Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነዳጅ አከፋፋዮች ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙ ተጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአገሪቱ የሚገኙ ነዳጅ አከፋፋዮች ለሚያከፋፍሉት ነዳጅ ቅደመ ክፍያ እንዲፈጽሙ ጠየቀ፡፡ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ባለፈው ሰሞን ነዳጅ አከፋፋዮችን ጠርቶ በጉዳዩ ላይ የደረሰበትን ውሳኔ ያሳወቀ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. ከጁላይ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ለሚወስዱት የነዳጅ መጠን አሥር በመቶ ቅድመ ክፍያ እንዲፈጽሙ ማሳወቁንም ምንጮች አክለዋል፡፡

ነዳጅ አከፋፋዮች አዲስ የቀረበውን አሠራር የተቃወሙ ቢሆንም ከላይ የወረደ ውሳኔ በመሆኑ የሚቀየር ነገር እንደሌለ እንደተነገራቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሊትር የምናገኘው 0.7 ሳንቲም ትርፍ እንዲስተካከል እየተደራደርን ባለንበትና መፍትሔ ባላገኘንበት ሁኔታ አሥር በመቶ ቅድመ ክፍያ ፈጽሙ መባሉ ፍትሐዊ አይደለም፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የነዳጅ አከፋፋይ ድርጅት የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አሠራር መሠረት ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ለተረከቡት ነዳጅ ክፍያ የሚፈጽሙት ከ21 ቀናት በኋላ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የነዳጅ አቅራቢዎች ማኅበርም በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበውን አዲስ አሠራር በመቃወም በይፋ ደብዳቤ እንደላከ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን የተቀየረ ነገር አለመኖሩን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የነዳጅ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ጉዳዩ ገና በሐሳብ ደረጃ ላይ ያለ እንጂ ውሳኔ የተሰጠበት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ 3.5 ቢሊዮን ሊትር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አገሪቱ የምታስገባውን ዓመታዊ ፍጆታ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡት ደግሞ 13 ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ 740 የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ አሏቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች