Wednesday, April 17, 2024

የተዳከሙ ሲቪል ማኅበራትን መልሶ የማጠናከር አንገብጋቢነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ሲቪል ማኅበራት›› የሚለው ቃል የተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ላላቸው ሰዎች ጭምር በጣም የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና የቃሉ ትክክለኛ ትርጉምና በውስጡ የሚካተቱ ወይም የማይካተቱ ጉዳዮችን በተመለከተ የተለያዩ አረዳዶች አሉ፡፡

ሲሳይ ዓለማሁ (ዶ/ር) “CSO Law in Ethiopia: Considering its Constraints and Consequences” በሚል ርዕስ ባሳተሙት የምርምር ሥራ፣ ሲቪል ማኅበራት በቤተሰብና በአገር መካከል ያለውን ቦታ ለመድፈን የሚችሉ በርካታ ጉዳዮችን እንደሚያካትቱ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በጎ አድራጎትና የውትወታ ድርጅቶች፣ የባህልና ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች፣ መደበኛ ያልሆኑ ማኅበረሰባዊ ቡድኖች፣ የወጣትና የሴት ድርጅቶች፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የንግድና የሙያ ማኅበራትና ሚዲያ እንደሚካተቱ ዘርዝረዋል፡፡

አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል ዕውቅ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ብዙዎች በኢቲቪ/ኢቢሲ በሚያቀርቡት ‹‹ችሎት›› ፕሮግራም ያውቋቸዋል፡፡ አቶ ደበበ በሲቪል ማኅበራት አመራርነት ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ከመንግሥት ጋር ለመነጋገር ባደረጉት ጥረት ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ለአቶ ደበበ ሲቪል ማኅበራት ማለት መንግሥት ፍላጎት በማጣት ወይም በአቅም ማነስ ሊደርስባቸው የማይፈልጋቸው ወይም የማይችላቸውን ነገሮች፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ትርፍ የማያገኝባቸው ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ተቋማት ናቸው፡፡

አንዳንድ ጥናቶች በሲቪል ማኅበራትና በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ልዩነት ይፈጥራሉ፡፡ በ1999 ®.ም. የወጣው ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው የኢሕአዴግ ሰነድ፣ በሲቪል ማኅበራት ላይ ገዥው ፓርቲ ያለውን አቋም ይተነትናል፡፡ በኢሕአዴግም አረዳድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአብዛኛው የገንዘብ ምንጫቸው ከውጭ የሚገኝ ዕርዳታ በመሆኑ ድርጅቶቹ የጥቅም ትስስሮችን የሚፈጥሩና የኪራይ ሰብሳቢ መንግሥት ግልባጭ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) በምንም ተዓምር ዜጎች የራሳቸውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በአባልነት ተሰባስበው የሚፈጥሯቸው ድርጅቶች አይደሉም፡፡ የተወሰኑ ዜጎች ራሳቸውን አደራጅተው ፕሮጀክት እየቀረፁ ለዕርዳታ ሰጭዎች በማቅረብ የራሳቸውን ኑሮ በማሻሻል እግረ መንገዳቸውን ዕርዳታ በተገኘበት ጉዳይ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱባቸው አካላት ናቸው፡፡ አጀንዳቸውን የሚወስኑት ዕርዳታ ሰጭዎች እንጂ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ ስለሆነም የዴሞክራሲያዊ አሠራር ባህሪና ሚና ያላቸው ተቋሞች ሊሆኑ አይችሉም፤›› ሲልም የገዥው ፓርቲ ሰነድ ያትታል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የብዙኃን ማኅበራት የዜጎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብትና ጥቅምን ለማሰባሰብና የተወሰኑ አማራጮች በፖለቲካ መድረክ እንዲቀርቡ የማድረግ ድርሻ እንዳላቸው፣ ዜጎች በመብትና በጥቅማቸው ዙሪያ እየተወያዩና እየተከራከሩ፣ መሪያቸውን እየሾሙና እየሻሩ ዴሞክራሲን የሚማሩባቸው መድረኮች መሆን እንደሚችሉ፣ እንዲሁም አባሎቻቸውን ወክለው ከመንግሥት ጋር በመደራደር መንግሥት ለሕዝቡ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ እንደሚችሉ ያስገነዝባል፡፡ ‹‹በውጭ ዕርዳታ ላይ የተመሠረቱ፣ መንግሥት አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው ብሎ ሲያምንባቸው ወይም ቢያንስ ከፍተኛ ጉዳት አያስከትሉም ብሎ ሲያምን የሚፈቅድላቸው፣ በተለያዩ ሥራዎች ሊሰማሩ ቢችሉም በዴሞክራሲ መድረክነት ዕውቅና የማይሰጣቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአባላት የገንዘብና የጊዜ መዋጮ የሚሠሩት ግን የዜጎች የመደራጀት መብት መገለጫ በመሆናቸው መንግሥት ሲፈልግ የሚዘጋቸው ሳይሆኑ፣ በወንጀል ተግባር ላይ መሰማራታቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ካልተዘጉ በስተቀር ህልውናቸው የተረጋገጠ ማኅበራት እንዲሆኑና በዴሞክራሲ መድረክነትም እንዲታወቁ ማድረግ አለበት፤›› ሲልም ሰነዱ አቅጣጫ አመልክቶ ነበር፡፡

የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሰነዶች ሲቪል ማኅበራት ለአንድ አገር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሕይወት እምርታ ማሳየት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል በመርህ ደረጃ ሲቪል ማኅበራት የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ከምዕራባዊያን ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻል ይጠቅሳል፡፡ ይኼው ሰነድ ማኅበራቱ፣ ‹‹መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ተግባራት፣ ወዘተ ተከታትለው ከእነሱ መብትና ጥቅም አኳያ ይወያያሉ፣ መሻሻል መስተካከል አለበት የሚሉትን ለይተው ያቀርባሉ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች አካላትም ጋር ይደራደሩበታል፣ ይታገሉበታል፡፡ የብዙኃን ማኅበራት መንግሥት በሕዝቡ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ረገድም ሆነ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚታዩ የጥቅም ግጭቶችን የራሳቸውን ጥቅም አሳልፎ በማይሰጥና ጥቅሞችን ለማጣጣም በሚያግዝ መልኩ ለመፍታት ያገለግላሉ፤›› ሲል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታቸውን ይዘረዝራል፡፡

ይሁንና ማኅበራቱ እነዚህን ጠቀሜታዎች ለመስጠት የሚችሉት ዜጎች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በራሳቸው ተነሳሽነት የሚፈጥሯቸው፣ በአባላት መዋጮና ተሳትፎ የሚንቀሳቀሱ፣ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን የሚንቀሳቀሱና መሪዎቻቸውን ራሳቸው መርጠው የሚያንቀሳቀሱ ማኅበራት ሲሆኑ ብቻ እንደሆነም ያሰምርበታል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲቪል ማኅበራት የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ወሳኝ ድርሻ መጫወት እንዳልጀመሩ ይደመድማል፡፡

ይህ ሰነድ የዛሬ አሥር ዓመት ይፋ የሆነውና የገዥው ፓርቲ አባላት የመከሩበት ከምርጫ 97 በኋላና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ነው፡፡ በሰነዱ የሠፈሩት አብዛኛዎቹ ሐሳቦችም የሕጉ አካል ሆነዋል፡፡

የሲቪል ማኅበራት ጉዳይ ከ1997 ®.ም. በፊት ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ዘርፉን የሚመራ የሕግ ማዕቀፍም አልነበረም፡፡ በመሠረቱ በአገሪቱ ታሪክ ሲቪል ማኅበራት ጠንካራ መሠረት ያላቸው ተቋማትም አይደሉም፡፡ እንደ ሲሳይ (ዶ/ር) ገለጻ በአገሪቱ ረሃብ በ1960ዎቹና 70ዎቹ ሲከሰት እሱን ለመቋቋም መንግሥት ሲያቅተው ዕርዳታ ለመስጠት የመጡ የልማት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፣ እንደ መጀመሪያ ሲቪል ማኅበራት በአገሪቱ የተቋቋሙት፡፡

ይሁንና ከ1983 ®.ም. በኋላ በኢሕአዴግ አመራር በአገሪቱ የተፈጠረው የሕግና የፖለቲካ ሁኔታ ለሲቪል ማኅበራት ዘርፍ መስፋፋት በአንፃራዊነት ምቹ የሆነ ነው፡፡ በ1987 ®.ም. ወደ ሥራ የገባው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም የመደራጀት መብትን ጨምሮ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶችን በስፋት ያቀፈ መሆኑ ተጨማሪ ማትጊያ ሆኗል፡፡ ሲሳይ (ዶ/ር) እነዚህ ሁኔታዎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ ሲቪል ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ የንግድ ምክር ቤቶችና ጥቂት ውትወታ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ ማስቻላቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ በ1992 ®.ም. 310 የተመዘገቡ አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት ነበሩ፡፡ ይሁንና አብዛኛዎቹ በአገልግሎት አሰጣጥና በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ በሰብዓዊ መብትና በአስተዳደር ውትወታ ላይ የተሰማሩት በጣም ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ የሆነው መንግሥት በዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ስለሚጠላ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የ1997 ምርጫ እስኪመጣ ድረስ የሲቪል ማኅበራት በአንፃራዊ ሁኔታ የነቃ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፖለቲካ ተንታኝ ከ1983 ®.ም. እስከ 1997 ®.ም. ድረስ በኢትዮዽያ በሥራ ላይ የነበሩ ሲቪል ማኅበራት ቁጥራቸው ብዙ የሚባል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹የነበራቸውም የገንዘብ አቅምና የሰው ኃይል የተሻለ ነበር፡፡ በአንፃራዊነት የሚያሠራ ከባቢ ሁኔታ ነበር፡፡ ለአንዳንድ ልዩ ጉዳዮች በመቆምና በሕግና በፖሊሲ ላይ ለውጥ ለማምጣት ጫና የመፍጠር ትልቅ ሚና ነበራቸው፤›› ብለዋል፡፡

በከፊል የነበረውን የሕግ ማዕቀፍ እጦት ለመቅረፍ በ2001 ®.ም. የበጎ አድራጎትና የሲቪል ማኅበራት አዋጅ ወጣ፡፡ ይሁንና በሥራ ላይ ያለው ሕግ እንዲወጣ ለመንግሥት መነሻ ሆነዋል ከሚባሉት ምክንያቶች አንዱ፣ በምርጫ 97 ብዙዎቹ መብት ላይ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ለቅንጅት ድጋፍ ሰጥተዋል ተብሎ መታመኑ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞችና የተለያዩ የጥናት ሥራዎች ያመለክታሉ፡፡

ፖለቲከኛ ማኅበራት

በሲቪል ማኅበራቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ግለሰቦች በምርጫው ዕጩ ሆነው መቅረባቸው መንግሥትን ይበልጥ እንዳስከፋው በበርካታ ሪፖርቶች ተጠቅሷል፡፡ በወቅቱ ገዥው ፓርቲ ቅሬታውን ሲገልጽላቸው፣ ‹‹ሥልጣን ለመያዝ አንታገልም እንጂ አንድ ፓርቲን መደገፍ አንችልም ማለት አይደለም፤›› ብለው እንደመለሱለትም ይነገራል፡፡

አቶ ደበበ በአፍሪካ ብዙዎቹ ሲቪል ማኅበራት ሲፈጠሩ አፈጣጠራቸው ከመብት ሥራ ጋር የተያያዘ እንደነበር ያስገነዝባሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ አፈጣጠራቸው ከዕርዳታና ከበጎ አድራጎት ጋር የተያያዘ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹በኢትዮዽያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (ኤንጂኦስ) ከስንዴና ከዘይት ጋር ተያይዘው ነው የሚታወሱት፡፡ መብትን ከማስከበርና ከሥነ ዜጋ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ አይደሉም፡፡ አንዱ መሠረታዊ ችግርም ይኼው ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ መብት ላይ የሚሠሩ እንደ ኢሰመጉ፣ አፓፕና ኢውላ የመሳሰሉ ሲቪል ማኅበራት ብቅ ማለት የጀመሩትም ሆነ መብዛት የጀመሩት ከ1983 ®.ም. በኋላ ነው፡፡ ‹‹ቁጥራቸው ብዙ አልነበረም፡፡ አዋጁ በወጣበት በ2001 ®.ም. ላይ ከመብት ሥራ ጋር ተያይዞ በሰብዓዊ መብት ላይ ትምህርት ለመስጠት፣ በምርጫ፣ በሴቶችና ሕፃናት መብት ላይ ለመሥራት ተመዝግበው የነበሩት ወደ 125 የሚሆኑ ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጠንካራ የሚባሉት ከአሥር አይበልጡም ነበር፡፡ አጠቃላይ የኤንጂኦዎች ቁጥር ግን ከ4000 በላይ ይገመት ነበር፤›› ብለዋል፡፡   

ሲቪል ማኅበራት የፖለቲካ አቋም ሊኖራቸው አይገባም በማለት የሚቀርበውን ክርክር የማይደግፉ ምሁራን አሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ ሲቪል ማኅበራት በቀጥታ በፓርቲ ተቀጥላነትና በፓርቲ መዋቅር አመራር ሥር አይገቡም ማለት ነው እንጂ፣ ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ የፀዱ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡ 

በእርግጥም ከ1997 ®.ም. በኋላ መንግሥት ሲቪል ማኅበራትን ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች  ለይቶ ለማየት እንዳዳገተው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ከዚያ በኃላ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ ላይ እየሠሩ የቀጠሉት ጥቂት ማኅበራት ብቻ ናቸው፡፡ የተፈጠረው ከባቢ ሁኔታ እንደ ተቋም መቀጠላቸውን ራሱ እንደ ተዓምር እንዲታይ እንዳደረገው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ሕጉ በዋነኛነት የጎዳውም እነዚህኑ ማኅበራት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በመንግሥት ኃላፊዎች የሚነገረው ሕጉ የአብዛኛውን ሲቪል ማኅበራት ጥቅም እንደማይነካ ነው፡፡ እርግጥ አብዛኛዎቹ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ እርሻ ያሉ የልማት ሥራዎች ላይ ነው ትኩረት የሚያደርጉት፡፡

አቶ ደበበ ሲቪል ማኅበራት ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉ ተቋማት እንዳልሆኑ ይቀበላሉ፡፡ ነገር ግን የተደራጁ ሲቪል ማኅበራት ካሉ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የዚህና የዚያ ፓርቲ አባል ነኝ ሳይባባሉ፣ እርስ በርስ ለመነጋገርና ሐሳብ ለመለዋወጥ እንደሚያስችል ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ብዙ ጊዜ ራሱ ተቋም ውስጥ ስላለ የመልካም አስተዳደር ችግር ያነሳል፡፡ የተጠናከረ የሲቪል ማኅበር በሌለበት ሁኔታ ስለመልካም አስተዳደር የፈለግከውን ያህል ብታወራ ለውጥ ልታመጣ አትችልም፡፡ መንግሥት በተቃውሞ የመኖር ባህልን ማወቅ አለበት፡፡ የተለየና የሚቆረቁር ሐሳብ መቀበል መቻል አለብን፡፡ ያን ማድረግ ካልቻልን በወድያኛው ወገን ያለውን ስሜትና ሐሳብ ልናውቅ አንችልም፡፡ ሲፈነዳ አብረን ተያይዘን ነው የምንጠፋው፡፡ ሲቪል ማኅበራት እያንዳንዱ ሰው ምን መብት አለው? ምን ግዴታ አለበት? ሌሎቹንስ ምንድን ነው ማድረግ ያለበት? የሚለውን ማስተማር መቻል አለባቸው፡፡ አሁን ፈሪ የሆነና መብቱን የማያውቅ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ይኼ ችግር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሊፈታ ካልቻለ፣ በዘላቂነት እንደ አንድ ማኅበረሰብ ለመኖር እጅግ ከባድ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በሌሎች አገሮች ሲቪል ማኅበራት ሥልጣን የያዙ አካላትን በማግባባት፣ በመሞገት፣ ሕዝባዊ ግፊት በመፍጠር ለሕዝብ ይበጃል የሚሉት ጉዳይ እንዲከናወን፣ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ያደርጋሉ፣ ይታገላሉ፡፡     

የሕጉ ተፅዕኖ

አቶ ደበበ በመንግሥትና በሌሎች አካላት በወቅቱ በርካታ ልዩነቶች ቢንፀባረቁም፣ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ግን አንኳር እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ አንደኛው መንግሥት የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ሥራ ሊከናወን የሚገባው በዜጎችና በአገር ውስጥ በሚገኝ ገንዘብ ብቻ ነው የሚል አቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ማራመድ መጀመሩ ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 31 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ አቶ ደበበ ሕገ መንግሥቱ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው›› በሚል ያስቀመጠ በመሆኑ ለዜጎች ብቻ የተተወ መብት ነው ለማለት አዳጋች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አንዱ ትልቁ ልዩነትና ዋና አከራካሪ የነበረው ይኼ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላኛው አከራካሪ ጉዳይ ከማኅበራቱ ለሦስት መከፈል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንደኛው ምድብ እዚሁ አገር ውስጥ የተመዘገቡና በአገር ውስጥ በሚገኝ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱ ተካተዋል፡፡ በሁለተኛው ምድብ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የሚባሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገቡ፣ ነገር ግን ከውጭ ገንዘብ የሚቀበሉ ተካተዋል፡፡ በሦስተኛው ምድብ ደግሞ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ተካተዋል፡፡ አቶ ደበበ፣ ‹‹አዋጁ እኮ ድርጅታቸው ከውጭ ገንዘብ ስለሚቀበል ብቻ ኢትዮጵያዊያንን የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በሚል ያስቀምጣቸዋል፡፡ በነዋሪና በዜጋ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤›› ብለዋል፡፡

የዜጎች ሲቪል ማኅበራትን በገንዘብ የመርዳትም ሆነ ያለመርዳት አዝማሚያ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መስፋትና መጥበብ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ መንግሥት ፓርቲና መንግሥትን ሳይለያይ ከነጋዴዎች ጭምር ገንዘብ እየሰበሰበ፣ ሲቪል ማኅበራቱ ከ90 በመቶ በላይ ወጪያቸውን ከዜጎች መሰብሰብ አለባቸው ማለት ፍትሐዊ አይደለም የሚል ነጥብም ይነሳል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የዜጎች የኢኮኖሚ ደረጃ በራሱ መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ገንዘብ ለማዋጣት የሚገፋፋ እንዳልሆነ መረዳት እንደሚቻልም ተከራክረዋል፡፡ 

ሦስተኛው ልዩነት ደግሞ ማኅበራቱ ከሚሠሩት የሥራ ዓይነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ገንዘብ እስካልተገኘ ድረስ ከውጭ በሚገኝ ገንዘብ ከሰብዓዊ መብትና ከዴሞክራሲ ጋር የተገናኘ ሥራ ማከናወን አይቻልም፡፡ አቶ ደበበ፣ ‹‹ሕጉ እያለ ያለው ትምህርት ቤት በመክፈት ወይም ደብተር በመግዛት ትምህርት ቤት እንዲሄድ አድርገው፡፡ ነገር ግን ትምህርት የመማር መብት እንዳለው አትንገረው ነው የሚለው፡፡ የጤና ተቋም መሥርቱ፣ መድኃኒት አቅርቡ፡፡ ነገር ግን ዜጋው የጤና መብት ያለው ስለመሆኑ አትናገሩ ነው የሚለው፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ዜጎች የተሰጣቸውን ብቻ ተመፅዋች እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሕጉ ማኅበራቱ ላይ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል በሚል ባለድርሻ አካላት ሥጋቶቻቸውን ለመንግሥት ለማሳወቅ ቢጥሩም፣ ይህ ማኅበራቱ ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ከራሳቸው የሚመነጭ ችግር የለባቸውም ከሚል እምነት የመነጨ እንዳልሆነ አቶ ደበበ ያስገነዝባሉ፡፡ ነገር ግን የችግሩ መፍቻ መንገድ ሕጉ ብቻ መሆን እንዳልነበረበት ይሞግታሉ፡፡ ‹‹ገንዘብ ከውጭ አታምጡ ከማለት ይልቅ የመጣውን ገንዘብ በዚህ መንገድ ተጠቀሙ ማለት የተሻለ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ 

አቶ ደበበ ራሱን የቻለ ዘርፉን የሚያስተዳድር ሕግ መኖሩ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሕጉ በዋናነት ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንዳመጣም ያምናሉ፡፡ ማኅበራቱ የሚሰበስቡትን ገንዘብ በእርግጥም ለተጠቃሚዎች እንዲያውሉት ከማስቻል አንፃር፣ ከበፊቱ የተሻለ ውጤት መታየቱም እንደማይካድ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ደበበ አብዛኛው ችግር ከአፈጻጸም ጋር የተገናኘ እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡ ሕጉ በሚረቀቅበት ወቅት ሕጉ በምንም ሁኔታ ማኅበራቱን እንደማይጎዳና ችግር እንደማያስከትል መንግሥት በተደጋጋሚ ቃል ይገባ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አሁን በተግባር ግን የታየው በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራት በየዓመቱ ሲዘጉ ነው፡፡ በዋናነት የሚዘጉትም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ለአቶ ደበበ ከማኅበራቱ ይዞታ ጋር የተያያዘው ሌላው ችግር የሚያስተዳድራቸው ኤጀንሲ የሕግ አተረጓጎም ችግር ነው፡፡ በኤጀንሲው የወጡ ደንቦችም በጣም የሚገድቡና የሚከለክሉ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በሕጉ የተነሳ ሲቪል ማኅበራቱ ቁጥር እጅግ እንዳይመናመን ተሰግቶ ነበር፡፡ መንግሥት ግን ሕጉ ተግባር ላይ ከዋለ በኋላ እንዲያውም ቁጥራቸው እንደተበራከተ ይከራከራል፡፡ አቶ ደበበ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ‹‹ይኼ ሐሰት ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ወደ 4,000 የሚጠጉ ሲቪል ማኅበራት ነበሩ፡፡ በቅርብ የወጣ የኤጀንሲው መረጃ የማኅበራቱ ቁጥር 3,300 እንደሆነ ያሳያል፡፡ የሠርተፊኬት ቁጥሩ እንደዛ ሊሆን ይችላል፡፡ መልሰህ ግን ይህን የኤጀንሲውን መረጃ ስትመረምረው የተሰረዙ ጭምር ተካተው ታገኛለህ፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላ ከ1,000 በላይ ሲቪል ማኅበራት ተዘግተዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ቁጥር ከ2,000 አይበልጥም፤›› ብለዋል፡፡   

ከሦስት ዓመት በፊት በአውሮፓ ኅብረት በተደረገና አቶ ደበበ በተካፈሉበት ሲቪል ማኅበራትን የተመለከተ ጥናትም በሥራ ላይ ያሉ ሲቪል ማኅበራት ቁጥር በኤጀንሲው ከሚገለጸው ያነሰ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በሥራ ላይ የነበሩና ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜ የሚቆይ ፕሮጀክት ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ማኅበራት ቁጥር ከ500 እንደማይበልጥ ጥናቱ ደምድሟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 300 የሚሆኑት የውጭ ናቸው፡፡ 

መንግሥት ምን ሊያሻሽል ይችላል?

የፖለቲካ ተንታኙ ሲቪል ማኅበራት የመንግሥት የፖለቲካ መዋቅር መሪና አዝማች መሆናቸው ማቆም እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ሲቪል ማኅበራት በተፈጥሯቸው በአባላት በጎ ፈቃድ የሚመሠረቱ ቢሆንም፣ ለገዥው ፓርቲ ተቀጥላ የሆኑ አንዳንድ ሲቪል ማኅበራት ግን የተመሠረቱት በራሱ በኢሕአዴግ ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው ከሚል ትችት በዘለለ ከአመሠራረታቸው፣ ከገቢ ምንጫቸው፣ ከአመራራቸውና ከእንቅስቃሴ ነፃነታቸው አንፃር በእርግጥም ሲቪል ማኅበራት ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብባቸው የፖለቲካ ተንታኙ ያስገነዝባሉ፡፡ ማኅበራቱ በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የተሻለ ሚና እንዲኖራቸው ከተፈለገ፣ በውስጥ ጉዳያቸው ከመግባት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ሌላ ማንኛውም ኃይል እንዳይነካቸው የሕግ ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባም ያክላሉ፡፡

ከምርጫ 2007 በኃላ ኢሕአዴግና መንግሥት የተለያዩ የብዝኃነት መገለጫዎችን በተሻለ መንገድ ለማስተናገድ ተነሳሽነት እንዳላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ለቃላቸው ታማኝ ሆነው ሚናቸውን ለማስፋት ከተፈለገ በነፃነት እንዲደራጁ፣ እንዲናገሩና እንዲቃወሙ መፍቀድ እንደሚገባ ብዙዎች ያሳስባሉ፡፡

ይህን ለማድረግም ሕጉ ያስቀመጠው የቁጥጥር ሥርዓት ሊላላ እንደሚገባ፣ የሲቪል ማኅበራት ጥፋተኛ ናቸው በሚል እምነት የተቀረፀው የሕግ ማዕቀፍም መሠረታዊ ክለሳ ሊደረግበት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡ ለአብነትም 70/30 የሚተረጎምበት መንገድ ሰፋ ማለት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ፣ ‹‹ለሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ስትሰጥ ከግብርና ከታክስ ግዴታህ ላይ ተቀናሽ እንዲሆንልህ ማድረግ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -