Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚያጠግብ እንጀራ!

 በኢትዮጵያ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ሲታሰብ በዘርፉ ከሚጠሩ ቀደምት ባለሀብቶች መካከል አንዱ ሐጂ ቱሬ ናቸው፡፡ የልጅ ልጆቻቸው ወይም ቤተሰቦቻቸውም አዲስ ስለጀመሩትና ወደፊትም ስላሰቡት ቢዝነስ ባለፈው ሳምንት የሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቦናል፡፡

      ስለአዲሱ የቢዝነስ ሐሳባቸውና ቢዝነሱን ለመተግበር የተጓዙበትን ረዥም ርቀት ከማድነቅ በላይ በአገራችን የቢዝነስ እንቅስቃሴ ባህል አንፃር ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላኛው ትውልድ ሥራን ማሸጋገር እምብዛም ባለመለመዱ እንዲህ ባለው መንገድ ተተኪ ማፍራት ብርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለማለት የደፈርኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ በራሳችን ችግር ወይም አስገዳጅ በሆኑ ሁኔታዎች ጠንካራ የሚባሉ ኩባንያዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረው በአንቱታ የምንጠራቸው የእኛ የምንላቸው የቢዝነስ ተቋማት የሌለን በመሆኑ ነው፡፡ በወላጆቻቸው የጀመሩ የቢዝነሶችን ትርጉም ባለው መንገድ ያስቀጠሉም ቢሆኑ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ የሐጂ ቤተሰቦች አያቶቻቸው ወይም አባቶቻቸው ያሳረፉትን መልካም የሚባል የቢዝነስ አሻራ በማሰብ እኛም የድርሻችንን ልንወጣ ነው ሲሉ መደመጡም መልካም ነው፡፡

ስለ ብልፅግናቸው የምናደንቃቸው ምዕራባውያን አገሮች ዛሬ ስመ ገናና የሆኑ ኩባንያዎች ሥር መሠረታቸው ከአንድ ምዕተ ዓመትና ከዚያም በላይ የቆየ ነው፡፡ ቅድመ አያቶቻቸው የወሰዱት ከዚያም በልጅ ልጆቻቸው እየታደሰ አዲስ ነገሮችን እያከሉ በቅብብሎሽ ኩባንያዎቻቸው እየሰፋ መምጣት ዛሬ አገሮቻቸውን አንቱ አስብለዋል፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

እንዲህ ባለው የሥራ ባህል ቅብብሎሽ የመጣ ቢዝነስ ወይም የሥራ ውርስ እዚህ አገር አልተለመደም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ይቆማል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ጭምር ጎድቶናል፡፡ በቅብብሎሽ መሀል ሊጎለብቱ ይቸሉ የነበሩ አሠራሮች እንዲጎድሉብን አድርጓል፡፡

ስለዚህ በቢዝነስ ዓለም የሚደረግ ቅብብሎሽ ለሥራ ፈጠራም፤ ቢዝነሱን በደንብ ለማራመድም ቢሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም፡፡ የሐጂ ቱሬ ቤተሰቦችም በእርግጥ እንደ አያቶቻቸው ሠርተዋል ወይም የእነሱን ፈለግ ተከትለው ጅምሩን አጎልብተዋል ለማለት ቢከብድም የቀደመውን በማሰብ አሁን እያደረጉ ያለውን ሥራ ልናደንቅላቸው ይገባል፡፡

ከዚህ እውነታ ባሻገር የሐጂ ቱሬ ቤተሰቦች የጀመሩትና ለመጀመር ያሰቡት ቢዝነስ በተለይ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የጤፍ ዱቄትና የእንጀራ ገበያ ላይ አንድ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚል ይታመናል፡፡

በተለይ ከዕለታዊ ፍጆታዎች መካከል ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ እየተደረገበት የመጣው የእንጀራ ገበያ በዚያው ልክ አደገኛ ውንብድና የሚፈፀምበት እየሆነ መጥቷል፡፡ የአኗኗር ዘይቤያችን ከመቀየሩ አንፃር እንጀራ ቤት ከመጋገር ከፎቅ ወረድ ብለን እንጀራ በፌስታል አንጠልጥሎ መግባት ተለምዷል፡፡ ሆኖም መደብሮች ገዝተን የምንገባው እንጀራ የተዘጋጀበት ግብዓት ከፉርሽካ ወይም ከሌላ የማናውቀው ባዕድ ነገር የተደባለቀ መሆን አለመሆኑን የማንለይ በመሆኑ በፍራንካችን የገዛነው እንጀራ በሽታ የምንሸምትበት የሚሆንበት አጋጣሚ እየሰፋ ነው፡፡

ቢዝነሱ ከመስፋቱ አንፃር ብዙ ችግሮች እየታዩ መሆኑን በማሰብ መፍትሔ ጤፉን ከፉርሽካና ከሰጋቱራ ቀላቅሎ በድፍረት የሚሸጡ ደፋሮችን ተሸክመን በምንኖርበት አገር ቢያንስ በሕግ የታወቀ እንጀራ ጋግሮ የሚያቀርብ መገኘቱ እንደመልካም ዕድል ሊወሰድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቢዝነሱ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለተበለሻሸው የእንጀራ ገበያ እንደ አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ የጤፍ መፍጫ ማሽኑም በጥራት እስከተዘጋጀ ድረስ የብዙዎችን ድካም ይቀንሳል፡፡ አማራጭ ገበያም ይፈጥራል፡፡

ከአዲሱ ቢዝነስ ከሁሉም በላይ ቀልቤን የሳበው ምናለ እንዲህ በሆነ በሚል ስመኘው የነበረው ነገር ከቱሬ ቤተሰቦች ማግኘቴ ነው፡፡ ይኸውም ጤፋችን ሠልጥና በዘመናዊ መንገድ መፈጨት መቻሉ ብቻ አይደለም፡፡ በእንጀራ ማምረቻው የሚመረተው እንጀራ እንጀራው ከጤፍ ብቻ ሳይሆን የጤፍ ዱቄትን ከተለያዩ እህሎች ጋር በመደባለቅ እንጀራ ጋግሮ ማቅረብ መቻሉ ነው፡፡

ነጭ ካልሆነ ከጉሮሮዬ አይወርድም የምትለዋ ቅምጥል አባባል ዛሬ ዛሬ ቦታ የላትም፡፡ አዳሜ ነጭ እንጀራ አገኘሁ ብሎ የሚበላው የግዥ እንጀራ ሙሉ ጤፍ ስላለመሆኑ ይታወቃል፡፡ እንጀራው ነጭ እንዲሆን ብዙ ግብዓት አለ፡፡ እነ እሩዝ ለዚህ አንድ መላ ናቸው ይባላል፡፡ ሩዝ ከሆነ ክፋት የለውም እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ግን ይህ አይነገረንም፡፡

በረካ የሚል ስያሜ ያለው እንጀራ ግን ከዘንጋዳ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ዘንጋዳና ጤፍ ተደባልቆም እንጀራ ይሆናል፡፡ ከሌላ እህል ጋርም ይደባለቃል፡፡ ይዘጋጃል፡፡

ቁም ነገሩ ግን በዘመናዊ መጋገሪያ የሚወጣው እንጀራ ከምን ምን እደተዘጋጀ የሚገልጽ ዘመናዊ አሠራር ይዞ መቅረቡ ነው ይህ ብቻ አይደለም እንጀራው እንደተዘጋጀበት የእህል ዓይነት የተለያየ ዋጋ ይዞ መቅረብ መቻሉ ነው፡፡ የጤፍ እንጀራና የዘንጋዳ እንጀራ ወይም ከዘንጋዳና ጤፍ ድብልቅ ተዘጋጅቶ የሚሸጥልን እንጀራ እኩል ዋጋ አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ከባዕድ ነገር ተደባልቆ የሚዘጋጅ እንጀራም ሆነ እግዜርን ፈርተው ከንፁህ እህል የተዘጋጀውን እንጀራ በሰመራ እንጀራ በአንድ ዓይነት ዋጋ መግዛት የለብህም፡፡ የገበያ ዋጋ ይወስነዋል፡፡ በእንጀራ ግብይት ላይ እያየን ላለው ክፍተት ጥሩ ምሳሌ የሚሆን መፍትሔ ይሆናል፡፡ ከንፁህም ከድብልቁም ከባዕድ ጋር ተቀላቅሎ የሚዘጋጅና የሚሸጥልን እንጀራ በስመ እንጀራ በአንድ ተመሳሳይ ዋጋ እንዲገዛ ሊያግዘን ይችላል፡፡

እንዲህ ዓይነት የተሻለ አሠራር ሲመጣ የሚገባን የገበያ ዋጋ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቢዝነስ ጋር ተያይዞ ሌላ የታሰበኝ ነገር ከባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ የሚዘጋጅ ምርትን መንደር ለመንደር እያሳደዱ ከመፈለግ እንዲህ በሕግ የሚታወቅ ቦታ ላይ ያለን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ይህም በዘርፉ የተፈጠረ አንድ እመርታ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ቢዝነሶች በሐጂ ቱሬ ቤተሰቦች ብቻ የሚተው ሳይሆን፣ ሌሎችም ቢሳተፉበት መልካም ይሆናል፡፡ እነሱን እንደ ፈር ቀዳጅ ወስደን ተወዳዳሪ የሚቀርብ ከሆነ ደግሞ በተሻለ የምንለው የእንጀራ ግብይት መስመር ማስያዝ ይቻላል፡፡ እንዲህ በተደራጀ መንገድ መምረቻዎች ካሉ ጥራትና ደረጃ ማውጣቱም ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ዛሬ በየመንደሩ ተጋግረው የኮከብ ማዕረግ ተሰጠን ለሚሉ ሆቴሎች ሁሉ የሚያቀርቡ ዜጎቻችንም ቢሆኑ ስብስብ ብሎ በጋራ የሚሠሩበት አሠራር ቢኖር ሕጋዊ ሆነው ቢሠሩና ቢወዳደሩ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት