Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አሁንም እየተመከረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዓመታት ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ዕርምጃ መውሰድ ያቃተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት አጥሮ በመያዝ የአንበሳውን ድርሻ ከያዙት ሚድሮክ፣ ኤምባሲዎችና መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ከማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ምክክር ጀመረ፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታውና በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ የተመራው የባለሙያዎች ቡድን፣ አጥረው ባስቀመጡ ተቋማት ላይ ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ውይይት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ለዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ታጥረው ከተቀመጡ 156 ይዞታዎች ውስጥ 20 የሚሆኑት ቦታዎችን ማልማት ያልተቻለው አስተዳደሩ በፈጠረው ችግር በመሆኑ፣ ኩባንያዎቹ የውል ዕድሳት እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡

ስልሳ ስምንት የሚሆኑ ይዞታዎች ደግሞ ችግሩ የራሳቸው የኩባንያዎቹ በመሆኑ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የስድስት ወራት ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን በድምሩ 70 ቦታዎችን አጥረው በመያዝ ለዓመታት ያስቀመጡት ሚድሮክ፣ የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎችና የመንግሥት ተቋማት ላይ ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት ውይይት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ ተቋማት ቦታዎቹን ለማልማት ያጋጠማቸው ችግር ምንድነው? የሚለውን ለማወቅና ውሳኔ ለመወሰን ውይይት ተጀምሯል፡፡ የተናጠል ውይይቱ ከማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው፣ የሚድሮክን የግንባታ ሥራዎች እንዲመራ የተቋቋመው ሲቲ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በተገኙበት ታጥረው በተቀመጡ የሚድሮክ ቦታዎች ላይ ውይይት ተካሂዶ እንደበር ይታወሳል፡፡

የውይይቱ ማጠንጠኛ ሚድሮክ በተለያዩ ጊዜያት የተረከባቸውን ቦታዎች ለዓመታት አጥሮ ማስቀመጡ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ ድርጊት በሚፈጽሙ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ፣ በሚድሮክ ይዞታዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ አለመቻሉ የሚያስወቅስ ጉዳይ መሆኑ በወቅቱ ጎልቶ ወጥቶ ነበር፡፡

ለሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ ቅርብ የሆኑትና የሲቲ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት የእኛም ችግር አለ፡፡ የማዘጋጃ ቤትም ችግር አለ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በእኛ በኩል የነበሩ ችግሮችን ፈትተን ከነሐሴ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በፒያሳ፣ በሸራተን ማስፋፊያና በሜክሲኮ (ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን) ግንባታ እንጀምራለን፤›› ያሉት አቶ አብነት፣ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮንስትራክሽኑን የሚመራውን የሰው ኃይል ከውጭ አገር እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አስተዳደሩ ወደ ግንባታ እንድንገባ ግፊት ማድረጉ መልካም ነው፡፡ እኛም አጥረን ያቆየን በመሆኑ ፕሮጀክቶቹን የማካሄድ ከፍተኛ ፍላጎት አለን፤›› በማለት አቶ አብነት ገልጸው፣ ‹‹መታሰብ ያለበት ግን የምናካሂዳቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደመሆናቸው፣ ፕሮጀክቶቹ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ወሳኝ ስለሆኑ መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ከሚድሮክ በተጨማሪ የበርካታ አገሮች ኤምባሲዎችና መንግሥታዊ ተቋማት በርካታ ቦታዎችን አጥረው ይዘው ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሳምንት አስተዳደሩ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች