Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአሜሪካን ገጽታ አደብዝዟል የተባለው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር

የአሜሪካን ገጽታ አደብዝዟል የተባለው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር

ቀን:

ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ወደ ነበረችበት ኃያልነት መመለስ ቃላቸውና ሕልማቸው ነው፡፡ ‹‹ሜኪንግ አሜሪካ ግሬት አጌይን›› እና ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› በሚባሉት መፈክራቸው የሚታወቁት ትራምፕ፣ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊትም ሆነ ከመጡ በኋላ አሜሪካ በዓለም ያላትን ኃያልነትና ተቀባይነት እንደሚያጠናክሩ ሲናገሩም ከርመዋል፡፡ ቀድሞውንም ቁንጮ የሆነችውን አሜሪካ የንግድና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎቻቸውን በመከለስ ከቁንጮም ቁንጮ ለማድረግ ሲፎክሩ ቢከርሙም፣ ለአሜሪካ ገጽታ ግንባታ የፈየዱት ጉልህ የሚባል አይደለም ተብለዋል፡፡

የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ከተቆናጠጡ አምስት ወራት ቢያስቆጥሩም፣ በእነዚህ ወራት የነበራቸውን አስተዳደር ለመመዘን በጥናት የተካተቱ ሌሎች አገሮች በአሜሪካ ገጽታ ላይ ያላቸው አዎንታዊ እምነት መደብዘዙ ታይቷል፡፡

መቀመጫውን በዋሽንግተን አድርጎ በአሜሪካ ፖለቲካና ፖሊሲ፣ በጋዜጠኝነት፣ በኢንተርኔት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማኅበራዊ፣ በዓለም አቀፍ ዕይታና ልማድ ዙሪያ ጥናት የሚያደርገው ፔው ሪሰርች ሴንተር፣ በዶናልድ ትራምፕ የአስተዳዳር ጊዜ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ በአስከፊ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን በጥናት ማረጋገጡን አሳውቋል፡፡

ጥናቱን ጠቅሶ ቴሌግራፍ እንዳሰፈረው፣ በጥናቱ ከተሳተፉት የተለያዩ አገሮች ዜጎች ብዙዎቹ በትራምፕ አመራር ላይ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ከያዙበት ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ በ37 አገሮችና ዜጎቻቸው ላይ የተሠራው ጥናት፣ ሌሎች አገሮች በአሜሪካ ላይ ያላቸው አዎንታዊ አመለካከት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሁለተኛውን ዙር የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸውን ሊያጠናቅቁ ሲሉ ከነበረው 64 በመቶ ወደ 49 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

በእንግሊዝ ለአሜሪካ ያለው መልካም አመለካከት በኦባማ ሥልጣን ማብቂያ ዘመን ከነበረው 61 በመቶ ወደ 50 በመቶ ወርዷል፡፡ በአሜሪካ ላይ ያላቸው መተማመንና ምልከታ አዎንታዊ እንደሆነ የገለጹ አገሮች ቢኖሩም፣ እንደ ሩሲያ በእጥፍ ለአሜሪካ ያላቸውን መልካም አመለካከት የጨመሩ የሉም፡፡

ሩሲያ በኦባማ ዘመን ለአሜሪካ ያላት አዎንታዊ ሥፍራ 15 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በትራምፕ አስተዳደር ወደ 41 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ቀድሞውንም የአሜሪካ ቀኝ እጅ በነበሩ አገሮች የታየው ደግሞ ከሩሲያ የተለየ ነው፡፡ የአሜሪካ ወዳጆች በአሜሪካ ላይ ያላቸው አመኔታ ተሸርሽሯል፡፡ ቀድሞ የነበራቸው አዎንታዊ አመለካከትም ተበርዟል፡፡

እንደ ጥናቱ፣ የአሜሪካ ጎረቤቶች ሜክሲኮና ካናዳ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ጀርመንና ስፔን ባልተጠበቀ ሁኔታ ለአሜሪካ ያላቸው ሥፍራ ወርዷል፡፡

ትራምፕ በጥር 2009 ዓ.ም. ሥልጣን ሲረከቡ ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› በማለት አሜሪካን ቁንጮ አደርጋለሁ ብለው ቃል ገብተዋል፡፡ በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር መካከል ግንብ እንደሚገነቡ፣ የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደማይቀበሉና ካናዳ፣ ቻይናና ጀርመን ከአሜሪካ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት ፍተሐዊ አለመሆኑን ሲኮንኑም ተደምጠዋል፡፡

በግንቦት 2009 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ባደረጉት ፕሬዚዳንታዊ የውጭ ጉብኝታቸውን ከሳዑዲ ዓረቢያና ከእስራኤል ሞቅ ያለ አቀባበል የተቸራቸው ትራምፕ፣ በሲሲሊ በተካሄደው የቡድን ሰባት ጉባዔ ለመሳተፍ ሲያቀኑ ግን ከአውሮፓ አጋሮቻቸው የተቸራቸው አቀባበል ቀዝቃዛ ነበር፡፡ አሜሪካ ለሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የምትከፍለው መዋጮ ትልቅ መሆኑንና ሌሎች አገሮችም በደንብ ማዋጣት እንዳለባቸው በመናገራቸው፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በካርቦን ልቀት ላይ መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎችና በንግድ ግንኙነት ላይ ከኦባማ የተለየ አቋም ያላቸው ትራምፕ፣ ከአውሮፓ ወዳጆቻቸው እምብዛም ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡

ሰላሳ በመቶ ሜክሲኳውያን ለአሜሪካ አዎንታዊ ምልከታ እንዳላቸው ሲገልጹ፣ ይኼም በኦባማ ዘመን ከነበረው 66 በመቶ ከግማሽ በላይ ያነሰ ነው፡፡ በካናዳና በጀርመን ደግሞ በ22 ነጥብ ቀንሶ በተከታታይ 43 በመቶና 35 በመቶ ሆኗል፡፡

ከአብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች የተገኘ ውጤት የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እ.ኤ.አ. በ2003፣ አሜሪካ ኢራቅን በመውረሯ ከገጠማቸው ውግዘት ጋር የሚነፃፀር ነው፡፡

በተለያየ የዕድገት ደረጃና ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የሚገኙት ላቲን አሜሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና አፍሪካ ለአሜሪካ ያላቸው ቀና አመለካከትም ተሸርሽሯል፡፡

ሩሲያ ግን ለዶናልድ ትራምፕ አስተዳዳር ከኦባማ በተሻለ ከፍተኛ የሆነ መልካም ምልከታ እንዳላት በጥናቱ ታይቷል፡፡ ከኑክሌር ማበልፀግ ጋር ተያይዞ ከኢራን ጋር ስምምነት የደረሱት ኦባማ፣ በእስራኤል ብዙም ድጋፍ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ደግሞ እስራኤል ለትራምፕ አስተዳደር ያላት ቦታ ከኦቦማ ጊዜ የበለጠ ሆኗል፡፡

40,447 ሰዎች የተሳተፉበትና የካቲት 9 እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሠራው ጥናት፣ በትራምፕ አስተዳዳር ላይ ጉልህ አለመተማመን መኖሩን አሳይቷል፡፡ 22 በመቶ ተሳታፊዎች ትራምፕ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች መልካም ነገር ሠርቷል ብለዋል፡፡ ይኼ በኦባማ ዘመን አገሮች ለኦባማ ከነበራቸው 64 በመቶ ዕምነት ሲነፃፀር፣ በጣም ያነሰ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዝቦች በመሪዎች ላይ ያላቸውን እምነት አስመልክቶ የተሠራው ጥናትም፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል የላቀ አመኔታ ያላቸው እንደሆነ አሳይቷል፡፡ መርከል 42፣ የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ 28 በመቶ፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን 27 በመቶ በሚያህሉ ተሳታፊዎች እምነት የሚጣልባቸው ሆነው ሲገኙ፣ የትራምፕ 22 በመቶ ነው፡፡

በዶናልድ ትራምፕ ከማይተማመኑ አገሮች ሜክሲኮ ቀዳሚ አገር ናት፡፡ በሜክሲኮ በትራምፐ ላይ ያለው መተማመን አምስት በመቶ ሲሆን፣ በስፔይን ደግሞ ሰባት በመቶ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በትራምፕ ላይ እምነታቸውን ከፍ ያደረጉት ሩሲያና እስራኤል ናቸው፡፡ ሩሲያ በኦቦማ ዘመን ከነበራት 11 በመቶ በትራምፕ ወደ 53 በመቶ የደረሰች ሲሆን፣ እስራኤል ደግሞ ለኦቦማ በነበራት መተማመን ላይ ሰባት ነጥብ በመጨመር በትራምፕ ላይ ያላትን ዕምነት 56 በመቶ አድርሳለች፡፡

75 በመቶ ተሳታፊዎች ትራምፕን እብሪተኛ ወይም ትዕቢተኛ ሲሏቸው፣ 65 በመቶ የሌሎችን የማይቀበሉ፣ እንዲሁም 62 በመቶ አደገኛ ብለዋቸዋል፡፡ 55  በመቶ ደግሞ ትራምፕን ጠንካራ መሪ ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

76 በመቶ ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር ግንብ እገነባለሁ በማለታቸው ያልተደሰቱ ሲሆን፣ 62 በመቶው ደግሞ ትራምፕ አሜሪካን ዋና ከሚባሉ የንግድ ስምምነቶች ማውጣታቸውን ተቃውመዋል፡፡ 62 በመቶ ደግሞ የሰባት ሙስሊም አገሮች ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ትራምፕ ያቀረቡትን ሐሳብ የኮነኑት  ናቸው፡፡

ጥናቱ በትራምፕ አስተዳዳር ላይ ባብዛኛው አሉታዊ ገጽታ መኖሩን ቢያሳይም፣ በአሜሪካውያን ላይ መልካም ምልከታ መኖሩን አስፍሯል፡፡ 58 በመቶ ተሳታፊዎች ለአሜሪካውያን አዎንታዊ አመለካከት ሲኖራቸው፣ ብዙዎቹ የጥናቱ ተሳታፊ አገሮች ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከዚህ ቀደም ከነበረው ተመሳሳይ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካን ገጽታ ለመገንባት ሌሎች ግብዓቶች ቢያስፈልጉም ዋናውን ሥፍራ የሚይዙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ናቸው፡፡ የሕዝቡ ባህልና አመለካከት ያላቸው ኃይል የሳሳ በመሆኑ፣ የገጽታ ግንባታው የፕሬዚዳንቱን ጠንካራነትና ተወዳጅነት ይፈልጋል፡፡ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በአምስት ወራት ውስጥ የተሠራው ጥናት ለአሜሪካ መልካም ዜና ይዞ አልመጣም፡፡ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ እየደበዘዘ መሆኑንም አሳይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...