Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢ አሁንም ግጭቶች መኖራቸው ታወቀ

በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢ አሁንም ግጭቶች መኖራቸው ታወቀ

ቀን:

በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢ በነዋሪዎች መካከል አሁንም ግጭቶች መኖራቸውን  የሪፖርተር ምንጮች አመለከቱ፡፡

በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ በነዋሪዎች መካከል ባለፈው ሳምንት በተቀሰቀሰ ግጭት፣ የሰው ሕይወትና ንብረት መውደሙንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቅርብ ርቀት ባሉ የድንበር አካባቢዎች ግጭት የተከሰተ ቢሆንም፣ መንስዔው ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሦስት የኬንያ ፖሊሶችን ከገደሉ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሦስቱ የኬንያ ፖሊሶች ግድያ የሁለቱን አገሮች መንግሥታት ቅራኔ ውስጥ ከቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሁለቱ አገሮች በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች አልሸባብ እንደሚንቀሳቀስ፣ ለሁለቱ አገሮች አልፎ አልፎ ግጭት መከሰትም ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ለመፍታት ሲባልም፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ኬንያ አቅንተው ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለመፍታት ከኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ተቀምጠዋል፡፡  

ሁለቱ አገሮች በሚዋሰኑበት አካባቢ በሚኖሩ አርብቶ አደሮች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ወደ ኬንያ ያቀኑት አቶ ካሳ፣ በሚደረሰው ስምምነት መሠረት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ኅብረት ከማጠናከሩ በተጨማሪ በቀጣናው እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ሊፈታ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ወርቁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረናና ዳዋ ዞኖችን ከሚያዋስኗቸው የኬንያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር አልፎ አልፎ እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ታስቦ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አበበ ገለጻ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚኖሩ ዜጎች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የጋራ ፕሮጀክቶች ሰነድ ተዘጋጅቶ፣ ከሁለቱም አገሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ሲወያዩበት ቆይተዋል፡፡ የዚህ ሰነድ ዋነኛ ዓላማም በአካባቢው ላይ ሰላምን በማስፈን ዘላቂ ልማት በማምጣት ኅብረተሰቡን ከድህነት ማላቀቅ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በተሟላ መንገድ በጋራ ለመገንባት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ሲፈጠር የነበረውን ግጭት ከማስወገድ በተጨማሪ፣ በሰባት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መፍትሔ በመስጠት ውጤት ለማምጣት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች ሰባት ሲሆኑ፣ እነሱም በሀብት ሽሚያ ምክንያት የሚፈጠረውን ግጭት መከላከል፣ በአካባቢው የገበያ ንግድ ትስስር እንዲጠናከር ማድረግ፣ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም፣ የእንስሳት ሀብት ልማትና የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት፣ የአደጋ ተጋላጭነትን መከላከልና ማስወገድ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርና የጋራ ተቋማትን የመገንባት ስምምነቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ይህ የጋራ ስምምነት ሁለቱ አገሮች በጋራ ፋይናንስ የሚያደርጉበትና ዕርዳታ የሚገኝበት ፕሮጀክት እንደሆነ አቶ አበበ አክለዋል፡፡

ወደ ኬንያ አብረው ካቀኑት ከፍተኛ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወካይ ይገኙበታል፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት አቶ ለማ፣ ‹‹ይህ የስምምነት ፕሮጀክት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የአርብቶ አደር ሕይወት የሚቀይር በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች መካከል የኦሮሚያን ክልል ከሚያዋስኑ ክልሎች ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የአቶ ለማ ወደ ኬንያ ማቅናትም የኦሮሚያ ክልል በድንበር አካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላው ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ኬንያ አልፎ አልፎ በድንበር አካባቢ ከሚፈጠረው ግጭት ባሻገር፣ የኦሞ ወንዝ ላይ የኃይል ማመንጫ በመገንባቱ ኬንያ ቅር መሰኘቷን ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ከቱርካና ሐይቅ ዓሳ በማስገር የሚኖሩ ኬንያውያን በሐይቁ መቀነስ ምክንያት ችግር ውስጥ መግባታቸው እየተነገረ ነው፡፡ ለቱርካና ሐይቅ ዋነኛ ገባር የሆነውን የኦሞ ወንዝ ኢትዮጵያ ለኃይል ማመንጫ መጠቀሟ ሐይቁ እየቀነሰ በመምጣቱ የኬንያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሰሞኑን ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ወደ ኬንያ ያቀኑት አቶ ካሳ በሁለቱ አገሮች መካከል ከተከሰተው ግጭት ባሻገር፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ባሉት ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ከኬንያ መንግሥት ጋር እንደሚነጋገሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...