Thursday, May 30, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ንብ ባንክ ሲወዛገቡበት የነበረው ሕንፃ በሐራጅ ሊሸጥ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲወዛገቡበት የነበረው፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አጠገብ የሚገኘው ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ በሐራጅ ሊሸጥ ነው፡፡

ራሳቸውን ያጠፉት የጌታነህ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ወንድም አቶ አጥናፉ ጌታነህ፣ በሊዝ ዋጋ 3,649,800 ብር በተሸጠው 2,926 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሕንፃ የሐራጅ ጨረታ ዓርብ ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ይከፈታል፡፡

አቶ አጥናፉ የተበደሩትን ብር መክፈል ባለመቻላቸው የሊዝ መብታቸውን የወሰዱትና ሕንፃውን የገነቡት፣ የመከታ ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና አራጣ በማበደር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ከሰባት ዓመታት በፊት 25 ዓመታት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ ከበደ ተሠራ (ወርድል ባንክ) ናቸው፡፡

አቶ ከበደ ለሕንፃው ማስገንቢያ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 55 ሚሊዮን ብር ተበድረው በመገንባት ላይ እያሉ በመታሰራቸው፣ ሕንፃው የማጠናቀቂያ ሥራ የቀረው ቢሆንም ሳይጠናቀቅ ላለፉት አሥር ዓመታት ቆሞ ቆይቷል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ በአቶ ከበደ ላይ የመሠረተውን ክስ በ25 ዓመታት እስራት (የሥር ፍርድ ቤት በ22 ዓመታት እሥራት የቀጣቸው ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ብሎ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅጣቱን ወደ 25 ዓመታት ጽኑ እስራት ከፍ አድርጎታል) የቅጣት ውሳኔ ሲያጠቃልል፣ ሕንፃውን ‹‹የወንጀል ውጤት ነው›› በማለት እንዲወረስ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲወርስ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ለሕንፃው ማሠሪያ 55 ሚሊዮን ብር ብድር የሰጠው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የይገባኛል ጥያቄ በማቅረቡ፣ ጉዳዩ ወደ ክርክር አምርቶ ከርሟል፡፡ በመጨረሻ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በድጋሚ በመዝገብ ቁጥር 82321 ሲያከራክር ከርሞ፣ ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሳኔና ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ሕንፃው በሐራጅ ተሸጦ ንብ ባንክ ያበደረው 55 ሚሊዮን ብር ከነወለዱ ተሰልቶ እንዲከፈለው ብሏል፡፡ የባንኩ ድርሻ 120 ሚሊዮን ብር መድረሱም ታውቋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሕንፃውን በመነሻ ዋጋ 72,740,053 ብር ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. አጫርቶ ለመሸጥ ሐራጅ አውጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች