Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዋጋ መውረድ ምክንያት መንግሥት በቆሎ ኤክስፖርት እንዲደረግ ፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በምዕራብና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ያመረቱት የበቆሎ ሰብል በኩንታል ከአራት መቶ ብር ባነሰ ዋጋ ለገበያ ማቅረባቸው ያሳሰበው መንግሥት፣ በሰፋፊ እርሻዎች የተመረተ በቆሎ ኤክስፖርት እንዲደረግ ወሰነ፡፡

መንግሥት 19 የግል ኩባንያዎችና የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በቆሎ ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ፈቅዷል፡፡

በዚህ መሠረት በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት 564 ሺሕ ኩንታል በቆሎ ለጎረቤት ኬንያ ገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ ዩኒየኖች አንድ መቶ ሺሕ ኩንታል በቆሎ ለኬንያ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት በአንድ ቶን 388 ዶላር ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ በቆሎ ኤክስፖርት በመደረጉ በኦሮሚያ ክልል በወለጋና በአጎራባቹ አማራ ክልል ጎጃም አካባቢ የአንድ ኩንታል በቆሎ ዋጋ ከአራት መቶ ብር ወደ ስድስት መቶ ብር ከፍ ሊል መቻሉ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን መንግሥት በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ 7.8 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው አደጋ ላይ በሆነበት ወቅት፣ እንዲሁም በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በትግራይ ክልሎች በበቆሎ ከተሸፈነው አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 135 ሺሕ ሔክታር ላይ የሚገኝ የበቆሎ ማሳ በመጤ ተምች እየተጠቃ ባለበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በቆሎ ወደ ውጭ መላኳ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ‹‹በቆሎውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ማቅረብ አይሻልም ወይ?›› የሚሉ አስተያየቶችም ከተለያዩ ቦታዎች እየቀረቡ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ንግድ ሚኒስቴር ይህንን መላምት አይቀበለውም፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2007 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም. በኤልኖና በላኒና ክስተቶች የምርት እጥረት ተከስቶ ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. ግን ብዙ ምርት ተገኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የበቆሎ ምርት ችግር የለም፡፡ በዚህ መሠረት እንዲልኩ የተፈቀደው ከሰፋፊ እርሻዎች የተገኙ ምርቶችን በመሆኑ የሚያመጣው ክፍተት የለም፣ ብለው፣ እንዲያውም የተሻለ ጥቅም ይገኝበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የበላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግብርና ምርት ማምረቻ ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፡፡ የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና የሰው ኃይል የዋጋ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የአርሶ አደሮችን የማምረቻ ዋጋ ከፍ አድርገውታል፡፡ ‹‹በአንፃሩ ደግሞ የበቆሎ ዋጋ በኩንታል ቅናሽ እያሳየ በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ በሙሉ ኃይሉ ወደ እርሻ ከመግባት ይልቅ ተስፋ ወደ መቁረጥ እንዲሸጋገር አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በቆሎ የዕለት ተዕለት ምግባቸው አይደለም፡፡ በአንፃሩ ስንዴ ያዘወትራሉ፤›› በማለት የገለጹት አቶ በላይነህ፣ ‹‹በቆሎ ኤክስፖርት የማድረግ ሐሳብ የመነጨው እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች መነሻ ተደርገው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ አሠራር ሌሎች ጥቅሞችን ማምጣቱንም አቶ በላይነህ ይገልጻሉ፡፡ አንድ ቶን ስንዴ እየተገዛ ያለው በ225 ዶላር ነው፡፡ በቆሎ ደግሞ በአንድ ቶን እየተሸጠ ያለው እስከ 388 ዶላር ነው፡፡ ‹‹በሌላ በኩል የኬንያ ወንድሞቻችን ችግር ባጋጠማቸው ወቅት ከጎናቸው እንዳለን አሳይተንበታል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በኬንያ ሰፊ ገበያ መኖሩን የተረዳንበት ነበር፤›› በማለት አቶ በላይነህ የጉዳዩን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡

ኬንያ 2.7 ሚሊዮን ዜጎቿ በምግብ ዋስትና ችግር ወስጥ ይገኛሉ፡፡ የኬንያ መንግሥትና የኬንያ ዱቄት አምራች ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡

የዘርፉ ተዋናይ ኩባንያዎችና የኢትዮጵየ መንግሥት ይህንን የጎረቤት ኬንያ ገበያ በመልካም ጎኑ እንደተመለከቱት፣ በቀጣይ ዓመታትም በዚህ ዘርፍ በጥልቀት እንደሚገቡበት ተገልጿል፡፡

በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ይህንን የበቆሎ ምርት በስፋት ሊያቀርብ የቻለው በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ማጂ አካባቢ ካለው 2,750 ሔክታር የቡናና የበቆሎ ማሳ ካገኘው ምርት፣ እንዲሁም የሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ኩባንያ ሆራይዘን ፕላንቴሽን ሥር የሚገኘው ኢትዮ አግሪ ሴፍት ካመረተው ላይ የገዛውን 340 ሺሕ ኩንታል በቆሎ ነው፡፡    

መንግሥት ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ የሚገኘውን የሰብል ምርት በ2007 ዓ.ም. ከነበረው 270.3 ሚሊዮን ኩንታል፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል የማሳደግ ዕቅድ ይዟል፡፡

ከዚህ ውስጥ የአንድ ሰብል ምርታማነት በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 29 ኩንታል በሔክታር በ2012 ዓ.ም. ወደ 42.64 ኩንታል በሔክታር የማሳደግ፣ ዓመታዊ ምርቱንም በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 115 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ዓ.ም. ወደ 171.78 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ ዕቅድ ነድፏል፡፡

ነገር ግን በተለይ የበቆሎ አምራቾች ካመረቱ በኋላ ተገቢውን ዋጋ የማያገኙ ከሆነ፣ በቀጣዩ ዓመት ይኸው የገበያ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በሚል ሥጋት ወደ ምርት ከመግባት ይቆጠባሉ የሚል ሥጋት አለ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በተለይ የምዕራብ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አንድ ኩንታል በቆሎ ከሁለት መቶ ብር በታች ለመሸጥ ተገደው ነበር፡፡ መንግሥት በዚህ ወቅት ወደ ውጭ እንዲላክ ፈቅዶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡          

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች