረቦቹ በተለይም ሳዑዲና ኳታር በእነዚህ አገሮች ወታደራዊ ሠፈር ገንብተዋል/የመገንባት ዕቅድ አላቸው፡፡ በአስመራና በጂቡቲ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ሲያይልና ወደ ጦር መማዘዝ ሲገባ ቀድመው አለሁ የሚሉት እነዚሁ ዓረባዊያኑ ናቸው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2008  ኤርትራና ጂቡቲ በራስ ዱሜራ ተራራና ደሴት እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ኳታር 450 ሠራዊት የያዘ ‹ሰላም አስከባሪ› ወደ ቦታው ስትልክ የቀደማት የለም፡፡ ከዚያም በኋላ በጦርነቱ ወቅት የተማረኩ እስረኞችን ለማለዋወጥ ስትጥር ቆታለች፡፡ በጥቂቱ ተሳክቶላት እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2016 የተወሰኑ የጂቡቲ እስረኞችን ከኤርትራ አስፈትታለች፡፡ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት ‹‹Understanding Eritrea›› በሚለው መጽሐፉ እንደሚተርከው፣ እ.ኤ.አ በ1996፣ በ1999፣ በ2008 ኤርትራ ጂቡቲን ስትወር ብዙ ወታደሮችን ገድላለች፣ አቁስላለች፣ ማርካለች፡፡ በዚህ የግጭት ዘመን የሁለቱም አገሮች የጦር መሣሪያ ምንጭ ዓረቦች ነበሩ፡፡ እስረኛ በማለዋወጡና በማስፈታቱ ሒደት ውስጥም የእነዚሁ አገሮች ሚና ወፍራም ነበር፣ በተለይም የኳታር፡፡

  ሰሞኑን የዓረቡ ዓለም ለሁለት ሲሰነጠቅ ግን ሁለቱም አገሮች ጂቡቲና ኤርትራ ከእነ ሳዑዲ ወገን ሆነዋል፡፡ ይኼ ውሳኔያቸው ለኳታር ሰላም የሚሰጥ ስላልሆነ፣ አሥር ዓመታትን ለተጠጋ ጊዜ በራስ ዱሜራ ተራራ ላይ አሥፍራው የነበረውን ጦር አስወጣች፡፡ ኤርትራም የዶሃ ወታደሮች እግር እንደወጣ ጦሯን በአወዛጋቢዋ ራስ ዱሜራ ላይ አሰፈረች፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከልም ሌላ ውዝግብ ተጨማሪ ውጥረት ነገሠ፡፡ ጥያቄው ‹‹ሁለት የማይዋደዱ አገሮች፣ የሁለቱም ‹ወዳጅ› የነበረችውን ኳታርን ስለምን ‹ከዷት›? ውግንናቸውስ ስለምን ከጠላቶቿ በኩል ሆነ?›› የሚለው ነው፡፡

  ጂቡቲ፣ ኳታርና ሳዑዲ

  ጂቡቲ ከኳታር ጋር ያላት ወዳጅነት እየቀዘቀዘ ስለመምጣቱ በአደባባይ ተነግሮ አያውቅም፡፡ ሆኖም ከኤርትራ ጋር ለማሸማገል ኳታር የምታደርገው ጥረት ጂቡቲን እንዳላስደሰተ ይገመታል፡፡ ወዲህ ደግሞ በተያዘው ዓመት ሳዑዲ ዓረቢያ በጂቡቲ የጦር ሠፈር ለመገንባት ከእስማኤል ጊሌህ መንግሥት ይሁንታ ማግኘቷ ኳታርን ያስደስታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም አገሮች ኳታርና ሳዑዲ በአካባቢው ወታደራዊ፣ ሃይማኖታዊና ዲፕሎማሲያዊ መስፋፋት ዓመል አድርገውት እየሠሩበት ነውና፡፡ እናም በጂቡቲ ሽኩቻ ቢያደርጉ የሚገርም አይሆንም፡፡ ጂቡቲ ግን ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር አስቀድማ ወታደራዊ ስምምነት አድርጋ ስለነበር መጨረሻ ላይ ውግንናዋን ከኳታር በኩል አደረገች፡፡

  ኤርትራ፣ ኳታር፣ ሳዑዲና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ

  እ.ኤ.አ በሚያዚያ በ2015 ከሳዑዲ ዓረቢያና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የተላከ ሁለት ልዑክ ወደ አስመራ ቤተ መንግሥት አቀና፡፡ እነዚህ አገሮች ከዚያ በፊት ባሉት ዓመታት ከኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ጋር አለመግባባት ውስጥ ነበሩ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በዳህላክ ደሴት ላይ የኢራን ሠራዊት ይሠፍር ዘንድ ኤርትራ በመፍቀዷ ነው፡፡ ኢራኖችም ከኤርትራ እየተነሱ በሚያደርጉት ድጋፍ ሁቲዎች ሰንዓን (የየመንን ዋና ከተማ) ተቆጣጠሩ፡፡ አካሄዱ ያልጣማቸው እነ ሳዑዲም ወፍራም ጉርሻ ይዘው አስመራ ገቡ፡፡ ወዲ አፎምም አዎንታዊ ምላሽ ሰጧቸው፡፡ በኤርትራና በኢራን ድጋፍ ሰንዓን የተቆጣጠሩት ሁቲዎችም፣ እንደገና ከኤርትራ በሚነሱ ሚጎች ይደበደቡ ዘንድ የአስመራው መንግሥት ፈቀደ፡፡

  ማርቲን ፕላውት ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ ‹‹ኢንዲያን ኦሽን ኒውስሌተር›› የተባለውን የደኅንነት ጋዜጣ ጠቅሶ እንደጻፈው፣ የሚያዚያ 2015ቱ የሳዑዲና የኤምሬስ ልዑክ ወደ አስመራ ይዞት የመጣው ጉርሻ ነዳጅ በነፃ ማግኘት፣ የአስመራ አውሮፕላን ጣቢያን በዘመናዊ መንገድ መገንባት፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት…ወዘተ የሚል ነበር፡፡ አቶ ኢሳያስም፣‹‹እንዲያማ ከሆነ…›› ብለው 400 እግረኛ ሠራዊት የመን ድረስ በሞቅታ ላኩ፡፡ በእርሳቸው እገዛ ሰንዓ የገቡትን ሁቲዎችም መውጋት ቀጠሉ፡፡ እስካሁንም ጦራቸውን ስለማስወጣታቸው የተባለ ነገር የለም፡፡ ለነገሩ ማስገባታቸውንም አስተባብለዋል፡፡ የጉዳዩ እውነትነት ግን በመንግሥታቱ ድርጅት አጣሪ ቡድን ተረጋግጧል፡፡

  ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ከኢራን ጋር ተወዳጅቶ፣ ለሰሞነኛ ጥቅም ብሎ ከእነ ሳዑዲ ጋር ሆድና ጀርባ የነበረው የኤርትራ መንግሥት አሁን ደግሞ በወቅታዊው የባሕረ ሰላጤው ፖለቲካ ምክንያት ኳታርን ፊት ነስቷል፡፡ ውግንናውንም ከእነ ሳዑዲ ወገን አድርጓል፡፡ በእርግጥ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ መርህ በዘላቂ ፍላጎቶች ላይ የተመሠረተ  (Strategic) ሳይሆን በጊዜያዊ ጥቅሞች ላይ የተንጠለጠለ (Tactical) ቢሆንም፣ ሰሞኑን  ለምን እነ ሳዑዲን መረጠ ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡

  ኤርትራ ከጂቡቲ ጋር ዕርቅ ታወርድ ዘንድ ኳታር ስታሸማግል መቆየቷ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አስመራዎች የዶሃው መንግሥት ገለልተኛ ሆኖ እያደራደረን ነው ብለው አያምኑም፡፡ ይህ ጥርጣሬያቸው ባለበት ወቅት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ውጊያ ባደረጉበት ዘመን ሳይቀር ትጥቅና ስንቅ ትሠፍርላቸው የነበረችው ኳታር ድንገት አየር መንገዷ ወደ አስመራ እንዳይበር አደረገች፡፡ ከዚያ ይልቅ ወደ ጂቡቲና አዲስ አበባ የሚያደርገውን የበረራ ብዛት እንዲጨምር ተደረገ፡፡ ይህ ኳታር ገለልተኛ አይደለችም ለሚሉት የኤርትራ ሹማምንት ተጨባጭ ማስረጃ ሆኖ ቀረበ፡፡ በመጨረሻም የባሕረ ሰላጤው አገሮች ኳታርን ማግለል ሲጀምሩ ኤርትራ ተቀላቀለች፡፡ ይህ ኤርትራ እነ ሳዑዲን የደገፈችበት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሳዑዲና ኤምሬትስ ከላይ ከተጠቀሰውና ለኤርትራ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሌላ ገንዘብ ሰጥተዋታል የሚለው መላምት ነው፡፡ ለሶማሊያ 80 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንልቀቅ ያሉት እነ ሳዑዲ፣ ለኤርትራ ይህንን ከማድረግ የሚቆጠቡበት ምክንያት የለም፡፡

  ኢትዮጵያ፣ ኳታርና እነ ሳዑዲ

  በሰሞነኛው ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ኢትዮጵያ መሀል ሰፋሪ ሆና ችግሩ በሰላም ይፈታ የምትል መሆኗን አሳውቃለች፡፡ ‹‹ችግራችሁ ይፈታ ዘንድ የምችለውን አደርጋለሁ›› የሚለውን መግለጫዋን ባወጣች በሳምንቱ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ኩዌት ልካ ‹‹ይኼንን ነገር እናሸማግል›› ብላለች፡፡ ኩዌት እስካሁን በእሰጥ አገባው ውስጥ እጇን አላስገባችም መባሏ ተሰምቷል፡፡ ይህ በእርግጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባህርይ አንፃር የሚገመት ውሳኔ ነው፡፡

  የኢትዮጵያና የባሕረ ሰላጤው መንግሥታት ፍቅር እንደ ዘንድሮ አይሎ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ የሳዑዲ ሹማምንት ህዳሴ ግድብ ድረስ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለት ጊዜ፣ እንዲሁም አሚሩም አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ሲወያዩ ከርመዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንትም ወደ ሪያድና ዶሃ በተደጋጋሚ ተመላልሰዋል፡፡ በመጨረሻም በሳዑዲ መራሹና በኳታር መካከል አለመግባባት ሲከሰት ‹‹ሁለታችሁም ወዳጆቼ ናችሁ›› ብላ የምትቆምለት ወገን እንደሌለ ግልጽ አደረገች፡፡ ይህ ገለልተኝነቷ እስከምን ድረስ ይዘልቃል የሚለው ጥያቄ ግን መነሳቱ አይቀርም፡፡

  የኢትዮጵያን ገለልተኝነት የሚጠራጠሩ ሰዎች ምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡ ይኼውም የባሕረ ሰላጤውን ቀውስ ተከትሎ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ለአንዱ ወገን እንድትቆም ሊያስገድዳት ይችላል የሚለው ነው፡፡ የአገሪቱ 90 በመቶ ገቢና ወጪ ንግድ የሚካሄድባት ጂቡቲ፣ የኢትዮጵያ ጠላት በሆነ መንግሥት ተወረርኩ ስትል ሥጋት ይፈጥራል፡፡ ሁለቱን አገሮች የሚያጋጨው ራስ ዱሜራ ከፍተኛ ሸቀጥ ለሚዘዋወርባት ባብኤል መንደብ በቅርብ ርቀት ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ዓይንና ጆሮ በሆነው የጂቡቲ ወደብ አቅራቢያ የተከሰተው የኤርትራና የጂቡቲ ውጥረት አሥጊ መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ነገሩ ከከፋ እስከ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የሚደርስ ዕርምጃ እንድትወስድ የሚያስገድዳት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡

  ይህን ብታደርግ ደግሞ የምትጋጨው ከኤርትራ ብቻ አይሆንም፣ ከእነ ሳዑዲ ጋርም እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ወዳጅ አገር ተወረረ ብላ ጦር ብትልክ፣ አስቀድማ ከኤርትራ ጋር ፍቅር ከመሠረተችው ሳዑዲ ዓረቢያና ወዳጆቿ እዚህ ቡድን ውስጥ ግብፅም መኖሯን ልብ ይሏል ጋር ሊያጋጫት ይችላል፡፡ ለዚያም ይመስላል ሰሞኑን ጂቡቲ ተወረርኩ ብላ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቤቱታ ስታሰማ፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተልኩት ነው ከማለት አልፋ ስታወግዝ ያልተሰማችው፡፡

  ኳታር ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስማማት እየጣረች ያለች አገር ስለመሆኗ በተደጋጋሚ ሲወራ የከረመ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን በተፈጠረው ፖለቲካ ምክንያት ግን አስመራና ዶሃ በመቆራረጣቸው፣ ጥረቱ አየር ላይ መቅረቱ የማይቀር ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የባሕረ ሰላጤው አገሮች የማይጨበጥና መድረሻው የማይገመት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚከተሉ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ የሚበጀው አሁን የያዘችው አቋም መሆኑን ብዙ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የምትወግንለት ወገን ቢኖር ዋጋ ያስከፍላታል፡፡ በተለይ በሁለቱም ወገን በእነ ሳዑዲም ሆነ በኳታር በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስለሚኖሩ፣ እነ ሳዑዲም በኢትዮጵያ ብዙ ኢንቨስትመንት ስላላቸው፣ ከዚያም አልፎ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ስለሚፈጠር፣ ላልተቋጨው የኤርትራ እሳትም ቤኒዚን የሚያርከፈክፍ በመሆኑ… ውግንና ለኢትዮጵያ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡    

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...