– ለቻይና ያደላው የንግድ ሚዛን እንዲመጣጠን ኢትዮጵያ ትጠይቃለች
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ በቻይና የድህነት ቅነሳ ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ከወራት በፊት ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በተካሔደው የቻይና-አፍሪካ ከፍተኛ የምክክርና የምሁራን ፎረም ከመጽሐፉ አንቀጾች እየተጠቀሱለት ሲብራራ ታይቷል፡፡ አንደኛው ነጥብም በጥሬው ‹‹ያገኛችሁትን አትገልብጡ›› (Don’t copy everything…) የሚል መልዕክት እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡
በዚሁ ፎረም እገረ መንገዳቸውን የተገኙት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ ይህንኑ መልዕክት ለአፍሪካውያኑ አስተጋተዋል፡፡ ፖሊሲዎችን ከየትም ቦታ እንዳሉ ከነነፍሳቸው ከመገልበጥ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚስማማ፣ ከአገርና ከሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮች አኳያ የሚስማማ የፖሊሲ ሐሳብ ብትጋሩ ይሻላችኋል የተባለበት መድረክ ነበር፡፡ ከቻይናውያኑ ባሻገር ስለመጽሐፉ በጨረፍታ እያጣቀሱ ማብራሪያ ከሰጡት መካከል፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነትና ክትትል ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ኃላፊው ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይጠቀሳሉ፡፡
ዶ/ር አርከበ የኢትዮጵያን የድህነት ቅነሳ ውጤቶች ባብራሩበት የቻይና አፍሪካ ከፍተኛ የምክክር ፎረም ወቅት በዓበይትነት የተጠቀሰው ጉዳይ ከቻይና በርካታ የልማት ፖሊሲዎች ልምድ መቀሰሙ ነው፡፡ ቻይና ለአፍሪካ የልማት ፖሊሲ ዓቢይ ሞዴል ነች ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ በፖሊሲ ረገድ ኢትዮጵያ ከቻይና በተማረችው መሠረት 60 በመቶ ዓመታዊ በጀቷን ለመሠረተ ልማት አውረታሮች እንደምታውል ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡ እርግጥ ነው ቻይና ብቻም ሳትሆን አብዛኛው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች በተለይም እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ቬትናም እና ሲንጋፖር ያሉ አገሮች ለአፍሪካውያን የልማት ተምሳሌቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከእነዚህ አገሮች በተገኙ ተሞክሮዎችና በተቀሰሙ ልምዶች ኢንዱስትሪ ተኮር ኢኮኖሚ ለመገንባት ስለተነሳው መንግሥታቸው ያብራሩት ዶ/ር አርከበ፣ በኢኮኖሚ መስክ ብቻም ሳይሆን በማኅበራዊ መስኮች የተገኙ ለውጦችን ጠቃቅሰዋል፡፡ ዋቢ ሲያደርጉም፣ በ1983 ዓ.ም. የአገሪቱ ሕዝብ አማካይ የመኖር ዕድሜ ወይም የዕድሜ ጣሪያ 45 ዓመታት እንደነበር አንስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህ ወደ 65 ዓመታት በማሻቀቡ፣ በአማካይ የ20 ዓመታት የዕድሜ ጭማሪ የታየው በአገሪቱ ተደራሽ የጤና መሠረተ ልማት በመስፋፋታቸው፣ የትምህርት መሠረተ ልማት አውታሮች በመጨመራቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ ለታየው ለውጥ መንግሥት 70 በመቶውን በጀት ደሃ ተኮር ለሆኑ ሥራዎች በመመደቡ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሦስት መሠረታዊ ችግሮችን ይፈታል የተባለውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መንግሥት እያስፋፋ እንደሚገኝ ሲጠቅሱም አንደኛው የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ በሰው ጉልበት የሚታገዙ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ እየተደረገ መሆኑ፣ ሁለተኛው አገሪቱ የሚታይባትን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለመቅረፍም የሚስፋፉት ማምረቻዎችና ምርቶቻቸው ለውጭ ገበያ በገፍ የሚቀርቡባቸው መሆናቸውን ከዶ/ር አርከበ ማብራሪያ መጨለፍ ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ የሚስፋፋው ኢንዱስትሪ ትልቅ የተባለውን የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን እያሳበ መሆኑም የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ ከትክክለኛው ምንጭ ለመቀዳቱ አስረጅ ተደርጓል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት ከአምስት የዓለም ዋና ዋና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ አንጎላን ተከትላ በሁለተኛነት እንደምትጠቀስ አስነብቧል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ ባህር አልባ፣ እንደ ነዳጅ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከሌላቸው አገሮች ተርታ የምትመደብ ሆና ሳለ፣ ሁለቱም ሀብቶች ካላቸው አገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ የ3.2 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን እንደበቃች ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ነጥቦች ያነሱት ዶ/ር አርከበ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ መጽሐፍ ሲያጣቅሱ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹አፕ ኤንድ አውት ኦፍ ፖቨርቲ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው ውስጥ የታሪክ ዳራ ያደረጉት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ይኖሩባት ከነበረችውና በፉጂያን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኒግዴ በተባለችው የትውልድ መንደራቸው ውስጥ የነበረውን አስከፊ ድህነት እንዴት እንዳሸነፉ፣ ሐሳባቸውና ልምዳቸው የተካተቱበት መጽሐፍ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
ቻይና ለአፍሪካ ከምትሰጠው ድጋፍ አኳያ ከፖሊሲ ሞዴልነት ባሻገር በምታቀርበው ከፖለቲካ ጫናዎች ነፃ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት ረገድም ተወድሳለች፡፡ በዚህ ወቅት እንደ ዶ/ር አርከበ ሁሉ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመትም ተመሳሳይ ነጥብ አንስተዋል፡፡ ቻይና የአፍሪካ የቀኝ አጋር ካሰኟት ምክንያቶች ሚዛን የሚደፋውም ይኸው ግራና ቀኝ የሌለው፣ ይህን አድርጉም አታድርጉም የሌለበት፣ የፖሊሲ ነፃነታችንን ያከበረ ብድር መስጠቷ ትልቅ ቦታ አለው ብለዋል፡፡
ይህም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ጋር ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በቻይና የበላይነት የሚቃኝ መሆኑም በግልጽ ተጠቅሷል፡፡ አፍሪካ የቻይና የጥሬ ዕቃና የተፈጥሮ ሀብት ማዕከል ብቻ መሆን እንደሌለባት ያሳሰቡት ዶ/ር አርከበ፣ ‹‹የተፈጥሮ ሀብት ላኪዎች ሆነን መቀጠል የለብንም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሳይገደቡ በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ሚዛኑ ይስተካከል በማለትም ቻይናን ጠይቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በቻይና እና በአፍሪካ አገሮች መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 230 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አርከበ፣ የዚህን አሐዝ አብዛኛውን ድርሻ የያዘችው ቻይና ስትሆን፣ የአፍሪካውያኑ ድርሻ ግን አምስት በመቶ ገደማ በመሆኑ ይህ ሊሻሻል ይገባዋል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ የቻይና ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ቢሆንም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ግን በአፍሪካ ትልቁን የኢንቨስትመንት ድርሻ በመያዝ ቻይና ትልቋ እንደምትሆን የአሜሪካውን አማካሪ ኩባንያ፣ የማኬንዚን ይፋ ያልወጣ ጥናት ዋቢ ያደረጉት ዶ/ር አርከበ፣ በጠቅላላው ከቻይና የሚገኘው ድጋፍም ሆነ የሚካሔዱ የትብብር ግንኙነቶች ጠቀሜታን አብራርተዋል፡፡
አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ምንጭ ሆና ሳለ ለምን ደኸየች ሲሉ ሙሳ ፋኪ ላቀረቡት ጥያቄ፣ አፍሪካ የባሪያ ንግድ ማዕከል ሆና መቆየቷና የቅኝ ግዛት ሰለባ መሆኗ ለድህነቷ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እውነታዎች ናቸው ሲሉ ምላሻቸውን አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከቻይናው ኢንስቲትዩት ኦፍ አፍሪካን ስተዲስ ኦፍ ዚያንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ያሰናዱት ይህ የምክክር ፎረም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳው በሁለቱ ተቋማት ትብብር ቢሆንም ሰሞኑን ሲካሔድ ግን ለስድስተኛ ጊዜው እንደሆነ ታውቋል፡፡