ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተገንብቶ ሥራውን ከጀመረ አንድ አመት አልፎታል፡፡ በ45.9 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ማዕከሉ 225 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ከ15 ዓመትና 17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በማዕከሉ አራት ዓመታት ቆይታ በማድረግ ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዲዘዋወሩ ያደርጋል፡፡
በጥሩነሽ ዲባባ ስም ተሰይሞ በአሰላ ቀበሌ 12 ከክልሉ መንግሥት ስምንት ኮንዶሚኒየሞችን በአሥር ሚሊዮን ብር ገዝቶ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ዓመታት ሥልጠናውን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ሚያዝያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ራሱ ወደ አስገነባው ማሠልጠኛ በመግባት በአዲስ መልክ ሥራውን የጀመረው ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የልምምድ መሣሪያዎችና የመሮጫ መም፣ ጂምናዚየምና ቤተ መጻሕፍት በማካተት ከበፊቱ በተሻለ ሥልጠናውን እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡
ማዕከሉ ቀድሞ ኮንዶሚኒየም በነበረበት ወቅት አስፈላጊው መሣሪያ ያላሟላ ሲሆን የመሮጫ ትራክ ስላልነበረውም አትሌቶች ልምምዳቸውን ለማድረግ የአሰላ አረንጓዴ ስታዲየምን በክፍያ ይጠቀሙ እንደነበር አቶ ጎሳ ሞላ፣ የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሠልጠኛ ማዕከል የትምህርትና ሥልጠና የውድድር ባለሙያ ያስታውሳሉ፡፡
በጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል ውስጥ ከሚገኘው የልምምድ መም (ትራክ) በተጨማሪ ለብቻው የ200 ሜትር ርቀት መለማመጃ መም ተካቷል፡፡ ዘመናዊ ጅምናዚየምም ከሁለት ወራት በፊት ሙሉ በሙሉ ለአትሌቶች ክፍት በማድረግ ሥልጠናውን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ማዕከሉ ዘንድሮን ጨምሮ በሰባት ዓመታት ዕድሜው 445 አትሌቶችን ለክለቦች ማዘዋወር በመቻሉ በአገሪቱ ለሚደረጉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አስተዋጽኦ ማበርከት እንደቻለ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በየዓመቱ በሚከናወኑ ውድድሮች ላይ አዳዲስ ሪከርዶችን ከሚያስመዘግቡ አትሌቶች ውስጥ ከዚሁ ማዕከል የወጡ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይ በሜዳ ተግባራት ላይ የተሻለ ውጤት በማምጣትም ይወሳሉ፡፡ በማሠልጠኛው ከሚሠለጥኑ መካከል በአራተኛው የታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይ በከፍታ ዝላይ ተወዳድሮ 1.94 ሜትር በመዝለል የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበው ማል ጎኝ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከረጅም ርቀቱ በተጨማሪ በአጭር ርቀት ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለተለያዩ ክለቦች ማበርከት ችሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ላይ ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3,000 ሜትር መሰናክልና ቀጥታ ሩጫ የተሳተፉት ጅግሳ ቶሎሳና ኃይለማርያም አማረ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ ኃይለማርያም አማረ በ3,000 ሜትር መሰናክል መሳተፉ ይታወሳል፡፡
ከማዕከሉ የሥልጠና ጊዜያቸውን አጠናቀው በ2008 ዓ.ም. ድሬደዋ ከተማ ወደ አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለቦች የተዘዋወሩ ሴት ተጨዋቾችም አሉ፡፡ ሴናፋ ቱማ ለአዳማ ከተማ፣ ትደግ ፍሥሐ ለድሬዳዋ ከተማ በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች ከ17 ዓመት በታች የኢትጵያ ብሔራዊ ቡድንን ተመርጠው ተጫውተዋል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾችም በክለቾቻው ከዘጠኝ ሺሕ ብር እስከ አሥር ሺሕ ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው ይገኛል፡፡
‹‹ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ማሠልጠኛ ተቋም ነው፡፡ ክለቦችም በእኛ ማሠልጠኛ ተቋም የሠለጠኑ አትሌቶች ላይ እምነት ስላላቸው የክለቦችን ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ጎሳ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከማዕከሉ 113 አትሌቶች በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎችና የስፖርት ዓይነቶች ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ሲሆን፣ 31 ወንድና 26 ሴት አትሌቶች በአህጉራዊ ውድድሮች፣ 13 ወንድና 11 ሴት አትሌቶች ደግሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ በቅተዋል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ በተከናወነው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጭርና በመካከለኛ ርቀት፣ በዝላይና በውርወራ ከተመዘገቡት አሥር ክብረ ወሰኖች ግማሹን በማዕከሉ ያለፉ ሠልጣኞች ማስመዝገባቸው መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ 214 ስፖርተኞች ሲገኙ፣ ከእነዚህም ውስጥ 88ቱ የወንድና የሴት እግር ኳስ ሠልጣኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አትሌቶች ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ በሁሉም ርቀቶችና በሜዳ ተግባር ላይ ሥልጠናውን እያገኙ እንደሆነም አቶ ጎሳ ገልጸዋል፡፡
አሠልጣኝ ጎሳን ጨምሮ በማሠልጠኛ ማዕከሉ ላይ 20 አሠልጣኞች ሲገኙ፣ ሦስቱ በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ 17ቱ አሠልጣኞች ደግሞ በስፖርት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውም ለመቀበል ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡
ማዕከሉ ካለው የመልክዐ ምድር አቀማመጥ አኳያ የአየር ንብረቱ ለአትሌቶች ምቹ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ከዚህም አኳያ በተለይ በስፖርት ቱሪዝም መስክ የራሱን ገቢ መፍጠር እንደሚችል እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ በተለይ ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በደብረ ብርሃንና ሱልልታ ልምምዳቸውን የሚያደርጉት አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ለተጠቃሚነት አንዱ ማሳያ መሆኑ ይገለጻል፡፡
የጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል ካለው የአየር ንብረት አመቺነት አንፃር የራሱን ግቢ ለመፍጠር ዕቅድ መሰነቁንና ጉዳዩን ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረበት እንደሆነ አቶ ጎሳ ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
በማዕከሉ ከታቀፉት ሠልጣኞች መካከል መደበኛ ትምህርታቸውን አሰላ በሰርቪስ በመመላለስ የሚማሩ ተማሪዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ጎሳ፣ ተሸከርካሪዎቹ ለልምምድና ለውድድር ወደ ክልል በሚያመሩበት ወቅት ግን ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ መፍትሔ የሚሉትም የሚመለከተው አካል ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ቢመድብ የሚል ነው፡፡ የስፖርተኞች ትጥቅ መዘግየትም ዋነኛ ችግር እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡