አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ ሠርቶ የሚያሠራው ቢያገኝ የሰው ሀብቷ ተዓምር መሥራት ይችላል፡፡ በጣም ድንቅ የሆነ የአየር ንብረት፣ ክረምት ከበጋ የሚወርዱ ወንዞች፣ እጅግ በጣም ሰፊ ለም መሬት፣ በጣም በርካታ የቱሪስት መስህቦች፣ የምሥራቅ አፍሪካ ገበያ መግቢያ በር መሆኗ፣ ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ፣ የመንገድና የባቡር መሠረተ ልማቶች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ፀጋዎች በአስተማማኝነት ለመጠቀም ደግሞ የተረጋጋ ማኅበረሰብ መኖርና ሰላም ሌላ መገለጫዎች ናቸው፡፡ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት አገር ከተፈጥሮና ከሰው ሠራሽ ዕምቅ ሀብቶቿ በተጨማሪ ተዝቀው የማያልቁ የተለያዩ ማዕድናት በውስጧ ይዛለች፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብም ጥሩ ጅምር አሳይታለች፡፡ ይህንን አጋጣሚና ዕድል በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ግን ወደ ኋላ መመለስ ይመጣል፡፡
መንግሥት አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በማረጋገጥ የተለያዩ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን በመስጠት የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ጥረት ቢያደርግም፣ በዚያው ልክ ደግሞ ኢንቨስትመንቱን የሚያዳክሙ ተግባራት ይፈጸማሉ፡፡ ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆነው የናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ መግለጫ አሳሳቢ ነው፡፡ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ለማቋረጥ እንደሚገደዱ በተወካያቸው አማካይነት ሲያስታውቁ፣ ችግሩን በሚገባ ተገንዝቦ መፍትሔ ማፈላለግ ውስጥ ካልተገባ ለአገሪቱ ገጽታ ጥሩ አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀደም በግርግሩ ጊዜ በንብረታቸው ላይ ውድመት ሲደርስ በአገር የመጣ ነው በማለት የችግሩ ተካፋይ የሆኑ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር፣ አሁን ምሬቱ በዝቶባቸው የተስፋ መቁረጥ መግለጫ ሲያወጡ መደንገጥ ተገቢ ነው፡፡ ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ እወጣለሁ ሲሉ እንኳን ሌሎች የውጭ ኢንቨስተሮችን ለማምጣት ያሉትንም ለማቆየት ከባድ ነው፡፡ መንግሥት ለኢንቨስተሮች ዋስትናና ከለላ እሰጣለሁ ሲል የይስሙላ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ተዘንግቶ ከሆነ ዞር ብሎ ማየት ይሻላል፡፡ መልካም ዕድሎችን ካበላሹ በኋላ መቆጨት ፋይዳ አይኖረውም፡፡
እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስተር መስተናገድ ያለበት በሕጉ መሠረት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ሕጉ ለኢንቨስትመንት የማይመቹ ክፍተቶች ካሉበት እነሱን ማስተካከል ይገባል፡፡ ሕጉ የተሟላ ሲሆን ለአፈጻጸም አያስቸግርም፡፡ ከጎረቤት ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጠብ እርግፍ በሚሉበት በዚህ ዘመን፣ ኢንቨስተሮችን የሚያበሳጩ ድርጊቶችን መፈጸም ተገቢ አይደለም፡፡ ይህች ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ትግል ላይ ያለች አገር በተለመደው ጨዋነት በተሞላበት የእንግዳ አቀባበል ባህል ኢንቨስተሮችን ካላስተናገደች፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው የሚጠባበቁ በርካታ አገሮች ዕድሉን ይጠቀሙበታል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ክፍላተ ኢኮኖሚዎች ውስጥ የሚሳተፉ ኢንቨስተሮች መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ካልተስተናገዱ አማራጫቸውን ይፈልጋሉ፡፡ በእርግጥ ኢንቨስተር እዚህ ሲመጣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ብርቱ ተወዳዳሪ ሆኖ እነሱን መማረክ የሚቻለው ከድጋፍ በተጨማሪ፣ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ባለመፈጸም ጭምር ነው፡፡ ሕግን መሠረት ያላደረጉ ድርጊቶች ሲበራከቱ ኢንቨስተሮች ስለማይመቻቸው ጥለው ይሄዳሉ፡፡
ኢንቨስተሮች ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ፈጣን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት፣ ከሙስና የፀዳ ቢሮክራሲ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ወዘተ. ይፈልጋሉ፡፡ የመንግሥት ተቋማት ጠንካራና ዘመናዊ እንዲሆኑም ይሻሉ፡፡ በብልሹ አሠራሮች ምክንያት መንገላታት አይፈልጉም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ጠቀሜታው ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ለማስተላለፍ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል ቀጥሮ ለማሠራት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት፣ ከውጭ የሚመጡ የፋብሪካ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማዳንና ለመሳሰሉት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይጠቅማል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች በብዛት ሲኖሩ ደግሞ ጥቅሙ እያደገ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው በተለያዩ የኢኮኖሚው ዘርፎች ውስጥ ብዛት ያላቸው የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲገቡ የሚፈለገው፡፡ ይህንን ምኞት ለማሳካት ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ የማግባባት ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ በስንት መከራ የመጣ ኢንቨስተር ሲያኮርፍ ወይም ምሬቱ ጨምሮ በቃኝ ሲል ያስደነግጣል፡፡ በተቻለ መጠን አግባብቶ ሐሳቡን ማስቀየርና ሌሎችን ማሳመን ካልተቻለ ግን አደጋ አለ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከዓለም ዙሪያ በሚመጡ የውጭ ኢንቨስተር መጥለቅለቅ ሲገባት፣ መንግሥታዊ ተቋማት ተጠናክረው ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲኖርባቸው፣ መንግሥት ከሚገመተው በላይ ተንቀሳቅሶ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን እያቀረበ ዓለም ማሰስ ሲኖርበት፣ ሥራ የጀመሩ ኢንቨስተሮችን እግር በእግር በመከተል የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች ማስወገድ ሲገባ ለማመን የሚከብዱ ምሬቶች ይሰማሉ፡፡ ለአገር ማሰብ ማለት የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስከብር ተግባር ማከናወን ማለት ነው፡፡ በአንድ አኩርፎ በሚሄድ ኢንቨስተር ሳቢያ ምን ሊከተል እንደሚችል አለማሰብ ደግሞ ተቃራኒ ነው፡፡ ‹ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ናት› በማለት መፈክር ከመደርደር ይልቅ፣ ለኢንቨስትመንት ፀር የሆኑ መሰናክሎችን ማስወገድ ይሻላል፡፡ በኢንቨስተሮች አካባቢ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ ረጋ ባለ መንገድ በውይይት መፍታት ይቻላል፡፡ ግብታዊነት የተሞላባቸው ዕርምጃዎችን በመውሰድ ማጣፊያው እንዳያጥር፣ ሁሉንም ወገን የሚያግባባ የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ ይጠቅማል፡፡ ሕግ አስከብራለሁ የሚል አካል ከምንም ነገር በላይ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዳይፈጽሙ መከላከል ይኖርበታል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን የአገሪቱን ዕድል የሚዘጋ ነው፡፡ ይታሰብበት፡፡
ሁሌም እንደምንለው ለሕግ የበላይነት ትኩረት ሲነፈግ ሕገወጥ ድርጊቶች የበላይ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት አይኖረውም፡፡ ግልጽነት በሌለበት ደግሞ ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ በደካማ መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ የተሸሸጉ ሙሰኞች ኢንቨስተሮችን አላሠራም ማለታቸው አንሶ፣ የተሽመደመደው ቢሮክራሲ የሚፈጥረው መንገላታት አልበቃ ብሎ፣ ኔትወርክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውኃና ሌሎች አገልግሎቶች እየተቆራረጡ የሚፈጥሩት ችግር ተዘንግቶ፣ በደካማው የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚስተዋለው መንቀርፈፍ ችላ ተብሎ፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሌሉ ተቆጥሮ አሁን እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ መባነን ካልተቻለ ብርቱ ፈተና ከፊት ይጠብቃል፡፡ ይህች አገር ሰላሟ አስተማማኝ የሚሆነውና ወደ ብልፅግና ማምራት የምትችለው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ሲሰፍን ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት የሚገዛ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ እየተንቀረፈፈ ግራ የሚያጋባ ሳይሆን፣ በፍጥነት ምላሽ መስጠት የሚችል አሠራር ወይም ሲስተም ሲኖር ነው፡፡ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ነው፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር እኩል የሚራመዱ የፖሊሲ ማዕቀፎች ሲኖሩ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ኢንተርኔት ሲዘጋ እየታገሱ፣ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ነገን ተስፋ እያደረጉ፣ ንብረቶቻቸው በአደጋ ሲወድሙ ኃላፊ ወይም ጊዜያዊ ነው እያሉ፣ ወዘተ. ጥርሳቸውን ነክሰው ሲሠሩ በመንግሥት መደገፍ አለባቸው፡፡ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የሚያስመርሩ ነገሮች በአስቸኳይ እንዲወገዱ ማድረግና የተቀላጠፈ አሠራር ማስፈን የመንግሥት ወግ መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን ማሰብ መቻል ጠቀሜታው ብዙ ነው፡፡ አለበለዚያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በከንቱ ይበላሻሉ!