Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሰሜን ቋንቋዎች እምን ላይ ናቸው?

የሰሜን ቋንቋዎች እምን ላይ ናቸው?

ቀን:

በኢትዮጵያ የጽሕፈት/የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ይነገራል፡፡ በተለይ በዘመነ አክሱም ከመጀመሪያው ምዕት ዓመት ወዲህ የጽሕፈት ባህሉ ከድንጋይ ላይ ተጀምሮ ወደ ብራና መሸጋገሩ በርካታ የጽሑፍ ቅርሶች መያዙም ይታወቃል፡፡ በአክሱም በተለይ በግእዝ፣ በሳባና በግሪክ ቋንቋዎች የተጻፉ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ቆመው ይታያሉ፡፡ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ለ1500 ዓመታት ያህል በሥነ ጽሑፍ ቋንቋነቱ ጎልቶ መዝለቁም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በአክሱም አካባቢ ይነገሩ ከነበሩት ስምንት ቋንቋዎች ውስጥ አንዱ ትግርኛ እንደሆነ፣ በጽሑፍ ደረጃም መስፈር የጀመረው ዘግይቶ መሆኑ ይወሳል፡፡ የትግርኛ በትግርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጁ ካሳ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) ኮንቲ ሮሲኒን ጠቅሰው እንደጻፉት፣ ትግርኛ ከ13ኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ በጽሑፍ ለመስፈር በቅቷል፡፡

ከ15ኛው እስከ 17ኛው ምዕት ዓመታት ባሉት ውስጥ ጎልተው የሚታወቁት ከሕግ ጋር የተያያዙ ጽሑፎች ናቸው፡፡ እነዚህም ‹‹ሕጊ ሎጎ ጭዋ›› (ሓማሴን)፣ ‹‹ሕጊ ሎጎ ሳርዳ›› (ኣከለጉዛይ)፣ በእምባሰነይቲና አካባቢው በሥራ ላይ እንደዋለ የሚነገረው ‹‹ሕጊ ገ/መስቀል›› (ትግራይ) ናቸው፡፡

በዘመናዊ ኅትመት ደረጃ የታተመው የትግርኛ መጽሐፍ በባስል ከተማ (ስዊዘርላንድ) በ1886 ዓ.ም. የታተመው ወንጌል ነው፡፡ ርእሱም ‹‹ወንጌል ቅዱስ ናይ ጐይታና ናይ መድኃኒትና ናይ ኢየሱስ ክርስቶስ ብትግራይ›› የሚል ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ ልደት ግን ከመቶ ሃያ ዓመት ገደማ በፊት እንደሆነ ጀማሪውም ፍሥሐ ጊዮርጊስ ዓቢየ እዝጊ ናቸው፡፡ ኃይለ ሀብቱ (ዶ/ር) የፍሥሐ ጊዮርጊስ ጦብላሕታ የመጀመሪያው የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታቸው፣ ፍሥሐ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ወደ ኢጣሊያ ያደረጉትን ጉዞ የሚያወሳ ነው፡፡ በ1895 ዓ.ም. በሮማ ከተማ የታተመው ‹‹ጦብላሕታ ብዛዕባ ወሬ መንገዲ እንካብ ጦብያ ንኢጣልያ›› በሚል ርዕስ ነው፡፡

እንደ አጥኚው አገላለጽ፣ የጉዞ ማስታወሻዋ እንደ ጉዞ ዘጋቢ መጽሐፍነት ብቻ ሳይሆን እንደ ሥነ ጽሑፍም በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ ከመጀመሪያዎቹ አንዷ ናት፡፡ ስለዚህ ቀዳሚነትዋ ጣልያናዊው ተመራማሪ ላንፍራንኮም ‹‹… ከመላው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ቀዳሚዋ ናት (በትግርኛም ቢሆን በአማርኛ)›› በማለት ገልጸውታል፡፡

አዲሱ የትግራይ ቋንቋዎች አካዴሚ

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ በዋናነት የሚገኙ ሦስት ቋንቋዎች ሳሆ (ኢሮብ)፣ ኩናምኛና ትግርኛ ዙሪያ በተለያዩ የቋንቋና ባህል ዘርፎች ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚያከናውን፣ ቋንቋዎቹም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽንሰ ሐሳብ የመግለጽ አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል አካዴሚ ከሦስት ዓመት በፊት ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የአካዴሚው ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ተኽሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አካዴሚው ዘንድሮ በዕቅዱ መሠረት ሁለት ታላላቅ ብሔራዊ ሲምፖዚየሞችን በዓዲግራትና በአክሱም ከተማዎች አከናውኗል፡፡

ሦስቱን ቋንቋዎች የሚመለከቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ከቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ ከባህልና ፎክሎር ታሪክን ጭምር ያካተቱ ልዩ ልዩ ጥናቶችን በሁለቱ መድረኮች አቅርበዋል፡፡

እንደ አካዴሚው ዳይሬክተር ዳንኤል (ዶ/ር) አገላለጽ በቋንቋዎቹ ሥነ ቃላት ዙሪያ፣ በሥርዓተ ጽሕፈት በተለይ በሳሆና ኩናማ ያሉትን ችግሮች ነቅሰው ያወጡ ጥናቶች ይገኙበታል፡፡

ትግርኛ በአካዳምያዊ ትምህርት እንደ ትምህርት ዓይነትና መማሪያ ሆኖ በደበኛነት የተጀመረው በ1974 ዓ.ም. በትጥቅ ትግሉ ወቅት ነው፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ ቋንቋ (ሳብጀክት) እና እንደማስተማሪያ ቋንቋ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

የትግርኛ ሥነ ጽሑፍ በ13ኛው ምዕት ዓመት እንደተጀመረ የሚያወሱት ዶ/ር ዳንኤል፣ ጉዞው ብልጭ ድርግም እያለ ቆይቶ በ19ኛው ምዓት መገባደጃና በ20ኛው መጀመሪያ እነ ደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ የጻፏቸው ልዩ ልዩ መጻሕፍት ለትግርኛ ሥነ ጽሑፍ ወሳኝ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ያልተሞከረው የጉዞ ማስታወሻ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ ‹‹ጦብላሕታ›› መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በ1900 ዓ.ም. የተጻፈው የግጥም መጽሐፍ ‹‹ብሰንኪ ክልተ አርዌ ተባረአት ምድሪ›› (በሁለት አውሬዎች ምክንያት መሬት ተቃጠለች) ሌላው ሥራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከስድስት አሠርታት በፊት በሮም (ጣሊያን) ሲጀመር ተካፋይ የነበሩት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ (ዶ/ር)፣ በ1922 ዓ.ም. ጽፈውት ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ የታተመው ‹‹ሓዳ ዛንታ›› ልብ ወለድም ይጠቀሳል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) በትግርኛ ከታተመው (1941-1968) የሥነ ጽሑፍ አዝመራ ውስጥ ልብ ወለድ ብቻ 43 መገኘቱን በዘመኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ በዘመነ ደርግ (1967-1983) ውስንነት አለው ይላሉ፡፡

በደርግ ጊዜ መሠረተ ትምህርት በ15 ቋንቋዎች ሲሰጥ አንዱ ትግርኛ ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በአሥመራ ከተሞች መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የትርጉም ሥራዎችም ወጥተው ነበር፡፡ በተለያዩ ዘርፎች በትግርኛ ስለተጻፉ ጽሑፎች በተደረገ ጥናት እ.ኤ.አ. ከ1889 እስከ 1991 486 መጻሕፍት መታተማቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በዘመነ ደርግ ሥነ ጽሑፍ ሁለት ገጽታ በመንግሥት አስተዳደር ሥርና በትጥቅ ትግል ውስጥ ተብሎ እንደሚታይ ያመለክታሉ፡፡

በአንደኛው ጥግ የመሠረተ ትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋነት ባለፈ የታዩ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ውስን ናቸው፡፡ በሌላው ጥግ በትጥቅ ትግል ዘመን (1967-1983) ለትግርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዩ ዘመን እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ዳንኤል፣ ይታተሙ ከነበሩት መጽሔቶችና ጋዜጦች በተጨማሪ በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ታላላቅ ከሚባሉት ሥራዎች መካከል ከእንግሊዝኛ ወደ ትግርኛ 13ቱ ተተርጉመዋል፡፡ የሌቪ ቶልስቶይና የማክሲም ጎርኪ ሥራዎች ይጠቀሳሉ ይላሉ፡፡

አካዴሚው ባካሄዳቸው ሁለት ሲምፖዚየሞች፣ በሳሆና በኩናምኛ ዙሪያ የቀረቡት ጥናቶች ጥቂት መሆናቸው አንዱ ክፍተት ነው፡፡ ወደፊት ከመንግሥትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር 12ኛ ክፍልን ጨርሰው የተቀመጡ የቋንቋዎቹን ተናጋሪዎች በመመልመል፣ በልዩ ሁኔታ የቋንቋ ሳይንስ በማስጠናት እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

እንደ ይይሬክተሩ አገላለጽ፣ ከሦስቱ ቋንቋዎች ሰዋስውን በተመለከተ በደንብ ተጠንቷል ተብሎ የሚታሰበው ትግርኛ ላይ የተሠሩትን ነው፡፡ ሳሆ አካባቢ የተወሰኑ ጥረቶች ቢኖሩም ኩናምኛ ግን ብዙ ነገር ይቀራል፡፡ አካዴሚው ሲቋቋም ዓላማዬ ካላቸው አንዱ የሦስቱ ቋንቋዎች ሰዋስው በስፋት በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና ማስቻል ነው፡፡ የተጻፉ መጻሕፍት፣ የተሠሩ ጥናቶች ቢኖሩም በመማር ማስተማር ሒደት፣ በሚዲያና በመሥሪያ ቤቶች አካባቢ ውጥንቅጥ አካሄድ ነው እንዳለ ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ይህም የግንዛቤ ችግር የፈጠረው መሆኑ በመረዳት በሒደት የሚስተካከል ይሆናል ብለዋል፡፡

‹‹ችግሩና ክፍተቱ በሰዋስው ብቻ አይደለም፡፡ ትግርኛ የመግለፅ ብቃቱ የለኝም ሳይል የትግርኛ ቃላትን እየተውን ቃላትን እየቀላቀልንና በሌሎች እየተካን ነው፡፡ በሳሆና በኩናምኛም ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት አካዴሚው የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡››

አካዴሚው በአክሱም ባካሄደው ሁለተኛው ሲምፖዚየሙ፣ በጥር ወር አካሂዶት በነበረው የመጀመሪያው ሲምፖዚየሙ ከቀረቡት ጥናቶች መካከል የመረጣቸው በመድበል ማሳተሙ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...