Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ የጥናት ውጤት እንደማትጠብቅ አስታወቀች

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ የጥናት ውጤት እንደማትጠብቅ አስታወቀች

ቀን:

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ደረጃ እንደፈቀደ ወደ ውኃ ሙሌት እንደሚገባ ኢትዮጵያ አስታወቀች፡፡

ባለፈው ሳምንት በኢንቴቤ ኡጋንዳ የተካሄደውን የዓባይ ተፋሰስ አገሮች መሪዎች ጉባዔ አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአፍታም እንደማይቋረጥ፣ በዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶች በግድቡ ተፅዕኖ ላይ የሚያደርጉትን ጥናት ውጤት ቆማ እንደማትጠብቅና የውኃ ሙሌት የግንባታው ደረጃ በሚፈቅድ ወቅት እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ‹‹የውኃ ዋስትና ለሁሉም›› የሚለውን መርህ በማክበር የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የውኃ ሙሌቱ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ የጎላ ተፅዕኖ በማይፈጥርበት ሁኔታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጥናቱን ቆመን አንጠብቅም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ ሙሌቱ የሚጀመርበትን ጊዜ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የዓባይ ተፋሰስ አገሮች መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንቴቤ ተገናኝተው መነጋገራቸው ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ዶ/ር ስለሺ ተናግረዋል፡፡ ከናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ግብፅና ሱዳን መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሱዳን ተመልሳ ገብታለች፡፡ በቅርቡ ግብፅ ተመልሳ ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበች ቢሆንም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች፡፡ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አባል አገሮች ግብፅ ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አንስታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትቀላቀል ስምምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢንቴቤ በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የናይል ቤዚን ኮሚሽን እንዲቋቋም ሐሳብ መቅረቡን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በጉባዔው ላይ በርካታ የናይል ቤዚን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እንደተካሄደባቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የዓባይ ተፋሰስን ደኅንነት ለመጠበቅ የተፋሰሱ አገሮች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

የዓባይ ተፋሰስ ለሌሎች ተፋሰሶች እንደምሳሌ የሚታይ እንዲሆን የተፋሰሱ አባል አገሮች ተባብረው እንዲሠሩ ሙሴቬኒ አሳስበዋል፡፡ ሙሴቬኒ ፈጣን የሕዝብ ብዛት ዕድገት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን፣ ሕዝቡን ምርታማ ማድረግ ከተቻለ ግን ሕዝብ ብዛት በራሱ ትልቅ የዕድገት አቅም ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በክልሉ በጣም አነስተኛ መሆኑን፣ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማሳደግ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የአካባቢ መራቆት፣ የደን መመናመንና ረግረጋማ ቦታዎች እየጠፉ መሄዳቸው ለዓባይ ተፋሰስ አሳሳቢ ሁኔታዎች መሆናቸውና አካባቢን በጋራ ተቀናጅቶ የመልሶ ማልማት ሥራ መሥራት እንዳለበት መሪዎቹ እንደተወያዩ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የማድረግ አስፈላጊነት፣ የግብርና አመራረት ዘዴን በማዘመን በግብርና የተሰማራውን ሕዝብ ቁጥር መቀነስ እንደሚያስፈልግ ሙሴቬኒ ሐሳባቸውን በጉባዔው አቅርበዋል፡፡ የተፋሰሱ አገሮች በኢኮኖሚ የተሻለ ትስስር መፍጠር አስፈላጊነት ላይ በጉባዔው ውይይት እንደተካሄደ ተገልጿል፡፡ በኢነርጂ፣ በመንገድና በባቡር መሠረተ ልማቶች የኢኮኖሚ ትስስሩን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...