Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ መውጣት የሚቻልበትን መፍትሔ የሚያጠና ኮሚቴ አቋቋሙ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ መውጣት የሚቻልበትን መፍትሔ የሚያጠና ኮሚቴ አቋቋሙ

ቀን:

  • ለስንዴ አቅርቦት ብቻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ለድጎማ ወጥቷል

ምግብ ነክ ለሆኑ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች የውጭ ግዥና የድጎማ ወጪ የመንግሥትን አቅም በከፍተኛ ደረጃ በመፈታተኑ፣ አስቸኳይ የመውጫ መፍትሔ የሚያጠና ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መደራጀቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደራጀው ኮሚቴ የሚመራው በቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ እንደሆነ፣ በአባልነትም በማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንዳካተተ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

እነዚህም ከፍተኛ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኑስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) እና የንግድ ሚኒስትሩ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) መሆናቸው ታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገሪቱ ገበያ ውስጥ የመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ፍላጎትና አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ አለመጣጣም ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳም የገበያ አለመረጋጋትና የዋጋ ንረት ዝቅተኛውን ሸማች የማኅበረሰብ ክፍል አቅምና ኑሮ በመፈተን ላይ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለልና የዋጋ መረጋጋት ለመፍጠር የፌዴራል መንግሥት በገበያው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት እጅግ መሠረታዊ ናቸው ብሎ የለያቸውን ሦስት ምግብ ነክ የዕለት ፍጆታ ሸቀጦች ከውጭ በማስገባትና ድጎማ በማድረግ፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለሸማቹ በማቅረብ ላይ እንደሚኝ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በመንግሥት የተለዩት ሦስት መሠረታዊ ምግብ ነክ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ዘይት፣ ስንዴና ስኳር ናቸው፡፡ እነዚህን የፍጆታ ሸቀጦች ዝቅተኛ የሆነውን የመንግሥት የውጭ ምንዛሪ ክምችት በመጠቀም ከውጭ ገበያዎች በመግዛት፣ በተወሰኑት ላይ የዋጋ ድጎማ በማድረግ፣ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በመፍቀድ ለአገር ውስጥ ገበያ በኮታ በማከፋፈል ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ በአማካይ 300 ሺሕ ቶን (ሦስት ሚሊዮን ኩንታል) ስኳር ከውጭ እየተገዛ በአገር ውስጥ የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመሙላት በመከፋፈል ላይ ነው፡፡ በዚህ የስኳር አቅርቦት ላይ መንግሥት ምንም ዓይነት ድጎማ ባያደርግም፣ ቀድሞውንም ዝቅተኛ መሆኑ የሚታወቀውን የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንደተቀራመተበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው መሠረታዊ የዕለት ፍጆታ ሸቀጥ የምግብ ዘይት ሲሆን፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ 548 ሚሊዮን ሊትር ከውጭ እየተገዛ በመከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የዘይት ግዥ የሚፈጸመው በመንግሥት እንደነበር፣ በኋላ ላይ ግን የግል አስመጪዎች ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ በመፍቀድና ስርጭቱን መንግሥት በመቆጣጠር እየቀረበ ነው፡፡

የዘይት ገበያን ለማረጋጋት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከመሸርሸሩም በላይ፣ መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ከዘይት አቅርቦት ሊገኝ የሚችለውን የቀረጥ ገቢ በማንሳት ነፃ የቀረጥ ዕድል ለአስመጪዎች መፈቀዱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በዋናነት የመንግሥትን አቅም በመፈታተን ላይ የሚገኘው የዕለት ፍጆታ ሸቀጥ ስንዴ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ስንዴን ከውጭ ገዝቶ ለማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ጥቅም ላይ እንዲውል ከመደረጉ ባለፈ በዝቅተኛ ዋጋ ለዝቅተኛው ሸማች እንዲቀርብ ለማድረግ በኩንታል ከ200 ብር በላይ ድጎማ እየተደረገበት እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዘንድሮ ድረስ በተደረገው ድጎማም መንግሥት ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ለስንዴ ድጎማ ብቻ ማውጣቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከወጪው እኩል መንግሥትን እያሳሰበ የሚገኘው ከውጭ በከፍተኛ ወጪ እየገቡ የሚገኙት እነዚህ ሦስት ምግብ ነክ ሸቀጦች፣ የታለመላቸውን ግብ መትተዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ለአብነት ያህል የስኳር አቅርቦቱ የሁሉንም ክልሎች ፍላጎትና የሕዝብ ብዛት መሠረት በማድረግ በኮታ እየተከፋፈለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለአዲስ አበባ 12 ሺሕ ቶን የስኳር ኮታ ተፈቅዷል፡፡ ይህ ኮታ የተፈቀደው የስኳር ፍላጎትና የከተማዋን የሕዝብ ብዛት መሠረት በማድረግ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በሥሌቱ መሠረት 3.6 ሚሊዮን ለሚሆነው የአዲስ አበባ ሸማች 12 ሺሕ ቶን ሲፈቀድ በወር 3.6 ኪሎ ግራም ስኳር ለአንድ ቤተሰብ ይደርሳል በሚል እሳቤ ነበር፡፡ በገበያው ላይ በገሃድ የሚታየው ግን ይህ አለመሆኑንና እስከነጭራሹ የስኳር እጥረቱን በአዲስ አበባ መፍታት አለመቻሉ ነው፡፡ ምክንያቱ የአቅርቦት ችግር ሳይሆን የሚቀርበው ስኳር ከአዲስ አበባ ገበያ ወደ ክልሎች፣ እንዲሁም ከአገር ሁሉ መልስ እየወጣ መሆኑ እንደተደረሰበት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የስንዴ አቅርቦትም ለታለመው ዝቅተኛ ሸማች በዝቅተኛ ዋጋ እየቀረበ አለመሆኑ፣ በግርድፉ መታየቱን በገበያው ያለውን የዳቦ ዋጋ በማንሳት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከቀን ሠራተኛው ይልቅ ከፍተኛና መካከለኛው ሸማች ዳቦ መግዛት በመቻሉ ድጎማው ላልተፈለገው አቅም ያለው ሸማች እየዋለ በመሆኑ፣ ዓላማውን ሳይስት እንዳልቀረ በግርድፉ ዳሰሳ መታየቱን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ኮሚቴም ይህንን በጥልቀት አጥንቶ መፍትሔ ያቀርባል ሲሉ ምንጮች አክለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...