Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከረመዳን ከሪም እስከ ኢድ

ከረመዳን ከሪም እስከ ኢድ

ቀን:

‹‹ቁርዓን የዚህች ዓለም ሕይወት መመሪያ ነው፡፡፡ ቀጥተኛና ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ ቁርዓን ለያዘውና ለተገበረው ቀናኢ መንገድ ነው፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍ የሚለውን ተከትሎ የተፈቀደውን (ሀላሉን) ላደረገ፣ የተከለከለውን (ሀራሙን) ለራቀ ብርሃን ነው፡፡በእውነትና በውሸት መካከል ያለውን የሚለየው ቁርዓን ነው፡፡ ቁርዓን ቧልት ሳይሆን ጥብቅ ቃል ነው›› ልዩ የረመዳን መግለጫዎች በሚል በአንድ እስላማዊ ድረ ገጽ ላይ ከሠፈረ ጽሑፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

የእስላም መሠረት የሆነው ቁዱስ ቁርዓን የወረደው በረመዳን ወር ነው፡፡ በጨረቃ ቀን አቆጣጠር ዘጠነኛ ላይ የሚውለው የረመዳን ወር፣ በሀይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ የወራት ሁሉ ቁንጮ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ከእስላም ማዕዘናት አንዱ የሆነው ፆም የሚተገበረውም በዚሁ በረመዳን ወር ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ወር የጀነት (የገነት) በሮች ይከፈታሉ ሰይጣንም ይታሠራል፡፡ መልካምነት ጎልቶ የሚሠፍንበት፣ የፈጣሪ ምሕረት የሚበዛበት ወር ነው፡፡ ረመዳን ክፉ ማሰብና መጣላት ቀርቶ የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት መልካም ወር ነው፡፡

ሰዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፆም በፀሎት የሚያስቡበት ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርቡበት ወር እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሚዋሽ የሚቀጥፍ በረመዳን ይታረማል፡፡ በረመዳን ወቅት ሁሉም ሙስሊም ለፈጣሪው ታማኝ ለመሆን ይጥራል፡፡ ከወትሮው በተለየ በጀመአ መስጊድ ሄዶ ሶላት ያደርሳል፡፡ ወንዶቹ ጀለቢያ መልበስ ያዘወትራሉ፡፡ ሴቶቹም እንደዚሁ ከሌላው ጊዜ በተለየ አለባበሳቸው የእስልምና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ እንዳይሆን አብዝተው ይጠነቀቃሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በፆም በፀሎት ፈጣሪን ከማሰብ ባለፈ ያለው ለሌለው የሚረዳበት ዘካ (ምፅዋት) የሚያወጣበት ወር ነው፡፡ እስላማዊ አገሮች በረመዳን ምእመናን ፀሎት የሚያደርጉበት በቂ ሰዓት እንዲያገኙ በማሰብ የሥራ ሰዓት ከሌላው ጊዜ በተለየ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡

የእስልምና እምነት ተከታዮች የዚህን ወር መግባት በጉጉት ይጠባበቁታል፡፡ ረመዳን ሊገባ ቀናት ሲቀሩት ሞቅ አድርገው ለመቀበል ተፍተፍ ማለት ይጀምራሉ፡፡ ዝግጅቱ ቤት ከማፅዳት ይጀምራል፡፡ ብዙዎች ቤታቸውን በአይነግቡ ምንጣፎች ያስውባሉ፡፡ በተቻላቸው ሁሉ በመልካም መንፈስ ወሩን ለመቀበል ይጥራሉ፡፡ በረመዳን ወር ሰላምታው ሳይቀር ‹‹ረመዳን ከሪም›› መልካም ረመዳን በሚል ይቀየራል፡፡

ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ ወር ለምግብነት የሚውሉ ነገሮችም ከወትሮው የተለዩ ናቸው፡፡ ማዕዱን የሚሞሉት ሳንቡሳ፣ ኩኪስ፣ ቴምር፣ ሾርባና ሌሎችም ጣፋጭ ምግቦች  ናቸው፡፡ ወሩ ለሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታዋቂ ነው፡፡ ቴምር፣ ሳንቡሳና ሌሎችም የረመዳን የፈጥር ምግቦች ረመዳን በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለየ ቦታ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡

ሾርባና ሌሎች የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችም የረመዳን ድምቀት ናቸው፡፡ በፈጥር ሥነ ሥርዓት ላይ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችም አብረው ሲቀርቡ ይታይል፡፡ ቀኑን ሙሉ ተዘግተው የሚውሉ የሙስሊም ሬስቶራንቶች አመሻሽ ላይ ሲከፈቱ፣ ያለሃይማኖት ልዩነት ብዙዎች በፆም ወቅት የሚዘጋጁ ምግቦችን ለመቋደስ ከሬስቶራንቶቹ ሲታደሙ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡

 በተለይ ቴምር የረመዳን ወር ገበያ ላይ በገፍ ይወጣል፡፡ በሌላው ጊዜ ቴምር ቢያሰኝዎ በቀላሉ ለማግኘት ይቸገሩ ይሆናል፡፡ በረመዳን ግን ቴምር እንደልብ ማግኘት ይቻላል፡፡  ከተለያዩ አገሮች የሚገባው ቴምር እንደ ሸማቹ አቅም በችርቻሮና በኪሎ ይሸጣል፡፡ ቀኑን ፆመው ውለው በሦስት ቴምር ማፍጠር ሱና (ደንብ) ነው፡፡ ለዚህም ለፈጥር ከሚዘጋጀው ገበታ ጎን ቴምርም አብሮ ይቀርባል፡፡

ከሕፃናት፣ ከሕመምተኞች፣ የወር አበባ ላይ ከሚገኙ ሴቶቸ፣ ከመንገደኞች በስተቀር ከአምስቱም የእስላም ማዕዘናት አንዱ የሆነውን የረመዳን ፆም መፆም የማንኛውም ሙስሊም ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን ወሩ ይዞት ከሚመጣቸው ትሩፋቶች አንፃር ምዕመናኑ እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ ሽልማት በጉጉት ይቀበሉታል፡፡

በተለያዩ ሁኔታዎች እንዳይፆሙ የተፈቀደላቸው ሰዎች እንኳን በተቻላቸው መጠን ለመፆም ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በተለይ አቅማቸው ያልደረሰ ህፃናት ከታላላቆቻቸው በመፎካከር ካልፆምን ብለው ወላጆቻቸውን ሲያስቸግሩ ማየት ፈገግ ያሰኛል፡፡ ወላጆች አንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው በመላ ሊያበሏቸው ይሞክራሉ፡፡ ከዚያ ሲያልፉም በልመናና በልምምጥ እንዲበሉ ይደረጋ፡፡ ከፍ እያሉ ሲመጡ ግን በቀን ውስጥ እስከ ተወሰነ ሰዓት ይፆማሉ፡፡

ነፍስ እስኪያውቁ ድረስ ቀኑን ሙሉ ለመፆም በሚያደርጉት ጥረት የተለያዩ ነገሮች አጋጥሟቸው ፆሙን ሊያፈርሱ ይችላሉ፡፡ ፆመኛ መሆናቸውን ዘንግተው አንድ ሁለት የሚጎርሱ፣ ውኃ የሚጠጡ ያጋጥማሉ፡፡ በተለይ ሦትና አራት ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ረመዳን ልዩ ድባብ ይኖረዋል፡፡ እርስ በርስ ያለው ፉክክር ደስ ያሰኛል፡፡ ስንት ቀን ፆምክ? ስንት ቀን ፆምሽ? እየተባባሉ ይጠያየቃሉ፡፡ የተበለጡት እልህ ይይዛቸዋል፡፡ ላለመበለጥ ሲሉ ያልፆሙትን ፆመናል ብለው ጨምረው የሚናገሩ ልጆችም ያጋጥማሉ፡፡ ከዘህ ባሻገር ረመዳን በልጆች ዘንድ የተለየ ቦታ አለው፡፡ የቱንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፉ በረመዳን እጁን የሚያነሳባቸው፣ የሚቆጣቸው የለም፡፡ ወላጆች ሰከን ብለው ከመምከር ባለፈ ዱላ አይቃጡም፡፡

ረመዳን ሊገባ ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ በየሲዲ መሸጫ ቤቶች የሚከፈተው መንዙማም ሌላው የረመዳን ድምቀተት ነው፡፡ ድምፃውያኑም አዲስ መንዙማ የሚያወጡት በረመዳን ወር ነው፡፡ ወሩ እስኪያልቅ ድረስም ተደራርበው የወጡ አዳዲስ መንዙማዎች በየመንገዱና በየቤቱ ይደመጣሉ፡፡ ድምፃውያን ታዲያ ነገሮች አልባ ባልጋ አይሆኑላቸውም፡፡ ከመንፈሳዊ ጥቅሙ ባሻገር የሚገባቸውንና በኢንዱስትሪው ለመቆየት የሚያስችላቸውን ያህል ገንዘብ አያገኙበትም፡፡ ብዙ ጊዜም ረመዳን በመጣ ቁጥር ያዘጋጁትን መንዙማ ለማሳተም አቅም አጥሯቸው እንደሚቸገሩ  ይናገራሉ፡፡

በረመዳን ፈጣሪውን ለማመስገን ወደ መስጊድ የሚነጉደው ሰው ብዛትም የተለየ ነው፡፡ በተለይ ከፈጥር ሰአት በኋላ መንገዶች ወደ መስጊድ በሚሄዱ ምእመናን ይሞላሉ፡፡ ምሽት ላይ ከየመስጊዱ የሚሰማው ፀሎት ሌላው የረመዳን መገለጫ ነው፡፡  

በረመዳን ወር በመጨረሻዎቹ አሥር ሌሊቶች እየሰገደ ያሳለፈ ሰው ቀደም ሲል የሠራቸው ወንጀሎች እንደሚማሩለት፣ ከእነዚህ አሥር ቀናት ውስጥ በየትኛው እንደሆነ ባትታወቅም የዓመቱ ትልቅ ሌሊት እንደሚገኝና በዚህ ሌሊት የሚሠራ መልካም ሥራ ለረዥም ዓመታት ከሚሠራ መልካም ሥራ በተለየ ሚዛን እንደሚደፋ ይታመናል፡፡

ረመዳን ሊጠናቀቅ ባሉት የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት አብዛኞቹ ምዕመናን ‹‹ኢዕቲካፋ›› ያደርጋሉ፡፡ ኢዕቲካፋ ማለት ማንኛውንም ዓለማዊ ነገር ወደ ጎን ብሎ ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ ለተወሰነ ጊዜ መስጊድ ውስጥ መቆየት ነው፡፡ ኢዕቲካፋ ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡ ባለመፈጸሙ የሚያስቀጣ ባይሆንም ቢያደርጉት ግን ምንዳ አለው፡፡

 ሌላው በረመዳን መገባደጃዎቹ ቀናት የሚከናወነውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ‹‹ዘካቱል ፈጥር›› ነው፡፡ ዘካቱል ፈጥር ለችግረኞች የሚሰጥ ምፅዋት ሲሆን፣ ሁለት ፊይዳዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ለፆሙ እንደማሟያና መጠገኛ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ችግረኞች በበዓሉ ዕለት ለልመና ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ምዕመን ምንም እንኳን ፆሙን ቢፆምም ዘካቱል ፈጥር እስካላወጣ ድረስ ፆሙ በሰማይና በምድር መሀል ተንጠልጥሎ እንደሚቀር የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡

በዚህ መልኩ በለጋስነት በርህራሄና በሰላም ደምቆ የረከመው ረመዳን ሲጠናቀቅ ደግሰው እንደተቀበሉት ደግሰው ለመሸኘት ሌላ ሽር ጉዱ ይጀመራል፡፡ አከባበሩ ከቦታ ቦታ የተለያየ ነው፡፡ የኢድ አልፈጥርና ሌሎችም የእስልምና ዕምነት በዓላት አከባበር የሚወሰነው ከጨረቃ ጋር ተያይዞ በመሆኑ፣ በዓሉ የሚውልበትን ቀን ቀድሞ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ይህም የበዓሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ብዙዎቹ ቀድሞ መዘጋጀትን ይመርጣሉ፡፡ በተቻለ መጠን ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮችን ቀድሞ ለማዘጋጀት ጥረት ይደረጋል፡፡ በትክክል በዓሉ የሚውልበት ቀን ሲታወቅም የተቀሩት ሥራዎች እንደ ቤት ማጽዳት፣ ልዩ ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀት፣ በዕለቱ የሚኖሩ ፕሮግራሞችን ማውጣት ይጀመራል፡፡ ይህም የሚሆነው ጨረቃ ሙሉ ሆና ስትወጣ ነው፡፡

ጨረቃ በወጣችበት ምሽት በረመዳን ወር ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት የሚሰገደው የአተራዊ ሶላት አይኖርም፡፡ ምዕመናን የበዓሉ ዕለት ጎህ ሲቀድ በሦስት ቴምር አፍጥረው ሶላት በጀመአ ወደሚሰገድበት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ስቴዲየም አልያም ወደ መስጊድ ያመራሉ፡፡

ለምስኪኖች ዘካ መስጠት በኢድ አልፈጥር በዓል ከሚከናወኑ ድርጊቶች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ይኼ ለምስኪኖች የሚሰጠው ዕርዳታ በሁለት መንገድ ይከናወናል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ዘካቱል ማል›› የሚባለው ሲሆን፣ አንድ ሰው ከ80 ግራም በላይ ወርቅ ካለው 2.5 የሚሆነውን ለችግረኛ እንዲሰጥ የሚገደድበት ነው፡፡ በወርቅ የተተመነውም የግለሰቡ አጠቃላይ ሀብት ድምር ነው፡፡ ሌላው ‹‹ዘካቱል ፊጥር›› ነው፡፡ ይህ የዕርዳታ አሰጣጥ ሥርዓት አንድ የሃይማኖቱ ተከታይ ከመደበኛ ቀለቡ ላይ ሁለት ኪሎ ተኩል የሚሆነውን ቀንሶ የሚሰጥበት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ለምስኪኖች የሚደረገው ዕርዳታ በዓሉን አለምንም ችግር እንዲያከብሩ ያስችላል፡፡ ከቤት ቤት በመዘዋወር የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት መግለጫ (ዚያራ) ሥርዓትም የክብረ በዓሉ አካል ነው፡፡ የቅርብ ዘመድ ወዳጅና ጎረቤትም ይዘየራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...