Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአንድ ዓመት ሲያጨቃጭቅ የቆየው የ3.7 ቢሊዮን ብር አርማታ ብረት የጨረታ ግዥ ተሰረዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ አንድ ዓመት ሙሉ ሲያጨቃጭቅ የነበረውን 220 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት ግዥ ጨረታ፣ እንዲሁም ለአቅራቢዎች ሰጥቶት የነበረውን የ3.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለውን አቅርቦት መሰረዙን አስታወቀ፡፡

በሐምሌ 2008 ዓ.ም. ኢንተርፕራይዙ ሦስት የአገር ውስጥ አምራቾች 3.7 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የአርማታ ብረት ለሚገነባቸው የ40/60 ቤቶች እንዲያቀርቡለት ተስማምቶ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት መጀመርያ ጨረታውን ላሸነፉ አቅራቢዎች እገዛዋለሁ ብሎ ተዋውሎት የነበረውን 220 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብረት መጠን 90 በመቶ በመቀነስ ወደ 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማድረሱ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህን አቅራቢዎች ከዓመት በፊት በሰጡት ዋጋ ብረቶቹን እንዲያቀርቡ ኢንተርፕራይዙ ማሳወቁን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንተርፕራይዙ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አቅራቢዎቹ መልስ ባለመስጠታቸው ኢንተርፕራይዙ ጨረታውንም ሆነ እንዲያቀርቡ ሰጥቷቸው የነበረውን ዕድል መሰረዙን አሳውቋል፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፈው ይህ የጨረታ ሒደት በርካታ ማስተካከያዎችና ማሻሻያዎች እንደተደረጉበት ይታወሳል፡፡

በግንቦት 2008 ዓ.ም. ወጥቶ በነበረው በዚህ ጨረታ ወደ አምስት የሚጠጉ የአገር ውስጥ የአርማታ ብረት አምራቾች ተሳትፈው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሦስት የአገር ውስጥ አምራቾች በተለያየ መጠን ወጥቶ የነበረውን የብረት ግዥ ለማቅረብ ተስማምተው ነበር፡፡

በዚሁ ጨረታ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በመጀመሪያ ኢንተርፕራይዙ 150 ሺሕ ቶን ለመግዛት ጨረታ አውጥቶ ተመሳሳይ የአገር ውስጥ አምራቾች ተሳትፈው የነበረ ሲሆን፣ የሚያቀርቡበትንም ዋጋ በማሳወቅ በኢንተርፕራይዙ የጨረታ ኮሚቴ የተገመገመ ቢሆንም፣ ኢንተርፕራይዙ ጨረታውን በመሰረዝ አሻሽሎ አውጥቶታል፡፡

በመጨረሻ ኢንተርፕራይዙ 220 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለመግዛት እንደሚፈልግ አሳውቆ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሲኤንድኢ ወንድማማቾች የብረት ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለአብዛኞቹ የብረት መጠኖች ዝቅተኛውን ዋጋ አቅርቧል፡፡ ለ12፣ ለ14፣ ለ16 እንዲሁም ለ20 ሚሊ ሜትር ብረቶች ለእያንዳንዱ ኪሎ ግራም 17.71 ብር፣ 17.11 ብር፣ 17.11 ብር እንዲሁም 17.24 ብር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ጨረታውን አሸንፏል፡፡ በአጠቃላይ ኩባንያው ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ዋጋ አቅርቦ ጨረታውን አሸንፎ ነበር፡፡

በመቀጠል ኢስት ስቲል የተባለው ፋብሪካ ከተወዳደረባቸው የብረት መጠኖች ወደ 39.4 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የስምንትና የአሥር ሚሊ ሜትር ብረቶችን ለማቅረብ፣ 718.4 ሚሊዮን ብር በማቅረብ አሸንፎ ነበር፡፡

ሌላው ሦስተኛው አሸናፊ ስቲሊ አርኤምአይ ሲሆን፣ ይህ አቅራቢ 1.3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አጠቃላይ ክብደት ያላቸውን አርማታ ብረቶች እያንዳንዱን ኪሎ ግራም በ22.9 ብር ለማቅረብ ተስማምቶ ነበር፡፡

ይህ አንድ ዓመት የፈጀው ጨረታ በወቅቱ ግንባታ ላይ ለነበሩ 38,790 ቤቶች፣ እንዲሁም አዲስ ይጀመራሉ ተብለው ለሚጠበቁ ቤቶች ታስቦ የተደረገ ግዥ ነበር፡፡

ነገር ግን በወቅቱ ኢንተርፕራይዙ ባጋጠመው የበጀት እጥረትና ቀድሞ የነበረው ለተቋራጮች ሲደረግ የነበረው የአከፋፈል ሥርዓት በመቀየሩ፣ የአርማታ ብረቱን አሸናፊዎቹ እንዲያቀርቡ ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡

በተቃራኒው ኢንተርፕራይዙ የአርማታ ብረቶቹን ማስረከቢያ ጊዜ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ማራዘሙ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አሁን ይህን ውሳኔ ኢንተርፕራይዙ በመከለስ፣ ውሳኔውን ካሁን ቀደም ጨረታውን ላሸነፉት ኩባንያዎች አሳውቋል፡፡

‹‹አሁን ያለን ፍላጎትም ሆነ የገንዘብ አቅም እስከ 20 ሺሕ ቶን አርማታ ብረት ብቻ ለመረከብ የሚያስችለን ነው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢንተርፕራይዙ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአሁን በኋላ ያለን አማራጭ አዲስ ጨረታ ማውጣት ነው፤›› ሲሉ ኃላፊው አክለዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ አቅራቢዎቹ ከዓመት በፊት ሰጥተውት በነበረው ተመሳሳይ ዋጋ እንዲያቀርቡ ቢፈልግም፣ በዓለም አቀፍ ደረጀ የአርማታ ብረት ዋጋ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት እንደ ለንደን ሜታል ኤክስቼንጅ ዓይነት የብረትን ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመተንተንና በመተንበይ፣ እንዲሁም በማገበያየት የሚታወቁ ተቋማት የአርማታ ብረት ካለፈው ዓመት የተወሰነ ጭማሪ እንዳሳየ ያመለክታሉ፡፡

በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2016 በኪሎ ከ9.14 ብር እስከ 10.1 ብር ሲሸጥ የነበረው፣ በዚህ ዓመት እ.ኤ.አ እስከ ግንቦት 2017 ድረስ እስከ 10.75 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በ40/60 ፕሮጀክት ከሚሠሩ ቤቶቸ 1,292 ቤቶች መጠናቀቃቸው ቢነገርም፣ እስካሁን ወደ ቆጣቢዎች አልተላለፉም፡፡ ወደ 164 ሺሕ የሚሆኑ ቤት ፈላጊዎች በዚህ ፕሮግራም ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለቀጣይ በጀት ዓመት አዳዲስ ቤቶች ይገነባሉ ወይ የሚለው ገና እንዳልተወሰነበት ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች