ሰላም! ሰላም! ዓረፍተ ነገሩ ሳይቀር ባለቤት አልባ በሆነበት ዘመን፣ ዘንድሮ እኮ አመልካችና ተመልካች ብዙ እየተዛዘብን ነው። ተመልካች እኔ አመልካች ማንጠግቦሽ መሆኗ ነው፡፡ ያለልማዷ እስኪ ወሬ እንስማ እያለች ማታ ማታ ዜና ትከፍትብኛለች። ደህና የዋልኩት ሰውዬ ሰምቶ ማለፍ አልችልምና የማይመስል ነገር የሰማሁ ሲመስለኝ ቀይሪው አልቀይርም በሚል ተኳርፈን ማምሸት ነው። “ሰው ሕገ መንግሥት ይሻሻል እያለ ይወያያል አንተ. . . ” ብላ ታያይዘኛለች። 70 በመቶ የሚሆነው የእኛ ሰው የሚሞተው በማያገባው እየገባ ነው የሚሉ ፖስቶች አንብባችሁ ይሆን? እውነት ያላት አባባል ትመስላለች። በሌላውስ እሺ አያገባኝም ብሎ መሸሽ ይቻል ይሆናል፡፡ ቻፓ ሲሆን ግን ምን ታደርጋላችሁ? ዘላችሁ ዳይቭ መግባታችሁ አይቀርም። ዋሸሁ? በተለይ ደግሞ እንደ አገራችን ባለቤት አልባ የሚመስል የበጀት አመዳደብ ዜና ስትሰሙ የሚያስችላችሁ አይመስለኝም። ከአገር በላይ ትዳር የለማ። አለ እንዴ? እና አንዳልኳችሁ አንድ ምሽት እኔና ማንጠግቦሽ ዜና እያየን ነው።
ለዴሞክራሲያዊ አቅም ግንባታ 40 ሚሊዮን ብር ተመደበ ሲባል ያንሳል ብለን አጨበጨብን። ቀጥሎስ? ለአዲስ አበባ ፅዳት አገልግሎት የሚውል 250 ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ ግብይት መደረጉን ስሰማ ግን በበኩሌ አልዋጥልህ ብሎኝ ጠገብኩ ብዬ ከማዕድ ተነሳሁ። ‹‹ያንተን ትራፊ የሚበላ የለ ጨርስ እንጂ፤›› ስባል፣ “ግዴለም በሚቀጥለው የበጀት ድልድል እጨርሰዋለሁ፤” ስላት ማንጠግቦሽ፣ “ከደላላነት ይልቅ የፖለቲካ ሰብዕና ግንባታ ጀምረሃል፤” ብላ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። መቼም ይኼ ሚሊዮን የሚባል ስም የማይፈታው ነገር የለም። ብላት ብሠራት ለቅሶዋን አላቆም አለች። በኋላ፣ “ነገ ሁለት ሚሊዮን ብር ኮሚሽን የሚያስገኝ ሥራ አለብኝ ሰላም ስጭኝ?” ብዬ ቆጣ አልኩ። እንባዋም ጭቅጭቃችንም ቆመ። እንግዲህ አስቡት? እኔ እንኳን የሚስቴን ለቅሶ ለማስቆም ሁለት ሚሊዮን ከጠራሁ መንግሥትማ የሕዝብ እንባ ለማበስ ገና ምኑን በጀተው? ይብላኝ ለኦዲተሩ እንጂ!
እንዳይነጋ የለም ነጋ። ጠዋት ነው ማንጠግቦሽም የሰማችው። ምኑን? ሁለት ሚሊዮን ብር ኮሚሽን ያልኩት ሥራ ሜዲትራንያን እንዳቋርጥ ግድ የሚል እንደነበር። የደለልኩት ተበልተው የሚሸጡ የከባድ መኪና ዕቃዎችን ነው። ደንበኛዬ ከብዙ ዘመን በፊት የማውቀው ጣሊያናዊ ነው። ማታውን ተነስተን ሮም። ለምን በዝርዝር ነገርከን በሉኝ። ሙሉ ሐሳቤና ቀልቤ ያለው ሥራዬ ላይ እንደሆነ ልብ እንድትሉ ፈልጌ ነው። ከፈለጋችሁም ፈቀቅ ብላችሁ እንዲህ እንደ ቀልድ እመር ተብሎ ሮም የሚሄድ ደላላ ኢትዮጵያ ማፍራቷ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ መንግሥታችን ምን ያህል ዕውቅናና ተቀባይነት ያለው አመራር እየሰጠ በመሆኑ ነው ብላችሁ ማመን ይቻላል። እኔ ፀሐዩ መንግሥታችን በአመቻቸው ሠርቶ የመለወጥ ሒደት ስጠቀም ምድረ ወሬኛ አገሬ፣ ቤቴ፣ ምኔ. . . ብሎ ያወራል?
“አንበርብር ጣሊያን አገር ሪፊውጅ ካምፕ ገባ፤” አሁን ይኼን ምን ትሉታላችሁ? ሮም ላይ ቆሜ እነ ዳንቴን፣ እነ ሲሴሮን፣ እነ ኔሮንና እነ ሲዛርን እያሰብኩ የአገሬን አሉባልተኛ ሳስበው እኒያ ነፍስ ያወቁ አርበኞች ባይኖሩ ኖሮ ምናልባት ይኼ ሐሜት ዛሬ በጣሊያንኛም ይደገም ነበር? በወሬ ተወልዶ በወሬ የሚሞተውን ሳስብ ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ ለምን እኛ ላይ እንደማይበረታ ገባኝ። ኋላ ከተመለስኩ በኋላ ባሻዬን፣ “እንዲህ ተብዬ ነበር፤” ስላቸው፣ “ሰምቻለሁ። ግን ረስቼዋለሁ። ምነው ግን አንተ እንዲህ እየጎለመስክ ሳለ ነገር መርሳት አቃተህ? ሆድህን አስፋው እንጂ፤” ብለው ገሰፁኝ። ባሻዬ የመሰላቸው ሆዴ አልሰፋ ብሎ እያደር ስስ የመሆኔ ውጤት ነው። እኔን ደግሞ አልመስልህ ያለኝ እኛ ስንባል የገዛ ራሳችንን ኑሮ ትተን እንደ ‹ሲሙሌሽን ጌም› የሰው ሕይወት መኖር የሚጣፍጠን ነገር ነው። የዓለም ባንክ የአሉባልታችንን ዕድገት እንደ ኢኮኖሚው መመዘን ቢችል፣ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ከእናንተ ጋር አልሠራም አይልም ትላላችሁ! የምሬን እኮ ነው።
ከሮም ተመልሼ መጣሁ። ገንዘቤና እግሬ የአገሬን መሬት ሲረግጡ ደስ አለኝ፡፡ ውዬ አድሬ ቀልቡ በጠፋው ወገኔ መሀል እጓዝላችኋለሁ። እንዲያው የወሬ አምላክ ምን ቢቀየማችሁ አንድ ነገር እንድትሰሙ ወይ እንድታዩ ሳያደርጋችሁ አይውልም። ነገሩን ነው እንጂ እኔም እኛን የመሰለ ወሬ አምላኪ የወሬ አምላክ ይቀየመናል ብዬ አይደለም። ይህቺን ርዕስ ሁል ጊዜ ሳላነሳባችሁ ቀርቼ አላውቅም መቼም። ምን ላድርግ እንዲያው ነገረ ሥራችን ዝም የሚያስብል አልሆን ስላለብኝ እኮ ነው። ሰሞኑን በየሄድኩበት ሰው ሲወያይ የምሰማው ነገር ሁሉ ሊያስቀኝ እየከጀለ መልሶ እያበሸቀኝ እንዲሁ ስቃጠል ሰነበትኩ። በቀደም አንድ ካፍቴሪያ እንደ አቅሚቲ በሻይ ተጎልቼ ወጭ ወራጅ ስገላምጥ አጠገቤ የተቀመጡ ሦስት ሰዎች ጨዋታቸው ተጀምሮ እስኪያልቅ ስለዝንብ ነበር። ተመልከቱ እንግዲህ! እንደሚታወቀው ወቅቱ ዝንቦች እንደ አሸን የሚፈሉበት አይደል? እናማ ሰዎቹ መልሰው መላልሰው ያው አንድ ዓረፍተ ነገር እየደጋገሙ አዛሉኝ። ‘አቤት ዝንቡ!’ ‘አይ ዝንቡ!’ ‘ወይኔ ዝንቡ!’ ሲሉ አሥር ጊዜ ብው አልኩ።
ቆይ እውነት እዚህ አገር ይህን ያህል የወሬ ተነሳሽነት እያለ ቢያንስ ደህና ወሬ የማይወራበት ምክንያት ምንድነው? በአጎበርና በድብርት ስለሕገ መንግሥት መሻሻል እያዛጉ የሚያዝጉንን መብለጥ ባለብን ሰዓት፣ የተሻለ ሐሳብና ራዕይ ማዋጣት ባለብን ጊዜ ዝንብ ብርቃችን ነው? ግዴለም ማውራቱን እናውራ። ምናለበት ካፌውን ሞልተነው የምንውለውን ያህል ቢያንስ ስለመሠረታዊ ችግሮቻችን ውይይት ቢለምድብን? ኧረ የወሬም ጡር አለው፡፡ “አይ እማማ ኢትዮጵያ ልጆችሽ ከችግርሽ ብዛትናና ከድህነትሽ ጥልቀት ለማማትም ተፀይፈንሽ እንቅር?” ያለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ‘ተወው የእኛን ነገር’፣ ‘አታንሳ ስለእኛ!’ ባዩ በዝቶ ለውጥ ከየት ሊመጣ ነው? ‘ልብህን ማን ወሰደው? ልብህን ማን ሰረቀው? ቁልፉንስ?’ ቢሉት አሉ “መቼ?” አለ አሉ።
ብቻ በየሄድንበት መላመድ እንችልበታለን። በተለይ ሐሜትና አሉባልታ ከሆነ ፍቅራችን ይደራል። ባለሥልጣኖቻችን ወይ አያልፉ ወይ አያሳልፉ ተገትረን ቆመን ልናድር መሆናችን የተገነዘብኩት የሰማሁትን ሰምቼ ስጨርስ ነው። “እኔ የማውቀው ሕግ የሰው ልጅ አገልጋይና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ነው እንጂ አትለፍ፣ አትቀመጥ፣ አትቁም እያለ የነፃነት ፀር ሲሆን አይደለም፤” ብሎ ሳይጨርስ አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ “ሁላችንም የምናውቀው እንዲያ ነው ወንድሜ። ይልቅ ሊገርምህ የሚገባው ስንት ከሕግ በላይ መኖር የለመደ ባለበት አገር ተራው ሰው ላይ ጥቃቅንና አነስተኛው ሕግ በርትቶ መተግበሩ ነው። ‘ምንድነው ስትል?’ ቢሮክራሲ ትባላለህ። ይሠሩልናል ብለን የሾምናቸው ሹማምንት እኛ ከኑሮ ጋር የሞት የሽረት ትግል ላይ እንዳለን እያዩ እነሱ በሞቀ ቤት ተቀምጠው፣ የሕግ የበላይነትን እስከ ማስተማር ይደፍሩናል፤” ብሎ ይናገራል።
የሕዝብ ብሶትና የሐምሌ ዝናብ አንዴ ከጀመረ ማባሪያ የለውም አይደል? በቃ ትንሹ ትልቁ የመጣለትን ሳያረቅ መናገሩን ተያያዘው። ታዲያ ወዳጆቼ መርጦ መስማትን የመሰለ ምንም ነገር አልኖር ብሏል። መስማት ብቻ ሳይሆን መዋልንም ይጨምራል። “አደራ ‘ብላክ ሊስት’ ውስጥ የገባው በርከት ስላለ የምትውላቸውን ሰዎችም እየመረጥክ፤” ያለችኝ ውዷ ማንጠግቦሽ ናት። ጦሱ እንደ ውርስ ከአንዱ ላንዱ ሲሆን እያየች እንዴት አታስጠነቅቀኝ? ለማንኛውም መንገዱ ሲከፈትና ከታጎርንበት ስንወጣ የመሰነባበቻ ነው መሰል አንዱ፣ “ተመስገን! እንኳን ‘ኦክስጅን’ በአንተ እጅ ሆነ፤” ቢል ሽቅብ ሰማይ ሰማይ እያየ ብሶታችንን ቆሰቆሰው። ‘ሕግ የሕዝብ አገልጋይ እንጂ ቀንበር መሆኑ ይብቃ!’ የሚል ጥቅስ በአዲሱ አውራ ጎዳና ላይ መጻፍ አማረኝ!
ወደ መሰነባበቻን ሰዓት ላይ ነን። የባሻዬ ልጅ በጥብቅ እፈልግሃለሁ ብሎ ደውሎልኝ ነበር። ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራሁ። “ምንድነው እሱ?” አልኩት ገና ሳገኘው እያፈጠጥኩበት። ጤና የያዘው ስላልመሰለኝ። ጠዋት ሲስቅ ያያችሁት ሰው ማታ ቀብሩን ድረሱ በሚባልበት ጊዜ ጤናውን ካልተጠራጠርኩ ምኑን ልጠራጠር ኖሯል? እንደ ፖለቲካና ኑሮው ከፍ ዝቅ፣ እንደ ብሔራዊ ቡድናችን አቋም ከፍ ዝቅ፣ የሰውንም ጤና እንዲህ ነው ብሎ መናገር ከባድ ሆነ እኮ። ታዲያ እንደገመትኩት ሳይሆን “ኧረ ደህና ነኝ። ብቻ የዚች ግሮሰሪያችን ነገር አስደንቆኝ ነው። ትዝ ካለህ እኛ መምጣት የጀመርን ሰሞን ባዶ ነበር፤” ሲለኝ፣ “አሁን ለዚህ ነው እንደዚያ እፈልግሃለሁ ብለህ ስሮጥ የመጣሁልህ?” ብዬ አኮረፍኩት።
“አንበርብር እኔማ ሰው ያለ አንድ ነገር ባንኮኒ ላይ አይሰየምም የሚል እምነት ስላለኝ፣ ስለዚህ ብሶት ስለወለደው የመጠጥ ገበያ የታዘብኩትን ላካፍልህ ነው፤” አለኝ። “የምን ብሶት?” ስለው ግንቦት ሃያ ትዝ እያለኝ፣ “የፍትሕ መጓደል ብሶት፣ የቤት ዕጦት ብሶት፣ የኑሮ ውድነት ብሶት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ብሶት፣ በአጠቃላይ የኑሮና የፖለቲካ ብሶት ሕገ ሥራ ላይ ቢውል በቅፅበት የሚቃለል ነገር ነው ብለህ ታስባለህ?” ሲለኝ፣ ‹‹ሥራ ላይ ለማዋል እኮ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፤›› አልኩታ ቱግ ብዬ፡፡ ብሶት እንዲህ ያደርጋል እንዴ? ግን ምን ቱግ አስባለኝ? የምን ደርሶ መገንፈል ነው? መልካም ሰንበት!