Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በእንግሊዝኛ የተጻፈ መልእክት (ቴክስት) በስልኬ ደረሰኝ፡፡ በምን ቋንቋ ተጻፈ? ወይም ምን ዓይነት አስደናቂ መፈክር (መልዕክት) ተላለፈ? የሚለው ላይ አላተኩርም፡፡ ቁም ነገሩ ያለው ሲቪል ሰርቫንቱ (በአማርኛ ተቀራራቢ ትርጉም ከሰጠነው አገልግሎት ሰጪው የመንግሥት ሠራተኛ) የሚሠራውን ያውቀዋል ወይ? ኃላፊነቱስ ምን ያህል እንደሆነ በቅጡ ተረድቶታል? የሚለው ላይ ይመስለኛል፡፡

  የዛሬ ዓመት ገደማ ይመስለኛል ‹‹ታላቁ›› የብዝኃነትና የህዳሴ አብሳሪያችን በሆነው ተቋም እግር ጥሎኝ (እሱም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ) ተገኝቼ ያጋጠመኝን የመልካም አስተዳደር መዝረክረክን በዚሁ ጋዜጣ ላይ ገልጬ ነበር፡፡ መቼም በምንም ዓይነት ጉዳይ የመንግሥት የተባለ መሥሪያ ቤት የሚወስደኝ ጉዳይ ሲኖረኝ ሆዴን ባር ባር ይለዋል፡፡ ሲጀመር ምንም ዓይነት የቀለለ ጉዳይ ኖሮኝ በአንድ ቀን ጨርሼ የወጣሁባቸው ቀናት ካሉ ከአሥር አንድ ቢሆን ነው፡፡ ባስ ካለ ደግሞ እንካ ሰላንቲያ ተለዋውጬና ስድቤን ጠጥቼ የተመለስኩባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡ ይህንን ጽሑፌን የሚያነብ ሰው ነገረኛ ልመስለው ብችል አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን የእኔ ችግር ነው ብዬ የምገምተው ከመስመር የወጣ አሠራር ሲገጥመኝ ‹‹ለምን?›› ብዬ መጠየቄና መልካም የሚሠራ ‹‹ፈጻሚ›› ሲያጋጥመኝም፣ አጥብቄ አመስግኜ መውጣትን ልተወው ያልቻልኩት አመሌ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡

  ባለፈው ሳምንት ወደ አንድ ወረዳ ጽሕፈት ቤት ሄጄ ያጋጠመኝን ልንገራቸሁ፡፡ ዓርብ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ ጉዳይ ጥሎኝ እዚሁ ወረዳ ንግድና ልማት ቢሮ ስገባ፣ መብራት ስለሌለ እየሠሩ እንዳልሆነ ቢሮውን ለብቻው ተቆጣጥሮት የሚገኘው ሰው ነገረኝ፡፡ ሌሎቹ ሠራተኞች በሙሉ ይህንኑ ‹‹መልካም›› አጋጣሚ በመጠቀም ጓዛቸውን ጠቅልለው የሳምንት መጨረሻቸውን (Weekend) ተያይዘውታል ማለት ነው፡፡ ይኼ ምን ይገርማል ትሉኝ ይሆናል፡፡ በትክክል እኔንም የገረሙኝ ከዚህ በኋላ የሆኑት ነገሮች ናቸው፡፡ በቅድሚያ እዚያው ግቢ ውስጥ የጄኔሬተር ድምፅ ይሰማ ስለነበር መብራት እንደሌለ ለነገረኝ ‹‹ሲቪል ሰርቫንት›› ጄኔሬተሩ የማን እንደሆነ ስጠይቀው፣ በቂ ኃይል እንደሌለው ነግሮኝ (ግልምጫውን ሳልቆጥረው) ፊቱን አዙሮ ሄደ፡፡

  እዚያው ከአጠገቡ የገቢዎች ቢሮ ሠራተኞችም ኮምፒዩተሮቻቸውንና መብራቱን አጠፋፍተው ሞቅ ያለ የግል ወሬያቸውን ይዘዋል፡፡ ተመስገን እናንተ ቢያንስ ቢሯችሁ ተቀምጣችኋል ብዬ በሆዴ አመስግኛቸው ወጣሁኝ፡፡ ግን የጄኔሬተሩ ተጠቃሚ ማን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ስል እስቲ ወደ ፎቅ ልውጣና በሥራ ላይ ያለ ቢሮ ካለ ልፈልግ ብዬ ቀጣይ ሁለት ቢሮዎችን ያለጉዳይ ጎራ እያልኩኝ ጎበኘሁኝ፡፡ የወሳኝ ኩነቶችና የአነስተኛና ጥቃቅን ቢሮዎችም በመብራት የለም ሰበብ የቢሮ እረፍታቸው ላይ ናቸው፡፡ ጄኔሬተሩ በእርግጠኝነት መስመሩ የተያያዘው ከወረዳው ጽሕፈት ቤት ጋር እንደሆነ አረጋግጫለሁ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሕዝብ በብዛት የሚገለገልባቸው ተቋማት ሥራ ካልሠሩበት በብቸኝነት እየተጠቀሙበት ያሉት ሥራ አስፈጻሚውና ጸሐፊያቸው ናቸው ማለት ነው፡፡

  እንግዲህ እኔ የማይገባኝ የከበደ ጉዳይ ኖሮባቸው ይሆናል ጄኔሬተር ያስገጠሙት ብዬ ግቢውን ለቅቄ ብዙም ሳልርቅ፣ በአቅራቢያው ካለው ካፌ ‹‹መብራት መጣ!›› የሚል የሠራተኞቹን ድምፅ ሰምቼ ‹‹ቸር ወሬ ያሰማችሁ›› አልኩና ጥዬው ወደወጣሁበት የወረዳ ቢሮ ተመለስኩኝ፡፡ በርግጥም መብራት መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል በኩራት መብራት እንደሌለ የነገረኝ ብቸኛው የቢሮው ሠራተኛም ኮምፒዩተሩ ላይ ተደፍቶ ይታትራል፡፡ ተመልሼ መምጣቴን ነግሬው ጉዳዩን ካስረዳሁት በኋላ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ መብራት ቢኖርም ኔትወርክ ስለሌለ ሰኞ ተመልሼ እንድመጣ ነገረኝ፡፡ ሰዓቱ ገና 10፡00 ሰዓት እንኳን ስላልሞላ ኔትወርክ የሚመጣ ከሆነ እንድጠብቅ ስጠይቀው (ሰኞ በታሳቢነት የኢድ አልፈጥር በዓል ስለሚሆን) በእጁና በትከሻው ‹‹መብትህ ነው›› ዓይነት ምላሽ ሰጥቶኝ ወደ ኮምፒዩተሩ አቀረቀረ፡፡ ከግማሽ ሰዓት በላይ ብቆይም ኔትወርኩን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ብቸኛው (ታታሪው) ሠራተኛ ግን ነፍሱም ሥጋውም ኮምፒዩተሩ ላይ ነው ያለው፡፡

  ምናለበት እንደ አብዛኞቹ ባንኮች በከፊል ተገልጋዩ ወደሚያየው አቅጣጫ የኮምፒዩተሩን ሞኒተር ቢያዞሩት ብዬ ተመኘሁ፡፡ በእርግጠኝነት ኔትወርክ ኖሮ ፌስቡኩን እየጠቀጠቀ ካልሆነ ጌም እየተጫወተ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ይህን ያህል ‹ማውዝ› ይዞ የሚመሰጥበት ጉዳይ ሊኖረው አይችልም፡፡ የእኔም ጥበቃ ተስፋ የሌለው መሆኑ ሲሰማኝ ተስፋ ቆርጬ ወደ ቤቴ መጣሁኝ፡፡ መቼም እንዳይነጋ የለም መሽቶ ሲነጋ፣ ደግሞም መሽቶ ሲነጋ የኢድ አልፈጥር በዓል እሑድ ሆኖ ቁጭ፡፡ ረዥም የሳምንት መጨረሻ አስቦ የነበረው ‹‹የቁጩ ሲቪል ሰርቫንት›› ሰኞ በጠዋት ቢሮው ገብቶ ከሸሸው ሥራ ጋር ሲፋጠጥ እኔም ገብቼ ጉዳዬን በ15 ደቂቃ ፈጽሜ ወደ ሥራዬ ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ መንግሥትም ሳይታክት እንዲህ ያሉ መንጋ ሥራ ጠሎችን ሰብስቦ መፈክር እያሳመረና ቀን እየቆጠረ በግል ስልካችን ላይ በማይገባን እንግሊዝኛ ይራቀቅብናል፡፡ ወሬ ብቻ …

  (ታዛቢው፣ ከአዲስ አበባ)

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img