Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአሸናፊ በቀለ የጋናውን የጨዋታ ሪፖርት አቀረቡ

አሸናፊ በቀለ የጋናውን የጨዋታ ሪፖርት አቀረቡ

ቀን:

  • ለውጤቱ የበረኛው ድርሻ 50 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል

ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በጋናውያን ጥቋቁሮቹ አንበሶች ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድናቸው በዕለቱ ጨዋታ የነበረበትን አጠቃላይ ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም ቡድኑ በዝግጅትና በጉዞ ሒደት ያጋጠመውን ውጣ ውረድ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለ የቀረበው የጨዋታ ሪፖርት፣ ለቡድናቸው ሽንፈት በዋናነት ጋናውያኑ በአካላዊ ብቃት፣ በቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም በፍጥነት የተሻሉ ሆነው በመቅረባቸው ሊያሸንፉ መቻላቸውንና ለውጤቱ መስፋት ግን የቡድናቸው ግብ ጠባቂ ስህተት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እንደ ሪፖርቱ የአንድ ቡድን ውጤት 50 በመቶ በረኛው በመሆኑና የተመቱ ኳሶች ግብ ሆነው መቆጠራቸው ተብራርቷል፡፡

የአሠልጣኙ ሪፖርት ሲቀጥል፣ ቡድኑ ምንም እንኳ በመጀመሪያው ግጥሚያው ያስመዘገበው ውጤት የተጨዋቾችን ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ ሞራል ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ፣ ከውጤቱ ጎን ለጎን በተለይም በጨዋታው ሁለተኛ ክፍለ ጊዜ መገባደጃ ላይ ተጨዋቾቻቸው ባደረጉት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እንደነበርና የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው እንደነበር አመላክቷል፡፡

ቡድኑ በጋናው ጨዋታ የነበሩበትን ጉልህ ስህተቶችና ክፍተቶች አርሞ ለቀጣይ ግጥሚያዎች የተሻለ ቡድን ሆኖ እንደሚቀርብ ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ለዚያም በቂ የዝግጅት ጊዜና የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚያስፈልግ ጠይቋል፡፡

ሪፖርቱ ሌላው ለማመላከት የሞከረው ዝግጅቱን አስመልክቶ ነው፡፡ ይኼውም አሠልጣኙ በያዙት ዕቅድ መሠረት በቂ የሚባል ዝግጅት ማድረጋቸውንና በመሀል ግን ለዝግጅት ከተያዘው ጊዜ ውስጥ ሁለት ቀን በዝናብ ምክንያት ልምምድ ማድረግ ያልቻሉበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ ያም ሆኖ ቡድኑ ወቅታዊ አቋሙን መገምገም ይችል ዘንድ ከመከላከያ ተስፋ ቡድንና ከፋሲል ከተማ እንዲሁም ከዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በሦስቱም ጨዋታዎች ሁሉን ተጨዋቾቻቸው በሁለት ምድብ በመክፈል እንዲጫወቱ መደረጉም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በእያንዳንዱ ጨዋታ እንደ ክፍተት በተወሰዱ ጉድለቶች የዕርማት ሥራ መሠራቱንና በተጨማሪም የጋና ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫም ሆነ በሌሎች ጨዋታዎች ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በቪዲዮ በመታገዝ በቡድንና በግል በመመልከት ያንን መሠረት ያደረገ ዝግጅት ስለማድረጋቸውም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ለውጤቱ መጥፋት የበረኛው ክፍተት እንዳለ ሆኖ ተጋጣሚያቸው የጋና ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በቴክኒክም ሆነ በታክቲኩ ግንዛቤ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በዓለም አቀፍ መድረክ በፕሮፌሽናል ደረጃ የተጫወቱ በመሆኑ ቀድመው ተጨዋቾቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተነጋግረው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የመስመር ኳሳቸው በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ ስለነበረ የበላይነት የወሰዱበት አጋጣሚም እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

አሠልጣኙ ሌላው በሪፖርታቸው ያካተቱት፣ በእሳቸው አተያይ ቀደም ብለው ከመረጧቸው ተጨዋቾች መካከል የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ክለቡ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በነበረበት ጨዋታ ምክንያት ተሟልተው አለመካተታቸው ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጨዋቾች በሚመለከት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና አሠልጣኙ ባደረጉት ውይይት መሠረት ተጨዋቾቹ መጨረሻ ላይ ከቡድኑ ጋር እንዲካተቱ ጥሪ የተደረገላቸው ስለመሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ሪፖርት አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የእግር ኳስ ሙያተኞች ሪፖርቱ ካቀራረቡ ጀምሮ መሠረታዊ የሚባል ክፍተት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ባለሙያተኞቹ እያንዳንዱ ተጫዋች ከበረኛው ጀምሮ በቦታው ጠንካራና ደካማ ጎኑ በቡድንም ሆነ በተናጠል ተዘርዝሮ ሊቀርብ ነበር ባይ ናቸው፡፡

እንደ ሪፖርቱ፣ ለቡድኑ ውጤት መበላሸት 50 በመቶ በረኛው መሆኑ የተገለጸበት አግባብም ቢሆን፣ የበረኛው ድክመት እንዳለ ቢሆንም እንደ ቡድን የሌሎቹ ተጨዋቾች ድርሻና በዚህ መሀል የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች እስከ በረኛው በመቅረብ ጫና እንዲያደርጉ ምክንያት የነበረው የታክቲክ ስህተት ምን እንደነበረ በሪፖርቱ መካተት ይገባው ነበርም ብለውም ያምናሉ፡፡

እንደ ሙያተኞቹ፣ በኢትዮጵያ ቡድን ላይ የተቆጠሩት አምስቱም ጎሎች መሠረታዊ በሚባል የታክቲክ ክፍተት እንደነበረበት ጭምር ይጠቁማሉ፡፡ ለሽንፈቱ 50 በመቶ ምክንያት ሆኖ የቀረበው በረኛው ከሆነም አሠልጣኙ ከመጀመርያው 45 ጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኋላ ለምን እንዲቀየር አላደረጉም? በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

ሙያተኞቹ ሲቀጥሉ፣ አሠልጣኙ በሪፖርታቸው በጠቀሱት መሠረት በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጨዋቾች አስመልክቶ ያቀረቡትን ምክንያት አይቀበሉትም፡፡ ምክንያቱም አንድ አሠልጣኝ ለሚመርጠው አጨዋወት ይመጥናሉ የሚላቸውን ተጨዋቾች የመምረጥ ሙሉ መብት እንዳለው ይታመናል፡፡ በዚህ አግባብ በዝግጅት ወቅት ያልተመለከቷቸውን ተጨዋቾች ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ተነጋግረው በቡድናቸው እንዲካተቱ ማድረጋቸው ከሙያ አኳያ ተቀባይነት እንደማይኖረው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት ካለባቸውም ያለውን ሁኔታ በተገቢው አግባብ ማሳወቅ የሙያ ግዴታ መሆኑን የሚናገሩት ሙያተኞቹ፣ ለውጤቱ ተጠያቂውም ሆነ ተሞጋሹ ራሳቸው አሠልጣኙ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡ ሌላው አሠልጣኙ ዕርምት ሊያደርጉበት ይገባል በማለት ያከሉት ደግሞ ውጤቱን አስመልክቶ አሠልጣኙ ለመገናኛ ብዙኃን የሚናገሩትን የተጠያቂነት ሚዛንና በሪፖርታቸው የሚያቀርቡትን አተያይ ማመጣጠን የሚገባቸው መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኝ አሸናፊ ከጋናው ጨዋታ በኋላ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተጠያቂነቱን አስመልክቶ ሲናገሩ የተደመጡት ሙሉ ለሙሉ እሳቸው መሆናቸውን ጭምር ያስረዳሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...