Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየውጭ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ከሕግ ውጭ ቫት ሰብስቡ መባላቸውን ተቃወሙ

የውጭ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ከሕግ ውጭ ቫት ሰብስቡ መባላቸውን ተቃወሙ

ቀን:

  • መንግሥት ሠራተኞችን ለሚልኩ ተቋማት ማበረታቻ እንደማይሰጥ በመግለጽ ጥያቄውን አጣጥሏል

በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት የሚሰጡ ኤጀንሲዎች ከሕግ ውጪ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እንዲሰበስቡና ደረሰኝ እንዲቆርጡ እየተጠየቁ መሆናቸውን በመቃወም፣ ይልቁንም ያላግባብ የተጣለባቸው የቫት ውሳኔ እንዲነሳላቸውና አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እንዲሰጥላቸው ጠየቁ፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ሥራ ሥምሪት አገልግሎት ሰጭ ኤጀንሲዎች ማኅበር ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ተካ መሓሪ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ ኤጀንሲዎቹ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የተጣለው የተጨማሪ እሴት ታክስ የሕግና የማስረጃ መሠረት የሌለው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የሰው ኃይል ወደ ውጭ በመላክ በሥራ መስክ የተሠማሩት እነዚህ ኤጀንሲዎች፣ ምርትና አገልግሎትን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡት እኩል ታይተው ከቫት ውጪ በዜሮ ምጣኔ የሕግ አግባብ ሊስተናገዱ ሲገባ፣ ይኼ ባለመደረጉ ምክንያት ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቤቱታቸውን እንዳቀረቡ አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ ከመድረሻ መርህ ጋር ለማጣጣም፣ የወጪ ንግድን ለማበረታታት፣ እንዲሁም የታክስ ጫናን የመቀነስ ዓላማን ታሳቢ እንደሚያደርግ ያስረዱት አቶ ተካ፣ በዚህ መሠረት ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሥራ ዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ እንደሚጣልበት በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 7/2/፣ እንዲሁም በደንብ ቁጥር 79/1995 ውስጥ ከአንቀጽ 34 እስከ 38 ድረስ የሠፈሩትን ድንጋጌዎች በመመልከት በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ የሚቀርበው የቫት ጥያቄ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡  

- Advertisement -

ኤጀንሲዎቹ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ወደ ውጭ አገር መልምለው በመላክ የሚሠሩት፣ ሠራተኛን የማገናኘት አገልግሎት የሰው ኃይል ወደ ውጭ በመላክ ሥራ ውስጥ የሚጠቃለል በመሆኑ በዜሮ ቫት ምጣኔ መሠረት ሊስተናገድ ሲገባው፣ ይህ ባለመደረጉ ኤጀንሲዎቹ አቤቱታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሕጉ መሠረት ቫት የሚሰበሰበው በአገር ውስጥ በሚደረጉና ታክስ በሚከፈልባቸው ግብይቶች በተመዘገበ፣ ወይም የመዝገብ ባለቤት በሆነ ሰው ሲከናወኑ፣ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ ማንኛውም ሰው ብቻ የሚሰበስበው ታክስ መሆኑ በግልጽ በሕጉ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ፣ ይህንን የሕግ መርህ በሚጥስ አኳኋን በኤጀንሲዎቹ ላይ ያልተገባ ውሳኔ መተላለፉን በመጥቀስ ይሟገታሉ፡፡

ምንም እንኳ አቶ ተካ የሕጎቹን አንቀጾች በማጣቀስ ኤጀንሲዎቹ ላይ አግባብ ያልሆነ ውሳኔ ተላልፏል በማለት ቢሟገቱም፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ምላሽ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የትህምርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን፣ የቫት ምጣኔ ጥያቄ ባለሥልጣኑን እንደማይመለከተውና የሚኒስቴሩ የኃላፊነት ወሰን በመሆኑ ባለሥልጣኑን እንደማይመለከተው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባለሥልጣኑ ባልደረባ ግን ምንም እንኳ ከቴክኒክ ጉዳዮች አኳያ የኤጀንሲዎቹ ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም፣ መንግሥት ሰዎችን ወደ ውጭ የሚልኩ ተቋማትን ከማበረታታት ይልቅ ትኩረቱ ሌሎች አገልግሎቶችና ምርቶችን በሚልኩት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የቫት ምጣኔ ጉዳይ ይመለከተዋል የተባለው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርም ከቀረበው የሕግ ክርክር ይልቅ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አንደምታ ያላቸው ነጥቦች ላይ አጠንጥኗል፡፡ የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተነሱት የሕግ ነጥቦች ላይ ምላሽ የሚሰጠው አዋጆቹን ያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይሁንና መንግሥት ወደ ውጭ ሰዎችን ከመላክ ይልቅ በአገር ውስጥ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ሰዎችን ወደ ውጭ ለመላክ የተሠማሩ ድርጅቶችን ከመደገፍ ይልቅ፣ በአገር ውስጥ የሚያመርቱና ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን የሚልኩትን በመደገፍ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት እንዲህ ያለ አቋም በሚያራምዱበት ወቅት፣ ያላግባብ ቫት እንድንሰበስብ ተጠይቀናል ያሉት ኤጀንሲዎች ወደ ውጭ ለሥራ ሥምሪት ከሚልኳቸው ሰዎች ለአገልግሎት ከሚያስከፍሉት ላይ ደረሰኝ ቁረጡ እየተባሉ መቸገራቸውን አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡ ደረሰኞችን ማወራረድ በማይቻልበት ሁኔታ ሰዎቹም ከአገር ውጭ በሚሆኑበት አኳኋን ውስጥ ደረሰኝ ቁረጡ ማለት፣ ከሕግም ከመርህም ውጪ በመሆኑ በመንግሥት ሊጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ኤጀንሲዎቹ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በሚያቀርቡበት ወቅት፣ መንግሥት ለሦስት ዓመታት ያገደውን የውጭ ሥራና ሠራተኞች ሥምሪት ዳግመኛ ለማስጀመር ከተቀባይ አገሮች ጋር ድርድር በማድረግ ወደ ስምምነቱ መምጣት እንደጀመረ ታይቷል፡፡ በቅርቡ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ስምምነት መደረሱም ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም የተባሉ ኢትዮጵያውያንን ከአገሯ እያባረረች ብትሆንም፣ በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ሠራተኞችን ለመቀበል ጥያቄ ማቅረብ መጀመሯ ታውቋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስም በድርድር ላይ እንደምትገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...