Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለሥራ ከተጓዙ የንግድ ምክር ቤት ልዑካን መካከል ሰባቱ ሮማንያ ቀሩ

ለሥራ ከተጓዙ የንግድ ምክር ቤት ልዑካን መካከል ሰባቱ ሮማንያ ቀሩ

ቀን:

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ የተመራውና ባለፈው ወር ወደ ሮማንያ ርዕሰ ከተማ ቡካሬስት ተጉዞ ከነበረው የንግድ ልዑክ አባላት መካከል፣ ሰባቱ እዚያው መቅረታቸው ታወቀ፡፡

ከምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እየተመራ ወደ ሮማንያ የተጓዙት የልዑካን ቡድን አባላት 27 ናቸው፡፡

ከአገሪቱ ንግድ ምክር ቤት ጋር የአቻ ለአቻ ግንኙነት ለመፍጠርና የልምድ ልውውጥ ዓላማ ነበረው የተባለው በዚህ የጉዞ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ የነበሩ የንግድ ልዑክ አባላት አባላት የሮማንያ ቆይታቸውን አጠናቀው  የተመለሱ ቢሆንም፣ በዚህ የልዑካን ቡድን ውስጥ ከነበሩት ሰባቱ ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ፣ ‹‹ቀሩ ስለተባሉት የልዑካን ቡድን አባላት በትክክል ስለመቅረታቸው ማጣራት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ይመለሱ አይመለሱም ሳይረጋገጥ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ምንጮች ግን ከቀሩት ሰባቱ የልዑካን ቡድን አባላት መካከል አራቱ ሃንጋሪ ድንበር ላይ በፖሊስ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ወገኖች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ በንግድ ምክር ቤቱ የልዑካን ቡድን ውስጥ ተካትተው የተጓዙትና እዚያው የቀሩት አባላት በትክክል በሮማንያው ጉዞ ላይ ለመሳተፍ የቻሉበት ምክንያት ግልጽ አልነበረም፡፡ በአንድ የጉዞ ፕሮግራም በዚህን ያህል ደረጃ ከአገር ወጥቶ የቀረ የንግድ ልዑክ እንዳልነበር የሚያመላክተው ይኼው የምንጮች መረጃ፣ አልፎ አልፎ ግን የሚከሰት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ አሁን በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያጋጥም እንጂ በሌሎች ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶችም እየተሻሻለ የመጣ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡  

የንግድ ምክር ቤቶች በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች የሚያገኟቸውን የውጭ ጉዞ ዕድሎች በተገቢው መንገድ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን የሚያሳይ ስለመሆኑም የገለጹ አሉ፡፡

በአንዳንድ የጉዞ ፕሮግራሞች ላይ የማይመለከታቸው ግለሰቦች እንዲሄዱ የሚደረግ ስለመሆኑ ውስጥ ውስጡን ሲወራ ነበር፡፡ ለልምድ ልውውጥ፣ ለኤግዚቢሽንና ለመሳሰሉት ዓላማዎች ያገኟቸውን ጉዞዎች አብዛኛዎቹ ንግድ ምክር ቤቶች በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተውን ሰው የማይወክሉ መሆኑም ይነገራል፡፡

እንዲህ ካሉ ጉዞዎች ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆነ አሠራሮች እንደሚታዩ የሚገልጹ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች፣ በንግዱ ኅብረተሰብ ስም ፈጽሞ በአባልነት የማይታወቁ ግለሰቦች እንደ አባል ተመዝግበው በውጭ ጉዞዎች እንደሚሳተፉ ይናገራሉ፡፡  

ሌላው ቀርቶ በአመራር ላይ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች ለንግድ ምክር ቤቶች ጉዞ በመጡ የውጭ ጉዞ ግብዣዎች ተጉዘው በዚያው መቅረታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ምንጮች እንዲህ ባለው መንገድ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በካናዳ ቀርተዋል ብለው ከጠቀሷቸው አመራሮች ውስጥ የቀድሞ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ ጸሐፊና የቦርድ አባላት ይገኙበታል፡፡

የአንድ ዘርፍ ማኅበር ምክር ቤት የቢሮ ጸሐፊም በተመሳሳይ መንገድ ዕድሉ ተሰጥቷት አውሮፓ መቅረቷን በጉዳዩ ላይ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ ለስብሰባ፣ ለንግድ ትርዒቶችና ለመሰል ፕሮግራሞች ተደጋጋሚ ግብዣዎች የሚያገኙ ቢሆንም፣ ይህንን ዕድል በሚጠቅማቸው መንገድ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

የግብዣ ጥሪዎችን በትውውቅ፣ አንዳንዴ ደግሞ በክፍያ እንዲሄዱ እያደረጉ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች፣ የንግድ ምክር ቤቶች የውጭ ጉዞዎች የሚደረጉት አገርን በመከወል በመሆኑ ጉዳዩ ክትትልና ማጣራት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡

በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የውጭ ጉዞዎች ምን ያህል ውጤት እንደተገኘባቸው ወይም ጉዞውን በተመለከተ የተደራጀ ሪፖርት የማይቀርብበትና ግምገማ የማይካሄድ በመሆኑ፣ ዓላማውን እየሳተ መሆኑን የተናገሩ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ነባር አባል በሮማንያ ስለቀሩ አባላት ጉዳይ ሲሰሙ መደንገጣቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርቶች ላይ፣ ከዓመታዊ ወጪዎቻቸው ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት ውስጥ ለውጭ ጉዞ የሚወጡ የትራንስፖርትና የአበል ወጪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...