Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጂቡቲ እየገነባችው ከሚገኙ ወደቦች ሦስተኛውንና ለጨው ምርት ማስተናገጃ የሚውለውን ወደብ ሥራ አስጀመረች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዶራሌ ሁለገብ ወደብ ተገንብቶ መጠናቀቁ በተበሰረ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ታጁራ የተሰኘውና በአብዛኛው የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያገልገል የሚጠበቀው ወደብ ሥራ በጀመረ በሳምንቱ፣ ለአገሪቱ አራተኛ የሆነውንና የጨው ምርት የሚስተናግደውን የጎውበት ወደብ አጠናቆ ለሥራ ማዘጋጀቱን የጂቡቲ መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡

በ64 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የጎውበት ወደብ፣ ለውጭ ገበያ የሚውል አምስት ሚሊዮን ቶን ጨው የማስተናገድ አቅም እንዳለው የጁቡቲ መንግሥት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ወደቡ በአብዛኛው ከአሳል የጨው ሐይቅ የሚወጣውን ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብሏል፡፡ የጂቡቲ ወደቦች አስተዳደርና ነፃ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡባካር ኦማር ሐዲ የጨው ማስተናገጃ ወደቡ ሐሙስ ሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲመረቅ እንደተናሩት፣ አዲሱ ወደብ ጂቡቲን በአፍሪካ የሎጂስቲክ አገልግሎት ማዕከል እንድትሆን የሚያበቃት የመሠረተ ልማት አውታሮች አካል ነው፡፡

ከጨው በተጨማሪ የጂፕሰም ምርቶችን የሚያተናግደው የጎውበት ወደብን ጨምሮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ ያደረጋቸው የዶራሌ ሁለገብ፣ እንዲሁም የታጁራ ወደቦችን ለመገንባት ከ730 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን የጂቡቲ መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተገንብቶ የተጠናቀቀው ሆራይዘን ጂቡቲ ተርሚናልስ የተባለው የድፍድፍ ነዳጅ ማከማቻና ማጣሪያ፣ እንዲሁም የኤክስፖርት ማድረጊያ ማዕከል ለመገንባት 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን የጂቡቲ መንግሥት አስታውቋል፡፡ በዓመት አሥር ሚሊዮን የቁም እንስሳት እንደሚያስተናግድ የተነገረለት የዳመርጆግ ወደብ ግንባታም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተጠቅሶ፣ ለግንባታውም 70 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመርከብ ጥገናና ኢንስፔክሽን ማካሄጃ ማዕከል ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2018 እንደሚጠናቀቅ ሲገለጽ፣ ለግንባታውም 200 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ጠቁሟል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተፈጥሮ ጋዝ ማከማቻና የኤክስፖርት ተርሚናል ግንባታም በ2.8 ቢሊዮን ዶላር እየተገነባ ሲሆን፣ ይህም እ.ኤ.አ. በ2019 እንደሚጠናቀቅ ይፋ ተደርጓል፡፡  

ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምር እንደነበር የሚጠበቀው የታጁራ ወደብ፣ ከኢትዮጵያ የሚጓጓዘውን 2,000 ቶን በቀን፣ ወይም አራት ሚሊዮን ቶን በዓመት የፖታሽ ማዕድን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፣ የሚያስተናግደው የፖታሽ ማዕድን በአብዛኛው በትግራይና በአፋር ክልሎች የሚገኝ ነው፡፡ ሁለቱ ክልሎች ለጂቡቲ ካለቸው ቅርበት አኳያ የታጁራ ወደብ ለፖታሽ ማዕድን ማስተናገጃነት እንዲውል መደረጉ፣ ከተዘረጋው የባቡር ትራንስፖርት አኳያም የፖታሽን የወጪ ንግድ ወጪ በመቀነስ አዋጭ እንደሚያደርገው ከኢትዮጵያ በኩል ይገለጻል፡፡ 

የጂቡቲ በጂቡቲ መንግሥት የ76.5 በመቶ ድርሻ እንዲሁም ቻይና መርቻንት ሆልዲንግስ በተባለውና ግንባታውን ባከናወነው ኩባንያ የ23.5 በመቶ ድርሻ የተገነባው የዶራሌ ወደብ፣ 57 ሔክታር የሚሸፍን ጠቅላላ የጭነት ቦታ እንዳለው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ትልልቅ ብትን ጭነቶች የሚስተናገዱበት 20 ሔክታር የሚሸፍን ስፋት ያለው ተርሚናል፣ እንዲሁም 23 ሔክታር የሚሸፍን የኮንቴይነር ማስተናገጃ፣ 15 ሔክታር የተሽከርካሪ ጭነቶች (ሮሮ) መጫኛና ማውረጃ ቦታን ጨምሮ 35 ሺሕ ካሬ ሜትር የማከማቻ መጋዘንና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎችን አካቷል፡፡ ይህ ወደብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ የበቃው ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ሲያስተናግድ የቆየው የጂቡቲ ወደብ እያደገ በመጣው ከፍተኛ ጭነት ሳቢያ እየተጣበበ በመምጣቱ፣ አዳዲስ ወደቦችን ለመገንባት መነሳቱን የጁቡቲ መንግሥት ይፋ ካደረገ ከአራት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና የሚያስፈልገውን መጠን ያህል ገንዘብ ሊያገኝ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በወደቦቹ ግንባታ መጓተት መከሰቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

በየዓመቱ በጂቡቲ ወደብ የሚስተናገዱና ትራንዚት የሚያደርጉ መርከቦች ቁጥር በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የሚገልጸው የጂቡቲ መንግሥት ከእስያ፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ አገሮች የሚመላለሱ ከ30 ሺሕ በላይ መርከቦችን በማስተናገድ የ20 በመቶ ጭማሪ የሚታይበት ከ5.7 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት በየዓመቱ በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የዶራሌ ወደብን የገነባው የቻይናው መርቻንት ሆልዲንግስ ኩባንያ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በሽርክና መሥራት የጀመረው ከአራት ዓመታት በፊት ነው፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነውን የንግድ መርከብ ድርጅትን የ40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ጥያቄ አቅርቦ ድርድር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ምንም እንኳ የጂቡቲ መንግሥት ተጨማሪ አራት ወደቦችን በማዘጋጀት በአብዛኛው የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ዕቃዎች በቅልጥፍና ለማስተናገድ ያለውን ፍላጎት በተግባር እያሳየ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች አገሮች የሚገኙ አማራጭ ወደቦችን ማፈላለጉን አልገታም፡፡ በቅርቡ ይፋ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፣ በሶማሌላንድ በሚገኘው የበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ በመግዛት በወደቡ የባለቤትነት ብቻም ሳይሆን የተጠቃሚነት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሱዳን በሚገኘው ፖርት ሱዳን ወደብም ከፍተኛ የማዳበሪያ ጭነቶችን ማስገባት ከጀመረ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ሪፖርተር  ዘግቧል፡፡

ከ900 ሺሕ ያነሰ ሕዝብ ያላት ጂቡቲ ለወደቦች፣ ለባቡር፣ ለመንገድ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይልና ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ጋር ለምትገናኝባቸው መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ በጠቅላላው 14 ቢሊዮን ዶላር ያህል በጀት መመደቧ ሲታወቅ፣ በአብዛኛው ከቻይና መንግሥት በምታገኘው ፋይናንስ እንደሚሸፈኑ ይታወቃል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት በጠቅላላው የ15 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል በመመደብ የሚካሂዳቸው የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታዎች አማካይነት፣ አገሪቱን በአፍሪካ ቀንድ የመልቲሞዳል ሎጂስቲክስ ማዕከል የማድረግ ዓላማ እንዳነገበም አስታውቋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች