ላለፉት 85 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ይዞ የቆየው አልፋራጅ ትሬዲንግ ኩባንያ፣ በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) ኦሎምፒያ አካባቢ በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ሊገነባ ያቀደው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል አፓርትመንት የቦታ ይገባኛል ተቃውሞ ገጠመው፡፡
የአልፋራጅ ፕሮጀክት በቀድሞው ወረዳ 18 ቀበሌ 18 ከደምበል ሲቲ ሴንተር ፊት ለፊት የሚገኝ ሲሆን፣ በአጠቃላይ አራት ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ 20 የሚጠጉ የቀበሌ ቤቶችና አቶ ሙክታር አብዱልራህማን የተባሉ ግለሰብ ይዞታ የሆነ 319 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት አለ፡፡
የቀበሌ ቤቶች ነዋሪዎች ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተሰጥተዋቸው የተነሱ ሲሆን፣ አቶ ሙክታር ቦታውን ለማልማት ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ አለማግኘታቸውን በመጥቀስ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመጠየቃቸው፣ ቦታው ከባለይዞታዎች ነፃ ተደርጎ ለአልፋራጅ ፕሮጀክት መዋል አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
አቶ ሙክታር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ይግባኝ ብለዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔው ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት፣ የአመልካቹን አቤቱታ ተቀብሎ የይግባኝ መዝገብ መከፈቱን አስታውቋል፡፡
አቶ ሙክታር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለረዥም ዓመታት በውጭ አገር ይኖሩ ነበር፡፡ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ በመመለስ በ1997 ዓ.ም. አሁን ያሉበትን መኖሪያ ቤት በመግዛት የተሻለ ግንባታ ለማካሄድ አቅደው ጥያቄያቸውን ለከተማው አስተዳደር አቅርበው ነበር፡፡
‹‹ያቀረብኩት የግንባታ ፈቃድ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶ ይዞታዬ ለሌላ ኩባንያ ሊሰጥ አይገባውም፤›› ሲሉ አቶ ሙክታር ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተለያዩ መዋቅሮች ግለሰቡ መኖሪያ ቤታቸውን አስረክበው ካሳና ምትክ ቦታ እንዲወስዱ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ቶላ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአቶ ሙክታር በጻፉት ደብዳቤ፣ የካሳ ክፍያ ተሠርቶ እንዲወስዱ ቢጠየቁም እስካሁን ያልወሰዱ ስለሆነ በቀጣይ ባሉት ሦስት የሥራ ቀናት መጥተው ካልወሰዱ ለሚወሰደው ዕርምጃ ኃላፊነቱን ይውሰዱ በማለት አስጠንቅቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ታሽጎ ይገኛል፡፡
በተለያዩ ንግድ ሥራዎች የሚታውቀው አንጋፋው አልፋራጅ ትሬዲንግ፣ ይህ ቦታ እንዲሰጠው ከ14 ዓመታት በፊት ተወስኖ ነበር፡፡
የአልፋሬጅ ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይድሩስ ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ቦታ ላይ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል አፓርትመንት ለመገንባት ያቀዱት የዛሬ 15 ዓመት ገዳማ ነው፡፡
‹‹ለአቅም ማሳያ ሰባት ሚሊዮን ብር በዝግ ሒሳብ ተቀምጦና ያለምንም ሥራ ታስሮ ይገኛል፡፡ 20 ለሚጠጉ የቀበሌ ቤት ተነሺዎች የኮንዶሚኒየም ቤቶች ገዝተን አስረክበናል፡፡ ቦታውን ግን እስካሁን ማግኘት አልቻልንም፤›› ሲሉ አቶ ኃይድሩስ አስረድተዋል፡፡
አቶ ሙክታር ለመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ፣ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔው ሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የጽሕፈት ቤቱን ምላሽ ለማድመጥ ቀጠሮ ይዟል፡፡